ለቀጣዩ ትግል ስኬት– የክህደት አቆራኝ ቀለበት ይበጠስ// መነሻ ኃሳብ – Girma Bekele
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ለቀጣዩ ትግል ስኬት– የክህደት አቆራኝ ቀለበት ይበጠስ// መነሻ ኃሳብ – #GirmaBekele – የአቶ ተክሌ በቀለ ‹‹ ሌላ አዲስ ፓርቲ ለምንና እንዴት ?›› 07/06/2008 ወዳጄ አቶ ተክሌ በዚህ ጽሁፋቸው ለማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት ይዘት ሲጠቃለል ለአንድነት ፓርቲ መፍረስ ‹‹ ከገዢው ፓርቲ ረጅም እጅ በተጨማሪ የአንድነት አመራርና አባላት በመከፋፈል የከፈቱት በር አስተዋጽኦ አድርጓልና በጥፋታችን ልክ ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል፣ እኔም የድርሻዬን ተቀብዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ…፣ ሌላ አዲስ ፓርቲ የመመስረት ኃሳብን ባልደግፍም እንደ መብት እቀበለዋለሁ፣ግን ፍላጎቱ ያልሆነውንና ይሁንታውን ያልገለጸ ሰው በፓርቲ አባልነት መመዝገብ በህግ ያስጠይቃል…..›› የሚል ነው፡፡
እኔ ይህን የአቶ ተክሌ ኃሳብ ከመቀበልም አልፌ ኃሳቡ እንዲዳረስ ለፌስቡክ ወዳጆቼ አሰራጭቼዋለሁ፣ ለረጅም ጊዜ ሲካድ የነበረውን ለፓርቲዎች መከፋፈል ፣ለአንጃ መፈጠር፣ በጋራ ለመስራት ያለመቻል፣… ከውስጥ የሚፈጠረው ችግር ያለውን አፍራሽ አስተዋጽኦ በመቀበል ችግሮችን ወደውጪ በመግፋት በተለይም ገዢውን ፓርቲ በምክንያትነት በማቅረብ ራስን ከደሙ ንጹህ የማድረግ ክፉ ልማድና የክህደት አካሄድ የመላቀቅና እውነታውን የመቀበል ‹‹በጎ ጅምር›› በመሆኑ ለቀጣዩ ትግል ገንቢ አስተዋጽኦ ያበረክታልና፡፡ ሆኖም ጅምሩን ሳደንቅ ለህወኃት/ኢህአዴግ ረጅም እጅ የተሰጠውን ቀዳሚና ወሳኝ ቦታ ሙሉ በሙሉ በመቀበል አይደለም፡፡ 

እኔ በእንዲህ እያሰብኩ ባለበት ከሌላው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ግርማ ሠይፉ (ም/ፕሬዝዳንት ) በአቶ ተክሌ (ተቀዳሚ ም/ፕሬዝዳንት) በቀረበው ኃሳብ ላይ ‹‹…የፓርቲው አመራርና አባላት ያጠፉት የለም፣ ይቅርታ ሊጠይቁም አይገባም፤ ችግሩ ገዢው ፓርቲ ጠንካራ አደረጃጀት የመቀበል ፍላጎትና አቅም ስሌለለው ነው ..›› የሚል ክርክር በመነሳቱ ህንን ለመጻፍ ተገፋፋሁ፡፡ ለዚህም መከራከሪያው የቱም ተቃዋሚ ፓርቲ ሲመሰረት ገዢው ፓርቲ ዕድሜውን ለማራዘም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ህግን ከለላ በማድረግም ሆነ በኃይል ‹‹ጠንካራ››ፓርቲዎችን ለማጥፋትና ለመከፋፈል የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር አውቆ ስለሆነ ይህን ዓይነቱን የማጥፋትና የማዳከም ሴራ ከፓርቲው ህልውናና እንቅስቃሴ ጋር አብሮ የሚመጣና የሚኖር መሆኑ በግልጽ ይታወቃልና ነው፡፡
