አይቻልም !!! ከ25 ዓመታት በኋላም …ለማታለልና ለማጭበርበር ? Girma Bekele
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከወራት በፊት100 በመቶ / 100 %/ መረጠኝ ያሉት ህዝብ ለሚያሰማው ተቃውሞ እንደምን ጥይት መልስ ሊሆን ይችላል ?
ይቅርታ ያሉበትን ጥፋት አጠናክረው፣ የጥፋት ጎዳናውን አስፍተው እየተጓዙ እንደምን በህዝብ አመኔታ ማግኘት ወይም መጠበቅ ይቻላል ?
አብሮኣቸው ሲያቦኩ የነበሩ ባለስልጣናትን ማባረር እንደምን ለህዝብ ጥያቄ መልስ ሊሆን ይችላል ?
ሚዲያውን እያፈኑ፣ የኃሳብ መንሸራሸርን አግዶ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ አፍኖ፣የፖለቲካና ኅሊና እስረኞች፣ በወህኒ እየማቀቁ …. እንደምን ከህዝብ ጋር በመወያየት ስለሚመጣ መፍትሄ መነጋገርና መተማመን ይቻላል ?
እንደምን በአገሬ መዲና ‹‹የግለሰቦች እስር ቤት አለ ›› ብሎ የሚነግረን መንግስት ግለሰብ ባልተቆጣጠረ አቅሙ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና የመንግስትን ሁለንተናዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይቻለኛል ብሎ ያስባል ?.
ሲጠቃለልም- በአምባገነንነት የታጀበ የዘረኝነት በሽታ እንደምን ከበሽታው አምጪ ህዋስና ከበሽታው ተሸካሚና አስተላለፊ ጥገኞች መድሃኒት/መፍትሄ ይመጣል ብሎ ማሰብ ይቻላል ? ከበሽተኛ አዕምሮ ጤናማ መፍትሄ ? …..
በፍጹም አይቻልም፡፡ ይህንን በመረዳት ነው ህዝብ ከዳር እስከዳር ሳይነጋገር በአንድ ሃሳብ ተስማምቶ ‹‹ በቃን ›› ያለውና የግፍ ጽዋው በሞላበት ከ25 ዓመታት በኋላም …ለማታለልና ለማጭበርበርው የሚደረገውን ሙከራ አይቻልም የሚለው፡፡ ሙከራው ከእብሪትና ህዝብ ንቀት ውጪ ሌላ ሊሆን አይችልም ፣ ከእንግዲህ ብዙ ርቀት አያስጉዝም፡፡
ስለዚህ መፍትሄው አንድና አንድ ነው ፤ ህዝብ እየጠየቀ ያለውን በእኩልነት ላይ የቆመ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ስለሚመሰረትበት ሁሉም ያገባኛል ባይ ወገን (የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ …) ተሳትፎ በብሄራዊ መግባባት ዕርቀ-ሰላም በማውረድ፣ በአገሪቱ ነባራዊና ወቅታዊ ችግሮችና ለቀጣይ ዘላቂ አገር-በቀል መፍትሄ የሚመቻችበት ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት መመስረት፡፡
ይህ ደግሞ ከአምባገነናዊ መንግስታት በልመና የሚገኝ የበጎ ፈቃድ ሥጦታ አይደለም፤ በየትም አገር አልታየምም፡፡ የዕድራችን ድክመት እንጂ ይህ አምባገነናዊ መንግስት አብቅቶለታል፣ ለዚህም በግልጽ የምናያቸውንና የምንኖራቸውን ተጨባጭ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ‹‹ሙት ይዞ ይሞታል›› እንዳይሆንብን መላው/ዘዴው ዕድሩን ማጠናከር ነው– ትግሉን የእያንዳንዳችንም፣ የሁላችንም ማድረግ፡፡ ልብ ያለው ልብ በል፣ ጊዜው ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡ ለአገራችንና ወገን የሚበጀውን ያሳስበን፣ ያሰራን፤ ደግ ደጉን ያሰማን፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡ 16/07/08 .UNITE. Gtima bekele