ኢትዮጵያዊነት ማለት? ( በያቤፅ ካሳ ግችሌ )
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ብዙን ግዜ እራሴን ኢትዮጲያዊ ማለት ምን ማለት ነው ብዬ ጠይቄያለው፡፡ ኢትዮጲያዊ ማነው? ማነው ባለአገር ?እንዴትስ ነው ይምንለየው?ሃይማኖቱስ ምንድን ነው?ብሔሩስ ምንድን ነው?ወይስ ብሔር የለውም?ምን ሙዚቃ ነው የሚያዳምጠው? ቋንቋውስ ምንድን ነው? በሚሉ ጥያቄዎች እራሴን አጨናነኩና መልስ ከሆነኝ ብዬ ኢትዮጲያ ተብሎ በሚወራበት ሁሉ ጆሮዬን ጣለ አደረኩ፡፡ ብዙ ይወራል ኢትዮጲያዊ ይሄ ነው ተብሎ ባይወራም ግን ከሚሰጠው ትንተና ኢትዮጲዊ በምናብህ ይሳልልሃል፡፡ ከዛ እንዴ ይሄ ነገር እከሌን ይገልጻል? እንዴ እከሌስ እንዲህ ነው እንዴ? ታዲያ እሱ ኢትዮጲያዊ አይደለም ማለት ነው? ትላለህ፡፡
ኢትጲያዊ ማነው ብዬ በማስስበት ግዜ አንድ ጥሩ መጸሃፍ አገኝው፡፡የመጽሃፉ ርእስ የአማራው ህዝብ ከዬት ወዴት ይላል፡፡የመጽሃፉም ጸሃፊ የምናቀው ብዙ የምናውራለት አንዳርጋቸው ጽጌ ነው፡፡የመጽሃፉ ርእስ ስለ አማራው ህዝብ እንጂ ስለ ˝ኢትዮጲያ˝ የሚያወራ አይመስልም ገለጥ አድርጌ ማውጫውን ሳነበው ግን ስለብሄርተኝነት ስለ ኢትዮጲያዊነት ከዛም እንደ ርእሱ ደግሞ ስለ አማራው ህዝብ ያወራል ስለዚህ እንደው የማስሰውን እና የፈለኩትን ኢትዮጲያዊነት ከነገረኝ ብዬ እህ ብዬ ማንበቤን ቀጠልኩ
˝ዙሪያችንን ስንቃኝው አውላላ ሜዳ ላይ ብቻችንን ቆመናል፡፡ግማሹ አንገቱን ደፍቷል፡፡ከፊሉም መንገድ የጠፋበት ይመስላል፡፡ገሚሱም እንደ እብደት አድርጎታል፡፡ቀሪው ብዙኃኑ በያለበት ኩርምት ጭርምት ብሎ ተቀምጧል፡፡ይህ ሁኔታ ነው ምነው ጎበዝ ምን ነካን ያሰኘን፡፡የአማራ ብሄርተኝነት ጽሁፍ ምንጭ ይህ አሳዛኝና አሳሳቢ ትርኢት ነው፡፡˝ በመግቢያው ላይ ይህንን ይላል፡፡አዎ እኛ ማለት የተገለጸውን ነን ጭርምት ካልንበት ብቻችንን ከቆምንበት እንድንሰባሰብ አስቲ እውነታውን መፈለጋችንን እንቀጥል፡፡
በምእራፍ አንዱ መሰረታዊ ጥያቄ ያነሳል ብሔርተኝነት በኢትዮጲያ ፈጠራ ወይስ እውነታ? ይህን ጥያቄ ከላይ እንዳልኩት ኢትዮጲያ ተብሎ በሚነገርበት ወሬዎች መካከል ይሄ ሃሳብ ብቅ ይላል፡፡ ማነው ብሔርተኝነትን ኢትዮጲያ ውስጥ የፈጠረው?ኢህአዴግ ይሆን የፈጠረው?ማንም ሰው ኢትየጲያ ውስጥ ብሔር የመጣው ኢህአዴግ ከመጣ በውሃላ ነው አይለኝም (ጤነኛ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡)ነገር ግን አንዳርጋቸው እንዳለው ˝ኢትዮጲያ የሚገኝው ብሔርተኝነት አንድ ኢትዮጲያዊ ብሔርተኝነት ብቻ ነው የሚሉ አልታጡም˝ ኢትዮጲያ ተብሎ በሚወራበት አካባቢ ኢትዮጲያ ውስጥ ብዙ ብሔር አና ብሔርሰቦች እንዳሉ ሳይክዱ ስለ ኢትዮጲያዊነት ብቻ አውራ ብለው ያስጨንቃሉ፡፡አንተ ደሞ ብሔርህን ከኢትዮጲያዊነት መለየት ያቅትሃል፡፡ምክንያቱም ኢትዮጲያ የሚባል ብሔር የለም ኢትዮጲያ የብሔር ብሔረሰቦች ሃገር ናት ኢትዮጲያ አንድ ቋንቋ፡ አንድ ሃይማኖት፡ አንድ ባህል እንዲሁም አንድ ወጥ የሀገር ባህል አልባሳት የሏትም፡፡ቢመቸንም ባይመቸንም አንድ ግለሰብ ብቻውን