የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ ትክክል ባይሆንም ሊደገፍ ይገባል! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ



ለሦስት ሳምንታት አልነበርኩም ከመረጃ ውጭ የሆንኩበት ስፍራ ነበርኩ፡፡ ሀገር ሰላም ብየ ሐሙስ ለታ ወደ አዲስ አበባ በምመለስበት ወቅት ገብረጉራቻ በወያኔ የአድማ በታኝና በተሸከርካሪያቸው ላይ መትረየስ በደቀኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተወጥራ ደረስን፡፡ ለካ መሰንበቻውን ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ኦሮሚያ ክልል ሲሉ በሚጠሩት የሀገራችን ክፍል ባሉ የዩኒቨርስቲ (የመካነ ትምህርት) እና የፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ታች አምና ተቀስቅሶ ብዙ ሳይቆይ ቀዝቅዞ እንደነበረው የአዲስ አበባ ከተማን ዐቢይ የማስፋፊያ አቅድን በመቃወም ቁጣቸውን በዐመፅ ሲገልጹ ሰንብተው ኖሮ ገብረ ጉራቻም የድርሻዋን ለመወጣት ስትሞክር ነው ወያኔ ይሄንን ኃይሉን ያፈሰሰው፡፡ ከአንድ ቀን በፊትም በዚሁ መንገድ ላይ ከገብረጉራቻ ብዙ በማትርቀው ሙከ ጡሪ ላይ ተማሪዎች ዐመፅ ቀስቅሰው መንገዱን ዘግተው በዚህ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ክፍላተ ሀገራት የሚወጡትንና የሚገቡትን በማገድና በማገት ቁጣቸውን ገልጸው እንደነበር የተሳፈርኩበት ተሸከርካሪ ሾፌር አጫወተኝ፡፡

አሽከርካሪው እንዳጫወተኝ በዚህ በሙከጡሪው ዐመፅ ላይ በዐመፀኞቹ የተፈጸመው ተግባር ትንሽ ደስ የማይልና በእንጭጩ መታረም ያለበት ተግባር ነው፡፡ በሁለት የግል የሀገር አቋራጭ ተሸከርካሪዎች አንደኛው የጎንደር ሌላኛው የባሕር ዳር መስታውቶቻቸው በዐመፀኞቹ ተሰባብሮባቸዋል፣ ዐመፀኞቹ አሽከርካሪዎቻቸው ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑትን ተሸከርካሪዎች እየለዩ እንዲያልፉ ሲያደርጉ ያልሆኑትን ግን አድማ በታኞቹና የመከላከያ አባላት በቦታው ደርሰው ሁኔታውን እስኪቆጣጠሩት ጊዜ ድረስ አግተው አቆይተዋቸው ነበር፡፡ ይህ እኔ የተሳፈርኩበት ተሸከርካሪ አሽከርካሪ ኦሮሞና ኦሮምኛም መናገር ይችል ስለነበር ኦሮምኛ በመናገራቸው እንዲያልፉ ከተደረጉት አንዱ ነበር፡፡ ሁኔታው በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ይህ ዐመፅና እየለዩ የሚያሳልፉትና አግተው የሚይዙት ነገር አዝማሚያ ያላማራቸውና ያስፈራቸው ተጓዦች እየወረዱ እግራቸው ወዳመራቸው በመሔድ በመሸሽ እራሳቸውን ከፈሩት ጥቃት ለማዳን ተገደው ነበር፡፡
የአዲስ አበባን ዐቢይ የማስፋፊያ አቅድ በመቃወም ለምን እንደሚቃወሙት ምክንያት አድርገው የሚጠቅሷቸው ለምሳሌ “ገበሬው ተገቢው ካሳ ሳይከፈለው ተፈናቅሎ ከንቱ እንዲቀር እያደረገው ስለሆነ፣ ባሕሉ ማንነቱ ወጉ ስለሚቀየር ስለሚጠፋ” ወዘተረፈ. የሚሏቸው ምክንያቶች የጭብጥ ችግር ቢኖርባቸውም እተደረጉ ያሉ ዐመፅ ቀመስ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከላይ የጠቀስኩት ዓይነት አደገኛ አዝማሚያ ባይኖርበት ኖሮ ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ ነበር፡፡

“የገበሬው መፈናቀል…” የተባለው በወያኔ የተሳሳተና ጎጂ የመሬት ሥሪት ሕግ መሠረት እየተፈናቀለ ያለው ገበሬው ብቻ ሳይሆን ከጥቂቶቹ ሀብታሞች በስተቀር ያለውን ሁሉንም ከተሜ ኢትዮጵያዊያንንም በሙሉ በመሆኑ ተቃውሞው መነሣት ካለበት ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸው ተጠቃሚና ባለቤት እንዳይሆኑ ያደረጋቸውን ሸፍጠኛ የመሬት ሥሪት መመሪያን እንጅ ከከተሜው የተለየ ገበሬውን ተጎጅ የሚያደርግ መመሪያ በሌለበት ሁኔታ ገበሬው… ብሎ መጮህ ብልህነት አይደለም፡፡