በመሆኑም ለፓርቲዎች መከፋፈልና መፍረስ ያለውን መንግስታዊ አቅም በሙሉ በየትኛውም መንገድ የሚጠቀምን፣ ‹‹ጠንካራ ፓርቲዎች››ን እግር ሲያወጡ ለመቁረጥ እንደማይመለስ ላወጀና ለዚሁ የሚተጋ አስቀድሞ የሚታወቅ ውጫዊ አካል ላይ ማላከክ ወሳኝ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም እላለሁ፣ ለዚያውም የውስጥ ችግሩ ሊያስከትል የሚችለው ግልጽና የሚታይ አደጋ እየታወቀና እንዳይከሰትም ከፓርቲው ውስጥና ከውጪ ባለድርሻዎች ምክር እየተሰጠ ባለበት እውነታ ውስጥ፡፡ ዓላማዬም ይህ የገባንበትን ‹‹ካለፈው ያለመማር ችግር›› የሚያስቀጥል አስተሳሰብን የነበረውን እውነታ በማሳየት ለመሞገትና እንዳይቀጥል/እንዲገታ ኃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡
ስህተቶች እንዲታረሙ፣ ችግሮች እንዲፈቱ ፣መፍትሄዎች በሰከነ ግልጽና አሳታፊ መንገድ እንዲበጁ ፣ ከእንደዚህ ዓይነቱ የክህደት አዙሪት እንድንወጣና የተያያዝነው የክህደት መንገድ ካለፈው የመማርን ዕድል የሚዘጋ በመሆኑ በቀጣይ በሚደረገው ትግልም እንዳይደገም …የሚረዳ ኃሳብ ማቅረብ ከሞራል ግዴታ አልፎ በቀጥታ ዋጋ እየተከፈለበት ላለው ትግል ያለውን ገንቢ አስተዋጽኦ በመረዳት የበኩሌን ለማበርከት ነው፡፡ ለመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ አንባቢ በአገራችን ዛሬ ላይ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ያሉት ከ74 በላይ ፓርቲዎች የተቀፈቀፉት በታህሳስ 1986 በተደረገው የግዮን የሰላምና ዕርቅ ጉባኤ ከተመሰረተው የአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት አባል ከነበሩ ከመዐህድ፣ የደቡብ ኅብረት አባል ፓርቲዎች፣ ከብዲኅ፣ከኢዲዩ( በተከበሩ ራስ መንገሻ ሥዩም ይመራ የነበረው)፣ ከኢዳግ፣ከኢብአፓ (በተከበሩ ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ ይመራ የነበረው)፣ከኦሮሞ አቦ፣ ከአህዲን/አገው (የከሰመ) በጠቅላላው ከአስራ ስድስት ፣(የደቡብ ኅብረት አባላትን በአንድ ካየናቸው) ከስምንት ከማይበልጡ ፓርቲዎች /ድርጅቶች ነው፡፡ ወይም የበለጠ ከስህተት ለመራቅ ዘግይተው ከተመሰረቱት የኦሮሞ ፓርቲዎች- በዶ/ር መረራ /አብኮ/ ፣በተከበሩ አቶ ቡልቻ (ኦፌዲን)እና ከጀርመን አገር የመጡት አቶ አድማሱ ከመሰረቱት ፓርቲ በቀር የሁሉም ፓርቲዎች መስራቾችና አመራሮች በአመራርነት፣ በአባልነት፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤት አባልነት ፣ በደጋፊነት…. በነዚህ ፓርቲዎች በር አልፈዋል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
