በሕሊና ትግል ድል የሚነሡ ብፁዓን ጀግኖች ናቸው ጌታቸው ኃይሌ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በሕሊና ትግል ድል የሚነሡ ብፁዓን ጀግኖች ናቸው
ጌታቸው ኃይሌ
“ከሕዝቡ ጋር አብሬ ልሂድ ወይስ ልቅር?” “ተናጋሪው ከተናገረው ውስጥ ያልገባኝ ነገር አለ። ሰው እየሰማ፥ ልጠይቅ ወይስ ዝም ልበል?” መሄድ እፈልጋለሁ፤ ሕሊናየ ግን ሁኔታውን እየመረመረ፥ “ትክክሉና የሚገባህ ባትሄድ ነው፤ ዐርፈህ ተቀመጥ፤ ከጀሌ ጋር አትጓዝ” ይለኛል። “ለመጠየቅ የፈለከውንም ጠይቅ፤ ሰው ምን ይለኛል ብለህ ደንቁረህ አትቅር” ይለኛል።
ሕሊናየን ታዝዤ ከመሄድ ብቀር፥ ለመጠየቅ የፈልኩትንም ደፍሬ ብጠይቅ፥ ሰው ምን ይለኛል? የለም፥ አልቀርም እሄዳለሁ፤ ሰዉ ሁሉ ሲሄድ እንዴት አድርጌ ተለይቼ እቀራለሁ? ሰው ሁሉ የሚያውቀውን ጥያቄ ብጠይቅ፥ ሰው ምን ይለኛል? አልጠይቅም፤ ይቅርብኝ።
እውነቱና ትክክሉ አለመሄድ መሆኑን፥ ዐርፎ መቀመጥ መሆኑን ሕሊናየ እየነገረኝ፥ ብሄድ ምን ዓይነት ሰው እባላለሁ? ሕሊና ቢስ (ሕሊና የሌለው) ያሰኘኛል? የለም፥ እንደሱ አይደለም። ሕሊናማ አለኝ፥ ያውም የሚወተውት፤ ከዳሁት እንጂ። “ሕሊና-ቢስ” እና “ሕሊና-ከዳተኛ” የተለያዩ ናቸው። “ሕሊና-ቢስ” የሚባለው ወንጀል ሲፈጽም፥ ሰው ሲያሰቃይ፥ ሲገድል አንጀቱ ይርሳል። “ሕሊና-ከዳተኛ” ተመሳሳይ ወንጀል ሲፈጽም፥ አንጀቱ ይንሰፈሰፋል፤ ምናልባትም ሲበዛበት ያብድ ይሆናል። እናም መሆን የሚገባው ማንንም ሳልፈራ ጨክኜ መቅረት፥ ዐርፌ መቀመጥ፤ ጥያቄየንም ማንንም ሳልፈራ መጠየቅ እንደሆነ ሕሊናየ እየነገረኝ፥ ሰው የሚለውን በመፍራት ብሄድ፥ ጥያቄየንም ሳልጠይቅ ብቀር፥ በሕሊና ትግል ተሸነፍኩ ማለት ነው።
በሕሊና ትግል ተሸንፎ ማጥፋትና እርግጠኛ ባለመሆን (ባለማወቅ) መሳሳት የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ፥ አንድ ሰው መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲደርስና የትኛውን መንገድ ይዞ መጓዝ እንዳለበት እርግጠኛ ባለመሆን፥ የተሳሳተውንም መንገድ ቢመርጥ ባለማወቅ እንጂ፥ ለሕሊናው ባለመታዘዝ አይደለም፤ ሰውየው ይታዘንለታል እንጂ፥አይወቀስም።
በሕሊና ትግል የሚሸነፍን ሰው ግን ደካማ ነው፤ ቁም ነገር ላይ አትፈልጉት፤ እገሌ አለልን አትበሉ። የማያምንበትን ያደርጋል፤ ይከዳችኋል። ተሸንፎ እናንተንም ከሽንፈት ላይ ይጥላችኋል። ምሳሌ ልስጥ፤ ወያኔዎች አዲስ አበባን እንደተቈጣጠሩ፥ የሽግግር መንግሥት አቋቁመው፥ ሕገ መንግሥት አጸደቁ። ከዚያ ቀጥለው፥ ያቋቋሙትን የሽግግር ሸንጎ፥ “ኤርትራ ትገንጠል/ አትገንጠል?” በየሚል ጥያቄ ላይ አወያይተው ድምፅ እንዲሰጥበት ጠየቁት። ከአንድ ሰው (ከጀግናው ከፕሮፌሰር ዓሥራት ወልደየስ) በቀር ሁሉም “ትገንጠል” አለ። ጀግና ማለት “ተባአስ በእንተ ጽድቅ እስከ ትበጽሕ ለሞት” (ለሞት እስከምትደርስ ለእውነት ተሟገት) የሚለውን የመጽሐፍ ቃል የሚያከብር ነው።