“የሕዝባችንን ባሕሉን ቋንቋውን ማንነቱን ወጉን ሥርዓቱን ስለሚቀይር…” የተባለው ደግሞ መርዘኛ አሽሙርና ሸፍጠኛ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱም ያንን የገበሬው የነበረ መሬት ከአገዛዙ ገዝተው መኖሪያ ቤቶችን ሠርተው የሚኖሩበት “ከኦሮሞ ተወላጆች በስተቀር!” ተብሎ ሳይሆን ኦሮሞዎችን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም እንጅ አውሮፓዊያን ወይም የሌላ ሀገር ሕዝቦች አይደሉምና፡፡ ከኦሮሞ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያን ደግሞ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሚጠራው የሀገራችን ክፍል ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ኑሮን የመመሥረት ሀብት የማፍራት ወዘተረፈ. ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑና “ከኦሮሞ ተወላጆች ውጪ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ በኦሮሚያ መሮር መሥራት ሀብት ማፍራት አይቻልም!” ተብሎ የታወጀ ባለመሆኑ ሊታወጅም ስለማይችል ቢታወጅም የደናቁርት ቅዠትና ጩኸት በመሆኑ ተፈጻሚነትና ተቀባይነት ሊኖረው ስለማይችል፡፡ “ከኦሮሞ ውጭ ላሉ ኢትዮጵያዊያን ብቻ” ተብሎ ታውጆ ቢሆን ኖሮ ግን ተቃውሞውን ከሚቀላቀሉ ዜጎች የመጀመሪያው እኔ በሆንኩ ነበር፡፡

እናም የአዲስ አበባን ዐቢይ የማስፋፊያ አቅድ በመቃወም የቀረበውን ጥያቄ ታከው የሚመጡ ምክንያቶች ብስለትና ማስተዋል የጎደላቸው በመሆናቸው ዐመፀኞቹ እነሱን ትተው “ያለፈቃዳችን ራስ ገዛዊ (ፌደራላዊ) ድንበራችን ያለመገሰስ ያለመገፋት ሕገ መንግሥታዊ መብት” የሚለውን ወያኔ የሰጣቸውን መብት ከማስጠበቅ የሚለውን ምክንያት ብቻ ቢጠቅሱ መልካም ይመስለኛል፡፡
ቁጣቸውን በዐመፅ እየገለጹ ያሉ ወገኖች ጥያቄያቸው ትክክል የሚሆንበት ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ የወያኔው ሕገ መንግሥት ያረጋገጠላቸው መብት ስለሆነ፡፡ ይህም ማለት ወያኔ ዘርንና ቋንቋን መሠረት ባደረገው የራስ ገዝ (ፌደራላዊ) የአሥተዳደር ሥርዓቱ ኦሮሚያ ብሎ ከልሎ ያስቀመጠላቸው የራስ ገዝ የአሥተዳደር ክልል አለ የዚህን ክልል ድንበር ያለ እነሱ ፈቃድና ይሁንታ ማንኛውም አካል እንዳይነካባቸው የመጠበቅ የመከላከል የወያኔ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፡፡

ወያኔ መቸም ደንቆሮ እንደመሆኑ የሚሠራውን ሥራ በግምት እንጅ በእውቀት ላይ ተመሥርቶ አይሠራምና ይሄንንና ሌሎች የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ በሀገር ላይ ከባባድ ኪሳራ እያደረሱ ያሉ በርካታ ችግሮችን ከመፈጠራቸው በፊት ሊከሰቱ እንደሚችሉ ገምቶ አስቀድሞ መፍጥሔ ስለማያበጅ በግምት በሚሠራቸው ሥራዎቹ ሁሌም ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡
ችግሮቹ ሲያጋጥሙም በጉልበት እንጅ በሕግ በሥርዓት መፍትሔ ለመስጠት አይሞክርም የዚህ ዕድል የለውምና፡፡ የሚለው ነገር መሆን ካለበት አንባገነናዊ በሆነ አሠራር በጉልበት ከማስፈጸም ሌላ አማራጭ የለውምና፡፡

አስቀድሞ ሀገራችንን ዘርንና ቋንቋን መሠረት ባደረገ አከላለል “የኦሮምያ ክልል ይሄ ነው” ብሎ በሚያውጅበት ወቅት የአዲስ አበባ የቆዳ ስፋት ለዘለዓለሙም ለመስፋት የሚገደድበት ሁኔታ እንደማይኖር በማሰብ “የአዲስ አበባ ከተማ የቆዳ ስፋት በስተሰሜን በስተደቡብ በስተምዕራብ በስተምሥራቅ ይሄንን ያህል እስኩዌር ኪሎ ሜትር (አራት ማዕዘናዊ ሽህ ጉዘት) ነው” ብሎ መደንገጉ ደንቆሮነቱን የሚያሳይ ስሕተት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በየ ዐሥር ዓመቱ የከተማዋን ዐቢይ አቅድ (ማስተር ፕላን) ከመከለስ በስተቀር ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ እስከ አሁን የከተማዋን የቆዳ ስፋት በተመለከተ ምንም ሊያደርግ ሳይችል የቀረው፡፡ ለዚህም ነው “ወያኔ ሀገር አይደለም ጎጥ ለማስተዳደር የሚያበቃ ጭንቅላት ችሎታና አቅም የለውም!” የምንለው፡፡ በሚከተለው የራስ ገዛዊ (ፌደራላዊ) የአሥተዳደር ሥርዓት ምክንያት መከለሉ ግድ ከሆነ ከተማዋ በማያቋርጥ የመስፋፋት የመለጠጥ ዕድገት ልታልፍ እንደምትችል በመገመት የቆዳ ስፋቷን አስቀድሞ ሰፋ አድርጎ መከለሉ ዐዋቂነትን አርቆ አሳቢነትን የሚጠይቅ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የገዥዎቻችን የማሰብ አቅም ብቃት ችሎታ ከዚህም በታች ስለሆነ ስሕተቶቹ እየተፈጠሩ ሀገርንና ሕዝብን ያከስራሉ እንጅ፡፡

