ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ የተከሰሰው በጋዜጠኝነት ስራው ነው! በማእከላዊ ቆይታው አሰቃቂ ጊዜ አሳልፏል!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ክስ የተመሰረተበት ከጋዜጠኝት ስራው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የቀድሞ የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና አዘጋጅ የነበረው ሰለሞን ከበደ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ከቤቱ ወደ ስራ ቦታው ሲሄድ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በማእከላዊ ለአራት ወራት ያህል አሰቃቂ ምርመራ ተደርጎበታል፡፡
ሰለሞን ከበደ ላይ መንግስት ክሱን ከመሰረተ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ክሱን ከልሶ ያቀረበ ሲሆን በዚሁ በተከለሰው ክስ ላይም ሰለሞን የተከሰሰው በጋዜጠኝት ስራው መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ክሱ ‹‹… ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በመገናኘትና በአወሊያና በየመስጂዶቹ የተጀመረው አመጽ እንዴት መቀጠል እንዳለበት በመወያየት ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን በየወሩ በመጽሄት በተለያዩ ርእሶች ሲያወጣ ቆይቶ በመጨረሻም ይህንኑ በማሰባሰብ ‹‹የኢትዮጵያ ሙስሊም የት ጋር ነው?›› በሚል ርእስ አመጽ ቀስቃሽ ጽሆፎችን በማሰባሰብ መጽሀፍ በማሳተምና በማሰራጨት…›› በሚል በግልጽ በሙስሊሞች ጉዳይ መፅሄት ላይ ይሰራ በነበራቸው የጋዜጠኝነት ስራዎች መከሰሱ አውን ሆኗል፡፡
መንግስት ደጋግሞ ‹‹ጋዜጠኞች በሙያቸው በሰሩት ስራ አልተከሰሱም አይከሰሱም›› ሲል የቆየ ቢሆንም ሰለሞን ከበደ በዚሁ የጋዜጠኝነት ስራው ተከሷል፡፡ የመፅሄቱ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዩሱፍ ጌታቸው በተመሳሳይ መልኩ በመፅሄቱና በቢ.ቢ.ኤን ሬዲዮ ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ዘገባዎች ምክንያት ክስ ተመስርቶበት ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ዳኢዎችና ኡለማዎች ጋር ከ14 ወራት በላይ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ የጋዜጠኛ መብት ተሟጋች የሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውና ሰለሞን ከበደ ከእስር እንዲለቀቁ ተደጋጋሚ ጥሪ ለመንግስት አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞችን በማሰር መጥፎ ስም ማትረፏ የሚታወቅ ሲሆን በአፍሪካም ከኤርትራ ቀጥሎ ብዙ ጋዜጠኞችን ያሰረች አገር እንደሆነች አለም አቀፍ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡
Journalism is not a Crime!
By : ድምፃችን ይሰማ!