አስቸኳይ – ብሄራዊ ውይይት፣መግባባትና ዕርቅ – Girma Bekele


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አስቸኳይ// ብሄራዊ ውይይት፣መግባባትና ዕርቅ—
የሁላችን አሸናፊነት ማረጋገጫ ብቸኛው መፍትሄ፤ ለህወኃት ‹‹ የወንድ በር ፣የማሪያም መንገድ፤››
ዛሬ ላይ ሁሉም ነገር ከትናንቱ በጣም ፈጣን በሆነ መንገድ እየተለወጠ ነው፡፡ የህወኃት/ኢህአዴግ ችግሮችን በኃይል፣ክህደት፣እብሪትና በደረቅ ፕሮፖጋንዳ የማፈን አካሄድ አብቅቶለታል፤ አክቶሞለታል፡፡ ‹‹ማን ከማን ተጣላ›› ለሚለው ተደጋጋሚ አሰልቺ ጥያቄው በዓለም ፊት ግልጽ መልስ አግኝቷል፡፡ በህወኃት/ኢህአዴግ የተፈጸመውን ግድያ፣ ማፈናቀል፣እስራት፣ስደት፣ …እና በፖለቲካዊው መድረክ በገዢውና ተቃዋሚው መካከል ያለውን ልዩነት ብናቆየው በህወኃት/ኢህአዴግ መንግስትና ህዝብ መካከል በኑሮውና በህይወቱ ያለው እይታና ልዩነት፣ ህዝብ ኑሮው ከሸክሙ በላይ በሆነበትና በድርቅ ህይወት እየተቀጠፈ ባለበት፣ መንግስት በተደጋጋሚ ህዝብን እየዋሸ ያለበት በግልጽ በታየበት እውነታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ዛሬ ይህን በምንም መካድ አይቻለውም፡፡ የህዝብ ልብ በህወኃት/ኢህአዴግ ላይ ሸፍቷል፣ ከነጻነት በመለስ ከሸፈተበት አይመለስም፡፡


ትናንት ‹‹…ድርቁ ከአቅማችን በላይ አይደለም፣ከ11% ተከታታይ ዕድገታችን አቅም በላይ አይሆንም፤… በህዝብ ላይ የደረሰ ችግር የለም፣ ድርቁን አስቀድመን በማወቃችን በአግባቡ ልናስተዳድረው ችለናል(… properly managed ) ነው…. በድርቅ ለተጎዱት በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት የሚያስፈልገው ካሎሪ እየቀረበ ነው…›› እያሉ ‹‹ክህደት ›› በመፈጸም ወገንን ሆነ የዓለም ህዝብ እንዳይደርስ በማዘናጋት ለተቀጠፈው ህይወትና ለተጋረጠብን ቀጣይ ፈተና ብቻ ልንነጋገርበትና ህወኃት/ኢህአዴግ ከህዝብ ሊታረቅበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እውነት በህወኃት ሳይወድ የግድ ተቀባይነት እያገኘ ፣ እብሪቱ እየተነፈሰ መምጣቱን እናያለን፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በኦሮሚያ የተነሳውን ህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ‹‹ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነዋል›› ባሉበት አፋቸው ዛሬ ‹‹ ከሞላ ጎደል ተቆጣጥረነዋል ›› ፣የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ጉዳይ ሚ/ሩ የጋምቤላ ክልል ግጭት በሚመለከት ‹‹ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነው ህዝብ ወደ መደበኛ ህይወት ተመልሷል›› ያሉትን አቶ ጌታቸው ‹‹…በግጭቱ የለየለት ሊባል ከሚችል መተላለቅ ታድገነዋል፣ በቀጣይ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ህዝቡ ጋር መስራት ያስፈልጋል›› ወደሚል መውረዳቸው ነገ ‹‹ከአቅማችን በላይ ሆኗል›› ለማለት ስላለመገደዳቸው ምንም ማረጋገጫ ሊያቀርቡልን አይቻላቸውም፡፡