እንግዲህ ተመልከቱ፤ “ኤርትራ ትገንጠል” ብለው ድምፅ ከሰጡት ውስጥ በሀገር አንድነት የሚያምኑ፥ ቀደም ብሎ፥ ከሻዕቢያ ጋር ይደረግ በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት እንዲያሸንፍ የሚመኙ (ምናልባትም የሚጸልዩ) እንዳለባቸው አውቃለሁ። ሆኖም እነዚህ ሰዎች “ትገንጠል የሚል ድምፅ
ለመስጠት እጃችሁን አውጡ” በተባሉ ጊዜ፥ የሕሊና ትግል አላጋጠማቸውም ለማለት አንችልም። ግን ተሸነፉ፤ “አትገንጠል” በሉ የሚላቸውን ሕሊናቸውን ከዱት። ድምፅ አሰጣጡ እጅ በማውጣት መሆኑ ቀርቶ፥ በምስጢር ቢሆን ኖሮ፥ እነዚህ ሰዎች ለሕሊናቸው ታማኝነታቸውን ያሳዩ ነበር። ጥንቱንም የምስጢር ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት የተቋቋመው የማያምኑበትን አሳብ የሚቀበሉትን ሰዎች ከድቀት ለማዳንና አስከፊ ውጤቱን ለማስወገድ ነው። ግን ነፍሱን በሰማይ ይማራትና፥ ያ ተንኮለኛ ሰው፥ ምርጫውን በምስጢር ማድረጉ ቀርቶ “እጃችሁን አውጡ” ብሎ አፈጠጠባቸው። በዚህ ዘዴው ሕሊናቸውን አስከድቶና የማያምኑበትን አሳምኖ፥ ዐውቃ በፈቃዷ የመጣችውን ኤርትራ ሳታውቅ፥ ፈቃዷ መሆኑ ሳይታወቅ አባረራት።
የሕሊና ክህደት የተፈጸመባቸው ድርጊቶች በብዛት መጥቀስ ይቻላል። ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያህል፥ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሠራተኞች ፓርቲ የሚለውን ድርጅት አቋቁሞ ሀገሪቷን በኮሚኒስት ሥርዓት ሲያሰቃያት የማእከላዊው ኮሚቴ አባላት ይደግፉት እንደነበረ እናስታውሳለን። ከዕለታት አንድ ቀን ብድግ ብሎ ለግብር አበሮቹ፥ “ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትመራው በቅይጥ ኢኮኖሚ ነው” አላቸው። እነዚህ ቃላት ካፉ ሲወጡ፥ ጓደኞቹ የተሰማቸው ደስታ ወደር አልነበረውም። ከማህላቸው አንዱ ነሸጥ ብሎት ከመቀመጫው ተነሥቶ፥ “ክቡር ፕሬዚዴንት፥ ይኼ ዓዋጅ ሲነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል” ሲል ተናገረ። ፓርቲውን ሕሊናቸውን የከዱ አባላት ሞልተውት ነበር ማለት ነው።
ከዚያም ቀደም ብሎ፥ የደርግ አባላት ድምፅ በመስጠት ስድሳ ሁለት ባለሥልጣኖች በጥይት እንዳስደበደቡ የማይረሳ የጉድ ታሪክ አለን። ዝርዝሩን ስለማላውቅ ብዙ አልጽፍም፤ ግን ጥቂቶችም ቢሆኑ ሕሊናቸውን ክደው በሰዎቹ መፈጀት የተስማሙ ሳይኖርባቸው አይቀርም። መገደል እንደሌለባቸው ሕሊናቸው እየነገራቸው “ይሙት በቃ” ፈረዱባቸው። ለነገሩማ፥ መጀመሪያውኑ የደርግ አባላት እነዚህ የተፈጁት ሰዎች ባለሥልጣኖች ከመሆናቸው በቀር ስለነሱ ሌላ ምን ነገር ያውቁና ነው “ይኸም ይኸም ይሙት” እያሉ ድምፅ የሰጡት? ስንቱንስ ሕሊናቸው እንዳይገደሉ የነገራቸውን “አይገደል” ብለው አዳኑት?
