የዲሲ ማርያም ቤተክርስቲያን የባለ አደራዎች ቦርድ መግለጫ አወጣ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ የምትገኘው ርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሕጋዊ የባለ አደራዎች ቦርድ ህዳር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. (ዲሲምበር 6, 2015) ጠቅላላ የአባላት ስብሰባ አካሂዷል። ይህም ስብሰባ በቤተክርስቲያኗ መተዳዳሪያ ደንብ አንቀፅ 10 ቁጥር 11፣ ሠ መሠረት የተካሄደና ከ1/3 በላይ አባላት የተሳተፉበትና ምልዓተ ጉባዔ የተሟላበት ነበር። በዚህ ወሳኝ ስብሰባ ላይ በርካታ አባል ምዕመናን ንቁ ተሳትፎ ያሳዩ ከመሆኑም በላይ ቤተክርስቲያኒቷ በአሁን ሰዓት የገጠማትን ፈተና አስመልክቶ በጥልቅና በስፋት ነጻና ግልጽ ውይይት ማካሄዳቸውን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በዚህም መሠረት የቤተክርስቲያኒቷ አባላት እንዲያስተዳድሯቸው ከመረጧቸው የባለ አደራዎች ቦርድ ጋር አብረው መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበትና በቦርዱም ላይ ያላቸውን አመኔታ ያረጋገጡበትም አንደነበር ተገልጾልናል።
በሌላ በኩል ደግሞ በመምህር ተስፋዬ መቆያ፣ ቄስ ዘላለም አንተነህና ቄስ አብርሃም ሀ/ስ አዝማችነትና በአቶ አዲሱ አበበና አቶ ታደለ ገብረ ወልድ አጋፋሪነት ከተለያየ ቦታ ተለቃቅመው ለጥፋት የተሰበሰቡት የአባ መላኩ (ፋኑኤል) ተላላኪዎች የባለ አደራዎች ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የመጡትን አባላት ከስብሰባ አዳራሽ አጠገብ አድፍጠው በመጠበቅ የስድብ ናዳ በማወረድ እንዲሁም ፎቶግራፎችና ቪዲዮ በማንሳት ለማስፈራራትና ለማሸማቀቅና ያደረጉት መኩራ በአሳፋሪ ሁኔታ እንደከሸፈባቸው ተገልጾልናል። ስብሰባው ባለ 17 ነጥቦች ውሳኔ አስተላልፎ፣ ቦርዱ በዶክተር አክሊሉ ፊታውራሪነት ቤተክርስቲያኗን በህገ ወጥ ሁኔታና በማን አለብኝነት የተቆጣጠረውን አካል በፍርድ ቤት ክስ መስርቶ የአባላትን መብት ለማስከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ከዚህም በተጨማሪ የአገልግሎት ዘመናቸው ያለቀ አባላትን የሚተኩ አዲስ የቦርድ አባላትን የሚያስመርጡ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላትንም መርጧል።
ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያምን ቤተክርስቲያንን “ከእናት ቤተክርስቲያን እናዋህዳለን” በሚል በማር በተለወሰ መርዝ ቤተክርስቲያኒቷን በአባ መላኩ በኩል ለወያኔ አገዛዝ አሳልፎ ለመስጠት የተሸረበው ተንኮል በረቀቀ ሁኔታ በመካሄድ ላይ አንደሚገኝና ፍጻሜ ላይም እንደተቃረበ ጥቆማ ደርሶናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የወያኔው ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ እንደሚገኙና የእሳቸው ተላላኪዎች ከሆኑት ከነ መምህር ተስፋዬ መቆያ፣ ቄስ አብርሃም ሀ/ስ፣ ቄስ ዘላላም አንተነህ፣ ቄስ ኃይሉ ዘለቀ፣ ቄስ መጠኑና ሌሎችም ጋር ድብቅ ስብሰባዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኙና ቤተክርስቲያኗን በወያኔ አገዛዝ ስር ተጠቃላ የምትገባበትን ሁኔታዎች በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እየመጡ ነው። አንዳንድ ነባር የቤተክርስቲያኗ አባላት እንዴት ዶክተር አክሊሉ ህብቴን የመሰሉ በትምህርትና በዕድሜ የበለጸጉ አዛውንት ለእንደዚህ ዓይነት ወራዳና አሳፋሪ ድርጊት መሳሪያ ሊሆኑ ቻሉ እያሉ በመገረም ሲጠይቁ ሌሎች ደግሞ ዶክተር አክሊሉ እዚህ አዘቅት ውስጥ የገቡበት ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ጊዜ አገራቸው ላይ በድናቸው እንዲቀበር ለወያኔ የሚያደርጉት መለማመጥና መሞዳሞድ ነው የሚሉም አሉ።
የቤተክርስቲያኗ የባለ አደራዎች ቦርድ ያወጣውን መግለጫ ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። ከባለአደራዎች ቦርድ የተሰጠ መግለጫ