የዘር እልቂት ሊፈጥሩ የሚችሉ ዘረኛ ካርታዎች – ግርማ ካሳ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የዘር እልቂት ሊፈጥሩ የሚችሉ ዘረኛ ካርታዎች – ግርማ ካሳ
ላለፉት 25 አመታት በወጣቱ አይምሮ ዉስጥ ሲበትን የነበረው የዘር ፕሮፖጋንዳ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የኦሮሞ ብሄረተኝነትን ፈጥሯል። በኦሮሞዎች ተቃዉሞ አንድም ቦታ የኢትዮጵያ ባንዲራ ሲውለበለብ አላየም። በአንጻሩ የኦነግ ባንዲራን ነው በብዛት ያየነው፡ ብዙ ወጣቶች “ኦሮሚያ” የሚለውን እንጂ “ኢትዮጵያ” የሚለውን መስማት አይፈልጉም።
ላለፉት 25 አማርኛ ተናጋሪዎች ከማንም በላይ በኦሮሞ አክራሪዎችና በአገዛዙ ሲጠቁ ኖረዋል። እጅግ በጣም ብዙ አማርኛ ተናጋሪዎች ከኦሮሚያ ክልሎች አማርኛ ተናጋሪ በመሆናቸው ብቻ በገፍና በጫካኔ ተባረዋል። ይህ ጭካኔ ጽዋውን ሞልቶ በመፍሰሱ፣ ከመቼዉም ጊዜ በላይ “ሳንጠፋ ራሳችንን መከላከል አለብን” በሚል በ”አማራ” ስም መደራጀት ጀምረዋል። እነርሱን የዘር፣ የአማራነትን ካርድ እየመዘዙ ነው። አሁን ከመቼዉም ጊዜ በላይ የአማራ ቤሄረተኝነት በጣም ጠንክሮ ወጥቷል። “እኛን እንደ ጠላት የሚያዩን ከሆነ እኛም እኮ የኛን ታሪካዊ መሬት ይዘን ብቻችን መኖር እንችላለን “ ብለው የከረረ አቋም ወደ መያዝም የደረሱ አሉ።
የአማራ መንግስት በሚል አንድ ካርታ ተለቆ ነበር። የቀድሞ የቤጌምድር፣ የጎጃም፣ የሸዋና የወሎ ክፍለ ሃገራትን፣ አሁን ወደ ትግራይ በሃይል የተጠቃለሉ ሁመራ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴን ፣ ጨለምትንና አላማጣን ያጠቃልላል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኦነግ ካርታ አለ። ከሞላ ጎደል አሁን ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራዋን፣ ኦነግና ሕወሃት በጦርነት አሸናፊ ስለሆኑ፣ በሕዝቡ ላይ በኃይል የጫኑትን ክልል ይመስላል። በተጨማሪ ከወሎ ብዙ ግዛቶችንም ያካትታል።
የኦሮሞ ብሄረተኞች “ከመቶ አመት በፊት፣ በሚኒሊክ ጊዜ፣ አማራዎች መጥተው ነው የኦሮሞን መሬት የነጠቁን። ሸዋ፣ ፊንፊኔ የኦሮሞ መሬት ነው” ይላሉ። “አማራዎች” ደግሞ ኦሮሞዎች ከሶስት መቶ አመት በፊት ነው ክባሌ መጥተው መሬታችንን የነጠቁን ይላሉ። ሁለቱም ትክክል ናቸው።በየትኛውም አገር በጦርነት የበላይነት የያዘው ሌላውን እያስገበረ ነው የሚገዛው። ለምሳሌ እንግሊዝ የምትባለዋን አገር መጀመሪያ ታሪክን ከመረመርን ሁለቱም ትክክል ናቸው። እንግሊዝን ብንመለከት፣ ሮማዉያን ለአምስት መቶ አመት ገዟት። ከዚያም ጀርመኖች (ሳክሰኖችና ኤንግልሶች) ወረሯት። በኋላ ደግሞ ከፈረንሳይ ኖርማኖች ገዙ። አሁን እንግሊዝን የነዚህ የሁሉም ገዢዎች አሻራ ያለባት አገር ናት። አሁን ሳክሰን፣ ኖርመን፣ ቫይኪንግ ..እየተባባሉ የተከፋፈሉ አይደለም። ታሪክን ለታሪክ ትተው በአንድነት ጠንካራ አገር ሆነው ወጡ።
አሁን በአገራችን ያለፈው እንዲህ ነበርና ብሎ ዉዝግብ ዉስጥ መግባት ሳይሆን አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመመልከት ለሁሉም የሚበጅ መፍትሄ መፈለግ ነው የሚሻለን።
ሁለቱም ካርታዎች አዲስ አበባን እና የሸዋ ክፍለ ሃገርን ወደ እነርሱ ቀላቅለዋል። ካርታዎቹ ተግባራዊ ይሁኑ ከተባለ፣ ሸዋን እና አዲስ አበባን የ”አማራ መንግስት” ዉስጥ ለማድረግ፣ ወይንም በኦሮሚያ ዉስጥ ለማስቀጠል ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ሊደረግ ነው ማለት ነው። አዲስ አበባን እና ሸዋን የኦሮሞ ወይንም የ”አማራ” ግዛት ማድረግ አይቻልም።