እንግዲህ ያለ አቅማቸው ያለ ችሎታቸው ሥልጣን ለእነሱ ይገባ ዘንድ የሚያበቃ አንዳችም ነገር ሳይኖራቸው በኃይል ስለተቆጣጠሩት ብቻ በዓጽመ ርሥትነት ይዘው ሳይችሉበት በግምት በሚሠሩት ሥራ ሁሉ ሀገርና ሕዝብ እየከሰሩና በተደጋጋሚ እየታየም “ሀገርና ሕዝብ ዘለዓለማቸውን ሲከስሩ ይኑሩ እንጅ ስላቃተን ስላልቻልንበት ስላበላሸን ስላከሰርን… ሥልጣንን እንኩ ብለን ለሕዝብ አናስረክብም!” ባሉ ሥልጣንን የህልውና ጉዳይ አድርገው በሚመለከቱ ጨምድደው በያዙ ደናቁርት አንባገነኖች ነው ለ25 ዓመታት ሙሉ በእውር ድምብስ እየተገዛን የኖርነው ያለነውም፡፡

ወያኔ በሚጠቀምበት የራስ ገዛዊ (የፌደራላዊ) ሥርዓት የአዲስ አበባን ከተማ የማስፋት መብትና ሥልጣን የለውም፡፡ ይሄንን ማድረግ ከፈለገ በቅድሚያ ማድረግ የሚኖርበት ሁለት ዐበይት ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ነጥቦች የምጠቅሳቸው ወያኔ እነሱን የመጠቀም ዕድል አለው ማለቴ ሳይሆን እነኝህን መንገዶች መጠቀም ካለመቻሉ አንጻር ፖለቲካው (እምነተ አሥተዳደሩ) ምን ያህል የከሸፈ የከሰረ መሆኑን ከማሳት አንጻር ነው የምጠቅሳቸው፡-

የመጀመሪያው የኦሮሞን ሕዝብ ይሁንታና በጎ ፈቃድ ማግኘት ነበር፡፡ ዕያየነው እንዳለው በኃይል ዝም አሰኝቶ ካልሆነ በስተቀር ይህ ሊሆን የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ወያኔ ግን በፊተኛው ጊዜ ዐመፁን ተቆጣጥሮ ካበረደው በኋላ “ከሕዝቡ ጋር ተወያይቸ መግባባት ላይ ደርሻለሁ፣ ሕዝባዊ ይሁንታን አግኝቻለሁ…” ሲል መቆየቱ ይታወሳል፡፡ እውነቱ ግን የምናየው ነው የተቃውሞ ዐመፁ እንደ አዲስ ተቀስቅሶ የዜጎች ሕይዎት እየተቀጠፈበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን የሚያሳይ አይደለም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ይሄንን የብሔረሰብ አሰፋፈርን መሠረት ያደረገውን የፌደራል (የራስ ገዝ) የአሥተዳደር ሥርዓቱን መጣል መቅደድ መተው ብቻና ብቻ ናቸው፡፡ እነኝህን እስካላደረገ ጊዜ ድረስ አዲስ አበባን ኦሮሚያ ብሎ ወደሚጠራው የሀገራችን ክፍል ማስፋት በፍጹም በፍጹም አይችልም፡፡ መብት የለውም፡፡

ወያኔ ባለው ተፈጥሮ ምክንያት ሁለቱንም አማራጮች ሊጠቀም ሊያገኝ አይችልም፡፡ በመሆኑም እራሱ የሰጣቸውን መብት ለመጠበቅ መሥዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ተማሪዎችም ሆኑ “የሕዝቡ” ጥያቄ ከተቀስኩት ነጥብ አንጻር ትክክል ነው ማለት ነው፡፡ የሰጣቸውን መብት ስለጠየቁም ሊገደሉ ሊታሠሩ ሊንገላቱ አይገባም! ይሄንን ወንጀል እየፈጸሙ ያሉት በየ እርከኑ ያሉ የወያኔ የአሥተዳደር አካላት በአስቸኳይ ሊጠየቁና ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል!

የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ ተቃውሞ ትክክል የማይሆነው ደግሞ፡- ኢትዮጵያዊያን ነን ብለው እስካመኑና በሀገሪቱ ውስጥ እስካሉ ጊዜ ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ “መልማት” የእነሱም መልማት እንደሆነ በማሰብ የከተማዋን “መልማት” መስፋፋት ሊቃወሙት አይገባም ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄንን ከአንድ ሀገር ዜጎች የሚጠበቅ ቀናና በጎ አስተሳሰብ እንዳይይዙ እንዳያራምዱ ሁለት ማነቆዎች አንቀዋቸዋል፡፡

አንደኛው ወያኔ “መጀመሪያ አንተ ሰው ነህ እንደ ሰውነትህ ከሌሎች ሰዎች ጋር ዕኩል ነህ! ከሌሎቹ በልጠህ ወይም አንሰህ በሀገርህ ልትስተናገድ ልትታይ አይገባም! እንደዜጋ የምትቀበላቸውና የምትሰጣቸው መብቶችና ግዴታዎች አሉህ! እንደዜጋ ዕኩል መብት እኩል ግዴታ አለብህ!” ብሎ መሠረታዊውን ትክክለኛውንና ገንቢውን አስተሳሰብ መስበክ ማስተማር ማስጠናት ሲኖርበት ህልውናውንና ደህንነቱን ዕኩይ በሆነ መንገድ በብሔረሰቦች መለያየትና መከፋፈል ላይ የመሠረተ በመሆኑና የከፋፍለህ ግዛውን ሰይጣናዊ የአገዛዝ ዘይቤን የሚጠቀም በመሆኑ “መጀመሪያ አንተ ትግሬ ነህ፣ አንተ ኦሮሞ ነህ፣ አንተ ከንባታ ነህ… ከዚያ በኋላ ነው አንተ ኢትዮጵያዊ የምትሆነው” ብሎ ኢትዮጵያዊነትን በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲታይ በማድረጉ እንደምናየው እጅግ አሳፋሪ በሆነ መንገድ ሁሉም የጠባብነት ደዌና የፀረ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ ሰለባ በመሆናቸው በሚፈለገው ደረጃ አስፍተው ማሰብ እንዳይችሉ ስላደረጋቸው የአዲስ አበባን “እድገት ልማት” የራሳቸውም አድርገው እንዳያስቡና በጎ ምላሽ እንዳይሰጡት አደረጋቸው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ወያኔ “ኢትዮጵያዊነትን በአማራ ተጭናቹህት እንጅ ፈልጋቹህት መርጣቹህት የተቀበላቹህት አይደለም፡፡ የዚህ ሀገርና የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነት በመፈቃቀድ ላይ እንጅ በግዳጅ እንዲፈጠር መፍቀድ የለባቹህም!” እያለ የተገንጣይነት ስሜት በውስጣቸው ተኮትኩቶ እንዲዳብርና ጥላቻ እንዲያጎለብቱ ስላደረገ በእነዚህ ሁለት ማነቆዎች ስለተያዙ ነው፡፡
ዋናው ነጥብ “ለዚህች ሀገርና ለሕዝቧ ከብዙ አስገዳጅ ሁኔታዎች አንጻር አንድነት የሚጠቅም ነው ወይስ አይደለም?” የሚለው ነው እንጅ “በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ? ወይም በአስገዳጅ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ?” የሚለው አይደለም፡፡ ለአንድነታችን ፈተና የሆኑ ጉዳዮች ካሉ እነኝህን ችግሮች መቅረፍ የሁላችንም ተቀዳሚ ተግባር አድርጎ መሥራቱ ነው አንጅ መፍትሔው የተሸናፊዎች የማያዋጣና ለማንም የማይጠቅም የመገነጣጠል አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ይህ የመፍትሔ ሐሳብ አይደለም እራስን ማጥፋትን መምከር ነው፤ ጠላትነት ነው፤ ተሸናፊነት ነው፤ ደንቆሮነት ዕኩይነት ነው፤ ከአንድ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለኝ ብሎ ከሚያስብ ዜጋ የማይጠበቅ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው የጠላት አስተሳሰብና ተግባር ነው፤ የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የአሕያ አስተሳሰብ የወለደው ራስ ወዳድነት ነው፡፡

ዛሬ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ይህ ኋላቀር አስተሳሰብ በኃይል የመፈጸም አጋጣሚ ቢያገኝም እንኳን አይሠራም አያዋጣም፡፡ ይህ ዘመን አይደለምና በአንድ ሀገር ውስጥ በሚኖሩ ብሔረሰቦች መካከል ይቅርና በአንደኛው የዓለማችን ጫፍ ላይ ላሉ የሰው ልጆች የሰው ዘሮች በሌላኛው የዓለማችን ጫፍ ላይ ያሉት የሰው ዘሮች የግድ የሚመለከታቸው የሚያገባቸው የሚገዳቸው ዘመን የበሰለ የሠለጠነ አስተሳሰብ ላይ የተደረሰበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡

የጥፋት ኃይሎች ሀገርን ቆራርሰው እንደሚበሉት አንባሻ ወይም እንደ ፈራሽ ትዳር እንዲመለከቱ ያደረጋቸው ያለባቸው የአስተሳሰብ የአመለካከት ድህነትና ድንቁርናቸው ነው፡፡ ሀገር ማለት ግን አንባሻ አይደለችም የሚፈርስ እርባና የሌለው ትዳር ማለትም አይደለችም፡፡ ሀገር አንድ ሰው የሰውነት አካላቱ ለራሱ ማለትም አንደኛው የሰውነት አካሉ ለሌላኛው የሰውነት አካሉ ከሚሰጠው ትርጉም በላይ ወሳኝና ለህልውናውም አስፈላጊ የሆነበትን የአካል አንድነትና ውሕደት ማለት ናት፡፡ እናም አንዱ የሀገር ክፍል ለሌላኛው ያለው አስፈላነትና ወሳኝነት የዚህን ያህል ነው፡፡ እጅ ወይም እግር ወይም ሌላ የሰውነት አካል አልፈልግም ብሎ ቢቆረጥ ይሞታል ይበሰብሳል እንጅ ሕይዎት አይኖረውም፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው በተገነጠሉ ሀገራት ላይ ከአካለ ጎደሎነት የሚመጣ የአካለ ስንኩልነት የሚታየው፡፡ አካላቱ አንድ ካልሆኑ በስተቀር በተቆራጩም በተቆረጠበትም አካላት ላይ ቋሚ ጉዳት ወይም ችግር መታየቱ መከሰቱ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በሽተኛ ካልሆነ በስተቀር ይሄንን የሚፈልግ ጤነኛ አእምሮ ያለው ዜጋ ይኖራል ብሎ መገመት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

