[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
–    ምን አዲስ ነገር አለ?
–    ሪፖርቱ ነዋ፡፡
–    የትኛው ሪፖርት?
–    ሰሞኑን የወጣው፡፡
–    በምን ላይ?
–    በሕገወጥ ዝውውር፡፡
–    የሕገወጥ ዶላሩን ነው?
–    እ…
–    ለእነዚህ ኒዮሊብራሎች ግን የት እንሂድላቸው?
–    ምን እያሉ ነው?
–    ዶላር ከአገር ሸሸ ነው የሚሉት?
–    ኧረ እኔ ሕገወጥ የሰው ዝውውሩን ነው የምልዎት፡፡
–    እእእ…
–    ምነው ደነገጡ?
–    የምን ሕገወጥ ዝውውር ነው?
–    በአፍሪካ ቀንድ የሚደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነዋ፡፡
–    ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተባለ እንዴ?
–    በዚህ ወንጀል ላይ ባለሥልጣናትም ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
–    እኛ?
–    አይ የለም የኤርትራ ባለሥልጣናትን ነው፤ ምነው ደነገጡ?
–    እኔን ያልከኝ መስሎኝ ነዋ?
–    እርስዎማ በዚህኛው ዝውውር መቼ ይጠረጠራሉ?
–    በየትኛው ዝውውር ነው የምጠረጠረው?
–    እ…
–    ለመሆኑ ምንድን ነው ባለሥልጣናቱ የሚያደርጉት?
–    ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ከአገራቸው እንዲፈልሱ ያደርጋሉ፡፡
–    እኮ ለምን?
–    ዶላር ለማግኘት ነዋ፡፡
–    እንዴት ሆኖ?
–    በቃ ከሰዎቹ ዶላር ይቀበላሉ፡፡
–    ዕቃ ኤክስፖርት ማድረግ ሲያቅታቸው ሰው ኤክስፖርት ማድረግ ጀመሩ ማለት ነው?
–    እንደዚያ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ዘዴኛዎች ናቸው ባክህ፡፡
–    እንዴት?
–    ያው በተዘዋዋሪም ቢሆን እያገኙት ነዋ፡፡
–    ምኑን?
–    ዶላሩን፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር ይህ እኮ ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡
–    ማነው ያለው?
–    የሰዎች ዝውውር እኮ ነው፡፡
–    ቢሆንስ?
–    ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
–    ይኼ የኒዮሊብራሎች ትምክህት ነው፡፡
–    እንዴት ሆኖ?
–    እነሱ በገንዘብ ሰው ያዘዋውራሉ አይደል እንዴ?
–    መቼ ነው ያዘዋወሩት?
–    ይኼው እግር ኳስ ተጫዋቾቹ ከአንድ ክለብ ወደ ሌላው ክለብ በከፍተኛ ገንዘብ አይደል እንዴ የሚዘዋወሩት?
–    እሱ እኮ ሕጋዊ ነው፡፡
–    ይኼኛውስ?
–    ሕገወጥ ነዋ፡፡
–    ለምን እኛ አንሞክረውም ግን?
–    ምኑን? ዝውውሩን?
–    ሕጋዊ ዝውውሩን፡፡
–    በኳስ ተጨዋቾቻችን?
–    በእነሱ ሳይሆን በአትሌቶቻችን፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር አያውቁም እንዴ?
–    ምኑን?
–    በአትሌት ስም ስንቱ በርካታ ገንዘብ እየከፈለ ከአገር እንደሚወጣ፡፡
–    ምን?
–    ትንሽ ዘገዩ፡፡
–    ለምኑ?
–    ለዚህኛው ቢዝነስ፡፡
–    እንዴት?
–    በሌሎች ተቀድመዋል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ቦታ ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]
–    እዚህ ጋ አቁም!
–    ኧረ አይቻልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ለምንድነው የማይቻለው?
–    የተከለከለ ቦታ ነው፡፡
–    ማን ነው የከለከለው? አቁም!
–    ኧረ የእንጀራ ገመዴን ያስበጥሱብኛል፡፡
–    ከእኔ ውጪ ማን ነው የአንተን የእንጀራ ገመድ የሚበጥሰው?
