መስ’ዋትነት ምንድን ነው ( ሄኖክ የሺጥላ )
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ምርጫ 1997ትን ተከትሎ ፥ ኢትዮጵያን እየመራሁ ነው የሚለው ስርኣት፥ በሰላማዊ መንገድ ሊወገድ እንደማይችል ግንዛቤ በመውሰድ ፥ እኔና ወንድሜ ኣርበኞች ግንባርን ለመቀላቀል መወሰናችንን ለኣንድ እጅግ ለምናከብረው እና ምክሩን ለምንሰማው ሰው ኣማክረነው ነበር። በወቅቱ ይህ ሰው የጠየቀን ጥያቄ “ ለምንድን ነው ጫካ የምትገቡት ?” የሚል ነበር ። በቁጭት ፥ እና በእልህ የመለስንለት መልስ “ ለዚህ ህዝብ መስ’ዋት መሆን ስለምንፈልግ !” የሚል ነበር ። ይህ ኣስተዋይ እና ትልቅ ሰው ፥ ስለ ውሳኔያችን እርግጠኞች መሆናችንን ረጋ ብለን እንድናጤነው ከመከረን ወዲያ መስ’ዋትነትን በተመለከተ የኢያን-ራንድን ኣትላስ ሽሬግድ ( Atlas Shrugged ) የተባለ መጥሃፍ እንድናነብ ሰጠን ። ምክንያት ነበረው ። ዛሬ ኣስር ኣመት ወደ-ሗላ በመገስገስ ስለ መስ’ዋትነትን ያነበብኩትን እና እኔ ገባኝ ብዬ የማስበውን ላካፍላችሁ።
ኢያን ራንድ እንዲህ ትላለች፥
መስ’ዋትነት ትልቁን እና ዋጋ የምንሰጠውን ነገር ፥ ዋጋ ለማንሰጠው እና ዝቅ ላለው ነገር ኣሳልፎ መስጠት ነው። መስእዋትነት ማለት የማይጠቅመውን መናቅ ወይም መተው ኣይዶለም። መስ’ዋትነት ማለት ክፉን በበጎ መቀየርም ኣይዶለም ፥ ግን ጥሩን ለመጥፎ ሲሉ እንጂ ። ዋጋ የምትሰጠውን ዋጋ ለማትሰጠው ነገር ኣሳልፈህ ስትሰጥ የምትከፍለው ነገር መስእዋትነት ይባላል።
ለምሳሌ ኣንድ ሳንቲም በ ኣንድ ዶላር ብትቀይር መስ’ዋትነት ኣይዶለም ፥ ኣንድ ዶላር በኣንድ ሳንቲም ብትቀይር ግን መስእዋትነት ነው። ከብዙ ኣመታት ትግል እና ውጣ ውረድ በዃላ የምትፈልገው የትምህርት ደረጃ ላይ መድረስ እና ለመድረስ የምታደርገው ትግል መስ’ዋትነት መክፈል ተብሎ መታየት የለበትም ። አንተ የአንድ ብርጭቆ ጠርሙስ ወተት ባለቤት ብትሆንና ያንን አንድ ብርጭቆ ወተት ለተራበ ልጅህ ብትሰጠው መስ’ዋትነት አይደለም ። መስ’ዋትነት ሊሆን የሚችለው፣ ልጅህ በራብ እንደሚሞት እያወቅህ ፣ ይህንን አንድ ብርጭቆ ወተት ለጎረቤት ልጅ ብትሰጠው ነው ።
ወዳጅህን ለመርዳት ግንዘብ ብትለግሰው መስ’ዋትነት አይደለም ። ለማታውቀው እና <ዋጋ የማያወጣ > ብለህ ለምትለው ሰው ይህንን ገንዘብ ብትሰጥ ግን መስ’ዋትነት ነው ። መስጠት የምትችለውን ገንዘብ ለወዳጅህ ብትሰጠው መስ’ዋትነት አይደልም ፣ ቅር እያለህ ግን አሁንም መስጠት የምትችለውን ገንዘብ ብትሰጥ ፣ ከፊል የስነ ባህርይ -ምጥቀት/ልቀት ሊሆን ይችላል ። ግን ለወዳጅህ የምትሰጠው ገንዘብ አንተን ሙሉ በሙሉ < የወጣለት > አደጋ ውስጥ እንደሚጥልህ እያወቅህ ከሆነ ያደረከው እሱ መስ’ዋትነት ነው ።
