የብዙኃን መገናኛዎቻችን እባካቹህን ታረሙልን? – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አማርኛችንና ባሕላችን ለአክብሮት የሚሰጠው ዋጋ ከፍተኛና ከሌሎች ቋንቋዎች የተለየ ላቅ ያለ አስመስጋኝ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ የአክብሮት አንቱታ መጠሪያ የሆኑትን እርስዎ፣ እርሳቸው የሚባሉትን ቃላት የሚተኩ ቃላትን እንግሊዝኛን ጨምሮ በበርካታ ቋንቋዎች ላይ ብትፈልጉ ፈጽሞ አታገኙም፡፡ እነኝህ ቋንቋዎች ሽማግሎችን፣ የሃይማኖት መሪዎችን፣ ትልልቁን ሰው ሁሉ አንተ፣ እሱ እያሉ ነው አንጠልጥለው የሚጠሩት፡፡ ግፋ ቢል የተከረ ለማለት “ልብ በሉ የተከበሩ አይደለም ያልኩት አንቱታ በቋንቋዎቹ ውስጥ ስለሌለ አንጠልጥለው ነው የሚጠሩት” የተከበረ ለማለትም (Sir, his Excellency) የሚል ቃል ከፊት ያስቀድማሉ የሃይማኖት መሪ ሲሆኑም ቅዱስነቱ ለማለት “ልብ በሉ ቅዱስነታቸው ለማለት አላልኩም” (his Holiness) የሚል ቃል ይጠቀማሉ፡፡
ይሄንን ነጥብ እንዳነሣ ያስገደደኝ አንድ በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ አለ፡፡ ቀደም ብየ ባነሣሁት የቋንቋችንና የባሕላችን አዎንታዊ ተጽእኖ ሳቢያ የብዙኃን መገናኛዎቻችን አንቱ በማለት ግለሰቦችን ይጠሩና በተጨማሪም ያለ ማንጠልጠያ የአክብሮት ቃል ላለመጥራት ሲጠነቀቁ እናያላን፡፡ ለምሳሌ የፓርላፓ አባላትን፣ ባለሥልጣናትንና ትልልቅ ሰዎች ናቸው የሚሏቸውን “የተከበሩ” እያሉ ይጠራሉ፡፡
ትላንት ታኅሣሥ 28 2008ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በዓልን ማክበራችን ይታወሳል፡፡ አሁን ብቻ ሳይሆን በየ የጌታ በዓላቱ የብዙኃን መገናኛዎቻችን ስለ በዓላቱ ሲዘግቡ የሚጠቀሙት ቃል በጣም ይገርመኛል፡፡
ተራ ባለሥልጣናትን ሲጠሩ ስንት የሚሽቆጠቆጡት ቅጽል ለማበጀት ስንት የሚጨነቁት እነኝሁ የብዙኃን መገናኛዎች የጌታችን የመድኃኒታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓላት በምናከብርበት ወቅት ሁሉ ለጌታ ያለምንም የማንነቱ መገለጫ “የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ… ተከብሮ ዋለ!” በማለት ነው የሚዘግቡት፡፡
ስለ የሃይማኖት መሪዎቹ የሚሰጡትን የመልካም ምኞት መግለጫም ሲዘግቡ ለምሳሌ በቀደም ለት “የሃይማኖት መሪዎች” ስለ በዓሉ የመልካም ምኞት መግለጫ መስጠታቸውን የብዙኃን መገናኛዎቹ ሲዘግቡ ምን አሉ፡- “የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ ያሉ ወገኖችን በማሰብ በመርዳት እንዲሆን የተለያዩ የሃይማት መሪዎች አሳሰቡ!” አሉ፡፡
በዓላቱም በሚውሉበት ዕለት ዜናዎቻቸውን ከማቅረባቸው በፊት የየራሳቸውን የመልክም ምኞት መግለጫ ሲሰጡም አንጠልጥለው “እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት፣ የጥምቀት፣ የስቅለት፣ የትንሣኤ በዓል አደረሳቹህ!” በማለት ወይም ደግሞ “እንኳን ለገና በዓል ወይም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ፣ ለብርሃነ ጥምቀቱ፣ ለብርሃነ ስቅለቱ፣ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳቹህ!” ይላሉ እንጅ የጌታን የማንነቱን መግለጫ ከስሙ ፊት በመጥቀስ “ለጌታችንን ለመድኃኒታችን ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት፣ የጥምቀት፣ የስቅለት፣ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳቹህ!” ወይም “የጌታችን የመድኃኒታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ፣ የጥምቀቱ፣ የስቅለቱ፣ የትንሣኤው በዓል በሰላም ተከብሮ ዋለ!” በማለት አይገልጹም፡፡
ማለት ያለባቸው ነገር መሆኑን አውቀው ይሁን ወይም ደግሞ የሚናገሩት የንግድ ማስታወቂያ በመሆኑ ደንበኛን በማስደሰት ለመሳብ ይሁን አይታወቅም “እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስን ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳቹህ!” በማለት መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹት በብዙኃን መገናኛዎቹ ማስታወቂያዎቻቸውን የሚያስነግሩት አንዳንድ የንግድ ድርጅቶት ናቸው፡፡
