የተስፋሁን አለምነህ ጉዳይ እኔም ያሳስበኛል (ኤርሚያስ ቶኩማ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የተስፋሁን አለምነህ ጉዳይ እኔም ያሳስበኛል (ኤርሚያስ ቶኩማ) ተስፋሁን በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብቅ ካሉ ጠንካራ ወጣት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነው። ተስፋሁን በይፋ ፖለቲካዊ ድርጅት ውስጥ ገብቶ መታገል የጀመረው በ1996 አመተ ምህረት ገና በለጋ እድሜው በመኢአድ ፓርቲ ነው።
በመኢአድ ውስጥም በቆየባቸው ድፍን አሥራ አንድ አመታት የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ጅምር ሥራ ከዳር ለማድረስ ሲታሰር እና ሲገረፍ የነበረ ነው በኋላም በሰላማዊ ትግል ላይ የነበረው እምነት በመሟጠጡ ምክንያት ወደኤርትራ በረሃ ወርዶ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሐይሎች ንቅናቄን መቀላቀሉን በፌስቡክ መልእክት ሲልክልኝ በጣም መደንገጤን እና እንደተገረምኩኝ አጫውቼው ነበር የመገረሜ ምክንያት ሰምቼው የማላውቀው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሐይሎች ንቅናቄ የሚባል መኖሩ ሲሆን ድንጋጤዬ ደግሞ ሻእቢያን ስለማላምን ነው።
ተስፋሁን ጋር የነበረን ግንኙነት ከህዳር አካባቢ ጀምሮ ተቋርጧል ሆኖም ያን ያህል አላሳሰበኝም ነበር ምክንያቱም ኤርትራ የገባው ሊታገል እንጂ ከእኔ ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ሊያወራ አይደለም ሆኖም በቅርቡ እየሰማሁት ያለው ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነው። አንዳንዶቹ ተስፋሁን ኤርትራ የሚደረገው ትግል እንደጠበቀው ስላልሆነለት ጥሎ ለመውጣት ሲሞክር ተይዞ በሻእቢያ ወታደሮች ተረሽኗል ሲሉ የተቀሩት ደግሞ ይሄ አሉባልታ ነው ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ይላሉ። እኔ ሁለተኛው ቡድን የሚለው እውነት እንዲሆን እመኛለሁ ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን እንደተባለው ተስፋሁን ላይ ጥቃት ከተፈፀመበት ወይም ከታሰረ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን ትግል የሚጎዳ ይሆናል ምክንያቱም ዛሬ በረሃ ወርደው የትጥቅ ትግል ታጋዮችን መቀላቀል የሚፈልጉ ወጣቶችን ቅስም የሚሰብር ከመሆኑም በላይ ድሮም በቋፍ ላይ የነበረው ኢትዮጵያውያን ለኢሳያስና ለሻእቢያ ያላቸው ጥቂት እምነት ገደል የሚገባ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ በኤርትራ በሚገኙ ፖለቲካዊ ቡድኖች ላይ የሚደርሰው ፖለቲካዊ ኪሣራ ከፍተኛ ይሆናል። የተስፋሁን ጉዳይ አሁን የጥቂቶች መነጋገሪያ መሆኑ አብቅቶ አሁን በርካቶች በአደባባይ የሚያወሩት የአደባባይ ወሬ ሆኗል።
የተስፋሁን ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሐይሎች ንቅናቄ የተሰኘው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት እውነት እንደተባለው በሕይወት ያለ ድርጅት ከሆነ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ መልስ ሊሰጠን ይገባል። 1, ተስፋሁን አለምነህ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? 2, ተስፋሁን አለምነህ እንደተባለው ተረሽኖ ከሆነ በምን ጥፋት ተረሸነ? የረሸነውስ አካል ማነው? 3, ድርጅቱ እስካሁን በተስፋሁን ጉዳይ ላይ ስለምን ዝምታን መረጠ? እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ጥያቄዎች የእኔ ጥያቄ ብቻ አይደለም የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው። ተስፋሁን አለምነህ ኤርትራ የገባው ሊታገል እንጂ በሻእቢያ ሊረሸን አይደለም በመሆኑም የተስፋሁን ጉዳይ ያገባኛል። የተስፋሁን ጉዳይ ያገባኛል ስል ተስፋሁን ጓደኛዬ ስለሆነ አይደለም የዚህ ትውልድ ቀንዲል ስለሆነ እንጂ። #ኤርሚያስ_ቶኩማ