መስ’ዋትነት ዋጋ የምንሰጠውን ነገር ፣ ያነሰ ዋጋ ላለው ነገር አሳልፎ መስጠት ነው ። እውነተኛው መስ’ዋትነት በምትኩ ፣ ሙገሳም ፣ ይሁን ፍቅር ፣ ውዳሴም ይሁን ኩራትን አያስተናግድም ፣እንደዚህ ያለውን ነገር አያስብም ።
መሞት የግል ፍላጎትህ ሆኖ ሳላ ለሌሎች ሕይወትህን አሳልፈህ ብትሰጥ መስ’ዋትነት አይደለም ( It is not a sacrifice to give your life for others, if death is your personal desire) ። ድርጊትህ የመስ’ዋትነት ሚዛን እንዲደፋ ከፈለክ ፣ መኖር መፈለግ አለብህ ፣ ሕይወትህን ማፍቀር አለብህ ፣ በምድራዊ ፍቅር እና በምትሰጥሕ እምቅ እና ውብ ጸጋዋ ና የመኖር- ፍቅሯ ፍቅር መቃጠል አለብህ ። ሞትህ መስ’ዋትነት የሚሆነው ፣ ለመኖር ጽኑ ፍቅር እያለህ ለመሞት ስትወስን ነው። ካራ- ሆድህ ላይ ተሰክቶ አንጀትህን ሲጠመዝዘው ፣ ካራው በምድር ላይ የመኖር ፍቅርህን መጦ ሲያወጣው የሚሰማህ ከሆነ ነው ሞትህ መስ’ዋትነት የሚሆነው ። ሞት በራሱ ብቻውን መስ’ዋትነት የሚሆንበት አንዳች ምክንያት የለውም ። ይልቅ በሞት እና በምታፈቅረው ሕይወት ውስጥ ያለው ስቃይ ነው መስ’ዋትነት።
ክብርህን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ትግል መስ’ዋትነት አትበለው ። አንድ እናት ለራሷ ኮፍያ ከመግዛት ለልጇ ምግብ ብትገዛ መስ’ዋትነት አይዶለም። ምክንያቱም ከኮፍያው ይልቅ ለልጇ ዋጋ መስጠቷ እሙን ነውና ። መስ’ዋትነት ከሆነም/ ከተባለም ሊሆን እና ሊባል የሚችለው፣ ከልጇ ይልቅ ኮፍያ ለምታስበልጥ እናት ብቻ ነው ።
አንድ ሰው ለነጻነቱ ሲዋጋ ቢሞት መስ’ዋትነትት አይደለም ። ምክንያቱም ባርያ ሆኖ መኖር አልፈለገምና ። ግን ባርነትን ተቀብሎ መኖር የሚችል ሰው ፣ ለነጻነቱ ሲል ሞተ ቢባል ለሱ ሞቱ መስ’ዋትነት ነው የሚሆነው ። አንድ ሰው እምነቱን አሳልፎ ላለምስጠት ቆርጦ ቢቆም መስ’ዋትነት አይደለም ፣ መስ’ዋትነት የሚሆነው ፣ እምነት የሌለው ሰው ለሌሎች እምነት ሲል ቢሰዋ ነው ። እዚህ ጋ በደርግ ጊዜ በብሔራዊ ውትድርና ታፍሰው ውጊያ ላይ እንዲሰለፉ የተደረጉት ሰዎች ፣ በራሳቸው መንገድ በርሃ ከወረዱት ሰዎች አንጻር መስ’ዋትነት የከፈሉት ታፍሰው ተወስደው የሞቱት ናቸው ማለት እንችላለን ፣ ምክንያቱም የሚሞቱለት ነጻነት እና ክብር ስላልነበራቸው ። ( If a man dies fighting for his own freedom, it is not a sacrifice: he is not willing to live as a slave; but it is a sacrifice to the kind of man who’s willing. If a man refuses to sell his convictions, it is not a sacrifice, unless he is the sort of man who has no convictions.)
