ሃሰትና ክህደት የማይታክተው ዘረኛው የህወኃት አገዛዝ በስኳር ኮርፖሬሽን- ያስከተለው መዘዝ፤


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሃሰትና ክህደት የማይታክተው ዘረኛው የህወኃት አገዛዝ በስኳር ኮርፖሬሽን- ያስከተለው መዘዝ፤ መቼም በተመራጫችን ሚዲያ /ኢሳት/ መታፈን ጾማችን ቀርቶ የኢቢሲ/ኢቲቪ/የአየር ጊዜኣችን በመጨመሩ የማንሰማው ጉድ የለም፣ ይህ ሃፍረትና ይሉኝታ የማያውቅ መንግስት በራሱ ዓይን እያየን በራሱ ሚዛን እየመዘነን አያስታውሱም በሚል እሳቤ እስከሚሰለቸን ውሸቱን እያቀረሸብን የ50ኛ ኣመት ልደቱን ይነግረናል፣ ወይ አለማፈር፣ ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባለልወጣሽ፡፡ በዛሬ የማታ ዜና እወጃው ከዚህ በፊት በቲቪ መስተዋት ከሚመግበን የተትረፈረፈ ምርትና ከምንሰቃይበት ቁንጣን በተቃራኒ መርዶ አርድቶናል፡፡ የስኳር ዋጋ በአንድ ጊዜ ሦስት ብር ጨምረናል በማለት፡፡ አዲስ አበባ ላይ ብር 18.40 እንዲሸጥ መንግስት ፈቅዶልናል ብሏል ኮርፖሬሽኑ፡፡

በዚህ ላይ ከዚህ በፊት በመጀመሪያው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተነገረንን አስታውሰን ወደያዝነው መረጃ እንገባለን፡፡ እንዲህ ተብለን ነበር ‹‹ … አስር አዳዲስና የማስፋፊያ የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት አስገብተን እያደገ የመጣውን የሽኳር ፍላጎት በማሟላት ከውጪ ለማስገባት የምናወጣውን የውጪ ምንዛሪ ከማትረፍ አልፈን ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሪ ገብያችን እናሳድጋለን …›› ፡፡ በዕቅድ ዘመኑ ማብቂያ ደግሞ ‹‹ እነዚህን ፕሮጄክቶች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የአምስት ቢሊዮን ብር ብድር ከመንግስት እንዲፈቀድለት መጠየቁን …›› ነግረውናል፡፡ ከዚሁ በተያያዘ በስኳር ኮርፖሬሽን ውስጥ ቅጥ ያጣውን ሙስናና 800 ሚሊዮን ብር አየር -በአየር ደብዛው እንደጠፋና ለዚህም ተጠያቂው አቶ አባይ ፀሃዬ መሆናቸውን ፣የተኳቸው አቶ ሺፈራው ጃርሶም ‹‹…. ተብትቦና አሳስሮት ገድሎት በሄደው ቤት እንደምን ለአስከሬን ህይወት ዘርተን ልንሰራ እንችላለን…›› እያሉ ሲያማርሩ እንደነበር ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ሰምተናል፡፡ አሁን በአምባሳደርነት እስከተገላገሉበት ድረስ አንድም ቀን በሥራቸው ደስተኛ ሆነው እንዳልታዩና የከፍተኛ የሥራ አመራሩን ሰብስበው አነጋግረው እንደማያውቁ ም እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ዛሬ በአፈና ውስጥ ባይሆንበዕለት ተዕለት በሚጠቀመው ምርት /ስኳር/ላይ የተደረገው ጭማሪ ህዝቡን ለተቃውሞ የሚያስነሳ ነው፡፡ በየቱም ጊዜ እንዲህ ያለው ጭማሪ መንግስት በሚያቀርበው የእለት ተዕለት መጠቀሚያ ምርት ላይ ተደርጎ አያውቅም፡፡ ሦስት ብር በኪሎ ለደሃው ከፍተኛ ነው፡፡ ውስጥ አዋቂ ምንጮቹ ‹‹ በጭማሪው ቢያበቃ ጥሩ ነበር፣ ከዚያ አልፎ ለጭማሪው የተሰጠው ምክንያትና ከአዳዲሶቹ ሦስት ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ምርት ይጀምራሉ በማለት ዛሬም የተስፋ ዳቦ ማቅረቡ በመልካም አስተዳደር መድረክ ስለ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሚያወሩበት ጊዜ መሆኑን ካለው እውነታ ጋር ስናየው እንደዜጋ በጣም ያማል ›› ሲሉ ምንጮቹ ምክንያታቸውን እንደሚከተለው ያቀርባሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የስኳር ዋጋ የተጨመረው ኮርፖሬሽኑ በሙስና የገባበትን የገንዘብ እጥረትና ከጠየቀውን የቢሊዮኖች ብር ተጨማሪ ብድር ከፊሉን ለመሸፈን ካልሆነ በቀር የስኳር ማምረቻ ዋጋ በኪሎ በየቱም ፋብሪካ ከ 7/ሰባት /ብር አይበልጥም፣ እንደኮርፖሬሽኑ የማምረቻ አማካይ ዋጋ ስሌት ከዚህ በታች ነው ይላሉ ፡፡ ስለዚህ ማንም ጠያቂ በሌለበት ቢያንስ እኛን የምናውቀውን ባያከብሩ እንኳ እንደሰው ሊያፍሩን በተገባ ፣ የህዝብ አካል መሆናችን በተረዱ ነበር፤ ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ፡፡

