ህዝብን ማዘናጋት ያብቃ– የውይይት መድረክ ይከፈት// Girma Bekele
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አዎን ለለውጥ የሚደረገው ህዝባዊ ትግል ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ግን የሚያስተባብረውና የሚያቀናጀው የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚመጥን አመራር የሚሠጠው የፖለቲካ ድርጅት አላገኘም፡፡ ትናንት ሌሎችን እርሷቸው ብለን፣ተስፋ ጥለንባቸው የነበሩትና ህዝብ ሊደግፋቸው፣ እኛም ልንቀላቀላቸው ፣ እነርሱም ሊተባበሩ ይገባል ያልናቸውና ትዝብታችንና ምክራችንን የለገስናቸውን የመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የአደረጃጀትና አመራር ብቃት …. ተግባራዊ እንቅስቃሴኣቸውና የውስጥ ፍትጊያቸውን በቅርብ ለተከታተለና ለገመገመ የነጻነት ትግሉን የመመምራት ኃላፊነትን ለመሸከም እንዳልቻሉ ለመረዳት አይቸገርም፡፡ ከግልጹ የአምባገነናዊ ሥርዓቱ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ባሻገር በተናጠል ከሚታይባቸው አቅም ውስንነትና በውስጣዊ ፍትጊያ ከሚባክነው አቅም ከሚወጣው ጎታች ኃይል/ነጌቲቪ ኢኔርጂ/ ባልተናነሰ ወይም በበለጠ አብሮ ለመስራት ያላቸው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያለንበትን አሳሳቢ ሁኔታ ወደ ጎን በመግፋት ‹‹ በሌለው ሥልጣን›› ላይ በሚነሳው ጥያቄ እግር ተወርች ተጠፍሮ ወደፊት ሊገፋ አልቻለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለንበት ወቅታዊ አሳሳቢና አሰባሳቢ ሁኔታ ውስጥ የጋራ መግለጫ እንኳ መስጠት ባልቻሉበት መድረክና ሰማያዊ ‹‹ …አብረን ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው፣ በሂደት ላይ ነን…›› ቢባል ህዝብንና የለውጥ ኃይሎችን ከማዘናጋት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡
እውነቱ መድረክ በአባል ድርጅቶቹ መካከል ያለውን አብሮነት እንኳ ሊያሳየን አልቻለም፡፡ በኦሮሚያ እየተደረገ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ በሚመለከት ኦፌኮ ለብቻው ስንት መግለጫና ማብራሪያ ከሰጠ ከብዙ ጊዜ በኋላ መድረክ መግለጫ መስጠቱ፣ በኦፌኮና መድረክ መግለጫዎች መካከል የታየው የሟቾች ቁጥርና የመግለጫው ይዘት ልዩነት፣ ኦፌኮ ከሰማያዊ ጋር በተናጠል ለመስራት የጀመረው ውይይትና ስምምነት ከደረሱ በኋላ የመድረክ በአናቱ መግባት፣… የሚያመለክቱት ይሄንኑ ነው፤ በመድረክ ውስጥ ያለው አንዱ አባል ድርጅት/አመራር ለሌላው ባሰመረው ‹‹ቀይ መስመር›› ውስጥ ተቀንብበው /ታስረው የሚያደርጉትን የጎንዮሽ ፍትጊያ፡፡
በተመሳሳይ በሰማያዊ ውስጥ ከ‹‹ ጸረ-ኢያስፔድና ዮናታን ዘመቻ›› እስከ ከማኅበራዊ ሚዲያ ወደ ጋዜጣ የተሸጋገረው ‹‹ሰማዊን እናድን ›› አደባባይ የወጣው ‹‹ሰማያዊን የማዳን ይሁን የመግደል›› ውሉ ያልለየው ‹‹ትግል›› የሚያመለክተውም ይህንኑ ያለመናበብ የስልጣን ፍትጊያ ነው፡፡እዚህ ላይ ውሻ በቀደደው ጅብ ገብቶ የሚሰራውን ለማገናዘብ ‹‹ትናንት›› አንድነት ፕሬዝደንቱን በመረጠ ስምንት ወራት ለማውረድ የነበረውን ከደንብ የወጣ የውስጥ የስልጣን ፍትጊያና ውጤቱን ከዛሬው የሰማያዊ ችግር ጋር ያለውን ተመሳሳይነትና እስከዛሬ ሊኖሩ ከሚችሉት ተጨማሪ የገዢው ፓርቲ ሰርጎገቦችና የማፍረስ ተልዕኮኣቸው ሊከፍት የሚችለውን ቀዳዳ አስታውሶ ማለፍ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ፈቃደኝነቱ ካለ የመኢአድም ሆነ ሰማያዊን ‹‹የወለደው›› የቀድሞው አንድነትም ለዚህ ማሳያነት/ ምሳሌነት አያንሱም፡፡