ኢትዮጲያን በሙሉ ሊገልጽ አይችልም፡፡ ፕሮፌሰር ሐይሌ ገሪማ እንዳሉት ኢትዮጲያን በያለንበት ባደግንበት ገልጸናት የእያንዳንዳችን እይታ ደግሞ ሲገጣጠም ትልቅዋን ኢትዮጲያ ትታያለች፡፡ ነገር ግን እኔ ያደኩበት ብቻ ነው ኢትዮጲያዊነት ካልን ነው ኢትዮጲያን የምናደቃት፡፡ ችግሩ የሚፈጠረው እኔ ያደኩበትን ሙዚቃ ቋንቋ እና አለባበስ ኢትዮጲያዊ ነው ስል ሳይሆን የኔን አለባበስ ቋንቋና ሙዚቃ የሃገር ብዬ የሌላውን ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦች ስል ነው የ ሁላችን ሙዚቃ የሁላችን አለባበስ የሀገር ነው የትልቋ ሃገር የኢትዮጲያ፡፡ኢትዮጲያ ብሔረሰቦች ናት ብሔረሰቦችም ኢትዮጲያ ናቸው፡፡
መጽሃፉ ይቀጥልና እንድ ሌላ ሃሳብ ያነሳል ˝በኢትዮጲያ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ በመኖራቸውም ብሔርተኝነት ሁሌ የሚኖር ነው፡፡ነገር ግን ብሔርተኝነት ጎልቶ እንዲወጣ የብሔርተኝነት ስሜት እንዲጠናከር የሚያደርጉት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡˝ እዚህ ጋር ነው ታሪክ ማገላበጥ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው ብሔርተኝት ጎልቶ እንዲወጣ የሆነው?ብሔርተኝነት እንዲወጣ ያደረገው ያለፈው ዘመን የፖለቲካዊ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ነበረ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች በሚደርስባቸው ጭቆና እነርሱን ከሚመሳስሉ ሰዎች(በባህል በቋንቋ ..ወዘተ)ጋር ስርአቱን መቃወም ጀመሩ፡፡በአውሮፓ ግዛት ማስፋፊያዎች ሲካሄዱ የተቀላቀሉት ህዝቦች በኢኮኖሚ ስለሚተሳሰሩ አንድም ማእከላዊ መንግስት ስለሚኖራቸው በባህል በ ቋንቋ እየተሳሰሩ መጥተዋል፡፡ ኢትዮጲያስ? ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉት ብሔር ብሔረሰቦች ከ ዛሬ መቶ አመት በፊት የነበራቸውን አይነት ባህል ቋንቋ አለባበስ ወዘተ ይዘዋል ለምን? ምክንያቱም ግዛት አስፋፊው አካል የተሻለ ኢኮኖሚ የሌለው በመሆኑ የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግስት መመስረት አልቻለም፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጲያም ይሁን የአውሮፓ ግዛት አስፋፊዎች የተጠቀሙት የጦር መሳርያ ቢሆንም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ስዉ አንዳይነት ባህል የሌለው ደግሞም ራሱን መሳይ ፈልጎ ስርአቱን የተዋጋው፡፡ አንዳርጋቸው እንዳለው እነዚህ ግዛት ማስፋፊያዎች በጦርነት ከመሆናቸው የተነሳ ስቃያቸውና ቁስሎቻቸው አሁንም ድረስ ታሪክበዲሞክራሲያዊ በተነበበ ቁጥር የሚያሙ ናቸው ምክንያቱም ከዛ ሁሉ መከራ እንኳን በውኃላ የተፈጠረ የአንድነት ባህል ስለሌለ፡፡ ˝ህዝቦችን ለማስገበር የተደረጉ ጦርነቶች በህዝብ ላይ የፈጸሙት ግፎች የደረሱ ስቃዮች በታሪክ መጽሃፍ ውስጥ የተዘከሩ ትውልድ ቢያነባቸው ስሜት የማይቀሰቅሱ ደረቅ ሃቆች ብቻ ሆነው በታዩ ነበር፡፡ጦርነት በሰላም ኋላ ቀርነትን በእድገት የጠመንጃ አስተዳደርን ፖለቲካዊ መንግስት ለመክተት የተደረገው ሙከራ ተሳክቶ ህዝቡ አንድ እንዲሆን በታሪክ ከተደረገበት ጦርነትና ከተፈጸመበት ግፍ ይልቅ አሁን በሚኖርበት ሃገር ያገኛቸውን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ፖለቲካዊ ጥቅሞቹን በማሰላሰል በብሄራዊ ዜግነቱ እየኮራ ይኖራል፡፡˝ የአርባ ቀን እድላችን ሆኖ ይህ አልሆነም ስለዚህ አሁን አይናችንን ብንጨፍን እንኳን በምናባችን የሚታየንን እውነታ መቀበል አለብን፡፡
ሌላው ጉዳይ በመጽሃፉ በምእራፍ ሁለት የተነሳው ነገር ቢኖር ብሔራቸውን በኢትዮጲያዊ በሚባል የማይጨበጥ ነገር(ኢትዮጲያ ያለ ብሔር ብሔረሰቦች ህልውና የላትም እና) ብሔራቸውን ለመተካት ይሞክራሉ፡፡ ለምን ይሆን ሰዎች ብሔር ለመካድ የሚፈልጉት ይልና
1ኛ ከስነልቦና የሚመጣ ጭንቀት፡- ከተለያዩ ብሔረሰብ የመጡ ሰዎች ሲጋቡ ልጆቻቸው ላይ የሚፈጠር ስነልቦናዊ ጫና ይኖራል ታዲያ ለ እነዚህ ልጆች መፍትሄው ምንድን ነው? (አነዚህን ከተለያዩ ብሔረሰቦች የመጡ ሰዎች እንዴት ሊጋቡ ቻሉ ለሚለው ጥያቄ መጽሃፉ ትንታኔ ይሰጣል ብዙ ሳላተኩርበት በአጭሩ በድሮው ግዜ የመሳፍንት ልጆች ስልጣንን ለማመቻቸት በሚል ከሌላው ብሔረሰብ ጋር ስለሚጋቡና በተለያየ የስራ ምክንየት ደግሞ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚደረግ ጋብቻ ሌላው ምክንያት ነው እንደዚህ አይነት ሰዎች በአብዛኛው በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው፡፡)እነዚህ ክተለያየ ብሄር የተወለዱ ሰዎች ጥቂቶች እንደመሆናቸው አብዛኛው የኢትዮጲያ ክፍል እንደነበረ ነው ያለው፡፡ስለዚህ በእነዚህ ጥቂት ሰዎች ሙሉውን ኢትዮጲያ መሳል አይቻልም፡፡ ምንም እንኳን ጥቂቶች ቢሆኑ መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ነው ፡፡ መጽሃፉ መፍትሄ በሚቀጥሉት ምዕራፎች ውስጥ አማራነት ደምና አጥንት አይገልጸውም በሚል ርእስ ˝በእኛ እምነት የአንድ ብሔር አባልነት በግለሰቡ ውስጥ ባለ የአማራነት ደም ወይንም የአማራነት አጥንት የሚተረጎም አይደለም፡፡አማራነት ምንድነው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያገኘው በቋንቋ በባህልና በታሪክ ተመሳሳይነት ያላቸው ሕዝቦች ማህበራዊ ስሜት ነው ማለት ነው˝ ስለዚህ ሊገባን የሚገባው ነገር ቢኖር ብሔር የደምና የአጥንት ጉዳይ ሳይሆን የማንነት ጉዳይ ነው ሰው የሚያስበው በቋንቋው ነው የሚለብሰው አንደባህሉ ነው ስለዚህ ከምንም ከማንም ብሄር ተወለድክ የአንተ ስነልቦናዊ ማንነት የተገነባው ምን ላይ ነው? ነው ጥያቄው፡፡ስለዚህ አባቴ ብሔሩ ይሄ ነው እናቴ ደግሞ ብሔርዋ እንደዚያ ነው ታዲያ እኔ ምንድነኝ ብለህ ለጠየቅከው አንተ የምታወራው ቋንቋ ነህ፡፡ አንተ የምትለብሰው ልብስ ነህ አንታ ወደ ውስጥህ ስታስብ የሚገዛህ ስብእናና ታሪክ ነህ ስለዚህ ዘርህን መቁጠር ተውና ማንነትህ እራስህን ማነኝ ምነኛ ነኝ ብለህ ፈትሽ፡፡
