የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፈርጥ የሳክስፎን ንጉሡ ጌታቸው መኩሪያ በ81 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ::


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(Saxophonist  Getachew Mekuria Died ) – ጌታቸው መኩሪያንና ሳክስፎንን ነጣጥሎ ማሰብ ለብዙዎች ይከብዳል፡፡ በተለይም ጎፈር ደፍቶ፣ ካባ ለብሶ በሳክስፎኑ ሽለላውን ሲያስደምጥ የአድማጭን ቀልብ ይገዛል፡፡ ለረዥም ሰዓታት መድረክ ላይ ያለማቋረጥ ሙዚቃ በማቅረብ ዝናን ተቀዳጅቷል፡፡ ወኔውና ሙዚቃዊ ምልዐተ ኃይሉ ከወጣትነቱ አንስቶ በዕድሜ ገፍቶም አብሮት ዘልቋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን ከኢትዮጵያ ውጭ በችሎታው ያልተደመመ የለም ቢባል ማጋገን አይሆንም፡፡ የኢትዮጲክስ ስብስብ ቁጥር 14 ሽለላ በሳክስፎንና ሌሎችም ሙዚቃዎቹን ያካተተ ሲሆን፣ በአልበሙ  ‹‹የኢትዮጵያ ሳክስፎን ንጉሥ›› ተብሏል፡፡

ከወጣት እስከ አንጋፋ የአገር ውስጥና የውጪ ሙዚቀኞች ጌታቸው በሳክስፎኑ ያደመቃቸው መድረኮች ተካፋይ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፈርጥ በ81 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ መጋቢት 27 ቀን በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡

ለ68 ዓመታት ሳክስፎን የተጫወተው ሙዚቀኛው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሳክስፎን ድምፅ የሰማው የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለ በሬዲዮ እንደነበረ የታሪክ ገጹ ያስነብባል፡፡ ከትውልድ አገሩ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ መጀመሪያ ክራርና መሰንቆ ከዛም ሳክስፎንና ክላርኔት መጫወት ጀመሩ፡፡ በ1941 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሙዚቃ መጫወት ጀመረ፡፡ ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) ተጫውቷል፡፡ በ1950 ዓ.ም. የፖሊስ ኦርኬስትራ ባንድን በመቀላቀል ለ36 ዓመታት ሠርቶ ሕይወቱ በሙዚቀኛነት አጣጥሟል፡፡ ጡረታ ከወጣ በኋላ በሸራተን አዲስም ይሠራ ነበር፡፡

አርበኞች የጦር መሣሪያቸውን ከማንገባቸው አስቀድሞ፣ አንግበውና ከድል በኋላም ከአንደበታቸው የማይለየው ሽለላ በጌታቸው የሙዚቃ ሕይወት ልዩ ቦታ ነበረው፡፡ በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሽለላን ለሕዝብ ጆሮ ያደረሰ ግንባር ቀደም  ሙዚቀኛ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በ1962 ዓ.ም. የተለቀቀው የሽለላ ሙዚቃ አልበሙ ለዚህ ሕያው ምስክር ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ ዛሬም ድረስ ወኔና ድልን በሚያስተጋቡ መድረኮች ይደመጣሉ፡፡

ቀድሞ ከአንጋፋዎቹ ድምፃውያን ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሒሩት በቀለና አያሌው መስፍን ጋር የሠራ ሲሆን፣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ደግሞ ከደቾቹ ዘ ኤክስ ባንድ ሙዚቀኞች ጋር ይጫወት ነበር፡፡ የባንዱ ሙዚቀኞች የጌታቸውን ኅልፈት አስመልክቶ በድረ ገጻቸው በሰጡት መግለጫ፣ ሙዚቀኛው ዘ ኤክስን በአንድ ፌስቲቫል ላይ ካዳመጧቸው በኋላ አብረዋቸው ለመጫወት እንደወሰኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከኛ ጋር መጫወት ይወድ ነበር፤ እኛም ከሱ ጋር አስገራሚ ተሞክሮ ነበረን፣ ዘወትር ራሱን የሆነ ሙዚቀኛ ነበር፡፡ መሰጠቱና የሙዚቃ ፍቅሩ ወደር አይገኝለትም፤›› ብለዋል፡፡

