“ዲሞክራሲያዊ ውይይት ከሌለ አገሪቱ እንደአገር አትቀጥልም”
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ “ከጋዜጠኞች የሚሰነዘርብኝን ትችት አልፈራም፤ ነጻ ሚዲያ ለዲሞክራሲ ግንባታው ሂደትና ለልማት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው” ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ትናንት ዘገበ፡፡
“ፍጹም እንዳልሆንን እናውቃለን፤ በመሆኑም ከማንኛውም ጋዜጠኛ የሚቀርብብንን ትችት ለመቀበል ዝግጁ ነን” ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቢቢሲ የአፍሪካ አገልግሎት አዘጋጅ ሜሪ ሃርፐር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
“በዚህች አገር ውስጥ የማህበራዊ ሚዲያውን የመረጃ ፍሰት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው በስፋት የሚጠቀም ንቁና ወጣት የህብረተሰብ ክፍል እንደመኖሩ፣ ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ልውውጥና ውይይት በሌለበት ሁኔታ አገሪቱ እንደ አገር መቀጠል አትችልም፡፡ ከዚህ አንጻር በትክክለኛው ጎዳና ላይ እንገኛለን ብለን እናምናለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፡፡
ባለፈው አመት ታስረው የነበሩት አንዳንድ ጦማርያንና ጋዜጠኞች፣ “እውነተኛ” ጋዜጠኞች” አልነበሩም፤ ታሳሪዎቹ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የታሰሩትም በሙያቸው ሳይሆን መንግስትን ለመናድ ከሚፈልጉ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ በመገኘቱ ነው ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል፡፡
“ጋዜጠኞች በዚህች አገር ውስጥ የሚሰሩትን ስራና የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ ማምታታት እንደሌለብን ግልጽ ሊሆንልን ይገባል”
ሲሉም አክለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፡፡
source Addis admass