“ለሕጋዊ” ሕግ አልባ ምላሽ !
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
“ለሕጋዊ” ሕግ አልባ ምላሽ ! Yidnekachew Kebede
……………………
“ ማንኛውም ዜጋ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን መግለጽ ይችላል ፤ሕጋዊ መብቱ ነው፡፡በእኛ አገር ግን ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ሕግ-አልባ የሆነ፤በገዢው መንግሥት ፍላጎትና ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ሕገ-ወጥ አፈና ነው፡፡”
———————————
ተቃውሞ የዴሞክራሲ መገላጫ ነው! የመንግሥት አስተዳደር ጤናማነት መለኪያ ጭምር ነው፡፡ዴሞክራሲ በራሱ እጅ እግር ኖሮት የሚንቀሳቃስ ፍጡር አይደለም፤ዴሞክራሲ በሐሳብና በተግባራ በሰዎች የሚከወን መሠረታዊ መብት ነው፡፡ከመብቶች መካከል ደግሞ “መቃወም !” አንዱ ነው፡፡
ተቃውሞ በግለሰብ፣በቡድን እና በተቋም ደረጃ ሊከናወን ይችላል፤የሚቻለውን ነገር ለማደረግ የአመለካከት ነፃነት በቅድሚያ መኖር አለበት፡፡የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 29 ንዑስ-አንቀፅ 1 ይህንኑ ይደግፋል፤ “ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡”
ድንጋጌው ግን ለውህሓት/ኢህአዴግ የመንግሥት አስተዳደር፣አቀበት እንደመውጣት ነው፡፡ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሠራተኛ ግምገማ መመዘኛ ከሆኑት ውስጥ አንዱ “አመለካከት” ነው፡፡ከሥራ አፈፃፀም በላይ የፖለቲካ አመለካከት የደሞዝ እና የደረጃ እድገት ያስገኛል/ያሳጣል፡፡የትኛውም ሰራተኛ በተመደበበት ሙያ የቱንም ያህል ችሎታ እና የአፈጻጸም ብቃት ቢኖረውም “አመለካከቱ”በምዘናው መሠረት ዝቅተኛ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝ መብቱ በውህሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የሚደፈጠጠው ከዚህ ጀምሮ ነው፡፡ሌሎች ቡዙ ማሳያዎች ያሉ ቢሆንም ይሄን እንደ-ምሣሌ መውሰድ ይቻላል፡፡
የመንግሥት ጫና ተቋቁሞ፣ የአመለካከት ነጻነት በግለሰበ ጥረት እሁን ለማድረግ ቢፈለግ፣ ቀጥሎ የሚመጣው ሃሳብን መግለፅ ነው፡፡ለዴሞክራሲ እድገት እና ሞት ንጽጽሩ ፣ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ማክበር ወይም አለማክበር ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ተግባራዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 2 “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው” ይላል፡፡ ይህ ነጻነት የግዛት ወሰን የለውም፣በማንኛውም ዘዴ ሐሳብን ማሰራጨት በሕግ የተቀመጠ መብት ነው፡፡
ሐሳብን ከመግለጽ ጋር በተያያዘ የሰማሁት አንድ ነገር ትዝ ይለኛል፤ነገሩ የተከሰተው በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥነው ፡፡ እና በመሥሪያ ቤቱ በተደረገ ግምገማ ላይ-ነው አሉ-አንዱ ሠረታኛ ተራው ይደርስና “አመለካከቱን” ይገልጻል፤በኋላ በእርሱና በገምጋሚዎቹ መካከል ሰፊ ክርክር ተደረግ፤ክርክሩ፣ተገምጋሚው ያልገለጸውን አመለካከት፣ለመግለጽ አስበኻል በሚል የተነሣ ክርክር ነበር አል፤ይህቺ ቁም-ነገር ያዘለች ቀልድ/ጨዋታ፤ህውሓት/ኢህአዴግ አይደለም ሐሳብ ተገልጾ ፣ያልተገለጸ ሐሳብ እንኳ ምንኛ እንደሚያሸብረው የምትጠቁም ነች፡፡(“አዎ፣ሐሳቡን አስቤአለሁ፤”የሚለው የቀልዷ ማሰረጊያ ነች፤ “ተጸጽቻለው፤ግለ-ሒሴን አውርጃለው” ነው እንግዲህ፡፡)
ሐሳብ መግለጽ ይቅርና ፣ሐሳብን ማሰብ በራሱ ሐሳብ የሆነብን እኛው ነን !በእኛ አገር ሐሳብን በነፃነት መግለፅ ለእስራት፣ሞት፣አገር ጥሎ ለመሰደድ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ለዜጎች የሚሆንን ነገር በግድ የሚመርጥልን፣ ማሰብ ያለብንን ሐስቦ “እንዲህ እንዲህ ”መሆን አለበት የሚለን መንግሥት ለእኛ ምናችን ነው ? ምንም ! ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የሐሳብ ማሰራጫ ተቋማት በእጁ ናቸው! ለመረጣቸው ‹ጋዜጠኞች› ‹ይሄን አድርጉ!እንዲህ በሉ!› እያለ እንዳሻው የመዘወር ‹ሥልጣን› ብእጁ ነው!‹እነዚህ፣እነዚህ ሚዲያዎች ‹ፀረ-ምናምን….ናቸው እያለ የመፈረጅ ‹ሥልጣን›የእርሱ!‹አንተ አሸባሪ! እሱ አሸባሪ!› የማለት ‹ሥልጣን› ያለው በእጁ!