2ኛ ከጠንካራ ብሔራዊ ማንነት አለመኖር የሚመጣ ችግር ፡-እዚህ ላይ መጽሃፉ የሚለው በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የሚቸገረው የአማራው ህዝብ ነው፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቅም ወደ ኃላ መመለሳችን አይቀርም፡፡ ያለፉት ጭቆናዎች ከላይ በጥቂቱ እንደገለጽኩት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ባህላዊና ስነልቦናዊ ነው፡፡በፖለቲካናዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳይ የአማራው ህዝብ እንደሌላው ህዝብ የተጨቆነ ነው ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጭቆናዎች ከመደብ እንጂ ከብሔር ጭቆና ጋር ልናስተያያቸው ስለማንችል(አልፎ አልፎ የመደብ እና የብሔር ጭቆና እጅ ለእጅ ቢያያዙም፡፡) ነገር ግን በባህል ጉዳይ ላይ የአማራው ህዝብ ከገዢው መደብ ጋር አንድ አይነት ብሔር ስላለው የባህል ጭቆና አልደረሰበትም፡፡˝ ነገር ግን አማራውን ከሌሎች ህዝቦች የሚለየው ጉዳይ አለ፡፡በቋንቋ በስለልቦና ሌሎች ህዝቦች የደረሰባቸውን አበሳና ጭቆና አልደረሰበትም፡፡እንደ አጋጣሚ የአገሪቷን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባህል ህይወት በአምባገነንነት ሲቆጣጠር ከኖረው የአማራ ገዢ መደብ ጋር አንድ አይነት ቋንቋና ባህል በመጋራታችን የሌላ ብሔር ባህል እንድንላበስ የተገደድን አልሆንም፡፡የተለያዩ ብሔር አባላት ቋንቋቸው ሲንቋሸሽ ባህላቸው ሲዋረድ የግለሰቦች ስም እንኳን ሳይቀር ማፈሪያ ሆኖ ስማቸውን ሲቀይሩ እኛ እንዲህ ዓይነቱ የባህልና የስነልቦና ጭቆና ውስጥ አልገባንም፡፡̋ ˝በዚህም ምክንያት በባህልና በስነልቦና የተጨቆኑት ብሔሮች ብሔርተኝነታቸውን ሲያጠናክሩ የአማራው ብሔር ውስጥ ይህ ጎልቶ እንዳይታይ አደረገው፡፡ይህ ማለት ግን አማራ ብሔር የለም ወደሚል ድምዳሜ ውስጥ አያደርስም፡፡ለዚነው ሰዎች ብሔራቸውን ሲጠየቁ ኢትዮጲያዊ የሚሉት ምክንያቱም እነርሱ ያዳበሩት ብሄርተኝነት ስለሌለና በእኔ አስተያየት በቀደሙት ግዜያት የገዢዎቹ ብሔር አማራ በመሆኑ አማራነት የኢትዮጲያ ብሔር እንደሆነ በማሰብ ብሔርነታቸውን ከኢትዮጲያዊነታቸው ጋር አዛምደው ብሔራቸው ግራ ገብቶአቸዋል፡፡በዚህም ከ ዘመናዊ ኢትዮጲያ ምስረተ አኳያ ሌለውበደረሰበት ጭቆና ተመስርቶ ብሔሩን ሲያጠናክር የ አማራው ህዝብ ግን ይህንን ማድረግ አልቻለም፡፡ሌላው ብሔር ዜግነቱንና ብሔሩን ማየት ሲችል የአማራው ሕዝብ ግን ይህንን ለማየት እንዲሳነው ሆኗል፡፡˝ይህ ችግር የተፈጠረው የአማራ ገዢ መደብ በኢትዮጲያ ውስጥ የብሔሮችን ህልውና ለማጥፋት በብሔሮች ላይ አማርኛ ቋንቋን የአማራውን ባህልና ታሪክ የሁሉም ብሔሮች እንደሆኖ አድርጎ የኢትዮጲያ ህዝቦች ቋንቋ ባህልና ታሪክ በአንድ ብሔር ቋንቋ ባህልና ታሪክ ለመተካት ተቀባይነት ለማግኝት ባደረገው ሙከራ ነው፡፡˝ በዚህም ምክንያት አማራ እንደሌሎቹ ብሔሮች የኢትዮጲያ አንዱ ክፍል እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ሊረዳ ይገባዋል፡፡
