ምሁር ነን የሚሉ ክፍሎች በጎሳና በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የሕዝብን መልካም እሴቶች እየናዱት ነው:: (ምንሊክ ሳልሳዊ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) – ጎራ ለይቶ እሳት መቆስቆስ ለማንም አይበጅም፡፡ በፖለቲካው መንደር ውስጥ የነገሡት ጥላቻዎች፣ አሽሙሮች፣ ሐሜቶችና መፍትሔ አልባ ቧልቶች ለአገራችን አይበጁም፡፡ ከፖለቲካዊ ሥልጣን በላይ አገር ትቅደም፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡ በአገር ስም፣ በሕዝብ ስም፣ በዲሞክራሲ ስም መቀለድ ይብቃ፡፡ አንድ ትልቅ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ አለ::በኢትዮጵያ የፈለገውን ያህል የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖር እንኳ የኢትዮጵያውያን ተረዳድቶና ተሳስቦ መኖር መቼም ቢሆን ጥያቄ ተነስቶበት አያውቅም፡፡ትልቅ ግምት የሚሰጠው ተከባብሮ መኖር ዋነኛ መሠረቱ አስተዋይነት ነው፡፡

የአገራችን ሕዝብ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተፈራረቁት አገዛዞች ውስጥ በርካታ ችግሮችን ቢያይም፣ በፖለቲከኞች ምክንያት የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ቢያስተናግድም፣ በአስተዋይነቱ ምክንያት ለአንድነቱ ቅድሚያ ሰጥቷል፡፡ ይህንን የመሰለ መልካምና ታላቅ እሴት ባለበት አገር ውስጥ ግን ፖለቲከኞቻችን ጥላቻቸው ወደር የለውም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ተቃዋሚዎቹን አላስተነፍስ ብሎ መውጪያ መግቢያ ሲነሳ፣ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ በይደር የያዙት የመረረ ጥላቻ ውስጥ ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ልዩነት ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር መልካም ፀጋ መሆኑ እየተዘነጋ አገሪቱ እየተጎዳች ነው፡፡በባህል፣ በእምነት፣ በአኗኗር ዘይቤና በአመለካከት ብንለያይ እንኳን ተቻችለንና ተከባብረን በመኖራችን እዚህ ደርሰናል፡፡ የመከራ ቀንበር እንደ መርግ ቢከብደንም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢያጎሳቁለንም፣ ድህነት ህልውናችንን ቢፈታተነውም፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ቢያንገላታንም፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በመልካም እሴቶቻችን ታጅበን ሁሉንም ችለን አንድ ላይ በሰላም ኖረናል፡፡ ወደፊትም እንኖራለን፡፡

ምሁርን ነን ለሕዝብ እናስባለን ተመራምረናል የሚሉ ክፍሎች በጎሳና በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች ሲንዱ ይታያሉ፡፡ በአክራሪና በጽንፈኛ አመለካከታቸው የተቃኘውን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ብቻ እነዚህን የከበሩ እሴቶች ለማጥፋት ይታትራሉ፡፡ በአንድነት ውስጥ ልዩነት፣ በልዩነት ውስጥ ውበት መኖሩን ባለመቀበል ሁሉንም ነገር ከቡድናዊ ፍላጎት አንፃር ብቻ ማስተናገድ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ጠባብ ቡድናዊ አመለካከት አገራዊ እሴቶችን እንደሚያፈራርስ ተገንዝበው ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ከገዢው የወያኔ ጁንታ ጀምሮ እስከ ዲያስፖራ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ድረስ የፍጅት ፖለቲካቸውን እንዲያቆሙ ልንነግራቸው ይገባል::በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ትልቁ ችግር፣ ለዘመናት በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚታወቁትን መልካም እሴቶች ለማገናዘብ አለመፈለግ ነው፡፡ በሐሳብ የሚለይን በጠላትነት በመፈረጅ ዓይንህን ላፈር ማለት ትልቁ መለያ ነው፡፡ ዞር ብለን ስናይ ግን ኢትዮጵያውያን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ፣ ለትልቁ አገራዊ አንድነትና ክብር ቅድሚያ በመስጠት ነው የሚታወቁት፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ዜጎቻችን ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ አንድነታቸው ላይ በማተኮር በመተሳሰብ ሲኖሩ፣ ፖለቲከኞቻችን ግን በተቃራኒው አቅጣጫ ይጓዛሉ፡፡

ሥልጣን ላይ የሚወጣው ቡድን የተቀናቃኙን ነፃነት ባለመቀበል ለምን እኔ የምለውን አትሰማም በማለት ያስራል፣ ያጎሳቁላል፣ ይገድላል፡፡ ለሥልጣን የሚታገለውም ተቀናቃኙን ነገ አንተን አያድርገኝ በማለት ጊዜ ሲገኝ የሚወራረድ ዛቻ ይሰነዝራል፡፡ በዚህም ምክንያት በልዩነት ላይ ተነጋግሮ ችግሮችን በማስወገድ ነፃ ኅብረተሰብ እንዳይፈጠር በጠላትነት መፈራረጁ ይቀጥላል፡፡ ያለፉት 40 ዓመታት ጉዞ በደም የጨቀየውና በጥላቻ የተበላሸው የማኅበረሰባችንን መልካም እሴቶች ማክበር ባለመቻሉ ነው፡፡ አገር የሚያውቃቸው አዛውንቶች ባሉበት አገር ውስጥ ሸምጋይ ጠፍቶ ፖለቲከኞች ለከፋ ነገር ሲፈላለጉ ማየት አስተዛዛቢ ነው፡፡ ‹‹የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል›› እንዲሉ፣ አንዳንዶቹ ከመካሪነትና ከመገሰጽ ይልቅ የመጠፋፋት አራጋቢ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የፖለቲካው መንደር ውስጥ ያሉ የማኅበረሰባችንን መልካም እሴቶች ማየት ካልቻሉ ለአገር አደጋ ነው፡፡