የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን የመንቀፍ ሞራሉ ያለው ፖለቲከኛ ማነው? ኤርሚያስ ቶኩማ‬


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን የመንቀፍ ሞራሉ ያለው ፖለቲከኛ ማነው?
ማንም እየተነሳ በጥላቻ የሰማያዊ ፖርቲ አባላትን ስለነቀፈ እውነታው ሊቀየር አይችልም እነዚህ ወጣቶች የኢትዮጵያ ሕዝብን ከዃላ እየነዱ ሳይሆን ከፊት ቀድመው እየታገሉ መጠላለፍ እና ምቀኝነት በነገሰበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ህዝቡን ነፃ ለማውጣት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። እነዚህ የሰማያዊ ፖርቲ አባላት ለፖርቲያቸው የሚሆን ቢሮ ፍለጋ ሲንከራተቱ ሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚኖር እና አዲስ አበባ ላይ በልጁ ስም ህንፃ ያለውን ታዋቂ ፖለቲከኛ ኖሮ እንዲያከራያቸው ሲጠየቅ ምን አይነት ምላሽ እንደሰጠ የምናውቅ እናውቃለን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከሰውዬው ማንነት ጋር ከነሙሉ ማስረጃው የምገልፀው ይሆናል።
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ዲስኩር ከማሰማት ውጪ አንድ የረባ (የማይረባም ቢሆን) ምንም ነገር ሳይሠራ የሰማያዊ ፖርቲ አባላትን የሚተች ሠው ብዛትን ስመለከት ከባዱ ነገሩ ኢትዮጵያን ብቻ ሣይሆን የብእር ፖለቲከኞቻችንን ከሀሜት ነፃ ማውጣቱ ይመስለኛል ከባዱ ነገር።
ባለፉት 3 አመታት ውስጥ ዮናታን ተስፋዬ ረጋሣ የሰራውን ስራ የመተቸት ሞራሉ ያለው ማነው? ዮናታን ከሚሰራበት ትምህርት ቤት ፖለቲከኛ ነህ ተብሎ ተባሮ በተደጋጋሚ እየተደበደበ ሲታሰር ሲፈታ፤ ያለፍርድ እስር ላይ ይገኛል ይህንን ጀግና ነው መተቸት የሚፈልጉት። ሌሎችም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለምሳሌ ወረታው ዋሴ ከሚሰራበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተባሮ ችግር ላይ ወድቆ ሲታሰር ሲደበደብ፤ ኢንጂነር ይልቃል እጁና እግሩ እስኪሰበር ተደብድቦ እስከመታሰር ሲደርስ፤ ወይንሸት ሞላ ጭንቅላቷ በድብደባ ምክንያት ተሰንጥቆ መርካቶ አደባባይ ላይ ራሷን ስታ የሚያነሳት አጥታ በወታደሮች ተይዛ ስትታሰር፤ እያስፔድ ተስፋዬ በጨለማ ከቤቱ እየተወሰደ ሲደበደብ፤ አቤል ኤፍሬም በድበደባ ምክንያት የኩላሊት በሽተኛ ሆኖ ከሥራ ተባሮ ቤቱ ሲቀመጥ፤ ጋሻው መርሻ እንደጠላት በተገኘበት ሁሉ ሲደበደብ እና ሲታሰር፤ ስለሺ ፈይሳ በተገኘበት ሲደበደብ ሳሙኤል አወቀ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቱ ሲያልፍ ሌሎችም ስማቸውን ያልጠቀስኳቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የስቃይ ሰለባ ሲሆኑ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የት ነበሩና ዛሬም ተነስተው እንደአዋቂ የሰማያዊ ፖርቲ አባላትን የሚተቹት?
ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ አሉባልተኞች ነፃ መውጣት አለባቸው፤ ፖለቲካዊ ትግል ሕዝብን ሰብስቦ ንግግር የማድረግ ያህል ቀላል አይደለም።
‪#‎ኤርሚያስ_ቶኩማ‬