ከባንዱ ጋር በ1998 ዓ.ም. ‹‹ሞአ አንበሳ›› እና በ2004 ዓ.ም. ‹‹የአንበሳው ትዝታ›› የተሰኙ ሁለት አልበሞች ሲለቅ በተለያዩ አገሮች በመዘዋወርም ሙዚቃዎቹን አቅርቧል፡፡ ኔዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሣይ፣ ካናዳና አሜሪካ ያቀረባቸው ኮንሰርቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ለብዙ የጃዝ ፌስቲቫሎችም ድምቀት ሰጥቷል፡፡ በ1950ዎቹ ‹‹ሽለላ›› አልበምን ለቀዋል፡፡ የኢትዮጲክስ ስብስብ ቁጥር 14 እና ቁጥር 20 ከኢዘር ኦርኬስትራ ጋር የተጫወተው ሙዚቃ በ1996 ዓ.ም. ተለቋል፡፡ በ1999 ዓ.ም. ጌታቸው መኩሪያና ዘ ኤክስ አልበም ወጥቷል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጌታቸው የጤና ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ ከዘ ኤክስ ጋር ጉዞ ማድረግ ቢያቆምም፣ ዓምና በጥቅምት ወር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተካሄደው የመጨረሻው የመታሰቢያ ዝግጅት አይዘነጋም፡፡ ሙዚቀኛው እንደወትሮው በወኔ መድረክ ላይ መንጎራደዱ ቀርቶ ሕመም ተጫጭኖት ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳክስፎኑን ቢጫወትም፣ ትርኢቱ ግሩም ነበር፡፡ ‹‹ትሪቢውት ቱ ጌታቸው መኩሪያ›› በሚል በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ የቀረበው የመጨረሻ ትዕይንቱን ብዙዎች የታደሙት ነበር፡፡

በወቅቱ ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ጤናው በመታወኩ የመጨረሻ መድረኩ እንደሆነ ገልጾው፣ ‹‹ይኼ የመጨረሻ ዝግጅቴ ነው፤ ሁሉንም ተሰናብቻለሁ፤›› ብሎ ነበር፡፡ የአብዛኛው ሙዚቃው መነሻ የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ እንደሆነም ተናግሮ ነበር፡፡ ‹‹ቀድሞ የሚሸለለው በሰው ድምፅ እንጂ በመሣሪያ አልነበረም፡፡ እኔ የራሴን ቀለም አክዬበት በሳክስፎን ተጫወትኩ፡፡ በሳክስፎኔ ታሪኰችን ለመናገር እሞክራለሁ፤ እስካሁን ወደ 34 አገሮች ተጉዣለሁ፤ በእያንዳንዱ አገር ከራሴ ይልቅ ኢትዮጵያን ወክያለሁ፤›› ብሎ ነበር፡፡

ሚውዚኰሎጂስቷ ዶ/ር ትምክህት ተፈራ ሙዚቀኛው ታላቅ የኢትዮጵያና የሙዚቃው ዓለም ሀብት እንደሆነ በድረ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ ‹‹ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን በታላቅ ኩራት ወክሏል፡፡ በኅልፈቱ አዝኛለሁ፡፡ ታላቅ ሥራ ትቶልን አልፏል፤›› ብለዋል፡፡

የጌታቸውን ሙዚቃዎች በሥራዎቻቸው ካካተቱ ሙዚቀኞች ኬናንና ዴሚያን ማርሌ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹አይ ካም ፕሪፔርድ›› በተሰኘው ዘፈን የጌታቸው ሳክስፎን ተቀንጭቦ ገብቷል፡፡ ፈረንሣይ የሚገኙ የሙዚቃ ባንድ አባላት ከሙዚቀኛው ሥራ አንዱ ‹‹አካሌ ውቤን›› ለማስታወስ ባንዳቸውን ‹‹አካሌ ውቤ›› ብለው ሰይመዋል፡፡

መጋቢት 5 ቀን 1927 ዓ.ም. የተወለደው ሙዚቀኛው ጌታቸው መኩሪያ ባለትዳርና የልጆች አባት ነበረ፡፡

Source –  ከሪፖርተር
[youtube http://www.youtube.com/watch?v=h5-aO-5k-_g]