የብዙኃን መገናኛው ዓለማዊ (secular) በሆነ መርሕ ስለሚመራ ነው እንዳልል ይህ ችግር የእስልምና በዓላት በሚከበሩበትና በብዙኃን መገናኛዎቹ በሚዘገብበት ጊዜ ይሄ ችግር በብዙኃን መገናኛዎቹ አይፈጸምም፡፡ የእስልምና አማኞች በሚፈልጉት መልኩ ነው በዓሉ በትክክል የሚገለጸው፡፡ ስለዚህ ምክንያቱ ይሄ መርሕ አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱ ይሄ አለመሆኑና ችግሩ ያለው በክርስትና ላይ ብቻ መሆኑ ነው ለምን? የሚል ጥያቄ እንዳነሣ ያደረገኝ፡፡
ለምሳሌ አሁን በቅርብ ታኅሣሥ 13 የተከበረ የእስልምና በዓል አለ፡፡ የብዙኃን መገናኛዎቹ አንዳቸውም ሳይሳሳቱ ሙስሊሞች ብለው እንደሚያምኑት “እንኳን ለነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል በሰላም አደረሳቹህ!” ወይም “እንኳን ለነቢዩ መሐመድ የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳቹህ!” በማለት ነበር የዘገቡት፡፡
““ጌታችንን መድኃኒታችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማንነቱ መገለጫዎች አንዱንም ሳትጠሩ አንጠልጥላቹ “የኢየሱስ ክርስቶስ” በማለት እንደምትጠሩት ሁሉ የሙስሊሞችን ነቢይ መሐመድንም አንጠልጥላቹህ የመሐመድ… በማለት መጥራት አለባቹህ! ለእኛ ያልተደረገው ያልተፈቀደው ለእነሱ የሚደረገው የሚፈቀደው ለምንድን ነው?”” ብሎ ማለት ሰይጣናዊ ምቀኝነትና የእኔ ዓይን እንደጠፋ የጎረቤቴም ይጥፋ ማለት በመሆኑ እንዲህ በማለት አይደለም የብዙኃን መገናኛውን እየጠየቅን ያለነው፡፡
ነገር ግን መሐመድን አማኞቹ ወይም ተከታዮቹ በሚያምኑት በተቀበሉት የማንነት መገለጫው እንደምትጠሩት ሁሉ ጌታችንን መድኃኒታችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስንም እኛ አማኞቹ ተከታዮቹ በተቀበልነው በምናምነው የማንነት መገለጫዎቹ ጥሩልን ነው እያልን ያለነው፡፡
ስለሆነም የብዙኃን መገናኛዎች ሆይ! እባካቹህን አንደበታቹህን አርሙልን? የምትፈጽሙብንን አድልኦና በደል አቁሙልን? ለአንደኛው እሱ በሚጠራው የማንነቱ መገለጫ ለሌላኛው ያለምንም መገለጫው አንጠልጥላቹህ ልትጠሩ የምትችሉበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ አግባብ የለምና የእኛንም መብት አክብሩልን? አድልኦ አትፈጽሙብን?
ሙስሊሞች መሐመድን ነቢያችን ነው ስላሉ “ነቢዩ መሐመድ” እያላቹህ እንደምትጠሩ ሁሉ እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኃኒታችን ነው ብለን እናምናለንና ሦስቱንም እንኳን ባትጠቅሱ አንዱን እንኳን በመጥቀስ ትጠሩልን ዘንድ በታላቅ ትሕትናና አክብሮት እንጠይቃለን!!!
እዚህ ላይ ምናልባት ከብዙኃን መገናኛዎቹ በኩል ጥያቄያችንን ላለመቀበል አንድ ይሉት ይሆናል ብየ የምገምተው ነገር አለ፡- ““ዜና አንባቢው ወይም መልካም ምኞት ገላጩ ወይም ድርጅቱ በክርስቶስ አምላክነት ጌትነት መድኃኒትነት የማያምን የማይቀበል ሲሆን “እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት፣ የጥምቀት፣ የስቅለት፣ የትንሣኤ በዓል አደረሳቹህ!” ወይም ደግሞ “የጌታችን የመድኃኒታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ… ተከብሮ ዋለ! ብሎ የማያምንበትን ነገር አስገድዶ እራሱን አካትቶ እንዲናገር እንዲዘግብ ማድረግ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ረገጣ ነውና፣ መብትና ነጻነቱን መንፈግ መግፈፍ ነውና እንዲህ ማድረግ አንችልም!””
ይሉ ይሆናል ነገር ግን ክርስትና የመሐመድን ነቢይነት የማይቀበል እንደመሆኑ እምነታቸው ክርስቲያን የሆኑ ሰዎች የመሐመድን ነቢይነት ሳያምኑ “የነቢያችን” ሳይሆን “የነቢዩ” መሐመድ … በማለት እንደሚዘግቡት ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ጌትነት መድኃኒትነት የማያምን ዜና አንባቢም ሆነ መልካም ምኞቱን የሚገልጽ ማንኛውም አካልም የጌታችን ሳይሆን የጌታን፣ የአማላካችን ሳይሆን የአምላክን፣ የመድኃኒታችን ሳይሆን የመድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን … ብሎ በመዘገብ መልካም ምኞት በመግለጽ መብቱ ሳይገፈፍ ሥራውንም ሠርቶ የእኛንም መብት ሊጠብቅልን ይችላልና ይህ እንዲፈጸም የብዙኃን መገናኛዎችን በእክብሮትና በትሕትና እንጠይቃለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!