በአጭር ቋንቋ የዛሬዎቹ 74 ፓርቲዎች ከእነዚህ በተለያየ ምክንያትእንደ አሜባ እተከፈሉ የተራቡ ናቸው ማለት ይቻላል፤ ከዚህ ውጪ ነኝ የሚል ፓርቲ ካለ ይቅረብና እንነጋገርበት፣ እውነቱ ይህ ብቻና ብቻ ነው ፡፡ ወደ ርዕሳችን መነሻ አንድነት ፓርቲ ስንመለስ ደግሞ አንድነት ለ1997 ምርጫ ከተከሰተውና አመራሮቹ በወህኒ ቤት ባሉበት የተከፋፈለው ‹‹ ቅንጅት›› መንፈስ ወራሽ ሆኖ የተመሰረተና ብዙም ሳይራመድ ‹‹በመርህ ይከበር›› ጥያቄ የዛሬውን ሰማያዊ ፓርቲ የወለደ ነው፡፡ የ‹‹ቅንጅት››ን አነሳስና አወዳደቅ በወፍ በረር ስንመለከት ለዚሁ የ97 ምርጫ በተመሰረቱ ሁለት ፓርቲዎች (ቀስተደመናና አዲሊ) እና ከመዐህድ በተወለዱ ሁለት ነባር ፓርቲዎች (መኢአድና ኢዴፓ) ተመስርቶ በወህኒ ቤት ተከፋፍሎ አዲሶቹ ሲከስሙ ነባሮቹ ወደ ነበሩበት ሲመለሱ (እስከዛሬ ‹‹አሉ››) አንድነት በፍራሹ መንፈስ ተረካቢነት በቅንጅት ውስጥ የነበሩትን አባላት በማሰባሰብ የተወለደ ነው የሚለውን ሥዕል እናገኛለን፡፡
ከላይ በአጭሩ በተገለጸው ሁኔታ የተፈጠረው አንድነት ከተመሰረተ አምስት ጊዜ አመራር የቀየረ (ወ/ት ብርትኳን፣ ኢ/ር ግዛቸው፣ ዶ/ር ነጋሶ፣ ኢ/ር ግዛቸው፣ አቶ በላይ ) ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ለረጅም ጊዜ አመራር ላይ የቆዩት የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሲሆኑ እውነቱን ለማየት ለሚፈቅድ ሰው የተደረጉት የአመራር ለውጦች ሁሉ ከውስጥ ሽኩቻና ንትርክ በጸዳ የተረጋጋ ሁኔታ የተከናወኑ አልነበሩም፡፡ በሁሉም ጊዜ የተደረገው የሥልጣን ሽግግር የነበሩትን መሪዎች በተለያየ ደረጃም ቢሆን አስከፍቷል፣ በአባላት መካከል የተለያዩ የመተማመን ስሜት የሚፈታተኑ የልዩነትና ጥርጣሬ ስሜቶችን ፈጥሯል ማለትይቻላል፡፡ እስቲ በጥቅሉ እንመልከት፡፡
1ኛ/ ከወ/ት ብርቱካን ወደ ኢ/ር ግዛቸው — ኢ/ር ግዛቸው ብርቱካን በእስር ላይ እያለች ሥልጣን ለመረከብ ሲሉ ክህደት ፈጸሙባት፣ የታሰረችበትን ጉዳይ በበቂ አልደገፉም፣ አልተከታተሉም ፣ እንዲያውም ተመልሳ ወደ ሥልጣን እንዳትመጣ የተሸረበባት ተንኮል ነበር፤ …የሚሉ ቅሬታዎች፣
2ኛ/ ከኢ/ር ግዛቸው ወደ ዶ/ር ነጋሶ — ይህ ከላይ በተገለጸው የሥልጣን ሽግግር ወቅት በተፈጠረው ቅሬታ የታገዘ ሲሆን ኢ/ር ግዛቸው ከፓርቲው አመራር ኃላፊነት ራሳቸውን እንዲያገሉ/እንዲያርቁ ያስገደደ ፣ በመድረክ ውስጥ እንግባ/አንግባ ‹‹መርህ ይከበር›› የሚል ጥያቄ የተነሳበትና፣ ሰማያዊ የተወለደበትን …. ፣
3ኛ/ ከዶ/ር ነጋሶ ወደ ኢ/ር ግዛቸው– በፓርቲው ውስጥ የአማራ/አዲስአበባ ልህቃን የበላይነት መንጸባረቅ፣ የመድረክ አባልነት ይቀጥል/አይቀጥል ጥያቄ፣ የቡድን መብት ጉዳይ፣…. ልዩነት ፈጥረው በአግባቡ ሊስተናገዱ ያለመቻላቸው ፤ ዶ/ር ነጋሶን ‹‹የፓርቲ ፖለቲካ እርም አሰኝተው›› ኢ/ር ግዛቸውን ‹‹ካኮረፉበት›› አሸማግሎ ያስመጣና ከመድረክ ለመለያየት ያስገደደውን …. ፣
4ኛ/ ከኢ/ር ግዛቸው ወደ አቶ በላይ— ኢ/ር ግዛቸው ተጠርተው መጥተው አቶ ግርማ ሠይፉን በእጅግ ከፍተኛ ድምጽ አሸንፈው በአመራር ዘመናቸው ሊፈጽሙ በዕቅድ ካስቀመጧቸው አንዱ በሆነው ‹‹ወጣቱን ወደአመራር ማምጣት ›› ዓላማ ተጠልፈው በተመረጡ በስምንት ወራት ከሥልጣን እንዲወርዱ ከፓርቲው ህገደንብ ውጪ ጭምር በተለያየ ዘዴ ተጽዕኖ ያረፈባቸው፣ የፓርቲ አባላት በግልጽ በተለያየ ጎራ የተሰለፉበትና ልዩነቱ አደባባይ የወጣበት፣ …..