ሌላ ምሳሌ፤ ወያኔዎች “አማራው ጠላታችን ነው፤ መጥፋት አለበት” ሲሉ፥ ከመካከላቸው ሕሊናቸውን ክደው፥ “አዎን፥ አዎን፥ ጠላታችን ነው፤ መጥፋት አለበት” ያሉ አይጠፋባቸውም። አንዱ አቶ ገብረ መድኅን አርአያ ነበር። ሕሊናው ቢጨቀጭቀው የኋላ ኋላ አዳምጦት በጀግንነት ታዘዘው። ጥሏቸው ሄደ። እነ ሟቹና እነ ገና-ሟቾቹ የሚሠሩት ሥራ ወንጀል መሆኑን ሕሊናው በየቀኑ ሲነግረው፥ ሕሊና ከዳተኛነት ያሰረበትን ገመድ በጣጥሶ ወጣ።
አሁንም ቢሆን ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር ሲለያይ ከደጋፊ አባላቱ ውስጥ ሕሊናው እየወቀሰው አብሮ የሚጓዝ እንዳለባቸው አያጠራጥርም። ማስረጃው የሕሊናቸው ወቀሳ ስለበዛባቸው ጥለዋቸው የሄዱት ናቸው። አንዱ ኤርምያስ ለገሰ የሚባለው “የመለስ ትሩፋቶች . . .” መጽሐፍ ደራሲ ነው።
“እንገንጠል” ከሚሉት ኦሮሞዎች መካከልም ሕሊናቸው “ተዉ፤ አገራችሁን በዲሞክራሲ ሥርዓት አዳብሩ” እያለ ሲመክራቸውና ሲወቅሳቸው “ዝም በል” እያሉ የሚክዱት ብዙዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ምስክሬ ምርጫ 97 ነው። በዚያን ጊዜ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ የመረጠው በኢትዮጵያ አንድነት
የሚያምነውን ቅንጅትን ነው። ግን ከሕሊና ወቀሳ ይልቅ የንቅናቄው ግፊት (“ኦሮሞ ሆኜ ዝም ስል ቀንደኞቹ ምን ይሉኛል” የሚለው ግፊት) አይሎ ስላሸነፋቸው አብረው ይጓዛሉ።
ሕሊናቸው፥ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ታሪክ የተጫወቱትን ግዙፍ ሚና እንዲያስታውሱ፥ አያውቁትም እንደሆነ እንዲያውቁ ይወተውታቸዋል። ግን ይሉኝታ ፈርተው ካዱት፤ ተሸነፉ። ኦሮምኛን በኢትዮጵያ ፊደል መጻፍ እንደሚቻል፥ ከመቻልም አልፎ እንደሚሻል፥ ሕሊናቸው ይነግራቸዋል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በኦሮምኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ፊደል አምሮበት እንደተጻፈ ያውቃሉ። ትክክሉ በዚያው ቢቀጥሉ መሆኑን ሕሊናቸው ቢወተውታቸው፥ ቢወተውታቸው አልሰማ አሉ። ካዱት፤ ተሸነፉ። ሌላው ቢቀር፥ “እናንተ ካሠኛችሁ በላቲንም ሆነ በዐረቢ ፊደል ጻፉ፤ መብታችሁ ነው። እኛ ግን ኦሮምኛን ለመጻፍ እንዲቀለን፥ ሌሎችም ቋንቋውን እንዲማሩት ለማጓጓትና ለማበረታታት፥ በቀላሉ በአገራችን ፊደል እንጽፋለን” ብለው መነሣት አልቻሉም። ቢችሉ በውድድር የኢትዮጵያ ፊደል ያሸንፍ ነበር። ኦሮምኛ እንደዱሮው በኢትዮጵያ ፊደል እንዳይጻፍ የሚከለክል ሕግ የለም። እንዲያውምኮ ኦሮምኛ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ስለሆነ በምን ፊደል መጻፍ እንዳለበት ወሳኙ ኢትዮጵያን የሚወክል ድርጅት እንጂ አንድ ጎሳ አይደለም።
በሕሊና ትግል የሚሸነፍ ሰው የሕሊና ቢስ ታናሽ ወንድም ነው። ከላይ እንዳመለከትኩት፥ ከቁም ነገር ላይ አይገኝም። ለትዳር እንኳን አይበቃም፤ በቤቱ ያለለትን ትቶ ከውጪ ይቀላውጣል። እንዲህ ያለ ሰው፥ እንደምናየው፥ ራሱ ተሸንፎ አገርን ከአደጋ ላይ ይጥላል። አገር ወዳድ ነኝ የሚለው ሰው ሕሊናው “ተው” እያለው፥ ኀይል በመፍራት፥ ገንዘብ በመውደድ ሕሊናው የሚነግረውን ትቶ፥ የሰው ነፍስ የሚጠፋበትን፥ ሀገር የሚጎዳበትን አማራጭ ይመርጣል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን የሚያንገላቷት በጥላቻ ቆርጠው የተነሡ የትግራይ ልጆች ብቻ አይደሉም። እነዚህ ወስላቶች ኀይል ያገኙት ሕሊናቸውን የከዱ፥ ሕሊናቸው የሚነግራቸውን የማይሰሙ ሰዎች በሚሰጧቸው ድጋፍ ጭምር ነው። ወያኔዎች “ከዛሬ ጀምሮ ጎሰኝነት ቀርቷል” ብለው ቢያውጁ፥ ሕሊና ከዳተኞች በሙሉ ከበረት እንደተለቀቀ ጥጃ ይናጥጡ ነበር። ሕሊናቸውን ቢከተሉ ግን፥ በደስታ ለመናጠት የወያኔን ዓዋጅ መጠበቅ ባላስፈለጋቸው ነበር። የኦሮሞ ፖለቲከኞችም ኦሮምኛ ለመማር ቀናውን መንገድ ያሲዙን ነበር።
ሕሊናውን የማይከተል ሰው ደካማ ከሐዲ ነው። በሕሊና ትግል ድል የሚነሣ ግን ጀግና ነው።