ድል ‹‹እምቢ!›› ማለት መቻል ነው! ድል ለጭቆና እጅ አለመስጠት ነው! ድምፃችን ይሰማ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ድምፃችን ይሰማ

ድል ‹‹እምቢ!›› ማለት መቻል ነው!

ድል ለጭቆና እጅ አለመስጠት ነው!

የአላህ (ሱ.ወ) የምንዳ ሚዛን ጥረትን እንጂ መዳረሻን ያማከለ አይደለም!!!

የመንግስትን ረጃጅም እጆች በሀይማኖታዊ ጉዳዮቻችን ጣልቃ ከመግባት ተቆጥበው አያውቁም ነበር፡፡

በሀምሌ 2003 እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች የእምነት አስተሳሰብን ወደመምረጥና ወደማጥመቅ እርከን ሲሸጋገሩ፣ ይህን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊት መቃወም የአክራሪነት ተቀጥላ ሲያስለጥፍ፣ የህዝብ ሀብት የሆኑት መሳጂድና መድረሳዎች የመንግስትን እኩይ አላማ ለሚያስፈፅሙ አካላት በአደራ ሲበረከትላቸው ነበር የዚህ እኩይ ዓላማን ድምር ውጤት የሚያደርሰውን ጉዳት የተረዳው የኢትዮጵያ ሙስሊም እምነቱንና የእምነት ተቋሙን ለመጠበቅ በሰላማዊ መንገድ ትግል የጀመረው፡፡

ይህ ጭቆና የወለደው የመብት ማስከበር የትግል ሂደት እነሆ አራተኛ አመቱ እየተቃረበ ነው፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሰል የሰላማዊ ትግል ተሞክሮ ባለመኖሩ እነዚህ የትግል አመታት ፈር ቀዳጅና ብዙ የተማርንባቸው ነበሩ፡፡

በትግል ሂደት ውስጥ ከባዱ ነገር ትግልን ለመጀመር የሚያስችለውን ብርታትና ወኔ ማግኘት እንጂ ድል ማድረግ አይደለም፡፡ ድል ሂደት አንጂ መዳረሻ አይደለም፡፡ ይህ ረጅም ሂደት ደግሞ የሚጀምረው ጭቆናን እምቢ የሚል ወኔ መላበስ በቻልንበት ቅፅበት ነው፡፡ ድል ‹‹እምቢ!›› ማለት መቻል ነው! ድል ለጭቆና እጅ አለመስጠት ነው!

ድል የበደል ሸለቆ ስር ለመኖር ባለመፍቀድ የነፃነት መዳረሻ ተራራውን መውጣት መጀመር ነው! ድል የተጫነብህን የባርነት ቀንበር ተሸክሞ ለመኖር አለመፍቀድ ነው!የአላህን (ሱ.ወ) ውዴታ በመሻት የማህበረሰቡን ተጨባጭ ለመቀየር የሚታገል የዘወትር ትኩረቱ በትግሉ ሂደት እንጂ በመዳረሻው አይደለም፡፡ በትግል ሂደት ውስጥ በርካታ ስኬቶች ይገኛሉ፡፡

እነዚህን ስኬቶች በተገቢው መልኩ በመጠቀም ወደ መዳረሻው የሚያደርስውን መንገድ ለመደልደል ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ድል በትግል ሂደት የሚገኙ ስኬቶች ድምር ውጤት በመሆኑ በሂደቱ የሚገኙ ስኬቶችን የማህበረሰባችንን ንቃተ ህሊና በሚያጎለብትና ተጨባጩን በሚቀይር መልኩ መጠቀም፣ የጭቆናን በር ለመዝጋት ማዋል፣ ወኔና ብርታታችን እንዳይደበዝዝ የትግል ስንቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የአላህ (ሱ.ወ) የምንዳ ሚዛን ጥረትን እንጂ መዳረሻን ያማከለ አይደለም፡፡ ታላቁ ነቢይ ኢብራሂም ሰላም በርሳቸው ይሁንና በወቅታቸው የነበረውን ጣዖት አምልኮ ባለመቀበላቸው ችግርን “አይተዋል፡፡ ግና አልተሸነፉም፡፡ በደልን አልተቀበሉም፡፡ ይልቁንም በሐቅ መንገድ ላይ በእምቢተኝነት ጸኑ፡፡ እምቢታቸውን ለመስነር በዳዮች እሳት ውስጥ ጣሏቸው፡፡

ውጤቱ ግን መቃጠል ሳይሆን በበደል ሐይሎች ላይ የበላይነትን መጎናጸፍ ሆነ፡፡ ቁርኣን በሱረቱል ቡሩጅ የጠቀሳቸውንና በእምነታቸው ሳቢያ ብቻ ጉድጓድ ተቆፍሮ የሞትን ጽዋ እንዲቀምሱ የተደረጉትን የ‹‹አስሐቡል ኡኽዱድ›› (የጉድጓዱ ባለቤቶች) ሰዎች እናስታውስ፡፡ በደልን ታገሉ፡፡ ‹‹መንፈሳዊ ውርደትን አንቀበልም!›› ሲሉም በእምቢተኝነታቸው ጸኑ፡፡ በእምቢታቸው እንደጸኑ የሞትን ጽዋ ቀመሱ፡፡

እነሱም ቢሆኑ ግን በቁርአኑ የተወሱት፣ ዝንተዓለም ሲወሱም የሚኖሩት በስኬት እና በበላይነት ስሜት እንጂ በተሸናፊነት ሆኖ አናገኘውም፡፡ ድል በቁሳዊ መለኪያዎች ብቻ የሚሰፈር ሆኖ አያውቅም፡፡ ለእኛ ደግሞ በጎና መልካም ተነሳሽነትን ከነብያዊ ፈለግ ጋር አዋህዶ ጥረትና ልፋት ማድረግ፣ እንዲሁም አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም በትግል ሂደት ቋሚ መርሆቻችን ናቸው፤ ድልም በመዳረሻ ሳይሆን የትግል ሂደት መሰረት በሆኑት በእነዚህ መርሆዎች ይተረጎማልና!!!

ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
Image