ይህን ኃሳባቸውን በመረጃ ሲያጠናክሩም ፡- አቶ ሺፈራው ያነሱት የነበረውን የተተበተበ መዋቅርና በቅርቡ በኮርፖሬሽኑ የመልካም አስተዳደር ስብሰባ ላይ የተነሱትንና በከፍተኛ አመራሩ መካኪል በግልጽ ያለውን ልዩነትና የአሰራር ዝርክርክነት ያቀርባሉ፡፡ ስለመዋቅሩ ካነሳን ‹‹ማንም ወደ ኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት የሄደ ሰው ፣ መቀሌ ያለና የሥራ ቋንቋውም ትግርኛ ቢመስለው አይፈረድበትም፡፡ ዘጠና ከመቶው ሊባል የሚችለው የድጋፍ ሰጪ ሰራተኛ ትግራዊያን ሲሆኑ፣ ከጥቂት የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ቦታዎች በቀር ሁሉም የተያዙት አቶ አባይ በተከሏቸውና ከትግራይ ወረዳ ጭምር በመጡ ከያዙት መደብ ጋር ተገቢ ሙያና በቂ ልምድ በሌላቸው የህወኃት አባላት ነው›› ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮርፖሬሽኑ ስራ መሪ አማካሪ ሆነው የተመደቡት በሙያው ልምድ የሌላቸውና ሊያማክሩ አይደለም ሊመከሩ የሚገባቸው አቶ ኃ/ማሪያም እንደ ልጃቸው ያሳደጓትና የዳሯት የእህታቸው ልጅ ባለቤት በመሆናቸው ብቻ ከአዋሳ መጥተው የተመደቡ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

በቅርቡ በተደረገው የመልካም አስተዳደርና የአመራር ግገማ ላይ የተስተዋለው በእርግጥም አመራሩ ተወያይቶ እንደማይሰራ የውስጥ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት የሌለውና ሁሉም የሕወኃት አባል ማለት በሚቻል ደረጃ በየመዋቅሩና በተመደበበት ‹‹የየድርሻውን›› እየቀራመተ ያለበት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ምንጮቹ በዚህ የሁለት ቀናት ስብሰባ ላይ የታየው ሙስናው የደረሰበትን ደረጃ፣ የተመዘበረውን ሃብት/ገንዘብና ቁሳቁስ/ ፣ የተረገጠውን የግዚ ስርዓት ጥሰትና የአንዳንዶችና ከህግ የበላይነትና በአጠቃላይም ኮርፖሬሽኑ የገባበትን አዘቅት በግልጽ ያመላከተና የነጻ ባለሙያዎችን የሥራ ተነሳሽነት ያዳከመ፣ ተስፋ ያስቆረጠ በመሆኑ ሥራ ለመልቀቅ እየሞከሩ እንደሚገኙባቸውም ይገልጻሉ፡፡ ከተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮችም–

