ከእነዚህ ከሁለቱ ይልቅ ግን ምሁራኑ በዐውደ ጥናትና በጆርናሎች ብቻ እንዲወሰኑ የሚያደርጋቸው ሌላ አመክንዮ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዘንድ መከራከሪያ ሆኖ የሚቀርብ ሐሳብ፡፡ ‹አካዳሚያዊ ምሁራን(academic elites) ከሕዝብ ልሂቃን(popular elites) መለየት አለባቸው› የሚል ሐሳብ፡፡ አካዳሚያዊ ምሁራን አካዳሚያዊ መንገድን ብቻ ተከትለው፣ ለአካዳሚያዊ ሥራ የሚውልና ለአካዳሚያዊ ምኅዳር የተስማማ ሥራ መሥራት እንጂ የሕዝብ ሊቅ መሆን የለባቸውም› የሚል ነው አስተሳሰቡ፡፡ ክርክሩም፣ ውይይቱም፣ ኅትመቱም፣ ጥናቱም፣ መዓርጉም እዚያው በአካዳሚያዊ ዐውድ ውስጥ መንጭቶ እዚያው እንዲቀር የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ የታሪክ ምሁራኑ ›ታሪክን በአካዳሚያዊ መንገድና፣ ለአካዳሚያዊ ዓላማ ማጥናት፣ ማሳተምና ማስተማር እንጂ ለሕዝብ የሚሆን የታሪክ ድርሳን የማቅረብ ዓላማ ሊኖራቸው አይገባም› ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡
እነዚህ ሐሳቦች ግን ምሁሮቻችንን ከወንዝነት ይልቅ ኩሬነትን እንዲላበሱ አድርጓቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንንም ደሴቶች አድርገዋቸዋል፡፡አካዳሚያዊ መንገድ የራሱ ሥርዓት፣ ባሕል፣ ዘዴና አቀራረብ እንዳለው ይታወቃል፡፡ የማቅረቢያ፣ የመገምገሚያና የማሳለፊያ የዳበረ ልማድም አለው፡፡ በተለይም ሥራዎቹ በሌሎች ልሂቃን (peer evaluation) የመገምገም ዕድል ስለሚኖራቸው ጥራትና ደረጃቸውን ይጠብቃሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ማለት ግን ምሁራኑ በዩኒቨርሲቲ አጥሮች ውስጥ ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ የሚያደርግና ‹የገመድ ውስጥ ኃያላን› (Lord of the rings) እንዲሆኑ አሳልፎ የሚሰጣቸው መሆን የለበትም፡፡ የገመድ ውስጥ ኃያላን ቡጢኞች ቡጢያቸው ክብርም ገንዘብም የሚያስገኘው በገመዱ ውስጥ ጨዋታው እስከተደረገ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከገመዱ ውጭ ከተደረገ ግን ወንጀል ይሆናል፡፡ ምሁራኑም በዩኒቨርሲቲ ገመዶች ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብቻ ሕጋዊ፣ ከዚያ ውጭ ሲሆን ግን ነውር ከሆነ ሀገር የምትጠቀመው ነገር አይኖርም፡፡
ዩኒቨርሲቲ ወንዝ መሆን አለበት፡፡ በዕውቀቱ ስዩም
ከተመኙ ላይቀር ወንዝነት መመኘት
ሀገርን ሳይለቁ ሌላ ሀገር መገኘት
እንዳለው፤ ወንዝነት ከአንድ ቦታ መንጭቶ፣ ነገር ግን ቦታውን ሳይለቅ የደረቁ መሬቶችን ሁሉ እያጠጣ ወዳልመነጨበት ሥፍራ መጓዝ ነው፡፡ ምሁራን ወንዝ የሚሆኑት አካዳሚያዊ ባሕሉን፣ መንገዱን፣ ዘዴውንና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለሌላውም ማኅበረሰብ ሲተርፉ ነው፡፡ አካዳሚያዊ ባሕሉ፣ ደረጃው፣ ዘዴውና ደረጃው ለኅብረተሰቡ የሚጠቅመው ነገር አለ፡፡ ማኅበረሰቡ ደረጃውን የጠበቀ፣ የተገመገመ፣ የነጠረና ሳይንሳዊ የሆነ ነገርን እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ማኅበረሰብን በመለወጥ ሂደት ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል፡፡ ምሁራን ከማኅበረሰቡ የራቁና በዩኒቨርሲቲ አጥር የተከለሉ በመሆናቸው እነርሱ መያዝ የነበረባቸውን ቦታ ደፋሮችና ጨዋዎች እንዲረከቡት አድርገውታል፡፡ ፖለቲከኞችን፣ የማኅበረሰብ መሪዎችን፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ያልቻለውን ማኅበረሰብ በሐሳብ ለመምራት የነበራቸውን ዕድል አጥብቦታል፡፡ ይሄንን ነው ኩሬ ምሁርነት የምንለው፡፡ በመነጨበት ቦታ በዚያው ተቁቶ ቀርቶ ራሱን ብቻ የሚለውጥ፡፡
