የብአዴን አመራሮች በሳን ሆዚ የጠሩት ስብሰባ በጉጉት እየተጠበቀ ነው ::
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የአማራ ክልልና የብአዴን ከፍተኛ ሹማምንት በካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት በምትገኘው ሳንሆዚ ከተማ ከአማራ ብሄር ተወላጆች ጋር ለመነጋገር ማሰባቸውን በመግለጽ ይደግፉናል በማለት አስቀድመው ላሰቧቸው የአማራ ብሄር ተወላጆች የስብሰባውን ቦታና ሰዓት የሚገልጽ የግብዣ ወረቀት በድብቅ ቢልኩም መረጃው ሾልኮ በመውጣቱ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አጋጣሚውን በመጠቀም ተቃውሟቸውን ለማሰማት መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በካሊፎርኒያ ሳንሆዚ የሚገኙ የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አመራሮች በበኩላቸው የብአዴን መሪዎች ያስተላለፉትን ጥሪ በመከተል ኢትዮጵያዊያን በስብሰባው ቦታ በመገኘት ተቃውሟቸውን በማሰማት በአገር ውስጥ ድምጻቸው ለታፈነባቸው ወገኖቻቸው ድምጽ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
የሰሜን አሜሪካ ኢትዮ አሜሪካ ካውንስል ባወጣው ጠንካራ መግለጫ በሳንሆዚ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በብሄር ለመከፋፈልና በጥቅም ለማነወር በህወሓት የሚመራው መንግስት በጠራው ስብሰባ ኢትዮጵያዊያን ባለመገኘት ወይም የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ለስርዓቱ ያላቸውን ተቃውሞ ያሳዩ ዘንድ ጥሪ አድርጓል፡፡
የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በስብሰባው ይገኛሉ በማለት ከስርዓቱ ጋር ቅርበት ይኖራቸዋል ተብለው ለታመነባቸው ሰዎች የተላከው ወረቀት ለስብሰባው የሚመጡት ባለስልጣናት እነማን መሆናቸውን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስጶራ ማህበረሰብ አመራሮች የስብሰባ አዳራሹን ለፈቀደው አካል ጭምር ደብዳቤ በመላክ በአገር ውስጥ አፈና፣ግድያና ዝርፊያ ለሚፈጽሙ አምባገነኖች ቦታው መፈቀዱን በመቃወም ድርጊቱ በሳንሆዚ የሚገኙ ኢትዮ አሜሪካዊያንን ማሳዘኑን ገልጸዋል፡፡
ነገ እሁድ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ስብሰባ ኮሚኒቲው ብጥብጥና ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት እንደሌለው የገለጹት የኮሚኒቲው አመራሮች ‹‹ወደስብሰባው ስፍራ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሟቸውን በህጋዊ ተቃውሞን የመግለጫ መንገዶች መግለጽ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