እናም እነኝህን ወገኖቻችን ወያኔ አማራን ለመጉዳት በማሰብ “ኢትዮጵያዊነትን በአማራ ተጭናቹህት እንጅ ፈልጋቹህት መርጣቹህት የተቀበላቹህት አይደለም፣ የዚህ ሀገርና የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት በመፈቃቀድ ላይ እንጅ በግዳጅ እንዲፈጠር መፍቀድ የለባቹህም፣ አማራ ጠላታቹህ ነው ከሀገራቹህ አስወጡ!” ምንትስ እያለ የሚሰብከው መርዘኛ ስብከቱ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ አቋም እንዲያንጸባርቁና እንዲላበሱ አድርጓቸው እያንዳንዱ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ክልሌ ብሎ ከሚጠራው ክልል ውጪ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ለሚሆነው ነገር ሁሉ ግድ የማይሰጠው የማይገደው እንዲሆን አድርጎታል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ የሚጠራው የሀገራችን ክፍል የኦሮሞ ተወላጆች እንደሚመስላቸውና እንደሚያስቡት የኦሮሞ አይደለምና ይሄንን ጥያቄያቸውን የምር አድርገው ይዘው ወያኔ በሌለ ጊዜም እንዳያነሡት አጥብቄ አደራ ልላቸው እወዳለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን ከላይ እንዳነሣሁት ወያኔ መብታቹህ ነው ብሏቹሀልና እጅ ሳትሰጡ በርትታቹህ ግፉበት በርቱ ማለትን እወዳለሁ፡፡
አሁንም ደግሜ ደጋግሜ አደራ የምላቹህ ነገር ቢኖር ስለፍትሕ ስለ መብት እየጮሀቹህ እንደገና ደግሞ እናንተው እራሳቹህ ፍትሕንና መብትን ነፋጊ ገፋፊ አሳዳጅ እንዳትሆኑ ነው፡፡ እናም እባካቹህ ለፍትሕና ርትእ ለመብት ታማኝ ኅሊና ሰብእናና ማንነት ይኑራቹህ፡፡ እሱ ካላቹህ ቅድመ አያቶቻቹህ እንዴትና መቸ በምን ሁኔታና በማን ሕዝብ ላይ ምን አድርገው ይሄንን መሬት እንደያዙትና እንደተስፋፉ እያወቃቹህ የኅሊና እምነታቹህን በመካድ ሀቅን ከውስጣቹህ ገላቹህ አስቀድሞ የመሬቱ ባለቤት የነበረውንና ለዚህም ማረጋገጫ ምስክር ክልላችን በምትሉት በሁሉም ቦታ በግራኝ አሕመድ እንዲፈራርሱ የተደረጉና ከመፍረስም የተረፉ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናትና ገዳማት ያሉትን ሕዝብ አሳፋሪ በሆነ ድርቅና እንደ ባዕድና እንግዳ ቆጥራቹህ “ከሀገራችን ውጡ! እንገነጠላለን!” ምንትስ እያላቹህ ግፍና በደል አትፈጽሙም፡፡

እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ በብዙዎቹ የኦሮሞ ተወላጆች ልኂቃን ግን ይሄንን የኅሊና ተጠያቂነትና እውነተኛ የፍትሕና የመብት ተቆርቋሪነትን ላይባቸው አልቻልኩምና ከባድ ሥጋት አለኝ፡፡ እውነታን ከመቀበል ይልቅ እጅግ አስገራሚና አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ለጥፋት ተልእኳቸው የሚረዳቸውን ልብ ወለድ ድርሰቶችን እያዘጋጁና እውነት አስመስለው እያወሩ ፍጹም ኃላፊነትና ተጠያቂነት በጎደለው መልኩ ሕዝብን ለማሳሳት የሚጥሩ የሞራል (የቅስም) የእምነት፣ የግብረገብ፣ የሥነምግባር ተጠያቂነት ጨርሶ የማይሰማቸው ጉድ ፍጥረቶች ናቸው፡፡