በመጨረሻም ኢ/ር ግዛቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከግምት ሳይገባ ከቢሮኣቸው ‹‹ በወጡበት ›› እንዲቀሩ ብቻ ሳይሆን ከፓርቲው የተፋቱበትን፤ ….. ሁኔታ ስንመለከት በእያንዳንዱ የሥልጣን ሽግግር ወቅት ቢሸፋፈንም በድምር ውጤቱ ከተረጋጋ የመተማመንና አንድነት ስሜት ይልቅ ወደ መጠራጠርና ወደ ጎራ ለይቶ መፋተግ የሚገፉ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፡፡ በዚህ ሁሉ የህወኃት/ኢህአዴግ አፍራሽ ሰርጎገቦች አብረው እተከታተሉ መሆናቸው ሳይዘነጋ፡፡ ይህን ያህል መግቢያና መንደርደሪ ያቀረብኩት አንባቢዎች ከዚህ ቀጥሎ የተነሳሁበትን ርዕስ ጉዳይ ለማስረዳትና እና መነሻ የሆነኝን የአቶ ተክሌ ጽሁፍ ላይ ለመከራከር ለማቀርበው አስተያየት እንዲያግዝ የተቃውሞ ጎራውና አፈጣጠር ፣ የእስከዛሬውን የጉዞ ሂደት፣ ዛሬ ላይም በተቃውሞ ጎራው እየሆነና እየተደረገ ያለውን ፣በተለይም በፈረሰው አንድነት ውስጥ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ በግርድፉ እንዲመለከቱ ለማስቻል ነው፡፡ ወደ ዋናው ርዕሰ – ጉዳይ እንግባ፡፡ እየተነጋገርን ያለነው ኢ/ር ግዛቸው ለሁለተኛ ጊዜ የአንድነት መሪ ሆነው ከመጡበት ጊዜ በኋላ ስላለው ሂደት ነውና የጽሁፌ ትኩረትም በዚሁ ላይ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ዓላማዬ ከላይ የገለጽኩት ለቀጣዩ ትግል ገንቢ አስተዋጽኦ የማበርከት ነውና በተቻለ መጠን ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ላለመግባት ፣ግን ደግሞ አስፈላጊ ጠቋሚ መረጃና ማስረጃ በጥቅል ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
የአንድነት የውስጥ ችግርና የኢ/ር ግዛቸው ፈተና የጀመረው ከተመረጡበት ጉባኤ ወዜማ ሲሆን ተጠናክሮ የቀጠለው በተመረጡ ማግስት ካቢኔኣቸውን ለመመልመል ደፋ ቀና በሚሉበት ጊዜ ነው፡፡ በኢ/ር ግዛቸው ወደፓርቲው ተመልሶ መምጣትና በምርጫ ማሸነፍ ያኮረፉ ኢ/ሩን ‹‹የማስወገድ›› ስውርና ረቂቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ያዘጋጇቸውን ተልዕኮውን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሲያስፈጽሙ የነበሩ አባላት ወዳጅ ሆነው በመቅረብ ማንን መመልመል/ያለመመልመል ፣ ለምን …እንደሆነ በማማከር ሥራ አሰማሩኣቸው፡፡ ኢ/ሩ ከፓርቲው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተለይተው በመቆየታቸው ደባውን ሳይረዱ የእነዚህን ባለተልዕኮዎች ምክር ለመቀበልና የቅርብ ወዳጆቻቸውን ለማራቅ ብዙ አልተቸገሩም፤ ተፈጥሮኣዊ ቅን አመለካከታቸውም አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በመሆኑም ስውር አካሄዱ የገባቸው የቅርባቸው ሰዎችና ሌሎች የአንድነት ጉዳይ ከፓርቲ አልፎ በአገራዊው ፖለቲካ ያለውን