ሰማህ ወይ ሕዝቤ፥ ሰማህ? /ዮሐንስ ሞላ/
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ሰማህ ወይ ሕዝቤ፥ ሰማህ?
ሰማህ እንዴ ሲጣሩ፥ ሰማህ ከቶ ያን ሰማይ?
ሰማህ ሲጮህ ባህሩ፥ ሰማህ ሲተራመስ ቀላይ?
ሰማህ ሲታመስ ሀገሩ፥ ሰማህ ሲላወስ ያ ተባይ?
ሰማህ መንገድ ሲማትር፥ ሰማህ ሲከለከል ከልካይ?
ሰማህ ወገኔ ምድሩን፥ ሰማህ ጎኔን ዓለሙን?
“እህ” አልከው ይሆን ከቶ፥ ግዑዝ ሲጮህ አፍ አውጥቶ?
ብቻ ሁን ሰላም፥ ባትሰማም!
ሰማህ እሳት ሲንቀለቀል፥ ተግ እያለ ሲንበለበል?
ሰማህ ህዝቤ ሰቀቀኑን፥ ሰማህ ህመም ሲንበለበል?
ሰማህ እሳት እሳት ሲተፋ፥ የጎረሰውን ሲደፋ?
ሰማህ ወይ ሰውነት ተጠብሶ፥ ገላ በገላ ተላኩሶ?
ሰማህ ውሃ ሲል ሃገሩ፥ ሰማህ ምህረት ሲል መንደሩ?
ሰማህ ወይ አጥፊ ሲጣራ? ሰማህ ነገ ሲሰራ?
ሰማህ ሲነዳ ወዳ’ለም በቃኝ ጎራ፥ ንቁ ሲጠፈር በተራ?
ሰማህ እግረሙቁ ሲጮህ፥ ሰማህ ወፍ ወፌላላ ሲያጓራ?
ብቻ ሁን ሰላም፥ ባትለማም!
ሰማህ ወይ ዘር በዘር ሲቆላ፥ ሰማህ ጭንቁን ደጋ ቆላ
ሰማህ ሰው ሲናፍቅ ሰው ሞልቶ፥ ሰማህ ሲያነጥፍ ወገን ገፍቶ?
ሰማህ ሲከብድ ሰው ለሰው፥ ሰማህ ወይ ሲጨንቅ ቀን ለቀን?
ሰማህ ወይ ሲጨነቅ ወገን? ሰማህ በወገን ሲጓነን?
ሰማህ ሲወጣ ሲገባ፥ ሰማህ ሲኖር በሰቀቀን?
ሰማህ ወይ ሲሄድ ተነድቶ፥ ሰማህ ሲጮህ ተረትቶ?
ሰማህ ዘመድ ሲሆን ባዳ፥ ሰማህ እሾህ ሆኖ ስጋ፥ ሲወጋ?
ብቻ ሁን ሰላም፥ ባትሰማም!
ሰማህ ግን አንተ ሰው ሰማህ፥ ሰማህ ግፌን፣ በደሌን?
ሰማህ ጉዱን፣ ታምሩን፥ ሰማህ ጭንቄን ህመሜን?
ሰማህ የሀገሩን ዋይታ፣ ሰማህ ወይ የጠላትን ሆታ?
ሰማህ ወገኔ ጭንቄን፣ ሰማህ ወይ ጩኸቴን ጣሬን?
ሰማህ ወድቄ ሳምጥ፥ የዋይታ ለሃጬን ሳላምጥ?
ሰማህ ወገኔ ሲንቃቃ ጎኔ፥ ስንቀጠቀጥ አጥቼ ወኔ?
ሁንልኝ ሰላም ባትለማም!
ሰማህ ዓላማህን ለየኸው፥ ከጭንቁ ገበያ ታየህ?
የወገንህ ደም ነጣ ወይ? ስጋ ጠረኑ ተሰማህ?
ሰማ አፍንጫህ ሰማ? ሰማ እጅህስ ሰማ?
ሰማ ምላስህ ሰማ? ሰማ ዐይንህስ ሰማ?
ክፉን ከደጉ ለየ ወይ፥ ሰማ ኑሮዬን ሰማ?
ሰማህ ጠላትህ ሲያደባ? ሰማህ ወዳጅህ ሲያነባ?
ሰማህ ጉድጓዱን ሲምስ? ሰማህ ወገንህ ሲያለቅስ?
ሰማህ መቃብር ሲቀልስ? ሰማህ ሰው ጥጋት ሲያስስ?
ሁንልኝ ሰላም ባትሰማም!
ሰማህ ወንድምህ ሞቶ፥ ደረት ሲፈርስ ተደቅቶ?
ጎድን ሲበተን በሜዳ፥ ስጋ ሲሆን እንደ ጭዳ?
ሰማህ ወይ ዋይታዬን ሰማህ፥ ድረሱልኜን ዋይታዬን?
ሰማህ ድንቁርና ሲያምሰን፥ መሀይምነት ሲቀምሰን?
ሰማህ ወይ ሲቃጠል ጎኔ፥ ጭንቁ ቀሰቀሰህ ወገኔ?
ብቻ ሁን ሰላም ባትሰማም!
ሰማህ ሲፈትሹ ጉያዬን፥ የታሪክ ያንተ ቅርቃሬን?
ሲበረብሩ ማጀቴን፥ ሰማህ ሲዳብሱ ጎኔን?
ሰማህ ሲታገሉኝ ህልሜን፥ ሲዋደቁ ቅሚያ ተስፋዬን?
ሰማህ ተዘርፎብኝ ቀኔ፥ ስፍጨረጨር ዝርፊያ ቅኔ?
ትሰማለህ!
ከእኔ ጭንቀት ሰምና ወርቅ ታነጥራለህ!
ብቻ ሁን ሰላም ባትለማም!
/ዮሐንስ ሞላ/