መስ’ዋትነት የሚለው ነገር እንግዲህ አግባብ የሚሆነው ፣ ምንም መስ’ዋት የሚያደርጉት ነገር ለሌላቸው ሰዎች ነው ማለት ነው ። ሰለሚያደርገው ነገር በደንብ የሚያውቀው ሰው ግን ፣ ፍላጎቱ ከምክኒያታዊነት ለመነጨ ሰው ግን ፣ መስእዋትነት ማለት መልካሙን ለመጥፎ ሲሉ መተው ነው/ አሳልፎ መስጠት ነው ። (For a man of moral stature, whose desires are born of rational values, sacrifice is the surrender of the right to the wrong, of the good to the evil.)
ሚስቱን በፍቅር የሚወድ ሰው ፣ ያለውን ገንዘብ በሙሉ ሚስቱን ከክፉ ደዌ ለማዳን ቢጠቀምበት መስ’ዋትነት አይደለም ። ለሚስቴ ስል ንብረቴን መስ’ዋት አደርኩ ሲል ቢሰማ ፣ ሃሳቡ በራሱ አሳፋሪ እና ግልጥ ያልሆነ ነው የሚሆነው ። ምክንያቱም የሚወዳት ሚስቱ በሕይወት መቆየት፣ ለራሱ ደስታን የሚሰጠው ነገር ነውና ፣ለራሱ ደስታ ሲል ያደረገው ነገር በምንም መልኩ መስ’ዋትነት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልምና ። ይልቅ የሚወዳት ሚስቱ በጽኑ ደዌ ተይዛ ሳለ፣ ገንዘቡን ለማያውቃቸው እና ምናልባት ምንም አይነት ፍቅርም ይሁን ስጋዊ ትስስር ለሌላቸው አስር በሽተኞች ማሳከሚያነት አውሎት፣ የሚወዳት ሚስቱ መታከሚያ አጥታ እያያት ብትሞት ፣ ይህ ሰው ገንዘቡን መስ’ዋት አደረገ ልንል እንችላለን ።
አንድ ሰው የሚወደው ልጁን ትቶ በርሃ ቢገባ ( ለምሳሌ እኔ ራሴ ) ፣ ውሳኔዬ መስዋትነት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ፣ ልጄ ከምገባበት በርሃ ከበለጠብኝ ብቻ ነው ። ልጄ ከዓላማዬ እንደሚሻል እያወቅሁ ፣ ልጄን ትቼ በርሃ ከወረድኩ ብቻ ነው ውሳኔዬ መስ’ዋትነት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ። ልጄ ከሀገሬ አይበልጥም ብዬ የማስብ ከሆነ እና ራሴን ለሀገሬ አሳልፌ ለመስጠት ብወስን ፣ ከላይ እንዳስቀመጥኩት ፣ በአንድ ሳንቲም አንድ ዶላር እንደመቀየር ነውና ፣ መስ’ዋትነት ከፈልኩ አያስብለኝም ። እኔ ከራሴ ሕይወት እንደተረዳሁት ፣ ትልቁ ችግርም ያለው ይህንን መረዳቱ ላይ ይመስለኛል ።
አላማ በጽናት በምቆም እና ቃልን መጠበቅ በሞት ሲደመደም መስ’ዋትነት ተብሎ የሚባለው ነገር ለኔ ስህተት ነው ። እሱ መስ’ዋትነት ሳይሆን አላማን ማሳካት ነው ። እየተታኮሰ የሞተ ሰው የሞተው መተንፈስ ስላቆመ ብቻ ነው ። እንጂ ባንተ በትግል አጋሩ ደም ውስጥ መተኮሱን አያቆምም!! ምክንያቱምም አልሞተማ ! መስ’ዋት አልሆነማ ! ባንጻሩ ፣ በግድ ከጥይት ፊት ለፊት ያቆምከው ሰው ( ምናልባት ኣፍሰህ ያመጣኸው ሊሆን ይችላል ፥ ምናልባት ኣግባብተህ እና ውሽት ሞልተኽው ) ፥ ይህ ሰው ሳይሞት በፊት ነው የሞተው ፣ ሞቱ ደሞ በመስ’ዋትነት ይደመደማል !!!
ማሳሰቢያ
ጀግንነት ከመስዋ’ትነት ጋ የሚያዛምደው ነገር ሊኖር እንደሚችል ሁሉ ፣ ፍጹም የማይዛመዱበትም ሁኔታ እንዳለ እንረዳ ። አብርሃም ይስሐቅን ሊሰዋ ሲል ፣ አብርሃምም ይሁን ይስሐቅ ጀግኖች ስለነበሩ አይመስለኝም !