የማሰባሰብና የማስተባበር ሚና የተረዱ ባለድርሻዎች በግልና በቡድን ቀርበው ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄና የተጀመሩ የጋራ ጥረቶች ላይ የሚኖረውን አንድምታ ሲያስረዷቸው አመስግነው ቢቀበሉም ተግባራዊ አላደረጉትም፡፡ በዚህ መልክ በባለተልዕኮዎች ምክር መሰረት ካቢኔኣቸውን መሰረቱ፡፡ ይህ ከሶስት አራተኛ በላይ ወጣቱን የሸፈነው ካቢኔ በቀደመው ስውር የማስወገድ ውጥን መሰረት ኢ/ሩን ለመፈታተን ጊዜ አልፈጀም፡፡ የኢ/ሩ ኃሳብና የተግባር ዕቅድ በሥራ አስፈጻሚው ይታገት ጀመር፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከኢ/ሩ አመራርና ቁጥጥር ውጪ በራሳቸው ጊዜ መንቀሳቀስ ጀመሩ፣ አልፎም ለተወሰነ ተግባር የሚቋቋሙ ጊዜያዊ ኮሚቴዎችም በተመሳሳይ የራሳቸው ትንሽ መንግስት ሆኑ፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ከኢ/ሩ አቅም በላይ መሆንና የፓርቲው ዕለት ተዕለት ተግባር ወደ እርስ በርስ ፍትጊያ መሸጋገሩ አልፎም ‹‹የማስወገዱ›› ስውር ተልዕኮ ለኢ/ሩ ግልጽ እየሆነና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በግልጽ ሁለት ቦታ በመከፈሉ የፓርቲው ስራ ወደ ማዕከላዊ ምክር ቤቱ ተሸጋገረ በሚያስብል ደረጃ ተደጋጋሚ የማዕከላዊ ም/ቤት ስብሰባዎች ይካሄዱ ጀመር፡፡ እነዚህ ስብሰባዎችም እንደ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሁለት ተከፍሎ ከመነታረክ ስያልፍም ከመሰዳደብ ውጪ ለችግሩ መፍትሄ ሊያስገኙ አልተቻላቸውም፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ልዩነቱ እየጠነከረና እየሰፋ የፓርቲውን ኦፊሴሊያዊ ድረገጽ ጨምሮ በኢ/ሩ ላይ የተሸረበው ስውር የማስወገድ ውጥን ወደ አደባባይ ወጣ፡፡ ኢ/ሩ‹‹ በወጣት መሪ ይተኩ›› ጥያቄ ይፋ ከመሆን አልፎ ቀታዩ መሪ ተለይቶ በየሚዲያው ይገጠምለትና ይሸለልበት ጀመረ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ኢ/ሩ በማያውቁት መንገድ በግልጽና በድብቅ ይከናወን የነበረው የክልል አመራሮችንና የውጪ ደጋፊዎች የማስወገድ ዘመቻው አካል እንዲሆኑ የማሳመን/ሎቢ/ ሥራ ተሳክቶ በኢ/ሩ ላይ ከአገር ውስጥና ከውጪ ደጋፊዎች ከፍተኛ ጫና ይደረግ ጀመር፡፡ ይህን ተከትሎ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በቡድን ለአንዳንዶች ሌላው የፈረመበት ራሳቸውን ከኮሚቴ አባልነት ማግለል ማመልከቻ አስገቡ ፡፡ እነዚህ ኢህገደንብና ከአሰራር ሥርዓት ውጪ የሆኑ አፍራሽ ድርጊቶች ከኢ/ሩ ቁጥጥር ውጪ በሆኑት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች በግልጽ ይታገዙ ጀመር፡፡ የመድረክ/አንድነት ግንኙነት መቋረጥ አስፈላጊነት ኢ/ሩም ሆነ ሥራ አስፈጻሚው ባላጸደቀው ሪፖርት ይፋ ወጣ፣ ሞቶ የነበረው የመኢአድ/አንድነት የውህደት የጋራ ኮሚቴ በህገወጥ የመንገድ ላይ ደብዳቤ ህይወት እንዲዘራ ተደረገ፣ ከዐረናና ትብብር ጋር የተጀመረው የውህደት ጥረት በተንኮል እንዲስተጓጎል ሆነ…. በዚህ ጊዜ ሁሉ የተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ፣ ማዕከላዊ ም/ቤትና የክልል የፓርቲው አመራርና አባላት ስለደንብ ማለታቸው አልቀረም፣ ባለድርሻ አካላትም ምንም ጥያቄ ማንሳትም ሆነ የውስጥ ትግል ማድረግ ተገቢ ቢሆንም የፓርቲውን ደንብና የአሰራር ሥርዓት ተከተለ መሆን እንዳለበት፣ ያለበለዚያ በዚህ መሃል ለህወኃት /ኢህአዴግ የመግቢ በር በሰፊው ተከፍቶ ሊከተል የሚችለውን የማይቀለበስ አደጋ አስመልክተው በግልና በቡድን ለሁለቱም ጎራ በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡ ሆኖም ከጅምሩ የተወጠነው ኢ/ሩን በማንኛውም (ህጋዊም ሆነ ህገወጥ) መንገድ የማስወገድ ተልእኮ፣ በተጀመረው ዘመቻ ስፋትና ባገኘው ተቀባይነት ተጋርዶ ፣ ከአሰራር ውጪ በውስጥ በሚወሰዱ እርምጃዎች ታግዞ አቤቱታዎችም ሆኑ ማሳሰቢያና ምክሮች ሰሚ አላገኙም፡፡ኢ/ሩም ችግሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን እየተረዱ በመምጣታቸው በመጨረሻ ‹‹የወንድ/የማሪም በር›› መፈለጋቸው ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ሥልጣናቸውን ጉባኤ ጠርተው የጉባኤውን ድምጽ ሰምተው ለመልቀቅ ፍላጎት ማሳየት ጀመሩ፡፡ ግን የሚያርፍባቸው ጫናና የሚሰራጭባቸው አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ እስከዚህ ቀንም ሊታገሳቸው አልቻለም፣ የማስወገድ ውጥኑ ጠንሳሾችና ደጋፊዎቻቸው ከውስጥና ከውጪ በትሩን አጠነከሩት፤ ትዕግስታቸውን ተፈታተኑት፡፡ ግን ይህን ህገወጥ አካሄድ ሲቃወሙ የነበሩ የአመራር አባላትንና ወጣቶች ይህን ሊታገሱ አልቻሉምና በቃ በማለት ወደ አደባባይ ለመውጣት ተገደዱ፡፡….. በመኢአድ ላይ ይነሳ በነበረው በፍርድ ቤት የታያዘ የአመራሩ የህጋዊነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ እንደማይሳካ የህግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ምክር የተሠጠበትና በጋራ አመቻች ኮሚቴዎቸ የጋራ ስብሰባ አክትሞለት የነበረው ፣ ከመቃብር አፈር አራግፎ የተነሳውና አስቀድሞ የቅድመውህደት ስምምነት ተፈርሞበት የነበረው የመኢአድ/አንድነት ውህደት ጉዳይ ‹‹ ለኢ/ሩ የወንድ በር ፣ ለአስወጋጆች የድል መድረክ›› ይሆናል በሚል ጉባኤ እንዲጠራና ለአንድነት/መኢአድ ውህድ የአንድነት ዕጩ እንዲመረጥ በሚል አዲስ አመራር መምረጥ የሚል አጀንዳ ተቀረጸ፣ ጉባኤው ተጠራ፤ አስቀድሞ የታወቀው ወጣት መሪ ‹‹ተመረጠ ›› ፡፡ አስቀድመው የተመረጡትን የካቢኔ አባላት ያለችግር ሾመ ፡፡ ግን አስቀድሞ ከነበሩት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የጉባኤው አካሄድ ላይ ያነሱትን ደንብና የህግ ጥያቄ ይዘው አደባባይ ወጡ፣ በሆቴል መግለጫ ሰጡ፡፡ …………… ይህ ለህወኃት/ኢህአዴግ፣ አድፍጠው ለሚጠብቁት የህወኃት/ኢህአዴግ ስርጎገቦችና ለምርጫ ቦርድ የማይገኝ መልካም አጋጣሚ ፈጠረ፡፡…..