ዘጠኝ ሚሊዮን ከሚሆነውን የአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪ በብዛት አማርኛ ተናጋሪ ነው። ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው የኦሮሚያ ዋና ከተማ የሆነችው የአዳማ/ናዝሬት ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ነው። በአጠቃላይ በ1999 የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ቢያንስ 44% የሚሆኑት በኦሮሚያ አራቱ የሸዋ ዞኖች ነዋሪዎች አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ኦሮሚያ የኦሮሞ ግዛት ናት ከተባለ እነዚህ 44% ምን ሊሆኑ ነው ? አማርኛ ተናጋሪዉን በግድ “ኦሮሞ” ሊያደረጉት ነው ? በግድ አማርኛን ሊያጠፉ ነው ? በነገራችን ላይ ይሄ በ199ይ ቆጠራ ነው። አሁን በ2008 ያለ ምንም ጥርጥር የአማራኛ ተናጋሪው ቁጥር ኦሮሚያ ባሉ የሸዋ ዞኖች በእጅጉ ጨምሯል።
ሸዋ ወደ “አማራ መንግስት” የሚጠቃለል ከሆነ ደግሞ ወደ 54% የሚሆነው ኦሮምኛ ተናገሪው ምን ሊሆን ነው ? አስቸጋሪ ሁኔታ ነው የሚፌጠረው። ትርፉ፣ ንትርክ፣ ግጭት ፣ ምናልባትም የርስ በርስ ጦርነት ነው። አሁን በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዙሪያም የተነሳው ችግር ከዚሁ ጋር የተነሳ ችግር ነው።
እነዚህ ሁለቱም ካርታዎች ሕዝቡን ወደ ጦርነት የሚመሩ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ሰላም ካርታዎች ናቸው። አማራ፣ ኦሮሞ እየተባሉ ለሚጠሩት ወገኖች የሚጠቅሙ አይደለም። ይህ አይነቱ ካርታ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ለምሳሌ ሸዋ አማራ አይደለም ፣ ኦሮሞም አይደለም። ሸዋ ሸዋ ነው። ሸዋ ግማሹ አማርኛ ተናጋሪ፣ ግማሹ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ነው። የሸዋ ሕዝብ ከጥንት ተፋቅሮና ተዋልዶ የኖረ ነው። ሁለቱንም ቋንቋዎች የሚናገሩ የሸዋ ነዋሪዎች ብዙ ናቸወ፡፡
እነዚህ ካርታዎች ላይ የምናየዉን እብደት ትተን ፍቅርና መስማማት ሊያመጣ የሚችል መፍትሄ ማስቀመጥ አለብን። በተለይም ኦሮሞዉን እና አማራዉን መለያየት በጣም፣ በጣም ከባድ ነው። ኦሮሞ ፣ አማራ ከተባለ እኔ በግሌ 5/8ኛ አካሌ ወደ ኦሮሞ፣ 3/8ኛው ደግሞ ወደ አማራ ተሰንጥቆ ሊሄድ ነው ማለት ነው። ይይቅርርታ ይደረግለኝና ይሄ አማራ፣ ኦሮሞ የሚባለው ነገር በሽታ ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ ሸዋን እንደምሳሌ ጠቀስን እንጂ ተመሳሳይ ሐሳብ በሌሎች ቦታዎችም ማንሳት ይችላል። ይሄ ዘር ላይ ያተኮረ አስተሳሰብ በሽታ ነው። ዘረኝነት በሽታ ነው። የሚያዋጣው ተከባብረን ፣ ተስማምተን ለሁላችንም የሚበጅ፣ የሁላችንም መብት የተከበረባትን አገርን መመስረት ነው።
ይሄ እንዳይሆን አሁን ያለው ዘረኛው የሕወሃት መንግስት እንቅፋት እንደሆነና አሁን እያየን ያለነው የዘር በሽታ እንዲስፋፋ ፍላጎት እንዳለው የታወቀ ነው። አማራ ፣ ኦሮሞ እያለ፣ በተናጥል ሁለቱን እየመታ፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገዉን ጥረት መቀጠሉ አይቀርም። ሆኖም መንቃት አለብን። “እኛ እና እነርሱ ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ “ ወዘተረፈ ማለታችንን አቁመን “እኛ” ማለት መጀምር አለብን። እያንዳንዳችን በዘራችን ሳይሆን በስብእናችንና በተግባራችን መመዘን አለብን። መታወቂያችን ላይ ዜግነታችን እና የትዉልድ ቦታችን ብቻ ከተጻፈ ይበቃል።
(ከዚህ በፊት እንዳልኩት ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ካርታ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እስኪፈጠር፣ አሁን ያለውን አከላለል በመጠቀም፣ ክልሎቹ የአንድ ብሄር ክልሎች ሳይሆኑ የሁሉም ነዋሪዎች የሚሆኑበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለጊዜያዊነት መቀጠል ይቻላል። ለምሳሌ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት የሚለው እብደት ቆሞ ኦሮሚያ የነዋሪዎቿ ነው መባል አለበት። አማርኛም ከኦሮሚያ ጋር የኦሮሚያ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት)
