ካህን በካህን አፍ የሚመሰገነው መቼ ይሆን? መምህር ግርማ ወንድሙን የሚቃወሙ ካህናት ምቀኝነት እንጅ ሌላ ምክንያት የላቸውም
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲ አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር “ በተባለው ታላቅ የስነጽሁፍ ስራቸው ላይ በአገራችን ውስጥ በቤተክህነት ውስጥ የነበሩትን ችግሮች በስፋት ሽፋን ሰጥተውት ነበር። በዚህም መሠረት አብዛኛዎቹ ካህናት ለሹመትና ለስልጣን ያላቸውን ጉጉትና አይናቸው በገሃድ የሚመለከተውን ችግር እየካዱ እንዴት አንደሚያልፉት በተዋበና ለዛ ባለው አገላለጽ በጥሩ ገጸባሕርያት እየሳሉ አስነብበውናል። እኔ ላተኩር የፈለጉት ጉዳይ በመጽሃፉ ላይ ፊታውራሪ መሸሻ ተክለ አልፋ የተባለውን ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል አስመልክተው እቤታቸው ውስጥ ባዘጋጁት ግብዣ ላይ ከጠሯቸው ታዳሚዎች መካከል አንዱ በዛብህ ነበር። በዛብህም በዚህ በዓል ላይ ተገኝቶ አስደናቂ በሆነው ድምጹ የዘረፈው ቅኔ ታዳሚውን በሙሉ እጅግ አስደስቶ ታላቅ አድናቆትን አትርፎለት ነበር።ገጽ 80 ላይ እንዲህ ተጽፏል
“…ማታ አለቃ ክንፉ አንደልማዳቸው ዋዜማውን ዘርፈው ሲቀኙ በዛብህም ሲመራ ከቅኔው ይልቅ በበዛብህ ድምጽ ማማር ሰው ሁሉ ተገረመ…..። ካህን በካህን አፍ ተመስግኖ የማያወቀውን ያንለት ካህናቱ ሳይቀሩ በዛብህን አመሰገኑት።…..”
አቶ ሀዲስ አለማየሁ በመጽሃፋቸው እንዳመለከቱት ካህን በካህን አፍ ተመስግኖ የማያውቅ ከሆነ ከፍተኛ የሆነ ምቀኝነት በካህናት መካካል ነግሷል ማለት ነው። እንደሚታወቀው እግዚያብሔር የተለያየ ስጦታና በረከት ለተለያዩ ሰዎች ይሰጣል።ለአንዱ የዜማ ዕውቀት ሲሰጥ ለሌላው ደግሞ የስብከት ክህሎት ይሰጣል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለአንዱ የቅዳሴ አገልግሎት ችሎታ ሲሰጥ ለሌላው ደግሞ የጸበል ማዳን አገልግሎት ይሰጣል። ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው አንደተሰጠው ክህሎት አገልግሎት ቢሰጥ ለምዕመናን እጅግ በጣም የሚጠቅም ስራ ሊሰራ ይችላል። ሆኖም ከላይ እንደተመለከተው ጥሩ ስራ የሰራንና የተሳካለትን ማመስገንና ምሳሌውን መከተል ሲገባ ካህን ካህንንማመስገን እንደ ብርቅ የሚቆጠር ነገር ሆኗል።
አገራችን ውስጥ ከክርስትናው ዕምንት ባልተናነሰ ሁኔታ ህዝባችን ለመጽሃፍ ገላጭና ለጠጠር ጣይ ሲገብር የኖረና ክርስትናን ከተለያዩ የዲያቢሎስ ማምለኪያ ባህላዊ ዕምነቶች ጋር አጣምሮ የኖረ እንደሆነ የሚካድ አይደለም። ጠዋት ተነስቶ ቤተክርስቲያን ካስቀደሰና ቡራኬን ከተቀበለ በኋላ ከሰዓት በኋላ ቃልቻጋ ሄዶ ያፈነድዳል፤ ማታ ላይ ደግሞ የቡና ሲኒ ጭላጭ አንጋጦ ሲያስመለክትና የታረደ ከብት ሞራ ሲያስነብብ ያመሻል። በአገራችን ውስጥ ሌላም ሌላም ተዘርዝሮ የማያልቅ አምክኮተ ዲያቢሎስ ይፈጽማል። ይህ ለረጅም ዓመታት ከክርስትናው ጋር ተደርቦ የሚካሄድ የዲያቢሎስ አምልኮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወገኖቻችን ላይ የተለያየ በሽታና ቁራኛን አስከትሎ ተብትቦ ከመያዙም በላይ ከባርነት ባልተናነሰ ሁኔታ እስከ ዕለት ሞታቻው ድረስ እያሰቃየ ይገዛቸዋል።