ይህ በሆነበት በህወኃት ሰፈር (ኦፒዲኦ ስብሰባ በተከለከለበት) የሚሰማው ሁሉ የአገራችን ህዝብ ከዳር እስከዳር ነጻነት ወይም ሞት ማለቱ አጅግ እንዳሳሰበውና በህወኃት/ኢህአዴግ እና በኢትዮጵያዊያን መካከል የተጀመረውን የነጻነት ህዝባዊ ትግል ወደ ኢትዮጵያዊያን እና የትግራይ ህዝብ መካከል የተፈጠረ ለማስመሰል/ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ነው፡፡በዚህ መሰረት ትናንት የተከፋፈለውን ህወኃት ወደ አንድ ለማምጣትና የትግራይ ብሄረተኝነትን ለማጠናከር ባለፈው ክፍፍል ህወሓትን የለቀቁ፣ የተወነጀሉ፣የታሰሩ የቀድሞ አባላትን ከውጪ አገር ድረስ እየጠራ እንደሚያመጣ፣ አገር ቤት በተቃዋሚነት ያሉትንም እያግባባ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ለትግራይ ህዝብ በቅርብም ሆነ በዘላቂነት አይጠቅምም፡፡ ከዚህ ይልቅ ህወኃት/ኢህአዴግ ላለፉት 24ኣመታት የሰራለት ‹‹ የከፋፍልህ ግዛው ›› ስልትና ማስፈራራት (ህዝቡ ስለነጻነቱ ሞትን መናቁ እየታየ ነው) እንዳበቃለት አምኖ ወደ ብሄራዊ ውይይት፣ መግባባትና ዕርቅ መምጣት የግድ ይለዋል፡፡ የነጻነት ትግሉ ከህወኃት ፕሮፖጋንዳና የኃይል አፈና የመመከትና ትግሉን የመቀልበስ አቅም በላይ ሆኗልና ያለውን ‹‹የወንድ በር፣ የማሪያም መንገድ ›› በጊዜ እንዲጠቀም (በሚደረገው ተቃውሞ ፍጥነት ይህ ዕድል መቼ እንደሚያበቃ አይታወቅምና) ተጨባጭ ሁኔታው ግድ ይላል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል ብለን ኢትዮጵያዊ የወንድማዊ ምክራችንን እናቀርባለን፡፡ አስቸኳይ ነው፡፡


በሌላ በኩል ያለነው የፖለቲካ ኃይሎች የተበታተነውን ህዝባዊ ትግል በአንድ አገራዊ የጋራ ዓላማ ዙሪያ ወደ አንድ ለማምጣት/ለማስተባበር እንትጋ፤ የጎንዮሹን ፍትጊያ ( ለእኔ እየተደረገ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ትግል የኢትዮጵያዊያን ነጻነት ትግል አካል ነው፣ የወልቃይት ጠገዴ፣ የኮንሶ፣ የቁጫ ህዝብ የማንነት ጥያቄ፣ የሃመርና ቦዲ የፍትህ ጥያቄ፣የጋምቤላው ግጭት ያደረሰው ጉዳት፣ የተፈናቃዮች ፣ለሱዳን ሊሠጥ የተቆረሰው መሬት ጉዳይ… ጉዳዬ ነው፣የጋራችን ጉዳይ ነው፡፡) ለነገው ውይይት እናቆየው፡፡ለእኛም ይህ ዕድል መቼ ድረስ እንደሚቆየን አናውቅምና ህዝባዊ ትግሉ ከሁላችንም ቁጥጥር ውጪ ሆኖ አላስፈላጊ ዋጋ እንዳያስከፍል– የማይካስ የህይወትና የሃብት ውድመት፣…የማይለካ አገራዊ ጥፋት እንዳያስከትል በአገርቤትም በውጪም ውይይታችንና ተገቢውን የጋራ ዝግጅት ዛሬውኑ እንጀምር፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