ምሁራኑ ራሳቸውን የሚያዘጋጁት ለአካዳሚያዊ ዐውዶች ብቻ በመሆኑ የንግግርና የጽሕፈት ክሂሎትን ትኩረት አልሰጡትም፡፡ ምግብን እንዲበላ የሚያደርገው የምግቡ ይዘት ብቻ አይደለም፡፡ የምግቡ አቀራረብ ጭምር እንጂ፡፡ በሀገራችን ‹ከፍትፍቱ ፊቱ› የሚለው ብሂል ከይዘቱም በላይ አቀራረቡ ወሳኝ መሆኑን አመልካች ነው፡፡ ምሁራኑም ለተማሪዎቻቸውና ለአካዳሚያዊ ዐውዶቻቸው ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡ ዕውቀታቸውን እንዴት ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው ቢያስቡበት ኖሮ ያሉንን በጣት የሚቆጠሩ ሚዲያዎችና ሕዝባዊ መድረኮች በዋኙባቸው ነበር፡፡ በኅትመትና በማኅበራዊ ሚዲያ በሚደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ምሁራኑን በንቃት ማግኘት ባልከበደን ነበር፡፡ ምሁራኑም ከአካዳሚያዊ ክብርና መዓርግ በተጨማሪ ሕዝባዊና ሀገራዊ ክብርና መዓርግንም የማግኘቱ ዕድል ይኖራቸው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ከዚህ በፊት የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ መጀመሪያ በእንግሊዝኛ በኋላም በአማርኛ ጽፎ (ተርጉሞ) አሳትሞልናል፡፡ በእንግሊዝኛ ከታተመው መጽሐፍ ይልቅ በአማርኛ ተተርጉሞ የቀረበው መጽሐፍ ለተከታታይ ጊዜ በብዙ ሺ ቅጅዎች የመታተም ዕድል አግኝቷል፡፡ በአማርኛ የተጻፈው መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ከተጻፈው ቅጅ ይልቅ በብዙ ዓይነት አንባቢዎች ዘንድ የመግባት፣ በየጽሑፎችም የመጠቀስ ዕድል አግኝቷል፡፡ ለምን? የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ ማንሣት ይገባናል፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ዘርፍ የላቀ መዓርግ ላይ የደረሰው የፕሮፌሰር ባሕሩ መጽሐፍ በሚገባው የሀገሩ ቋንቋ ሊቀርብለት በመቻሉ ነው፡፡ የእንግሊዝኛው ለአካዳሚው፣ የአማርኛው ለሕዝቡ ስለቀረበ ነው፤ ከኩሬ ይልቅ ወንዝ ብዙ ቦታዎችን የማርካትና በመስኖ በየእርሻው የመድረስ ዕድል ስላለው ነው፡፡
ጥንታዊ ሊቃውንት በዚህ ዘርፍ የተሻለ ልምድ ነበራቸው፡፡ ተማሪዎቻቸውን በጉባኤ ቤት ያስተምራሉ፡፡ የጉባኤ ቤት(የአካዳሚ) ትምህርት ለሕዝብ የሚሰጥ ትምህርት አይደለም፡፡ የጉባኤ ትምህርት ነው፡፡ ጉባኤ ቤቱ ደሴት እንዳይሆን ግን ሊቃውንቱ ሕዝቡን የሚያገለግሉበት መድረክ ፈጥረዋል፡፡ ባለ ቅኔው በክብረ በዓሉ ጊዜ ቅኔ ያቀርባል፡፡ የጉባኤ ቤት ዘረፋ ይበቃል አይሉም፡፡ ከዜማ ጋር የተያያዘ ጉባኤ ያላቸው ደግሞ በክብረ በዓል ጊዜ ዋዜማ፣ ማኅሌት ይቆማሉ፣ በሠርግ ጊዜ ይወርባሉ፣ ያሸበሽባሉ፡፡ የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ በዳኝነት ያገለግላሉ፣ የቅዳሴው ሊቅ መቅደስ ይገባሉ፤ የመጻሕፍቱም ሊቅ ሕዝብ ያስተምራሉ፡፡ ሕዝቡ ይህን ጥቅምና አገልግሎት ስለሚያውቅ ነው መኖሪያና ድርጎ ሰጥቶ ትምህርት ቤቱን ሲደግፍ የኖረው፡፡ ለዕውቀታቸው ቅርብ ስለሆነ ነው አክብሯቸውና አፍሯቸው የኖረው፡፡
