በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ ወቅት የመንግሥት ድረ ገጾችን ሰብሮ የመግባት ጥቃት መፈጸሙን፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ለፓርላማው ገለጹ፡፡
የተሰነዘሩት ጥቃቶች በአብዛኛው ያተኮሩት በወረዳ ኔት ድረ ገጽ ላይ መሆኑን፣ ለሚመለከታቸው ተቋማትና ለመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የማሳወቅ ሥራ በማከናወን የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት መደረጉን፣ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን ችግር የገጠማቸው ድረ ገጾች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
የወረዳ ኔት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ሁሉንም የአገሪቱ ወረዳዎች በአንድ የሚያገናኝ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚገኘው የብሔራዊ የዳታ ማዕከል ውስጥ የተካተተ መሆኑ ይታወቃል፡፡
‹‹ግርግር ሲጀመር ነው የወረዳ ኔት ድረ ገጽ ላይ ጥቃት የተሰነዘረው፡፡ ከየትኛው አገር እንደተሰነዘረም አውቀነዋል፡፡ ልዩ ትኩረትም እንሰጠዋለን፤›› በማለት ሚኒስትሩ ለፓርላማው አሳውቀዋል፡፡
ዓላማውን በተመለከተም አንድ ግርግር በኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈጠር እሱን በማራገብ ለማቀጣጠል መሞከር እንደሆነ፣ የዚሁ አካል ሌላኛው ሙከራም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንደታየ ተናገረዋል፡፡
በኦሮሚያ በተከሰተው ተቃውሞ ወቅት የመንግሥት ድረ ገጾችን ሰብሮ የመግባት ጥቃት መፈጸሙን ዶ/ር ደብረጽዮን ገለጹ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።