የኦሮሞ ተማሪዎችና ደጋፊዎቻቸው የዋህነትና አለማስተዋል ነው ወደምለው ነጥብ ስንሻገር ደግሞ፡- አዲስ አበባ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በከለለው ክልል ውስጥ እንደመሆኗ በዚህም ምክንያት እነሱ እንደሚያስቡት ከተማዋ የራሳቸው እንደመሆኗ በአዲስ አበባ መሬት ላይ የሚፈስ ሀብት የሚገነባ የሪል ስቴት (ተንቀሳቃሽ ያልሆነ) ግንባታ ሁሉ ማንሣት ወደሌላ ስፍራ መውሰድ ማንቀሳቀስ የሚቻል እንዳለመሆኑ ሀገራችንን ከእነዚህ አውሬዎች ነጻ ማውጣት እስከምንችልበት ጊዜ ድረስ የወያኔ ባለሥልጣናትና ተሟሳኝ ባለሀብቶች ከሀገርና ከሕዝብ የዘረፉትን ሀብት በሪል ስቴት (ተንቀሳቃሽ ባልሆነ) ግንባታ ሥራ ላይ ማዋላቸው የሚዘርፉትን የሀገርንና የሕዝብን ሀብት የተቻለንን ያህል ከእጃቸው ነጥቆ ከማስቀረት አንጻር ጥሩ ዘዴና አጋጣሚ መሆኑን፤ ይሄንን ማድረጋቸውንም በማበረታታት የዘረፉትን ሀብት ይዘውት እንዳይሔዱ ወደሌላ ስፍራ እንዳያሸሹ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ብልጠት መሆኑን በማሰብ አዲስ አበባ ላይም ሆነ በሌላ ቦታዎችም የሚሠሯቸውን ሥራዎች በበጎ ዐይን አለማየታቸው ነው፡፡

የወያኔ ባለሥልጣናት አሁን እንደ ድሮው አይደሉም፡፡ ቀድሞ መሬቱን በመሸጥ ነበር ዘረፋ የሚያኪያሒዱት የነበረው፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን እላዩ ላይ ብዙ ወጭ የፈሰሰባቸውን ትላልቅ ግንባታዎችን በመገንባት ስለሆነ ዘረፋውን እያኪያሔዱት ያለው ይህ ሀብት ደግሞ አንዳች ነገር ቢፈጠር ቀርቅበው ይዘውት ሊሔዱት የሚችሉት ባለመሆኑ የተዘረፈብንን ሀብት ከማስመለስ ከማስቀረት አኳያ ዝርፊያ እስካላቆሙ ጊዜ ድረስ ግንባታ ማኪያሔዳቸውን ባንጠላው መልካም ነው፡፡ እኔ ከተማውን ስንዘዋወር የወያኔን ባለሥልጣናት እየተጠሩ ይሄ የእከሌ ነው ይሄ ደግሞ የእከሊት ነው ሲሉኝ እንዴት ደስ ይለኛል መሰላቹህ፡፡ በመዘረፋችን አይደለም ደስ የሚለኝ፡፡ ነገር ግን ከዘረፉን ሀብት ይሄ የሚቀርልን በመሆኑ እንጅ፡፡ እኔ የምበሳጨው የማረው እከሌ የተባለ ባለሥልጣን አውሮፓ ወይም ኤዢያ እንዲህ ዓይነት ድርጅት ከፈተ፣ እንዲህ በሚባል ባንክ (ቤተ ንዋይ) ይሄንን የሚያክል ገንዘብ አስቀመጠ ሲባል ነው፡፡ ይሄንን ልናገኘው አንችልምና፡፡ እናም ወያኔን በተቻለን ፍጥነት ከሥልጣን ለማስወገድ እየጣርን እስከዚያው ድረስ ግን ይሄንን የተዘረፈን ሀብት የማስቀረት ዘዴን ማሰብ አንድ አማራጭ እንደሆነ ብንገነዘብ መልካም ይመስለኛል፡፡
በአንድነትና በተባበረ ክንድ ወያኔን ስለ ማስወገድ ስንነጋገር ከወራት በፊት “የስደት መንግሥት የችግራችን መፍትሔ ይሆናል ወይስ መንስኤ?” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፍ ከታች ያለውን ቁምነገር መናገሬ ይታወሳል፡፡ ዕያየነው ያለው ሁኔታም አስቀድሜ ከተናገርኩት የተለየ አልሆነም፡፡ ይህ ተቃውሞና ዐመፅ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሆኖ ነው የታየው እየተደረገም ያለው፡፡ ይህ መሆኑን ያልወደዱት ከልኂቃን እስከ ተራው ያሉት የዐመፁ ተዋናዮች ብልጠት ይሁን ጅልነት አላውቅም “ጥያቄያችንን ደግፋቹህ አብራቹህን ውጡ! ይሄንን የማታደርጉ ከሆነ ከወያኔ ለይተን አናያቹህም፣ሀገራችንን ለቃቹህ ውጡ!” ከሚለው ጀምሮ ለመግለጽ የሚቀፍ ነገርን በመናገር “… እናገርጋቹሀለን!” በማለት ኦሮሞ ባልሆኑት ወገኖች ላይ ከባድ የሥነ ልቡና ጫናና ወከባ በመፈጸም ከኦሮሞ ውጭ ያለውን በተለይ የአማራ ተወላጆችን በማስገደድ ይሄንን አጋጣሚ ከወያኔና ከራሳቸው አልፎ ሌላውም ሕዝብ የክልል አከላለልን፣ የባለቤትነት ጉዳይን ጨምሮ አሁን ባለንበት ሁኔታ “ከሁለትና ሦስት ብሔረሰብ ያልተወለደ ዜጋ በሌለበት ሁኔታ ብሔረሰብ ጎሳ የሚባሉት ነገሮች በተጨባጭ ህልውና አላቸው ወይ?” እስከሚለው ድረስ በርካታ አወዛጋቢ ነገር ያለበትን ጉዳይ ክልላቸውን ሌላው ሕዝብ ያለማወላወል ተቀብሎና አምኖ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ለማስገደድ አጋጣሚውን ከወያኔና ከራሳቸው ባለፈ ሕዝባዊ እውቅና ለማግኛ መጠቀሚያ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ማረጋገጥ አልቻልኩም እንጅ በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው ወገኖች እንዳሉም ተሰምቷል፡፡ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ይህ የተማሪዎች ጥያቄ የወያኔ ፀረ ኢትዮጵያ የጥፋት ስብከት ስኬት ማሳያ መሆኑን ነው፡፡