በአንድ ጤናማ የዴሚክራሲ ሒደት ውስጥ፣ ማንኛውም ሰው በራሱ አመለካከቱ ለደረሰበት ድምዳሜ መሠረት ሕጋዊ ተቃውሞውን ሆነ ደጋፉን ፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመግለፅ መብቱ በእኛ አገር ሕግ ላይ ብቻ ሳይሆን፤በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ መብት ነው፡፡ይህ መብት በሕግ ከፍተኛ ከለላ የተሰጠው ጭምር ነው፡፡በእኛ አገር ሕገ-መንግሥት የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት የተጠበቀ ነው፡፡በዚህም መሠረት መቃወም የተቃወሙትን ነገር በሰልፍም ሆነ በስብሰባ መግለፅ የሕግ ከለላ አለው፡፡
መንግሥት የሕዝብ መብት ለመጠበቅ የቆመ የሕዝብ አገልጋይ ነው !ሕዝብ በመንግሥት ቅር ከተሰኘ የምርጫን ዘመን ጠብቆ ፣ኃላፊነት ከመስጠትና ከመንፈግ ባላፈ ፣በማንኛውም ጊዜና ቦታ ፣በመንግሥት ላይ ያለውን ተቃወሞ እና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ይሁን እንጂ የውህሓት/ኢህአዴግ የመንግሥት አስተዳደር ለአቅመ ትችት እና ተቃውሞ ያልደረስ ነው ፣ እንደሚባለው፤ የእውነትም “ድንክዬ ”መንግሥት ነው፡፡
የአገዛዙን ሥርዓት ለመደገፍ የሕዝብ ሀብት ከሆኑ ንብረቶች ጀምሮ፣እስከ ግለሰብ ደረጃ የውዴታ ግዴት እንዲገቡ በማድረግ ፣በሚያስፈልጋቸው ቦታና በወደዱት ሰዓት፣ ካለከልካይ የተፈለገው ነገር ሁሉ ይደረጋል፡፡ ደስ ካላቸውም በመገናኛ ብዙኃን የቀጥታ ስርጭት ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡የሚገርመው ነገር የአገዛዙን ሥርዓት በመቃወም የተጠራ ሰልፍ ወይም ሰብሰባ ከላ፣ በሕዝብ ሀብት በሚተዳደሩ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ‹ሰልፍ/ስብሰባ እውቅና ያልተሰጠው ስለሆነ ማንም እንዳይሳተፍ ፤ለመሳተፍ ቢሚሞክሩት ላይ ፖሊስ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል›በማለት ያስፈራራል፡፡
ማንኛውም ዜጋ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን መግለጽ ይችላል፤ሕጋዊ መብት ነው፡፡ በእኛ አገር ግን ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ሕግ-አልባ የሆነ፣በገዢው መንግሥት ፍላጎትና ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ሕገ-ወጥ አፈና ነው፡፡የዚህ ዓይነቱ ሥርዓት መንሰሄ የአስተዳደር አቅም ማነሰን ያሳያል፡፡ በሕዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጦ የሕዝብ ቅሬታን ለመቀበል ፍቃደኛ የአለመሆን ውጤት “የለሁበትም!…….የለሁበትም !….” እንዳይሆን!
“ዲሞክራሲ ማለት ምን ማላት ነው ?” ከሚለው መጽሐፍ የቀነጨብኩት አስፍሬ ጽሑፌን አበቃለው፡፡ “በመራጩ ሕዝብ ስምምነት ላይ የተመሰረተ መንግሥት በሙሉ ልቦና የመናገር እና የመወሰን ሥልጣንና ኃይል ይኖረዋል፡፡ይህ ልበሙልነት በወታደራዊ ኃይል ለተጨበጠ ሥልጣንና በሕዝብ ላልተመረጠ መንግሥት በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፡፡”