የሀገራችን ምሁራንም ዕውቀትን ከመማርና ማስተማር ጉዳይነት ባሻገር ሕዝብን የመለወጫ መሣሪያ ማድረግም አለባቸው፡፡ ለዚህ የሚጠቅመው ደግሞ አካዳሚያዊ ባሕሉን፣ መንገዱን፣ ዘዴውንና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለሕዝቡ የሚሆን ነገር ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ ማቅረብ ነው፡፡
አንድ ሰው በአካዳሚያዊ መንገድ ሊማርና ሊመረቅ የሚችለው በአንድ ወይም በጥቂት ሞያዎች ነው፡፡ ሌሎቹን ዕውቀቶችና ሞያዎች ሊያገኝ የሚችለው በማንበብና በአጫጭር ሥልጠና ነው፡፡ እነዚህን ዕውቀቶች ደግሞ ምሁራኑ በሕዝብ ቋንቋ ማቅረብ አለባቸው፡፡
የሀገራችን ኮሌጆች ምንም እንኳን ትምህርት የሚሰጡት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቢሆንም ተማዎቻቸው የሚኖሩት ግን በአማርኛ (በሀገራቸው ቋንቋ) ነው፡፡ የአማርኛ ፊልሞች ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ፊልሞች ይልቅ ተወዳጅ የሆኑበትን ምክንያት መጠየቁ ነገሩን በሚገባ ያስረዳናል፡፡
ከመጻሕፍቱ በተጨማሪ በሀገርኛ ቋንቋዎች የሚቀርቡ የጥናት መዛግብትም ያስፈልጉናል፡፡ እነዚህን የጥናት መዛግብት ውጤታማና ተደራሽ ለማድረግም ሀገራዊ የምርምር ጉባኤያትን ማስፋት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያላቸው ዐውደ ጥናቶች ከማካሄድ ይልቅ አንድ ፈረንጅ እንደምንም ጋብዞ የደከሙ ዐውደ ጥናቶችን ‹ዓለም ዐቀፋዊ› ማለትን እየመረጡ ነው፡፡
ዓለም ዐቀፋዊ ዐውደ ጥናት ማለት ከውጭ የመጣ ፈረንጅ የተካፈለበት ማለት ሆኗል፡፡ የደረጃ ጉዳይ አልሆነም፡፡
ከዚህ ይልቅ በሀገራችን ቋንቋ የሚዘጋጁና የማኅበረሰቡን ልዩ ልዩ አካላት ያሳተፉ ጉባኤያትን ማድረጉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አላቸው፡፡ ምርምር ወዲያው ገቢ የሚያስገኝ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህም ውድ ነው፡፡ በመንግሥትና በተቋማት በጀት ብቻ ሊከናወን አይችልም፡፡ የሌሎችን አካላት ድጋፍ ይፈልጋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚደረጉ የጥናት ጉባኤያት አካዳሚያዊ ደረጃቸውን እንደጠበቁ፣ ነገር ግን የንግዱን ማኅበረሰብ፣ ሞያዊ ማኅበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የሚዲያ ተዋንያንን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የፊልም ባለሞያዎችን፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራትን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ሌሎችን ያሳተፉ ቢሆኑ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ለምን? በአንድ በኩል ከአካዳሚው የመነጨውን ዕውቀትና የዕውቀት አካሄድ መንገድ ማኅበረሰቡ እንዲወስደውና እንዲጠቀምበት ያደርገዋል፡፡ በሌላም በኩል የዩኒቨርሲቲዎች የጥናት ጽሑፎች መደርደሪያ እያሞቁ ከመቀመጥ ይታደጋቸዋል፡፡