ብሔር ተኮር የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሙጥኝ ብለው ያሉ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ቡድኖች ከታች የገለጽኩትን ማድረግ እስካልቻሉ ጊዜ ድረስ የፈለገ ነገር ቢሆን ወያኔን በዐመፅ እንጥላለን ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ አሁንም ደግሜ ለማሳሰብ ያህል እንደገና አንሥቸዋለሁ የሚከተለውን ይመስል ነበር፡-

በግልጽ እንደምታዩት ወያኔ የፋሽስት ጣሊያንን “ከፋፍለህ ግዛ” የአገዛዝ ዘዴን እንዳለች ወስዶ በመጠቀም ሕዝቡን በብሔረሰብ በሃይማኖት በጾታ ሳይቀር ከፋፍሎ እጅግ ኃላፊነት በጎደለውና ድንቁርና በተሞላበት መልኩ እርስ በእርሱ እንዲተላለቅ ሊያደርጉት የሚችሉ ሰይጣናዊ ሴራዎችን በመጠንሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ እንዳይሆን፣ እንዳይተባበር፣ እንዲቂያቂያምና ተፈራርቶ በጎሪጥ እየተያየ እንዲኖር፣ ቀን እየተጠባበቀ እንዲኖር እንዳደረገው ይታወቃል፡፡

ወያኔ ይሄንንም ያደረገበት ምክንያት ሕዝቡ ሕዝባዊ ዐመፅን እንዳያስብ እንዳይሞክረው ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም እርስ በእርሱ የሚፈራራ በጎሪጥም እንዲተያይ የተደረገ ሕዝብ እየገዛው ያለው አንባገነናዊ አገዛዝ የቱንም ያህል አስከፊ፣ ፈላጭ ቆራጭ፣ አረመኔና ሊገላገለው የሚፈልግ ቢሆንም እንኳን እየመረረውም ቢሆን አርፎ ተሰብስቦ ይኖራል እንጅ ዐምፆ ለማስወገድ ሊሞክር አይደለም ሊያስብም አይፈልግም፡፡ በሆነ አጋጣሚ በአንድ አካባቢ ዐመፅ ቢቀሰቀስም እንኳ ሌላኛውም አካባቢ የዐመፁ ተካፋይ ተሳታፊ ተባባሪ አይሆንም፡፡ ይሄንንም ባለፈው ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሚጠራው የሀገራችን ክፍል ከተሞች ዐመፅ በተቀሰቀሰ ጊዜ ተመልክታቹህታል፡፡

የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዐመፁን ያልተቀላቀለበት ምክንያት የተቀረው የሀገሪቱ ሕዝብም ዐመፁን ተቀላቅሎ ይሄንን አስከፊ አንባገነን አገዛዝ በዐመፅ ቢያስወግደው “አገዛዙ በጠነሰሰው ሰይጣናዊ ክፉ ሴራ የእርስ በእርስ መተላለቅ ሊከሰት ይችላል!” ብሎ እጅግ ስለሚፈራ ይህ እንዳይሆን ከመፈለጉ አንጻር አገዛዙ ክፉና አረመኔ የተጸየፈው ቢሆንም “በዐመፁ ወያኔን አስወግጀ ወደባሰ ችግር ውስጥ ከምገባ ቢመረኝም ሰጥ ለበጥ ብየ እየተገዛሁ በሰላም ብኖር ነው የሚሻለኝ!” ብሎ እንዲያስብ ስላደረገው ነው፡፡ እያየነው ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ ነገም በሌላ ቦታ ተመሳሳይ ዐመፅ ቢቀሰቀስ ልናየው የምንችለው ተመሳሳዩን ነገር ነው፡፡

እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔ ካንገሸገሸው ካቅለሸለሸው ከበቃው የቆየ ሆኖ እያለ ዐምፆ እንዳይገላገለው ካደረጉት ምክንያቶች ሌላኛውና ዋነኛው ምክንያት በዘር በሃይማኖት ተከፋፍሎ እንዲፈራራ፣ ቀን እንዲጠባበቅ፣ እንዲቂያቂያም በመደረጉ ነው፡፡

