“ማስተር ፕላኑን ህዝቡ እንደማይቀበለው ተረጋግጧል” – ኦህዴድ – “ማስተር ፕላኑ መሰረዝ ያለበት በፓርቲ ውሳኔ አይደለም” – ተቃዋሚዎች


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“ማስተር ፕላኑን ህዝቡ እንደማይቀበለው ተረጋግጧል” – ኦህዴድ – “ማስተር ፕላኑ መሰረዝ ያለበት በፓርቲ ውሳኔ አይደለም” – ተቃዋሚዎች

“ማስተር ፕላኑ መሰረዝ ያለበት በፓርቲ ውሳኔ አይደለም” - ተቃዋሚዎችAddis Admass :- ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ እንዳይሆን የተሰረዘው ህዝቡ እንደማይቀበለው በውይይት በመረጋገጡ መሆኑን የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት የገለፀ ሲሆን ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ ማስተር ፕላኑ መሰረዝ ያለበት በም/ቤት እንጂ በፓርቲ ውሳኔ አይደለም ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳድረው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ለ3 ቀናት በአዳማ ከተማ ባደረገው ስብሰባ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያወዛግብ የከረመው የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ውሳኔ አስተላልፏል። የፓርቲውን ውሳኔ በተመለከተ የተጠየቁት የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ፤ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ከአርሶ አደሩ፣ ከወጣቱና በየደረጃው ከሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በተደረገ ውይይት ማስተር ፕላኑን ህዝቡ እንደማይቀበለው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ኦህዴድም የህዝቡን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ማስተር ፕላኑ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ መወሰኑን የገለፁት አቶ ዳባ፤ ህዝቡ በውይይቱ ወቅት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ማንሳቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ ማስተር ፕላኑ ቀርቷል የሚለው ምላሽ የተሰጠው አሳማኝ ባልሆነ መልኩ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
በኦሮምያ ክልል ማስተር ፕላኑን መነሻ በማድረግ የተነሳውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንቱ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከ500 በላይ አመራርና አባሎቹ እንደታሰሩበት የገለፀው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ “ማስተር ፕላኑን መሰረዝ ያለበት ፓርቲ ሳይሆን ምክር ቤቱ ነው” ብሏል፡፡
“ለህዝቡ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ በቂ አይደለም” ያሉት የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ጥያቄው የአዲስ አበባ መስፋፋት ብቻ ሳይሆን የሚፈናቀለው ገበሬ የካሳና ዋስትና ጉዳይን በዋናነት የያዘ በመሆኑ ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል ብቻ ብሎ ማለፍ በቂ መልስ አይሆንም ብለዋል፡፡
“ሁለት ወር ሙሉ ብዙ ሰብአዊ ቀውስ ሲፈጠር ኦህዴድ የት ቆይቶ ነው ሰሞኑን በአስቸኳይ ስብሰባ ይሄን ውሳኔ ያስተላለፈው?” ሲሉ የጠየቁት ዶ/ር መረራ፤ በግጭቱና ተቃውሞው ሳቢያ የሞቱና የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ በዝምታ መታለፉንም ነቅፈዋል።
“የኛ ክርክር አዲስ አበባ ባዶ መሬት ላይ አትስፋፋ የሚል አይደለም” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ዋናው ጥያቄ ገበሬው ከመሬቱ መፈናቀል የለበትም የሚል ሲሆን የግድ ከሆነም ቀሪ እድሜውን ሊያኖረው የሚችል ካሳ ተከፍሎት ሊነሳ ይገባል የሚል ነው” ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ኦህዴድን እየሰማው አይደለም ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ድርጅቱ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ስልጣን መልቀቅ አለበት ብለዋል፡፡
የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ “እኛ እስከምናውቀው ማስተር ፕላኑ በምክር ቤት አዋጅ የፀደቀ በመሆኑ መሻር ያለበትም በአዋጅ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት፤ አዋጁ ገና በረቂቅ ደረጃ ያለና ለህዝብ ውይይት በሰፊው ያልቀረበ መሆኑን በመጥቀስ እንደፀደቀ ተደርጎ የሚነገረው ትክክል አለመሆኑን በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡ ፕ/ር በየነ ግን አይቀበሉትም። “እኛ እስከምናውቀው ፀድቋል ተብሎ ነው ቢሮ  ተደራጅቶለት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የተገባው” ይላሉ፡፡
“የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብትና የህግ የበላይነትን እየጠየቀ ላለ ህዝብ ማስተር ፕላኑ እንዲቆም ተወስኗል ማለት ብቻ በቂ መልስ አይደለም ያሉት የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንደሰን ተሾመ በበኩላቸው፤ ኦህዴድ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የህዝቡ ጥያቄ እየሰፋ ሄዶ ከማስተር ፕላኑ በላይ ፖለቲካዊ ይዘት ከተላበሰ በኋላ ኦህዴድ መግለጫ መስጠቱ ብዙ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም ያሉት አቶ ወንደሰን፤ ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል የሚለው ውሳኔ ለህዝቡ በቂ ምላሽ አይደለም ብለዋል፡፡
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቱም ሆነ መንግስትም ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች የአፈፃፀም ችግሮችን በመቅረፍ ተግባራዊ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በበኩሉ፤ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ማስተር ፕላኑ እንዲቆም መወሰኑ እየተገነባ ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርአት በህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አረጋግጧል ብሏል – ትናንት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፡፡
“የህዝቦች ውሳኔ የተከበረበት ህገ መንግስታዊ ስርአት በጠንካራ መሰረት ላይ እየተገነባ ነው” ያለው መግለጫው፤ የክለሉ መንግስትና ህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ሆነ የልማት ጉዳዮችን በውይይትና ምክክር ለመፍታት መዘጋጀታቸውን አመልክቷል፡፡
የህዝብን ጥያቄ በመጥለፍ ሁከትና ብጥብጥ ሲፈጥሩ የቆዩ አካላት ከዚህ ውሳኔ ሊማሩ ይገባል ያለው ጽ/ቤቱ፤ እኒህ ወገኖች ወደ ህዝብ መድረኮች በመምጣት የሰለጠነ የሃሳብ ክርክር እንዲያደርጉ መክሯል፡፡፡