ሰመጉ በኦሮሚያ ተቃውሞ የደረሰውን ጉዳት እያጣራሁ ነው አለ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በግጭቱ ንብረት ብቻ እንደወደመ ተደርጎ መገለፁ ተነቀፈ
ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በተነሳው ግጭት ከ80 በላይ ዜጎች መሞታቸውን ኦፌኮ የገለፀ ሲሆን የክልሉ መንግሥት ጉዳዩ በጥንቃቄ እየተጣራ መሆኑን ጠቁሞ ሪፖርቱ እንደተጠናቀቀ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት መንግሥት ለተቃውሞው ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀም ያሳሰበው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በበኩሉ፤ ወደየአካባቢው ባለሙያዎችን አሰማርቶ የጉዳቱን መጠን ለማጣራት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የሰመጉ ሊቀ መንበር አቶ ቡዛየሁ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከመንግስት አካላት፣ ከተጎጂ ቤተሰቦችና ከሰልፈኞች መረጃ በማሰባሰብ ጉዳዩን በጥንቃቄ ለማጣራት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የሞቱትን ዜጎች ቁጥር ያወቅነው ቀብራቸው የተፈፀመ ሰዎችን መረጃ በማሰባሰብ ነው ያሉት የኦፌኮ ም/ፕሬዚዳንት አሁንም በየቦታው የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርት እየደረሰን በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል – ከትላንት በስቲያ ከመታሰራቸው እንደገለፁት፡፡
ፓርቲያቸው የሟቾች ትክክለኛ ቁጥር ታውቆ አስከሬናቸው በክብር እንዲያርፍ መጠየቁን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ አሁንም መንግስት ከወደመው ንብረት ባሻገር ለጠፋው ነፍስ ማሰብ አለበት ብለዋል፡፡ ኢዴፓ፣ መኢአድ እና ሠማያዊ ፓርቲ መንግሥት አንድ ዜጋ ህይወት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ተገንዝቦ የንብረት ውድመትን ብቻ ሳይሆን የሟቾችን ቁጥርና የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት በማጣራት ይፋ እንዲያደርግና ገዳዮችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ጉዳዩን በጥንቃቄ እያጣራ መሆኑን የጠቆሙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላ በበኩላቸው፤ የማጣራት ስራው ሲጠናቀቅ ሪፖርቱ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለማረጋጋት በመንግሥትና በተጎጂዎች መካከል ውይይት እንዲካሄድ የጠየቀ ሲሆን በግጭቱ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ሀዘን ገልፆ የሟች ቤተሰቦች ካሳ የሚያገኙበት መንገድ እንዲፈለግም ጠቁሟል፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲም በተመሳሳይ፤ በክልሉ የተከሰቱ ግጭቶች እንዲበርዱና በማስተር ፕላኑ ዙሪያ ሰላማዊ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