1ኛ/ የግብይትና አቅርቦት ክፍሉ በማያውቀው መንገድ የተንዳሆ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ እስከ ውጪ በመሄድ ተደራድረው የውጪ ግዢ በመፈጸም ክፍያ እንዲደረግ እንደሚታዘዝ፣በዚህም ለፋብሪካው የማያገለግል ዕቃ ተገዝቶ ፋብሪካ ከደረሰ በኋላ የማያገለግል መሆኑ በባለሙያ ተረጋግጦ ወደሌላ ፋብሪካ እንዲጓጓዝ በትዕዛዛቸው 170 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የገለጹት ምንጮች ይህ በመነሳቱ የተበሳጩት የፋብሪካ ስራአስኪያጅ ‹‹ ኮሎኔልና ደም የከፈልኩ መሆኔን አታውቁምን›› በማለት ማስፈራራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህና ተያያዥ በፋብሪካው ተከላ ላይ የተከሰተ የቴክኒክ ችግር የተንዳሆ ፋብሪካ በዚህ ዓመት ወደ ምርት ይገባሉ ከተባሉት አንዱ ቢሆንም ባለሙዎች ግን ይህ የአመራርና የቴክኒክ ችግር ባለበት ሁኔታ መቼውንም ወደ ምርት ሊገባ አይችልም ከሚል ግምት ቢያንስ መቼ እንደሚገባ ለመገመት አይቻልም ብለዋል፡፡

2ኛ/ ኮርፖሬሽኑ ያሉትንም ማስፋፋት እንደ አማራጭ ታይቶ እየተሰራ ባለበትና በፋብሪካ ማሳዎች ዙሪያ የሰፈሩትን ገበሬዎች እያፈናቀልና ባሎንበት በወንጂ ፋብሪካ እርሻዎች መሃል ከውጪ ኢንቨስተር በሚል ለአንድ የሕወኃት አባል የእርሻ ቦታ መሰጠቱን ቅጥ ያጣ ሃፍረተ-ቢስ ተግባር ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

3ኛ/በዚህ ዓመት ምርት ይጀምራሉ ከተባሉት እንዲያውም በመጪው የካቲት ወር ወደ ምርት ይገባል ተብሎ የተነገረለት የኩራዝ አንድ ፋብሪካ ጉዳይ በሚመለከት እንኳን ወደ ስራ ሊገባ በባለሙያዎች ግምት መሰረት እስካሁን የተሸፈነው ከፋብሪካ ግንባታና ተከላ ሥራው ከግማሽ አይበልጥም ላሉ የፋብሪካው ሰራተኞች፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመትም እንዲሁ ተብሎ የተተከለው የሸንኮራ አገዳ ጊዜው አልፎበት ለተከላ የዋለ ሲሆን ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ዳግም ጊዜው አልፎበት ለተከላ ለመጠቀምም የተዘጋጀ ማሳ ባለመኖሩ ማኔጅመንቱ ምን ማድረግ እንዳለበት እየተጨነቀበት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ አሁን ባለው እውነት ኩራዝ ሁለት እንዳይቀድመን ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ የአካባቢው ህዝብ ጥያቄና የፀጥታው ሁኔታ ተጨምሮበት ከሁለትና ሦስት ዓመታት በኋላ ወደ ምርት ከገባን ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የሚታየው የመልካም አስተዳደር እጦትና የአሰራር ሥርዓቱ በህወኃት አባላት መደፍጠጡ፣በተጠቃሚዎቹ ይሉኝታ ቢስነት ታግዞ ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ ዓመታትም ለተመሳሳይ የብድር ጥያቄ እንጂ ለምርት የሚታሰብ አለመሆኑን ፣ የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ክፍሉ ከዚህ ከፋ የግዢና ፋይናንስ አጠቃቀም ጥፋት መኖሩን ለማኔጅመንቱ በተደጋጋሚ መግለጽን በስብሰባው ላይ መግለጹን፣ ከህወኃት ውጪ ያሉ ባለሙያዎችም እኛን እንኳ እንደዜጋ ያገባቸዋል ቀርቶ እንደሰው ይታዘቡናል ያለማለታቸው፣ አድሎኣዊነቱ ዓይን ያወጣና የፈለጉትን በገሃድ መፈጸማቸው በእጅጉ ያስገርማል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የ7መረጃ ምንጮቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ስንት ጊዜ ይዋሻል፣ እስከ መቼስ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ይቀጥላል፣ እናስ መቼ ይሆን እንደዜጋ የምንታየው፣ ብለው ከጤቁ በኋላ ከዚህ ዘረኝነት ለልማት የቱን ያህል መሰናክል እንደሆነ ለመረዳት የሚፈልግ የኛን ኮርፖሬሽን ጠጋ ብሎ ይመልከት በማለት የሚያደምጠን ካገኘን ብዙ የምንለው አለን ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል፡፡