‹‹አገሪቱ እየተዘረፈች ነው›› : ዋና ኦዲተሩ – የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች ላይ ከፍተኛ ወቀሳ ሰነዘሩ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
‹‹አገሪቱ እየተዘረፈች ነው›› ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ
‹‹የማዕድን ዘርፉን እየመራችሁ ስለመሆኑ ሥጋት አለን›› የፓርላማው አባላት
በፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የፌዴራል ዋና ኦዲተር የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችን ክፉኛ ወቀሱ፡፡
የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ረቡዕ ጥር 18 ቀን 2008 ከቀትር በኋላ ፓርላማ እንዲቀርቡና በ2005 ዓ.ም. በተደረገ የክዋኔ ኦዲት፣ በከበሩና በከፊል በከበሩ ማዕድናት ፈቃድ አስተዳደር ግብይትና ቁጥጥር አስመልክቶ የተገኘባቸውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተቀጥረው ነበር፡፡
በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ስብሰባው ሊካሄድ ሰዓታት ሲቀሩት ለቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአስቸኳይ የመንግሥት ኃላፊነት መገኘት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
በምትኩም ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ዋቅጋሪ ፉሪ የሚመሩት የከፍተኛ አመራሮች ቡድን በፓርላማው ልዩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝቷል፡፡
ባሉት የሥራ ኃላፊዎች መልስ ሰጪነት ስብሰባው እንዲቀጥል የወሰኑት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ በመጀመሪያ በኮሚቴው የተዘጋጁ ጥያቄዎች እንዲቀርቡ ፈቅደዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ከቀረቡት ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ መካከል ሚኒስቴሩ ለሦስት ኩባንያዎች የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ፈቃድ ከመስጠቱ በፊት ፈቃዱን እንዲሰጥ ይሁንታ ያገኘበት ማስረጃ አለመገኘቱ፣ እንዲሁም የማዕድን ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃን ያላገናዘቡ መሆናቸው ተነስቷል፡፡ የአዘዋዋሪነት ፈቃድ የተሰጣቸው አዘዋዋሪዎች የከበሩ ማዕድናትን ያገኙበት ሕጋዊ ምንጭና አካባቢያቸውን ሚኒስቴሩ የሚከታተልበት ሥርዓት አለመኖሩ ሌላው የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡
በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የማዕድን ምርመራ ሥራዎች የሚያከናውኑ ባለፈቃዶች ለማዕድን ሥራ ከውጭ ከቀረጥ ነፃ ያስገቡዋቸውን መሣሪያዎች በፕሮጀክት ውስጥ ማግኘት አለመቻሉ፣ ይህንን በመከታተል ረገድም የተከናወነ ሥራ እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡
የከበሩ ማዕድናት አዘዋዋሪ ባለፈቃድ በእያንዳንዱ የበጀት ዓመት በስምምነት የሚወሰነውን የወርቅና የብር ማዕድናት መጠን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ ሁሉም ፈቃድ ሰጪ አካላት ባለመቆጣጠራቸው ወጥ በሆነ መንገድ እንደማይከታተል፣ ክትትል ባደረገባቸው ክልሎችም የወርቁ መጠን የቀነሰበት ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ የተወሰደ የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል፡፡
