ከኦነግና ኦነጋውያን ጋር ሰልፍ ስለመውጣት? Achamyeleh Tamiru
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከኦነግና ኦነጋውያን ጋር ሰልፍ ስለመውጣት?
ኦነግና ኦነጋውያንን ወያኔንና የወያኔን ፖሊሲ ሲተቹ ስመለከት ይገርመኛል! ኦነግም ወያኔም አንድ ጡት የጠቡና ዛሬም የሚጠቡ የኢትዮጵያና የአማራ ጥላቻ ውላጆች የሆኑ የአንድ «ርዕዮተ አለም» መንትያ ልጆች ናቸው። የሁለቱ ልዩነት ወያኔ መሰሪነቱን አሟጦ በመጠቀም ለስልጣን ቋምጦ ሲቅበዘበዝ የነበረውን ኦነግን እንደ ባትሪ ድንጋይ ተጠቅሞ ከስልጣኑ አባርሮ በብቸኝነት ስልጣን ላይ መሆኑና ኦነግ ከስልጣን ውጭ መሆኑ ብቻ ነው። ወያኔና ኦነግን ከስልጣን ውጭ የሚለያቸው አንዳች ነገር የለም። በርግጥ ኦነግ ስልጣን ላይ ባይኖርም የኦነግ መንፈስ ስልጣን ላይ ነው።
ዛሬ ወያኔ ኢትዮጵያውያንን የሚያጋጭበትን የጠብ ሰነድ ወይንም እነሱ ህገ መንግስት የሚሉትን «የሽግግር መንግስት ቻርተር» ከወያኔ በላይ ድምጽ እየሰጠ ያጸደቀውና ወዲያም በተግባር አውሎ አማራን ለመጨፍጨፍ የተጠቀመበት ኦነግ ራሱ ነው። ልብ ብለን አስተውለንም ከሆነ ኦነግ ወያኔን እየጠየቀ ያለውም «የሽግግር መንግስቱ ቻርተር» ወይንም ዛሬ ህገ መንግስት የሆነውን ድርሳን ወያኔ እንዲያከብር ነው። ኦነግ ወያኔን እየጠየቀ ያለው የማሻሻያ ወይንም የreform ጥያቄም አይደለም። እንዴውም የወያኔ ህገ መንግስት አንድም አንቀጽ እንዳይቀየር ከወያኔ በላይ የሚታገለው ኦነግ ነው። ይህንን ኦነግ ነው እንግዲህ የወያኔ ተቃዋሚ አድርገነው «አብረንህ እንታገል» የምንለው።
ለኢትዮጵያ በተለይም ለአማራ ህዝብ ከኦነግ ጋር መሰለፍ ከወያኔ ጋር ከመሰለፍ በላይ የባሰ ጥፋት ነው። ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ ከሚያወራርደው ሂሳብ በላይ ኦነግ ገና ያልተወራረደ ብዙ ሂሳብ አለው። ህጻናትና ወጣቶች «ፊንፊኔ ኬኛ፤ ቡራዩ ኬኛ፤ ሰበታ ኬኛ፤ ወዘተ» እያሉ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው መብት ቢሆንም «Ethiopia out of Oromoa» የሚለው የኦነጋውያን የፖለቲካ ትግል ስር ሰድዶ ፍሬ ማፍራቱን እንደታዘብን ግን ሳንናገር አናልፍም።
የወያኔ የግፍ ዘመን እንዲረዝም የኦነግን ያህል ሚና የተጫወተና ለወያኔ ውለታ የዋለ የፖለቲካ ድርጅት የለም። ይህ ድርጅት ወያኔን ለመጣል የሚደረግን የህብረት ትግል ሁሉ የወያኔን የግፍ ዘመን በሚያራዝም የጥላቻ «ትንተና» እየመነዘረ ወያኔን ሲያፈረጥምና የአንድነት ትግሉን ደግሞ ሲያኮሰምን የኖረ ድርጀት ነው። ኦነግ ትልቁ የኦሮሞ ህዝብ እንደ ትልቅነቱ በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ ለኢትዮጵያ አለኝታ ሆኖ ሲጫዎት የነበረውን ሚና በማሳጣት ኢትዮጵያን ያለ ኦሮሞ ህዝብ ተከላከይነት ታሪኳን ለሚያወድሙና ዘርፈዋት «በራቸውን ለመዝጋት» ለተቃረቡ ወያኔዎች በማስረከብ ለወያኔ ወደር የማይገኝለት ውለታ የዋለ የጥላቻ ማህበር ነው።
የኦሮሞ ልጆችን ሞትና የኦሮሞ ገበሬዎችን መፈናቀል በሰላማዊ ሰልፍ መቃወም የሚፈልግ ማንም ኢትዮጵያዊ ኦነግ በጠራው ሰልፍ መገኘት የለበትም። ኦነግና ወያኔ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ስለሆኑ የወያኔን ወንበር ኦነግ ቢይዝ ኖሮ ወያኔ የኦሮሞ ልጆችን እንደገደለው ኦነግም ሊቃወሙት የወጡትን በግፍ መግደሉ ስለማይቀርና ይህንንም በተግባር ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ሰላማዊ ሰልፍ ሳይወጡ አገር ሰላም ብለው ቤታቸው ተኝተው የነበሩ ንጹሀ ህጻናትና ነፍሰ ጡር እናቶችን አማራ ስለሆኑ ብቻ በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በባሌ፣ በጉጂ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ጭካኔውን ስላሳየን ዛሬ ንጹሀን የሚገድሉትን ህሊና ኑሮት የሚያወግዝበት የሞራል የበላይነት ስለሌለው ከኦነግ ጋር ሰልፍ ወጥቶ ወያኔን ማውገዝና ከኦነግ ጎን ተሰልፎ የንጹሀንን መገደል መቃወም ሞራላዊ አይደለም።
ከኦነግ ጋር የንጹሀንን መገደል ለመቃወም በአንድ መድረክ መገኘት አርባጉጉና በደኖ በተጨፈጨፉት አማሮች ደምና አጥንት መነገድ ነው። በወያኔ ልዩ ሀይል የተገደሉ የንጹሀንን ሞት ለመዘከርና የድሀ ገበሬዎችን መፈናቀል ለሚቃወም «Ethiopia out of Oromoa» ከሚል የጥላቻ ቡድን ጋር ለመሰለፍ መሞከርም በሞቱት መሳለቅ ነው። የኦሮሞ ልጆችን ሞትንም ሆነ የሌሎች ንጹሀን ሞት መነቀፍ ያለበት በንጹሀን ብቻ እንጂ የአማራ ደም በጠማው ኦነግና ክርስቲያኖችን በሜንጫ ለመቅላት ሜንጫቸውን ስለው ቀን ከሚጠብቁ አራጆች ጋር ህዝብረት በመፍጠር መሆን የለበትም። የኦሮሞ የልጆችን ሞትም ሆነ የኦሮሞ ገበሬዎችን መፈናቀል ንጹህ የሆነ ሁሉ የራሱን ፕሮግራም አውጥት በሚፈልገው መስሪያ ቤት ፊትለፊትና አደባባይ ተገኝቶ ተቃውሞውን መግለጽ ይችላል። ይህን የማድረግ ሰብዓዊም ሞራላዊም ግዴታ አለበት። በአማራ ደም እጁ ከቦካው ከኦነግና ኦነጋውያን ጋር የሚደረግ ጉድኝት ግን የወያኔን የግፍ ዘመን ያራዝምና ትዝብትም ላይ ይጥል እንደሆን እንጂ ለጸረ ወያኔ ትግሉ የሚፈደው አንዳችም ነገር የለውም።