3ኛ ከነቃ የፖለቲካ ተቃውሞ የሚመነጭ ችግር፡- ˝በዚህ ክልል የሚነሳው ችግር ኢትዮጲያ የብዙ ብሔሮች ሃገር መሆኗን ካለማወቅ(ካለመረዳት) የሚመነጭ አይደለም፡፡ ህዝቦች በብሔር በመደራጀታቸው ብሔራዊ መብታቸውን ለማስከበር በመነሳታቸው የራሳችንን እድል በራሳችን እንወስን በማለታቸው ራሳችንን እናስተዳድር በሃብታችን ተጠቃሚዎች እንሁን ቋንቋችንን ባህላች ታሪካችን ይከበር በማለታቸው በቀጥታ ስልጣንንና ተጠቃሚነት በበላይነት ይዘው ከኖሩ ሃይሎች ጋር የሚያፋጥጥ በመሆኑ ነው፡፡˝ ለእነዚህ አይነት ሰዎችም መፍትሄ አለ፡፡ መፍትሄው ደግሞ ያለፈው ዘመን አልፏልና ከዚህ በውሃላ በምንም በየትም አይነት ሁኔታ ተመለሶ እንደማይመጣ ነው፡፡አነዚህ የድሮ ዘመን ናፋቂዎች ሊረዱት የሚገባው ነገር ቢኖር አነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የገነቡት ብሔርተኝነት በምንም ሊናድ የማይችልና እንዳንበሳ ተቆጥቶ ሲነኩት የሚገነፍል ነው፡፡ስለዚህ ሁላችንም የኢትዮጲያ ብሄር ብሔረሰቦች ነን ማንም ማንንም የሚገዛበት ግዜ ሳይሆን ጥቅማችንን ቁጭ ብለን አውጥተን አውርደን የምንመሰርታት ሀገር እንጂ ለአንዱ የብሄር ጥቅም ሌላው የሚያጎነብስበት አይደለም፡፡ማንም በሀገሩ አጎንብሶ መሄድ የለበትም ማንም እንደ ስደተኛ ሌላን ባህል ሌላን ቋንቋ ሊጫንበት አይገባም፡፡ኢትዮጲያ ልትኖር የምትችለው ብሔረሰቦች በእኩልነት ሲታዩና በእኩል ሃገራቸው ላይ ነጸነታቸው እና መብታቸው ሲገለጽ ነው፡፡ኢትዮጲያ ያለዚህ እኩልነት ህልውና ሊኖራት አይችልም፡፡ብታምኑም ባታምኑም ብዙ ነን አብረን እንድንኖርና ጠንካራ የሆነች ሉአላዊ የሆነችን ሃገር ለመመስረት የግድ ብዙሃነታችንን መቀበል ይኖርብናል አለበልዚያ ኢትዮጲያ የእነንትና እንጂ የሁላችንም አትሆንም፡፡ አንድ ብሄራዊ ስሜት ሊሰማን የሚችለው ሁላችንም በእኩል ባህላችን ሲንጸባረቅ ነው አለበለዚያ ግን ኢትዮጲያ የምትባል ሃገር አትኖርም የሚኖረው አንድ በታጠረ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሃገሮች ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በየቤታችን ስራ ልንሰራ ይገባናል ብሔራችን በእኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊ ይሁን ፖለቲካዊ እቅዶችን ማቀድ ይኖርብናል፡፡
ምእራፍ ሶስት አማራ ምንድነው? ብሎ ጥያቄ ይጠይቃል ምዕራፉ አማራነታቸውን በኢትዮጲያነት ውስጥ ለሸፈኑ ሰዎች መፍትሔ ለመስጠት ይሞክራል፡፡አማራ የሚባል ነገር እንዳለ እንደሌላው ብሔር የተጠናከረና በግልጽ ጎልቶ ባይታይም ነገር ግን ተሸፈነ እንጂ አልጠፋም ይለናል፡፡በተለይ እንደጥሩ ምሳሌነት የተጠቀሰው ነገር ቢኖር ˝አንድን አማራ የሚባል ህዝብ የሚል አመለካከት ያለውን ግለሰብ ኦሮሞ ወይንም ወላይታ ነህ እንዴ?