እያንዳንዱ ማዕድን አምራች የተመረተውን ማዕድን በንግድ ልውውጥ በተሰጠበት ዋጋ ላይ ኦዲት በተደረገበት ወቅት ለከበሩ ማዕድናት ስምንት በመቶ፣ በከፊል ለከበሩ ማዕድናት ደግሞ ስድስት በመቶ መክፈል እንደሚገባውና በአግባቡ እንደማይሰበሰብ ጠቅሰዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. ብቻ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 427 ሚሊዮን ብር የሮያሊቲ ገቢ ማጣቱንና ይህንን ለማስተካከል ምን እንደተሠራ የቀረቡት ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የሚኒስቴሩን የኃላፊዎች ቡድን የመሩት ሚኒስትር ዴኤታው ከተሾሙ ገና ሦስት ወራት ብቻ መሆኑንና ስለጉዳዩ በስፋት የሚያውቁት አለመኖሩን ከግንዛቤ አስገብተው፣ በስብሰባው ላይ ለተገኙ ሌሎች ባልደረቦቻቸው እንደየኃላፊነታቸው ምላሽ እንዲሰጡ ዕድሉን ሰጥተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዳይሬክተሮቹ በማስረጃ የቀረበውን የኦዲት ውጤት ያለማስረጃ ለመከላከል ሲሞክሩ፣ እንዲሁም በአንዳንድ ጥያቄዎች ላይ የሚኒስቴሩ ሥልጣን አይደለም በማለት ምላሽ ሲሰጡ፣ ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ግን መልስ አልነበራቸውም፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዳግመኛ ዕድል ለኮሚቴው አባላት የፈቀዱ ሲሆን፣ ይህንን ዕድል በመጠቀም ጥያቄ ካቀረቡ አባላት መካከለ ወ/ሮ ስፍራሽ ብርሃኔ አንዷ ናቸው፡፡ ‹‹አንዳቸውም የሥራ ኃላፊዎች ተገቢውን ምላሽ አልሰጡም፤›› ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል በአንድ ዓመት ብቻ ያጣውን 427 ሚሊዮን ብር በተመለከተ አንዳቸውም አልነኩትም፤›› ብለዋል፡፡
በመቀጠል አስተያየት የሰጡት ሌላው የምክር ቤቱ አባል ዶ/ር አድሃነ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ‹‹ሥርዓት ያለው አሠራር ዘርግተን በማዕድን ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በተሰጠን ኃላፊነት መሠረት እየመራን ነው ብላችሁ ታስባላችሁ?›› በማለት ቢጠይቁም ምላሽ ከኃላፊዎቹ አልጠበቁም፡፡ ‹‹አይመስለኝም የኦዲት ሪፖርቱ ብቻ ሳይሆን ለቀረቡ ጥያቄዎች የሰጣችሁት መልስ ይህንን ሥጋት ፈጥሮብኛል፤›› ብለዋል፡፡
ወደ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን መቀነስና ሕገወጥ ዝውውር መጨመሩን አስመልክቶ ለቀረበ ጥያቄ አንድም ኃላፊ መልስ ለመስጠት አለመሞከሩና የኦዲት ሪፖርቱ መሠረታዊ ግኝት አንዱ ይህ መሆኑን በመጥቀስ ወቅሰዋቸዋል፡፡
‹‹በተለይ ከላይ ያላችሁ ኃላፊዎች እንደምትገነዘቡት ማዕድን ከሠሩበት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ካልሠሩበት ለጥፋት እንደሚዳርግ ታውቃላችሁ፤›› በማለት ሊመጣ የሚችለውን በመገመት እንዲጠነቀቁ አሳስበዋል፡፡
ሌሎቹ የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው፣ የሥራ ኃላፊዎቹ ከአንድ ተቋም የመጡ እንኳን እንደማይመስል በመጥቀስ ተችተዋል፡፡
በፈታኝ ስብሰባ ላይ የተገኙት ለጉዳዩ አዲስ የሆኑት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ዋቅጋሪ ፉሪ ቋሚ ኮሚቴውን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ ጉዳዩን እንደ አዲስ እንደሚመለከቱት ቃል ገብተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል የተሰጣቸው ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ፣ በኦዲቱ ወቅት የታየው ጥቂት ናሙና ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከተመረመሩት 65 ማዕድን አምራቾች ውስጥ 28 ሮያሊቲ ክፍያ ከፍለው እንደማያውቁ፣ 25 ደግሞ በወቅቱ እንደማይከፍሉ ጠቁመዋል፡፡ በከፍተኛ የማዕድን አምራችነት ፈቃድ አግኝተው የተሰማሩትም ቢሆኑ ምን ያህል እንዳመረቱ ሪፖርት ያደርጋሉ እንጂ ሚኒስቴሩ የምርት መጠኑን አይከታተልም ያሉት አቶ ገመቹ፣ ‹‹አገሪቱ እየተዘረፈች ነው፡፡ እየተጠቀሙ ያሉት ኩባንያዎች ናቸው፤›› በማለት ኃላፊዎቹ በአግባቡ ሥራቸውን እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን የዋና ኦዲተሩን ንግግር ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበሉ ገልጸው፣ በአስቸኳይ የድርጊት መርሐ ግብር ተቀርጾ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ለቋሚ ኮሚቴው እንዲላክ አሳስበዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ወደ መፍትሔ ሚኒስቴሩ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር ዋቅጋሪ ማሳሰቢያውን እንደሚቀበሉትና ለሚኒስቴሩ ተጨማሪ ዕድል መሰጠቱን አምነው ስብሰባው ተጠናቋል፡፡
Reporter Amharic