የዜጎችን የፍትህ ጥያቄ በሀይል ለማፈን መጣር ስርዓቱ ለህዝብ ያለውን ንቀት አመላካች ነው! ድምፃችን ይሰማ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ድምፃችን ይሰማ
#OromoProtest #EthioMuslims #EthioMuslimPeacefulStruggle
የዜጎችን የፍትህ ጥያቄ በሀይል ለማፈን መጣር ስርዓቱ ለህዝብ ያለውን ንቀት አመላካች ነው!
ዘላቂ መፍትሄው መንግስት የህዝብን ድምፅ መስማቱ ነው!
ሐሙስ ህዳር 30/2008
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የፍትህ እና የሀይማኖት ነጻነት ጥያቄዎች በማንሳት እንቅስቃሴ ከጀመርን ይኸው ድፍን አራት አመት እየሞላን ነው። በእነዚህ መንግስታዊ አምባገነንነትን፣ ለሀገር እና ለህዝብ ደንታ ቢስነትን፣ እንዲሁም ጭካኔን በጉልህ ባንጸባረቁ ፈታኝ ዓመታት ሙስሊሙ የተለያዩ ሰላማዊ ኣካሄዶችን በመጠቀም የፍትህን አስፈላጊነት ለመንግትም ሆነ ለአገሪቷ ዜጎች ኣሳይቷል። በዚህም ይህን አልህ አስጨራሽ እና ከፍተኛ መስዋእትነት የሚጠይቅ ሰላማዊ የትግል መንገድ ለአገራችን እና ህዝቦቿ ያለን ፍቅር በመግለጽ፣ ስርዓቱ ህዝባዊ ጥያቄዎችን በሃይል ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ በሰላማዊ መንገድ አንዲፈታ፣ የዜጎችን ብሶት ዞር ብሎ መመልከት እንደሚገባውም እያሳስብን ቆይተናል።
በአንፃሩ ደግሞ በእነዚህ ባሳለፍናቸው አራት አመታት ያየናቸው ሁለት መሰረታዊ የመንግስት ባህሪዎች አሉ፡፡ አንዱ ‹‹የማውቅላችሁ እኔ ነኝ!›› የሚል ግትር ባህሪው ነው፡፡ አዎን! ‹‹ምን ዓይነት ሀይማኖት መከተል እንዳለባችሁ የማውቅላችሁ እኔ ነኝ!››፣ ‹‹መጅሊስን ማን እንደሚመራው የምወስነውና በቀበሌ የምመርጥላችሁ እኔ ነኝ!››፣ ‹‹የመስጊድ ኢማሞቻችሁንም (ባስቀመጥኳቸው የመጅሊስ ሰዎች) የምመርጥላችሁ እኔ ነኝ!›› የሚሉ እና የመሳሰሉ በርካታ የግዳጅ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ሁለተኛው የግትርነት ባህሪው ደግሞ ‹‹የምላችሁን ካልተቀበላችሁ በሀይልና በእስር እንድትቀበሉ አደርጋለሁ!›› የሚለው ባህሪው ነው፡፡
እንደ ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ሁሉ በአገሪቱ የሚገኙ ህዝቦች፣ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች የፍትህ እና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን ባነሱ ቁጥር መንግስት በሃይል ለማስቆም የሚያደርገው ሂደት አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለበትን ሁኔታ እናያለን። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ የፍትህና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎችን ተከትሎ እየተወሰዱ ያሉት የሃይል አርምጃዎች አገሪቱ ፈርማ ያፀደቀቻቸዉን አለም አቀፍ ስምምነቶች እና የህጎች የበላይ የሆነውን የአገሪቱን ህገ-መንግስት የሚጥሱ ናቸው። አገር ማለት ከምንም በፊት ህዝብ ነውና ህዝቦች ለሚያነሷቸው የሃይማኖትም ሆነ ሌሎች የሰብአዊ መብት ተማጽኖዎች ፍትሃዊና ህጋዊ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው። መንግስት ‹‹በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የጣለው ብሄራዊ ጭቆና ይወገድ!›› እያልን፣ ፍትህን ሽተው አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ አየተፈጸመ ያለው የሀይል እርምጃም በአስቸኳይ ሊቆም ይግባል። በየአቅጣጫው ያሉ የመብት ረገጣዎች ፍትሃዊ የሆነ ምላሽ ያሻቸዋል።
መፍትሄ የሚሆነው የህዝብን ድምፅ ማዳመጥና ምላሽም መስጠት ነው፡፡ በመንግስት ባህሪ ምክንያት በህዝብና በመንግሰት መካከል ሊኖሩ የሚገባቸው በርካታ ድልድዮች ተሰብረዋል፡፡ በህዝብና በመንግስት መካከል ድርብርብ መጋረጃዎች ተጋርደዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ‹‹የማውቅላችሁ እኔ ነኝ! ወደዳችሁም ጠላችሁም የምላችሁን ትቀበላላችሁ!›› በሚለው ባህሪው ነው፡፡ ይህንን የተሰባበረ ድልድይ በሀይል መጠገን አይቻልም፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎች በድርቅ ታስረው የድረሱልን ጥሪ በሚያሰሙበት ወቅት፣ በርካታ የአለም ሚዲያዎችና የእርዳታ ድርጅቶች ጩኸት እያሰሙ ባለንበት ሰአት ህዝብን ከማዳመጥ ይልቅ የሀይል እርምጃን እንደመፍትሄ ማየት በቁስል ላይ ጨው እንደመጨመር ነው፡፡ መንግስት ጉልበትን እንደመፍትሄ ቢቆጥረው እንኳን በህዝብ ልቦና ውስጥ ያለውን ቁጭትና ምሬት ሊያስወግደው አይችልም፡፡
ፍትህ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቀለም፣ ክልል እና ሃብት የማይገድባት የሰብዓዊነት የጋራ ሃብታችን በመሆኗ ስለ ፍትህ በአንድነት በጋራ ልንቆም ይገባል። ይህ እንዳለ ሆኖ እውነተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ከአላህ (ሱ.ወ) ብቻ የሚገኝ በመሆኑ በዚህ የፈተና ወቅት እውነተኛን መመለስ ወደእርሱው ልንመለስ ይገባል። በላያችን ላይ የተጫነው ግፍ እንዲራገፍ፣ እኛንም ዘላለም ለፍትህ ቋሚዎች ያደርገን ዘንድ ፈጣሪያችንን እንማጸነው!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