–    አዲስ ሕግ ወጥቷል፡፡
–    ምን የሚል?
–    ተደጋጋሚ ጥፋት ያጠፋ ይቀማል የሚል፡፡
–    ምኑን ነው የሚቀማው?
–    መንጃ ፈቃዱን?
–    መፍጃ ፈቃዱን ነው ያልከኝ?
–    በሉት፡፡
–    በል አሁን አቁም፡፡
–    ኧረ ይኼ ሦስተኛ ቅጣቴ ነው የሚሆነው ክቡር ሚኒስትር?
–    ሕጉን ያወጣነው እኛው አይደለን እንዴ?
–    የሚተገበረው እኛ ላይ ነዋ፡፡
–    እንዲያውም ትራፊኩ ያውና ንገረውና አቁመው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ትራፊኩን ክላክስ አድርጐ ጠራው]
–    እዚህ ጋ ላቁም?
–    አዲስ የወጣውን ሕግ ታውቃለህ አይደል?
–    በሚገባ፡፡
–    እዚህ ጋ ላቁም ብለህ በማሰብህ ራሱ ልቀጣህ እችላለሁ፡፡
–    ይቅርታ እንግዳ ስለያዝኩ ነው፡፡
–    አይደለም እንግዳ ለምን ባለሥልጣን አትይዝም?
–    ምን አልከኝ?
–    የእንጀራ ገመድህን እንዳልበጥስልህ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከኋላ የመኪና መስታወታቸውን አወረዱት]
–    እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
–    እዚህ ጋ አንድ ቀጠሮ ነበረኝ፡፡
–    ምን ላድርግልዎት ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
–    እዚህ ጋ ብናቆም ብዬ ነው፡፡
–    አይደለም ማቆም አዝለህ ውሰደኝ ቢሉኝ አልወስድዎትም እንዴ?
–    እንዲህ ነው እንጂ፡፡
–    ሊጋልቡኝ ይችላሉ ስልዎት፡፡
–    እሱን ሌላ ጊዜ፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር እኔም እፈልግዎት ነበር፡፡
–    ቢሮ ና፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋ ወሬያቸውን ቀጠሉ]
–    እኔ እኮ አይገባኝም፡፡
–    ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
–    የመልካም አስተዳደር ችግር አለ የሚባለው፡፡
–    እንዴት?
–    ከዚህ በላይ መልካም አስተዳደር አለ?
–    መልካም አስተዳደር ያለው እኮ ለእኛ አይደለም፡፡
–    ለማን ነው ያለው ታዲያ?
–    ለእናንተ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀጠሯቸው የውጭ ዜጐች ጋር ተገናኙ]
–    ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ብዙ ሥራ መሥራት እንፈልጋለን፡፡
–    የሚሠራን ሰው እናበረታታለን፡፡
–    አገራችሁን እንደ አገራችን ለማሳደግ ቆርጠን ተነስተናል፡፡
–    አገራችሁ አድጋለች እንዴ?
–    ለዓለም ሁሉ ዕቃ የምናቀርበው እኛ አይደለን እንዴ?
–    ለነገሩ እውነታችሁን ነው፡፡
–    እዚህ አብዮት ማስነሳት ነው የምንፈልገው፡፡
–    ኒዮሊብራሎች ናችሁ እንዴ? የምን አብዮት ነው?
–    የለም የለም፤ የገበያ አብዮት ነው የምልዎት፡፡
–    እሱኛውን አብዮት ማስነሳት ትችላላችሁ፡፡
–    አገሪቷን እናስመነድጋታለን ስልዎት፡፡
–    ለልማት በራችን ክፍት ነው፡፡
–    አንዳንድ ነገሮች ግን አስቸግረውናል፡፡
–    ምን ዓይነት አንዳንድ ነገሮች?
–    ቀረጥና ፈቃድ ማውጣት የመሳሰሉት፡፡
–    ያስቸገሯችሁ ከሌላ ጋር እየሠራችሁ በመሆኑ ነው፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ወሳኝ መሆንዎት ገብቶን እኮ አሁን ወደ እርስዎ የመጣነው?
–    ቢሆንም ዘግይታችኋል፡፡
–    አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች አሳስተውን ነው፡፡
–    ለማንኛውም እነዚህን ነገሮች እኔ እጨርሳቸዋለሀ፡፡
–    ምን እናድርግ ታዲያ?
–    በአስቸኳይ እንፈራረማ፡፡
–    ስለእሱ አያስቡ፤ አሁኑኑ ድርጅቱን እንመሠርታለን፡፡
–    እኔም ሌላውን እጨርሳለሁ፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር…
–    አቤት፡፡
–    ልንሠራው ያሰብነው ቢዝነስ ግን ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደ ነው፡፡
–    ታዲያ ምን ችግር አለው?
–    እኛ የውጭ አገር ዜጐች ነና፡፡
–    ኢትዮጵያውያን ትሆናላችኋ፡፡
–    እንዴት?
–    በእኔ በኩል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ቁጭ ብለው በሞባይላቸው ካንዲ ክራሽ የሚባለውን ጌም ሲጫወቱ ጸሐፊያቸው ገባች]
–    ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ምን ፈለግሽ?
–    እንግዳ ይፈልግዎታል፡፡
–    ሥራ ይዟል በይ፡፡
–    ኧረ ስድስት ወር ሙሉ ሲመላለስ ነበር፡፡
–    በቃ ሌላ ስድስት ወር ይጠብቃ፡፡
–    ምን እየሠሩ ነው ግን?
–    ከባድ ሥራ ይዣለሁ፡፡
–    እንዴ ክቡር ሚኒስትር ካንዲ ክራሽ እየተጫወቱ ነው እንዴ?
–    ትጫወቻለሽ እንዴ አንቺም?
–    አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    እንዴት አዕምሮ የሚያሠራ ጌም መሰለሽ?
–    አውቃለሁ ስንተኛው ሌቭል ላይ ነዎት?
–    100 ደርሻለሁ፡፡
–    እርስዎና ኢሕአዴግ ግን ይኼን ቁጥር ትወዱታላችሁ፡፡
–    የቱን ቁጥር?
–    100!
[ክቡር ሚኒስትሩ የጌሙን ሌቭል ማለፍ አቅቷቸው ተክዘው ቁጭ ብለው ሚስታቸው መጡ]
–    ምን ሆነህ ነው የተከዝከው?
–    ኧረ ተይኝ እባክሽ፡፡
–    ምን ሆንክ?
–    ማደግ አቃተኝ እኮ፡፡
–    ያቺ 11 ፐርሰንቷ ቀረች እንዴ?
–    እሷማ እንደቀጠለች ነው፡፡
–    የሥራ ዕድገት ጠየቅክ እንዴ ታዲያ?
–    ሕይወት ተቀጥፎብኝ ነው፡፡
–    ምን ሆነሃል ሰውዬ? ሁላችንም ሰላም ነን እኮ፡፡
–    አይ እኔ መቼ የእናንተ ሕይወት አሳሰበኝ?
–    የማን ሕይወት ነው ያሳሰበህ ታዲያ?
–    የጌሙ ነዋ፡፡
–    የምን ጌም?
–    ምን ይቺ ልጅሽ ጊዜ ሲኖርህ ተጫወተው ብላ አንድ ጌም አሳይታኝ ይኸው ሱስ ይዞኝ አርፏል፡፡
–    ጌም ነው ያልከኝ?
–    አዎን፡፡
–    ሥራውን ትተህ ጌም?
–    እንዴት ጭንቅላት የሚጠይቅ ጌም መሰለሽ?
–    ምን የሚሉት ጌም ነው?
–    ካንዲ ክራሽ፡፡
–    በል ተጠንቀቅ፡፡
–    ምኑን?
–    አንተ ካንዲ ክራሽ ስታደርግ …
–    እ…
–    አንተ ራስህ ክራሽ እንዳትደረግ፡፡
–    በማን?
–    በሕዝቡ!

Source –  ሪፖርተር