ከዚህ በኋላ ከምርጫ ቦርድ ጋር ጉባኤውንና አዲሱን አመራር እንዲቀበል የተደረገው ድርድር በማን ኃላፊነትና በምን መንገድ እንደተካሄደ፣ በዚህም አንድነት የተጠየቀውን ቅድመ ሁኔታ ቢፈጽምም ቦርዱ የገባውን ቃል በማጠፉ የተፈጠረውን ውዝግብ በዝርዝር ከማንሳት ተቆጥበን እስካሁን ቀረብነው ለተነሳንለት ዓላማ በበቂ ያስረዳልና በመጨረሻም አንድነት እንዳይሆኑ ሆኖ ፈረሰ፣ተበተነ ፡፡ መፍረስ/መበተኑ ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት ስንመለከት ከፓርቲው ‹‹ህጋዊ››ህልውና ማጣት አልፎ በዋነኛነት በህዝቡ ላይ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና የተቃውሞ ጎራው ላይ ያለውን እምነትና ተስፋ ማመናመን/ማሳጣት፣ የፓርቲው አመራርና አባላት የትግል መድረክ/ማዕከል እንዳይኖራቸው በማድረግ ትግሉን በግል እንዲገፉ ወይም ከትግሉ ራሳቸውን እንዲያገሉ፣ ወይም እንዲሰደዱ ማድረግ፣ በፓርቲው ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ የታሰሩ አመራሮችና አባላት ላይ የሚያሳድረውን ሥነልቡናዊ ጉዳት በአጠቃላይ የተቃውሞ ጎራውን እንቅስቃሴ በማዳከምና ለገዢው ፓርቲ ዕድሜ መራዘም ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሁሉም ነገር አይነገርም፣ ጊዜና ሁኔታ ይጠብቅ ዘንድ ግድ የሚላቸው መኖራቸው ይታወቃልና በጥቅል ስለሂደትና ውጤቱ ይህን ብለን እናብቃ፡፡ እንግዲህ ሂደቱና በሂደቱ የተፈጠረው እውነታና በውጤቱም የደረሰው ጉዳት ይህ በሆነበት እንደምን አይደለም በዚህ ሂደት አመራር የሰጠና በተለያየ ደረጃ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፈ አመራር ቀርቶ በጉባኤ ፣በማዕከላዊ ምክር ቤት ፣ በክልል መዋቅር የተሳተፈና የውሳኔው አካል የሆነ አባል ከአንድነት መፍረስ ተጠያቂነት ነጻ ነኝ ሊል ይቻለዋል ? ይህንን ተቀብለን ዝም ካልን ለቀጣዩ ትግል ተመሳሳይ የህገወጥነት አካሄድ ልምድ ማካፈል አይሆንምን ? እንደምንስ በሌላ ወገንና ገዢው ፓርቲ ላይ ተጠያቂነት፣ የሥልጣን መባለግ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ….ጥያቄ ማንሳት፣ ትችት ማቅረብ የሚያስችለን ሞራል የሚኖረን ?… እንነጋገርበት፡፡ ውድ ወዳጆቼ አበክሬና አጠንክሬ የማሳስባችሁ ይህ ጽሁፍ በምንም መንገድ ትናንትን/ያለፈውን በማማረር መጪውን ጊዜ ለማጨለም አይደለም፤ ይልቁንም ያለፈውን ስህተት ካለፈም በኋላ እንኳ የመቀበል ድፍረት በታጣበት ሁኔታ ፣ ለቀጣዩ ትምህርት ለመውሰድና እንዳይደገም ለመከላከል ግርዶሽ እንዳይሆን ያለውን አስፈላጊነትና የሚሰጠውን ጥቅም በማሰብ ነውና በዚህ መንፈስ ተረዱልኝ፡፡ መፍትሄውም ማናችንም ዛሬ ላይ በምንወስነውና በምንወስደው አቋም በነገኣችን ላይ የምንወስን በተለይም