«ሱዳን የወደብ መሬት ሰጠችን » ወደብ ተገነባ አንዳች ነገር ቢፈጠር አንደ አሰብ ቢሊዮኖችን ለባዕድ ልናስረክብ ?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


«ሱዳን የወደብ መሬት ሰጠችን » Samuel Zewoin

ልክ የዛሬ አምስት አመት ገደማ በ October 2010 ፔሩ ወደብ አልባ ለሆነችው ቦሊቪያ ለንግድ ለመዝናኛ እና ለባህር ሐይል ግልጋሎት የሚሆን ቁራሽ የባህር ጠረፍ መሬት ለ 99 አመት በሊዝ መልክ በመስጠት ስምምነት ተፈራርመው ነበር።

ቦሊቪያ ከ130 አመት በፊት በተደረገው ጦርነት በቺሊ የባህር ጠረፍ ግዛቶቿን ካጣች በኋላ እስካሁን ድረስ በየአመቱ የባህር ጠረፎቿ የተወሰዱበት እለት በየአመት አስባ የምትውል ሲሆን የባህር ሐይል ጦሯንም ሳታፈርስ አሁንም በሐገሪቱ ባለው ትልቅ ሐይቅ ላይ ልምምዱን ቀጥሏል።

ወደብ ማለት ጤፍና ስንዴ የሚዘራበት መሬት ይመስል «ወደብ ረሀብን አያጠፋም ፣ወደብ እያለን በ1977 እና 66 ተርበን ነበር፣ ስለዚህ አያስፈልገንም» በማለት በአንድ ወቅት በአበል ለተሰበሰቡ ወጣቶች ንቀትና ድምቁርናውን ያሳየው መለስ ዜናዊ ከሞተም በኋላ ሌላው «የትግራይ ትግሪኝ ሪፐብሊክ» ናፋቂ አርከበ በተመሳሳይ «ወደብ ከሌለን አናድግም የሚሉ የኢኮኖሚክስ ሀሁ ያልቆጠሩ ናቸው» በማለት በተመሳሳይ የውሸት ዶክትሬቱንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ እንደ ድንጋይ የደረቀውን የወያኔን አቋም ግልፅ አድርጎታል።

የአባይ ግድብ ጊዜውን ያልጠበቀ ግንባታና በቢሊየን የሚቆጠር ብር ፈሶበት አይመለከታችሁም የተባልነውን የተከዜ ግድብ እንዲሁም የአሰብን ጉዳይ አረሳስቶ ስለ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ፖለቲካዊ ውህደት አንዳንድ ኮካዎች ሊያጃጅሉን የሚሞክሩትን እንተወውና እስኪ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ መጠቀም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት አገራችን በተለይ ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖረው ህዝባችን ምንያህል በጅቡቲ እጅ ኑሮው እየተዘወረ እንዳለ እንመለከታለን ።

ከ90 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው የወጪና ገቢ ንግድ በጅቡቲ በኩል የምትጠቀመው ኢትዮጵያ ባሁን ጊዜ በወር ከ አስር ሺህ ኮንቴይነር በላይ የምታስገባ ሲሆ በቀንም ከአምስት መቶ በላይ ከባድ መኪኖች ከጅቡቲ ወደብ ጭነው ይወጣሉ። በአውሮፓ አቆጣጠር እስከ 2008 ኢትዮጵያ ለወደብ አገልግሎት በየአመቱ ከ850 ሚሊዮን ዶላር በላይ ትከፍል የነበር ሲሆን ጅቡቲ የወደቡን አስተዳደር ለዱባዩ GP world ካስተላለፈች በኋላ ኩባንያው የ15% ወይም የ225 ሚሊየን ዶላር የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ በማድረጉ አገሪቷ በአመት በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጅቡቲ ለመገበር ተገዳ ነበር፤ በዚህም ምክንያት መንግሥት ወደ ፖርት ሱዳን ፣ሞምባሳና በርበራ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ተገዷል ።

በአሁን ወቅትም ኢትዮጵያ በየቀኑ ከሁለት ሚሊየን ዶላር በላይ ለጅቡቲ የምትከፍል ሲሆን ይህም የሐገሪቱ የወጪ ንግድ 16% ያህል ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ወደብ የሌላቸው ሐገሮች ወደብ ካላቸው ሐገሮች በንፅፅር እድገታቸው በ2% ወደ ኋላ ይጎተታል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ጅቡቲ የወደብ ኪራይ አንዳትጨምር ለማባበል በሚመስል መልኩ ርካሽ የኤሌክትሪክ ሐይል ፣ ለሩዝ የሚሆን ሰፊ ሄክታር መሬት ፣ ለመጠጥ ውሃ የሚሆን የከርሰምድር ውሃ ያለበት ግዛት በምልጃነት ያቀረበች ሲሆን ይህ ሁሉ ግን የጅቡቲን ልብ ያራራ አይመስልም ። በየጊዜው ከሚንረው የወደብ ኪራይ ሌላ የኮንቴይነር ማንሻ ጊዜን ከ10 ቀን ወደ 3 ቀን ማሳጠርን እና ሌሎች በርካታ ማነቆዎችን በኢትዮጵያውያን አስመጭዎች ላይ ከማሳረፍ አልተገታችም። እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን አንድ አሳዛኝ ነገር ከጥቃቅን የመገልገያ ቁሶች እስከ ዘይትና አልባሳትን ሳይቀር ከውጭ በምታስመጣዋ ሐገር ከገቢ እቃዎችና ከወደብ ኪራይ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው የሸቀጦች ዋጋ ውድነት ቀጥተኛ ተሸካሚ ሰፊው ዝቅተኛ ኑሮ ገፊ ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆኑ ነው ።

በተቃራኒው ከድንበር ግጭቱ በኋላ ኢትዮጵያን የመሰለ ታላቅ መና የወረደላቸው የጅቡቲ ዜጎች ኑሯቸው በሚታይ መልኩ ከመቀየሩም በላይ 500 ሺህ ለማይሞላው ሕዝባቸው ከኢትዮጵያ በአመት የ300 ሚሊዮን ዶላር ጫት የሚያስገቡ ሲሆን ፣ ከዚህም ሌላ ሙቀቱ በሚያይልበት የነሐሴ ወር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንደ ሸራተን ባሉ ታላላቅ ሆቴሎች ሲምነሸነሹ የዚህ ቁጭት ፀሐፊ ሳይቀር ታዝቧል።

ጅቡቲ የኢትዮጵያ ወሳኝ የኢኮኖሚ ኮሪደር መሆኗ የ90 ሚሊየን ህዝብ መኖሪያና በአፍሪካ ፖለቲካዊ ተደማጭነት አላቸው ከሚባሉ አገሮች መሀል የሆነችው ሐገር ላይ የፖለቲካ ጫና ለማድረግ እስከ መድፈርም ያደረሳት ሲሆን በተለይ የሶማልያው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች እና ኢትዮጵያ ውጊያ በገጠሙ ወቅት በጅቡቲ በኩል የታየው በግልፅ ኢትዮጵያን የማውገዝ ድፍረት በሰአቱ በበርካታ ዜጎች ላይ ቁጭት ፈጥሮ ነበር ።

ይህ ጉዳት ካልተባለ ታዲያ ጉዳት ማለት ምን ሊሆን ነው? ለመሆኑ ሱዳን «ሰጠች» በተባለውስ መሬት ወደብ ተገነባ እንበልና አንዳች ነገር ቢፈጠር አንደ አሰብ ቢሊዮኖችን ለባዕድ ልናስረክብ ነው?