የብሔር ተኮር ፖለቲካን እያቀነቀኑ ያሉ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ቡድኖች ደንበኛ የወያኔ ሰይጣናዊ ሴራ መጠቀሚያ ከመሆንና ለወያኔ ተጨማሪ ጉልበት አጋዥ ከመሆን ውጭ አእምሮ ልቡና ማስተዋል ኖሯቸው ይሄንን የወያኔን ሰይጣናዊ ሴራ በሚገባ ተረድተው ነቅተው ማርከሻውን ማክሸፊያውን መላ መንገድ ዘዴ ማመንጨት የሚችል ጭንቅላት የሌላቸው ሆኑ እንጅ መፍትሔው በጣም ቀላል ነበር፡፡

እሱም አንድነት ነው፡፡ ብሔር ተኮር የዘውግ ቡድኖች ዘውጌነትን ትተው አንድነት ቢፈጥሩ ወያኔ በሕዝቡ መሀል የዘራው የእርስ በእርስ ጥላቻ መፈራራትና መጠራጠር ሥጋት ይወገድና ሕዝቡ እንደ አንድ ልብ መካሪ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ አንድ ሐሳብ አንድ ግንባር ፈጥሮ በዐመፅ ወያኔን የሚገላገልበትን ዕድል መጠቀም እንዲችል በማብቃት ወያኔ የቀበረውን ሰዓት ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጅ ማምከን ማክሸፍ ይቻል ነበር፡፡

ይህንን የአንድነት ስሜት በሕዝቡ ልብ መፍጠር እስካልተቻለ ጊዜ ድረስ በሕዝባዊ ዐመፅ ወያኔ ይወገዳል ብሎ ማሰብ እጅግ ጅልነትና አለማሰብ አለማስተዋል፣ ያሉ ነገሮችን መረዳት አለመቻል ነው፡፡ እንዴትስ ነው በመንገዱ ላይ ስንት ዓይነት ፈንጅ ተቀብሮበት እያለ በዚያ መንገድ የተቀበረውን ፈንጅ የሚያውቀውን ሕዝብ ሒድበትና ነጻ ውጣ ልንል የምንችለው? አስቀድሞ ፈንጅውን ማምከንና መንገዱን ነጻ ማድረግ ግድ አይልም ወይ? አንድነትን ፈጥረን ያለበትን የእርስ በእርስ መፈራራት ካስወገድንለት ሕዝቡ መንገዱ ከፈንጅ ነጻ መሆኑን ያውቅና የማንንም ትዕዛዝ ሳይጠብቅ መሬት አንቀጥቅጥ ዐመፅ በማድረግ ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀብሮት ለመገላገል አንድ ቀንን እንኳን ማባከን የማይፈልግ ይሆናል፡፡

ይህ የወያኔ ፈንጅም ይመክንና መንገዱም ነጻ ይሆን ዘንድ የብሔር ተኮር የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ዘውግን በማቀንቀን የትጥቅ ትግልንም ሆነ ሰላማዊ ትግልን እያደረጉ ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የእምነተ አሥተዳደር ቡድኖች) ማስተላለፍ የምፈልገው ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር፡- ኧረ እንዲያው እባካቹህ! ከዛሬ ነገ በስላቹህ ነገሮችን ትረዱና መፍትሔው ገብቷቹህ ወደ ትክክለኛውና ሁሉንም ተጠቃሚ ወደሚያደርገው አስተሳሰብ ትመጣላቹህ ብለን ስናስብ እናንተ ግን እጅግ በሚገርምና ግራ በሚያጋባ መልኩ አድሮ ጥሬ እየሆናቹህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻ የሚወጣበትን ብሩሕና መልካም ቀን የሚያይበትን ዘመን እጅግ እያራቃቹህት ትገኛላቹህ፡፡

ኧረ ተው! እባካቹህ! እያራመዳቹህት ያለው አስተሳሰብ ወያኔን ጠቅሞ እድሜውን እያራዘመው እንደሆነ እንዴት መገንዘብ ይሳናቹሀል? በዚህ የምትቀጥሉና ወያኔን በማገዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ልብ እንዳይሆን የምታደርጉ ከሆነ ወያኔ ዘለዓለማዊ ሆነ ማለት አይደለም ወይ? ወያኔ እናንተንም በመጠቀም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ አንድ እንዳይሆን፣ እርስ በእርሱ እንዲቂያቂያም፣ እንዲጠራጠር፣ ቀን እንዲጠባበቅ አድርጎት እንዳለ በሌላ በአንዳች አጋጣሚ ቢወድቅ ቢወገድ እንኳን እያራመዳቹህት ያላቹህት ዓላማ አቋም አስተሳሰብ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ተላልቆ፣ ተጠፋፍቶ፣ ተፋጅቶ፣ እንዲያልቅ ያደርገዋል እንጅ እንዴት ሆኖ ነው ሰላምና መረጋጋት፣ ፍትሕና እኩልነት፣ ነጻነትና መብት ሊያገኝ ሊጎናጸፍ የሚያስችለው? ሰው እንዴት ዕድሜው እየገፋ ሲሔድ አይበስልም? እድሜ እኮ! ሰውን ይለውጣል ብዙ ያስተምራል አይደለም እንዴ? እንዴት ነው ታዲያ እናንተ ላይ ይሄ ሊሠራ ያልቻለው? እኔ እኮ ግራ ገባኝ!
ነበር ብየ የነበረው አሁንም ግራ እንደገባኝ ነው፡፡ ዘውጌዎቹ እስካልነቁ እስካልገባቸው ጊዜ ድረስም ግራ እንደገባኝ እቆያለሁ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
[email protected]