ሚስቴና መንግስቴ – /ዮሐንስ ሞላ/
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ሚስቴና መንግስቴ
—————-
አንቺንስ አፍቅሬሽ…
ጭንቅላቴን ፈተሽ የምትገጣጥሚ፣
ቀልቤን የምትገፊ፣ ቀኔን የምትቀሚ፣
ሕይወት ምትቀምሚ፤
የሳቄ የበላይ፣ የእንባዬ ጠባቂ
ድብርቴን አፍላቂ፣ ደስታዬን አርቃቂ፤
በወደድኩሽ ቅጽበት፥
‘ልሁን’ ባልኩኝ ባልሽ፣ ‘ሁኚ’ ባልኩሽ ሚስቴ
አካሌ፣ ሕይወቴ፤ …ብትሆኚ ድክመቴ፤
ሲሻሽ በቁራጭ ቃል፥
ከሰማይ ከፍ አርገሽ ምታስፈነጥዢኝ፥
ደግሞ ሲደብርሽ፥
በሌላ ቁራጭ ቃል…
ሰማይን አውርደሽ ከላዬ ጥለሽው የምታስተክዢኝ፣
በሙሉም አይደለ፥ በሽርፍ ፈገግታ፥
ቁር አመዳይ ሸሽተው፣ አምራ ገጼ ወዝታ፣
ሞቆኝ በርቶልኝ ማድር ፀሐይ ልቤ ገብታ፤
ደግሞ ስትቆጪ ገጽሽ ሲኮሳተር፣
ይገባበት ጠፍቶት እግሬ ‘ሚደናበር፣
አፌ ‘ሚተሳሰር፣ ቀልቤ የሚሸበር…
አንቺንስ አፍቅሬሽ!
ወድጄ እንደራሴ፥
ሁኜልሽ አንገትሽ፣ አድርጌሽ ራሴ!
እሱ ግን በምኑ?
እንዳንች አቅሜን ገፍፎ የሚገዳደርሽ፣ በስልጣንሽ መጥቶ
አንቺ ብቻ ችለሽ ደፍረሽ ከዘለቅሽው ልቤ ግዛት ገብቶ፣
የሚመላለሰው፥ መንገዱን ዘርግቶ፣ ላዬ ላይ ቤት ሰርቶ፤
አፍርሶ ሚሰራኝ፣ የሚጫወትበት ጭንቅላቴን ፈትቶ?!
/ዮሐንስ ሞላ/