የሚል ጥያቄ እናቅርብለት፡፡ኦሮሞ ከሆነ ኦሮሞ ነኝ ይላል፡፡ወላይታ ከሆነ ወላይታ ነኝ ይላል፡፡ካልሆነስ?ካልሆነ ሶማሌ ከሆነ ሶማሌ ነኝ ይላል፡፡ይህንን አይነት መልስ ለመስጠት ቆይ ላስብበት የሚል የለም፡፡ ጥያቄውን እንደተጠየቅን መልሳችን ከመቅጽበት ይከተላል፡፡አማሮች ከሆንም ኦሮሞ ነህ እንዴ ለሚለው ጥያቄ አማራ ነኝ ብለን መመለሳችን የተለመደ ነው፡፡̋ ˝ ስለዚህ አማራ የሚባል ህዝብ አለ፡፡ከላይ ብዙ እንደተባለውም ኢትዮጲያ ውስጥ አማራን ጨምሮ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡አንዳንድ ሰዎች አማራን ከክርስትና ጋር ያያይዛሉ፡፡በተለይ በገጠር ያሉ ሰዎች እስላም ነህ ተብለው ሲጠየቁ ከሆኑ አዎን ካልሆኑ ደግሞ አይ አማራ ነኝ ይላሉ ይህ ደግሞ እነደማያስኬድ የምናውቀው 1ኛ ከላይ እንደጠቀስነው ኦሮሞ አይደለሁም አማራ ነኝ ስንል ክርስቲያነኝ ለማለት ሳይሆን የራሱ ቋንቋ ባህል አኗኗር ያለውን ህዝብ እያመለከትን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡2ኛ አማራ ሆነው ሙስሊም የሆኑና ሌላ ብሔር ሆነው ክርስቲያን የሆኑ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡˝እውነት ነው ይህ አማራነት የምንለው ነገር ለብዙዎቻችን አዲስ ነገር ነው፡፡አዲስ ነው ስንል ግን በቅርቡ ጠፍጥፈን የሰራነው ነገር ማለት አይደለም፡፡̋ ˝ሌላው ቅድም ከተለያዩ ብሔር የተወለዱ ሰዎችን ስናነሳ እንዳልነው ብሔር የደምና አጥንት ጉዳይ ሳይሆን የማንነት ነው በመጽሃፉም አማራነት ደምና አጥንት አይገልጸውም በሚል ርእስ ስር ˝ከሃገራችን ሁኔታ ስንነሳ ከእነዚህ ውጭ ያሉ የአማራው ብሔር በቋንቋና በባህል በሁሉም ህዝቦች ላይ በነበረው የበላይነት የብሔራቸውን ቋንቋና ባህል የረሱ ቋንቋቸው አማርኛ ባህላቸው የአማራ ባህል የሆኑ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ጉዳይ አንድ ላይ ማየቱ ጥሩ ነው፡፡̋˝ይልና ˝በእኛ እምነት የአንድ ብሔር አባልነት በግለሰቡ ውስጥ ባለ የአማራነት ደም ወይም አጥንት የሚተረጎም አይደለም፡፡አማራነት ምንድነው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያገኝው በቋንቋ በባህልና በታሪክ ተመሳሳይነት ያላቸው ህዝቦች ማህበራዊ ስሜት ነው በሚል ነው፡፡በደም በአጥንት በዘር ሃረግ ቆጠራ የደረስንበት አይደለም፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ በቋንቋው በባህሉ በስነልቦናው አማራነት የሚሰማው ማንኛውም ግለሰብ እራሱን አማራ አድርጎ የማየት መብት አለው፡፡̋˝ ስለዚህ ብሔር የማንነት ጉዳይ እንጂ የደምና የአጥንት ጉዳይ አይደለም፡፡