በተቋማቱ በኩል ደግሞ ምርምሮችንና የምርምር ጉባኤያቱን ለማካሄድ ማኅበረሰባዊ ድጋፍ ለማግኘት ይረዳቸዋል፡፡ የምርምር ተቋማትንና አብያተ መጻሕፍትን ለመገንባት፤ የምርምር መሣሪያዎችን ለመግዛት፣ የምርምር መጽሔቶችን ለማሳተም ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የንግዱን ማኅበረሰብ አካላትና ማኅበራትን ዩኒቨርሲቲዎች በቀላሉ ለማግኘት ይችሉ ነበር፡፡
የዩኒቨርሲቲዎችና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ያለው ማኅበረሰብ ግንኙነት በተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ብቻ እየተወሰ ነው፡፡
ግንኙነታቸው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን ነበረበት፡፡ ይህንን ድልድይ ለመፍጠር ደግሞ እነ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እያደረጉት እንዳለው ዕውቀቶችን ሊረዳው በሚችል ቋንቋና መንገድ ለሕዝቡ ማቅረብ ይጠበቃል፡፡ ከኩሬ ምሁራን ይልቅ ወንዝ ምሁራንን ሀገራችን ትፈልጋለችና፡፡
ኩሬና ወንዝ ምሁራን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ኩሬና ወንዝ ምሁራን ዲ/ን ዳንኤል ክብረትAddis Admass
ሰሞኑን ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን የሕይወት ታሪክ አሳትሞ አቅርቦልናል፡፡ መጽሐፉ በላቀ የታሪክ ሞያ የተሠራ፣ የታላላቅ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ለሚሠሩ ሰዎች እንደ ሞዴል ሊያገለግል የሚችል የታሪክ ጥናት ድርሳን ነው፡፡ መጽሐፉን ሳነብ ከመጽሐፉ ይዘት ይልቅ የመጽሐፉ አዘጋጅና አዘገጃጀት ነበር በአእምሮዬ የሚመላለሰው፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ታሪክ የተመለከቱ ጥናቶችንና መጻሕፍትን አዘጋጅቶ አሳትሞ ያውቃል፡፡ አብዛኞቹ የጥናት ጽሑፎቹና መጻሕፍቱ የተዘጋጁት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ ብዙዎቹም የታተሙት ከሀገር ውጭ በሚታተሙ ጆርናሎች ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የፕሮፌሰር ባሕሩ ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቹ የሀገራችን ምሁራን መንገድ ነው፡፡ በሁለት ምክንያት ያደርጉታል፡፡ በአንድ በኩል በአካዳሚው የሚኖራቸውን የሞያ ሂደት ማስቀጠልና አካዳሚያዊ መዓርጎችን ማግኘት የሚችሉት በታወቁ ዐውደ ጥናቶች በሚያቀርቧቸውና በዕውቅ ጆርናሎች በሚያሳትሟቸው የጥናት ወረቀቶች አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህ ጆርናሎች ደግሞ በብዛት(እንዲያውም ሁሉም ማለት ይቻላል) የሚገኙት በውጭ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችን የአካዳሚያዊ ዕውቀት መሸመቻና ማስሸመቻ ቋንቋ እንግሊዝኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነርሱም የተማሩት፣ የመመረቂያ ጥናቶቻቸውንም የሠሩት በእንግሊዝኛ(አልፎ አልፎ በሌሎች የአውሮፓ ቋንቋዎች) በመሆኑ ሌሎች ሥራዎቻቸውንም በዚያው መንገድ ማቅረቡ ይቀላቸዋል፡፡