የፍትህ አካላቱ ጥጋብ ጣራ እየነካ የሕዝብን ብሶት ሊያፈነዳው ተቃርቧል::
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አንድ ዜጋ በገዛ አገሩ አንገቱን ቀና አድርጎ በነፃነት መራመድ የሚችለው መብቱ ሲከበርለትና እሱም የሚፈለግበትን ግዴታውን ሲወጣ ነው፡፡ ይህ ግዴታውን የሚወጣ ዜጋ ፍትሕ ሲነፈግና መብቱ ሲጣስ ግን ዜግነቱን ይጠራጠራል፡፡ ስለልማት፣ ስለዕድገትና ብልፅግና ቢወራ አይሰማም፡፡ በጉልበተኞች ንብረታቸውን የተቀሙ ዜጎች ፍትሕ ሲጠይቁ ተነፍገው ሲያለቅሱ፣ ያለጥፋታቸው ተከሰው በእስር የሚማቅቁ ዜጎች እሪ ሲሉ፣ እስር ቤት ለዓመታት ተዘግቶባቸው ፍርድ ቤት አልቀረብንም የሚሉ ዜጎች ሲጮሁ፣ አገር ሰላም ብለው የወጡ ዜጎች በጉልበተኞች በጭካኔ ሲገደሉ፣ ወዘተ ሰሚ የለም፡፡ በሌላ በኩል አንዱ በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ ባለመገንባትህ ካርታህ መከነ ተብሎ ወዲያው ይዞታውን ሲቀማ፣ ሌላው ለዓመታት አጥሮ ተኝቶበት ጠያቂ የለውም፡፡የፍትሕ ሥርዓቱ ከአስፈጻሚው አካል ከሚደርስበት ጫና በተጨማሪ፣ በሕገወጦች አማካይነት የሚፈጸምበት ውንብድና ሕዝብን እያስለቀሰ ነው፡፡
በገዛ አገሩ በመረጠበት ቦታ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና የመሳሰሉትን ተግባራት የሚያደናቅፉ በበዙበት ወቅት እንዴት ሆኖ ነው ስለፍትሕ መነጋገር የሚቻለው? ዜጎችን ዘርና ማንነታቸውን እየቆጠሩ የሚያፈናቅሉና ያፈሩትን ሀብት የሚዘርፉ ቀውሶች ሲያንገላቱዋቸው ዝም እየተባለ እንዴት ፍትሕ አለ ይባላል? ጉልበተኞች የተማመኑትን ተከልለው እንዳሻቸው እየፈነጩ ፍትሕን በስልጣን በገንዘብ እየሸቀጡበት ነው፡፡ ዜጎችንም እያስለቀሱ ነው፡፡
ገንዘብ ያላቸው በጥቅም የተገዙ ዓቃቢያነ ሕጎችን፣ ዳኞችን፣ ፖሊሶችንና የመሳሰሉትን የፍትሕ አካላት በመያዝ፣ የማይገባቸውን ጥቅም ያጋብሳሉ፡፡ ንፁኃንን ያስወነጅላሉ፡፡ የሰው ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ መንግሥትና ሕግ ባሉበት አገር ውስጥ እንደ ልባቸው ይፈነጫሉ፡፡ በጥቅም የታወሩ የፍትሕ አካላትም ለሕገወጦች ተባባሪ እየሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱን ጥቀርሻ ያለብሱታል፡፡ አንዳችም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ ሕገወጦች በሙስና እየከበሩ ያሉት ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ እየተገዛ በመሆኑ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነትና ገለልተኝነት እየተጣሰ ፍትሕ መጫወቻ ሲሆን ያማል፡፡ ያንገበግባል፡፡
ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ በቡድን የተደራጁ ኃይሎች ፍትሕን ጠልፈው የከንቱ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ሲያደርጉ፣ ለሕዝብ ታግለን ደማችንን አፍስሰናል የሚሉ ወገኖች የት ናቸው? ሥርዓተ አልበኞች ፍትሕን በገንዘብ እየሸቀጡ ሕዝቡን የደም እንባ ሲያስለቅሱ ለማኅበራዊ ፍትሕ ታግለናል የሚሉት ምን እያደረጉ ነው? አገርን የመምራትና ሕዝብን የማስተዳደር ሥልጣን ያላቸውስ ምን ይሠራሉ? ትናንት ትግል ላይ ሆነው ዛፍ ጥላ ሥር በፍትሐዊ መንገድ ይዳኙ ነበር የተባሉትስ ታጋዮች የት ናቸው? ከመፈክርና ከአዳራሽ ዲስኩር ያላለፈው ፍትሕን የማስፈን ጉዳይ እስከ መቼ ይድበሰበሳል? ለእነዚህ ጥያቄዎች ሕዝብ ቀጥተኛ መልስ ይፈልጋል፡፡ ሕዝብ ፍትሕ ተሸጦበት የፍትሕ ያለህ እያለ ነው፡፡