የፖለቲካ አመራሮች ስንሆን በአገርና ህዝብ ጉዳይም እየወሰንን እንደሆነ እንድንረዳ ፣ይህም ተጠያቂነት እንዳለበት ተረድተን ቢያንስ ከስህተታችን ለመታረምና ለይቅርታ እራሳችንን እንድናዘጋጅ ለማሳሰብ ነው፡፡ በዚህ መልክ ችግራችን እየፈታን ከልዩነታችን አንድነታችን ከሚከፋፍለን አንድ የሚያደርገን በጣም እንደሚበልጥ ተረድተን በአንድ ሁላችንን ተጠቃሚ ለሚያደርግ አገራዊ ዓላማ በኅብረት እንድንቆም ለማሳሰብ ነው፡፡ በመጨረሻም ሁለት ነገሮችን ላንሳና ኃሳቤን ልቋጭ፡፡ አንደኛው፡- በኢ/ሩ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ውጥረት፣በፓርቲው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በማገናዘብና በመኢአድ/አንድነት የውህደት ሂደት ላይ የተከሰተውን አለመግባባት ከግምት በማስገባት የኢ/ሩን ከሥልጣን መነሳት በሙሉ ልብ ተቀብዬ ይህንኑ ገልጨላቸው/ገልጸንላቸው ተቀብለው ነበር፡፡ ይህንኑ በማስረዳት ነገር ግን አፈጻጸሙ የፓርቲውን ህገደንብና የአሰራር ሥርዓት የተከተለ እንዲሆን፣ የታያዘው መንገድና አካሄድ አደገኛ መሆኑን ለአንድነት አመራር አባላት በግልና በጋራ በግንባር በተለያዩ የግንኙነት አጋጣሚዎች( በጋራ ስብሰባዎች፣ በግል ቀጤሮዎች ) ተነጋግረናል፤ በተደጋጋሚ አስረድተናል፡፡ ከነዚህም ኢ/ር ግዛቸውን፣ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ አቶ በላይ ፈቃዱ፣ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ግርማ ሠይፉ፣ አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ አቶ አስራት ጣሴ ፣ወ/ት ልዕልና ጉግሳ፣ ወጣት ነቢዩ ባዘዘው፣እና ሌሎች አምስት ስድስት ወጣቶች ይጠቀሳሉ፡፡በተለይ ደግሞ ከባህርዳር ሰልፍ ስንመለስ የመኢአድ/አንድነት ውህደት እንዲሣካ ከህጋዊነት ጥያቄው በተጨማሪ አቶ አበባው መሃሪና ኢ/ር ግዛቸው ከሥልጣን ለቀው <<ታሪክ>> እንዲሰሩ ፣ ያሊያም የፓርቲው አባላት በፓርቲያቸው ውስጥ ህጋዊ ትግል እንዲያደርጉ አቶ አበባውና ከ10 የማያንሱ የሁለቱም ፓርቲ አመራር አባላት ባሉበት ገልጫለሁ፡፡ ሁለተኛው ፡- በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የቀረበውን ችግርና የሂደቱን ህገወጥነትና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በሚመለከት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በግልና ከሌሎች የትግል አጋሮቹ ጋር በመሆን በሁለቱም ጎራ ከነበሩ ጋር ተገናኝቶ ለማስረዳት፣ የፓርቲውን ህገደንብና የአሰራር ስርዓት የተከተለ መፍትሄ እንዲፈለግ፣ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ፣ ስለተደረገው ጥረትና ከላይ የቀረቡት በሙሉ እውነት ስለመሆናቸው አስፈላጊ ከሆነ በተጨባጭ ለማስረዳት የሚቻል መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