ስለዚህ የውስጣቸው ስምምነትና አብሮነት ጥያቄ ውስጥ ያሉ ሁለት ወገኖች በአደባባይ የሚታይ ችግራቸውን አለባብሰው ለጋራ ጉዳይ በትብብር/ኅብረት እንሰራለን ቢሉ ‹‹የማያተማመኑ ጓደኛሞች በየወንዙ ይማማላሉ›› ከሚለው አልፎ ተበታትኖም ቢሆን ዛሬም ስለ አገርና ህዝብ በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ እያደረገና ዋጋ እየከፈለ ያለውን የለውጥ ኃይል ከማዘናጋት ሌላ ትርጉም አይኖረውም የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህም የለውጥ ኃይሉና ህዝቡ የራሳቸውን አማራጭ መፍትሄ ለማበጀት መመካከርና መወያየት የግድ ይላቸዋል፡፡ እንደእኔ አተያይ መልክ ባይኖረውም በማኅበራዊ ሚዲያው መፈንጠቅ ጀምሯል፡፡
ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ትብብር መቼ ? እና ለምን ? ለሚሉ ጥያቄዎች የራሱን መልስ እየሰጠ በራሱ ጊዜ በህዝቡ እየተመራ ጉዞውን እየቀጠለ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ፣ በገዢውም ሆነ በተቃዋሚው ታመነም አልታመነ ፣ ለመስዋዕትነት በተዘጋጁ ዜጎች ፍርኃት ቦታውን ለ‹‹ ቆራጥነት›› አስረክቧል፣ የከፋፍለህ ግዛ ስልቱ አርጅቷል፡፡ ስለዚህም ላለፉት 24 ዓመታት በተለያየ መንገድ አሳራቸውን ሲያዩ የነበሩ ነጻነት የተጠሙ ኢትዮጵያዊያን ፓርቲ ቢኖር- ባይኖር፣ ቢመራው- ባይመራው በጭቆናው ተንገሽግሸው‹‹በቃ›› እምቢ አልጨቆንም፣ አልገዛም ፣ በማለት የከፋፍለህ ግዛውን ስልት አደጋ ተረድተው ይታይ የነበረውን የጎንዮሽ መናቆር አሽቀንጥረው የትግል ኢላማቸውን በአንድ አቅጣጫ አድርገዋል ፤ በጨቋኙ አምባገነናዊ የአገዛዝ ሥርዓት ላይ ብቻና ብቻ፡፡ ይህም ህዝባዊ የነጻነት ትግሉ የለውጥ ጥማቱን ሳያረካ ወደማይመለስበት ደረጃ መሸጋገሩን በግልጽ ያሳያል፡፡
ስለሆነም ህዝባዊ ትግሉ ከደረሰበት ደረጃ ወደኋላ እንዳይመለስ፣ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ጉዞውና ዓላማው እንዳይቀለበስ፣የዚህ አምባገነናዊ ሥርዓት ‹‹ድንገተኛ ሞት›› ባልተዘጋጀንበት ደርሶ ለትርምስና ጥፋት ተዳርገን እንአገርና ህዝብ አላስፈላጊ ዋጋና መስዋዕትነት እንዳንከፍል አስፈላጊውን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ ከሚገባን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ እውነትና እውነት ነው፡፡ አይደለም ፣ እኔ እበቃለሁ፣ ተዘጋጅቻለሁ፣ እችላለሁ- እመራለሁ የሚል ካለ በመግለጫ ‹‹ አለሁ/አለን›› ከሚል ባለፈ የውስጥ ችግራቸውን በደንባቸውና በዲሞክራሲያዊ አግባብ ፈተው በተናጠልም ሆነ በጋራ/በትብብር ኃላፊነቱን ይቀበሉ፣ አብረው ለመስራት እንቅፋት የሆነውን ምክንያት በግልጽ/በአደባባይ ገልጸውልን ተጨባጭ ተግባራዊ አቋም ወስደው በድርጊት አስመስክረው፣ ከፊት ሆነው እንድንከተላቸው አመራር ይስጡን፤ ከዚህ ውጪ ግን በተለመደው ‹‹ የአለሁ/አለን ፕሮፖጋንዳ›› አያዘናጉን፡፡ ከነዚህ ፓርቲዎች ውጪ ያለው የለውጥ ኃይል እነዚህ የሚሉንን / የሚባለውን እየሰማን ሳንዘናጋ በዚህ ህዝባዊ ትግል ውስጥ በንቃት የምንሳተፍበትን፤ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የምናደርግበትን፣ ወይም/ እና እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች/መድረክና ሰማያዊ/ ለትግሉ የለውጥ ኃይሉን የሚያስባብሩበትንና የአመራር ብቃታቸውን የሚያሳድጉበትን አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳረፍ መምከርና መወያየት ካለብን ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ስለምንገኝ አጣዳፊ ተግባራት ከፊታችን መደቀኑን ተረድተን ስለአተገባበሩ/አፈጻጸሙ ኃሳብ ማዋጣት እንጀምር፡፡ እኔ የአይቲ ዕውቀቱ ያላችሁ አንድ የጋራ ውይይት መድረክ በፌስቡክ ብትከፍቱልን ብዬ የራሴን የታየኝን ማዋጣት ጀመርኩ ፣ እናንተስ ?? በቸር ያገናኘን//