ይህንን ህዝባችንን ከእግር እስከ ወርች የጠፈረን ችግር ተገንዝበው እግዚያብሔር በሰጣቸው ጸጋ ህዝቡን ከዲያብሎስ ቁራኛነት ለመገላገል ወስነው ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ወገኖቻችንን ከዲያቢሎስ ቁራኛ የገላገሉትን አባታችን መምህር ግርማ ወንድሙን በምቀኘነት የተነሳሱ ካህናት እነሱ ያልሰሩትንና ያቃታቸውን በመስራታቸው ለእስር እንዲበቁ አስደርገርዋቸዋል። ሲሆን የሚገባው እኝህን አባት ማገዝና እነሱም ተበረታተው ለቃልቻ ገባሪ የሆነውን ወገን ከችግሩ መርዳትና ምዕመናንን ክርስትና ላይ ሌላ ድሪቶ እንዳደርቡ አበክረው ማስተማር ነበር። እነዚህ በቅናት ያበዱ ካህናት ግን መምህር ግርማ ላይ የተለያየ የውሸት ወሬዎችን በማስወራት እየተፈታተኗቸው ይገኛሉ። በአገራችን ውስጥ ያሉት የተለያዩ የጸበል ስፍራዎች ዘንድ እየሄደ የሚፈወሰው ሰው እጅግ ከፈተኛ ቁጥር ያለው እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ በመምህር ግርማ ላይ በቅናት መንፈስ ተነሳስተው እኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ካህናት እነዚህን የጸበል ቦታዎችም የረሷቸው ይመስላል።
ምቀኝነታቸው እምነታቸውን ያጠፋባቸው ካህናት በጸበል ምክንያት የተፈወሱ ሰዎች ለእነሱ አዲስ የሆነባቸውና ሊያምኑ ያልቻሉት ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለካህናት ከሰጠው ጸጋ አንዱ በእርኩስ መንፈስ የተለከፉ ሰዎችን ማዳን መሆኑን ዘንግተው ይሆን? በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ መምህር ግርማ ወንድሙ አገልግሎታቸው ሰምሮላቸው በአገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ አገሮች የሚሰጡት የፈውስ አገልግልት እየተስፋፋ ሲመጣ እንዲሁም አገልግሎታቸው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የወጭ አገር ዜጎችንም መርዳት ሲጀምሩ ምቀኞቹ ካህናት ስም የማጥፋት ዘመቻቸውን አጠናክረው በመቀጠል በሃሰት መምህር ግርማ እንዲታሰሩ አስደርገዋቸዋል። መምህር ግርማ እውነተኛ የወንጌል አርበኛ ስለሆኑና የምቀኞችን ተንኮልና አመጣጥ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ መታሰራቸውን እንደ በረከት እንጅ እንደ ጉዳት እንደማቆጥሩት ለመገመት አያዳግትም። ይህንንም ለማረጋገጥ የሰጧቸውን ትምህርቶች መከታተል ይቻላል። መምህር ግርማ ከአሁን በፊትም የተለያዩ ፈታናዎችንና መከራዎችን አሳልፈዋል።ይህንንም እንደሚያሳልፉት አይጠረጠርም።
ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ ካህናት መምህር ግርማ የሚያካሂዱትን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ተገንዝበው አብረዋቸው የቆሙ አልታጡም። ከነዚህም መካከል የካናዳ፣ አውስትራሊያና እየሩሳሌም ጳጳስ የሆኑት አቡነ መቃሪዮስ አንዱ ናቸው። እኝህ አባት ለእውነተኛ ክርስትና ተልዕኮ የተጠሩና በመሆናቸው ለአገርም ሆነ ለሕዝብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህም መሠረት መምህር ግርማ ወንድሙ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በእየሩሳሌም ከተማ ተገኝተው በሰጡት ትምህርትና የፈውስ አገልግሎት ላይ አቡነ መቃሪዮስ ተገኝተው ቡራኬ ሰጠተዋል። መምህር ግርማ በእየሩሳሌም ያደረጉትን አገልግሎት እዚህ ላይ ይመልከቱ።
ከአንድ ታዛቢ ምዕመን፣ ዋሽንግተን ዲሲ
https://www.youtube.com/watch?v=JyJxGGUkqFY