ምዕራፍ አራት አማራነትና ብሔረተኝነት ይላል በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከላይ እንዳየነው የአማረ ህዝብ ብሔርተኝነቱን እንዳያጠናክር የተደረገበትን ምክንየቶች በዝርዝር ይተነትናል፡፡ባለፉት ግዜያት የኢትዮጲያ ዘመናዊ ታሪክ ከጀመረበት ከአጼ ቴዎድሮስ ተነስቶ እስከ ደርግ ያለው ሁኔታ እንዴት ተጽእኖ አመጣ የሚለውን ይመልሳል፡፡ዘመናዊው የኢትዮጲያ ምስረታ ልሎችን ግዛቶች በማሰገበር ወይም ግዛት ማስፋፊያ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡እነዚህ ግዛት ማስፋፊያዎች በሁሉም አቅጣጫ በሸዋ መሳፍንት እና መኳኳንንት ነው፡፡በዚህ ላይ የአማራ ክልሎች ሲያዙ መሰረት ያደረገው የክልል ጉዳይን ማለትም ግዘትን ማስፋፋት እንጂ ብሔራዊ የሆነ ለውጥን አላመጣም ይህ ማለት በቋንቋና በባህል ተጽእኖ አላመጣም ምክንያቱም ግዛት አስፋፊዎቹ አማሮች ስለነበሩ፡፡̋̋ ̋የወሎንና የጎጃም ንጉሶችን መገበርን ልዩ የሚያደርገው ነገር ግን አለ፡፡በእነዚህ ክልሎች የሚነሱ ንጉሶች የአማራውን ህዝብ የበላይነት ለማስተዳደር አማርነታቸውን መሰረት ያደረጉ ነበርና በመካክላቸው ትግሉ ብሄራዊ ልዩነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ክልላዊ መሆኑ ነው፡፡˝ አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ብሄሮች የመጡ ሰዎችም በግዛት ማስፋፊያው ላይ ስለተሳተፉ ግዛት ማስፋፊያው አማረነት ላይ መሰረት ያደረገ አይደለም ለሚሉትም እንሆ መልሱ ˝ የተለያዩ ብሔር ንጉሶች ባላባቶች ከሚኒሊክ ጋር ወደው ይሁን ተገደው ማበራቸው በስርአቱ የአማራው ንጉስ መሳፍንትና መኳኳንንት የነበራቸውን የበላይነት የነካ ጉዳይ አልነበረም፡፡̋˝ ስለዚህ ከተለያዩ ብሔሮች የመጡ ሰዎች ተሳታፊ ቢሆኑም የአማራ የበላይነት የቀጠለ ነበር፡፡ማስፋፋዊያውም የህዝቦችን ንብረት ሃብትን መውሰድ ከመሆን ባለፈ የቋንቋና የባህልም ጭቆና ነበረው፡፡እና ቅድም ደግመን ደጋግመን እንዳልነው የአማራው ህዝብ ክልላዊ እንጂ ብሔራዊ ትግል አላካሄደም በዚህም የተነሳ ብሔራዊ የሆነ አንድነት መፍጠር አቅቶት ነበር፡፡አጼ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት መጀመሪያ በአመለካከት የሆነን ነገር ሊያበጁ የቻሉ ሰው ናቸው፡፡ ከአውሮፓ የመጣው ካፒታሊዝም በገንዘብ የመተዳደርን ዘመናዊ ትራንስፖርትም ይዞላቸው ስለመጣ ጠንካራ የሆነ ማእከላዊ መንግስት የመመስረት እድል ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡̋ ̋አጼ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ማበብ በአማራው ህዝብውስጥ የተፈጠረውን የአመለካከት ለም መሬት ሆነ የአውሮፓ ስልጣኔ ያመጣውን የተለያዩ የአማራ ግዛቶች አስተዳደር በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የሚያስችሉ ስልቶችን በመጠቀም ጠንካራ የአማራ ክልላዊ ብሔራዊ አንድነት ለመፍጠር ሳይችሉ ቀሩ፡፡̋˝ ከአጼ ቴዎድሮስ ሞት በውሃላም የተነሱት አጼ ዮሃንስ የነገሱት ለጥቂት ግዜ ስለነበረ ለአማራ ብሔረተኝነት መመስረት በቂ ግዜ አልሰጠም፡፡ከዛም በአጼ ሚኒሊክ መሪነት የወጣው የሸዋ ፊውዳልም ሃይል ለአማራ ብሔር መገንባት አልቻለም፡፡ ህዝቡ በግዛቶች የተከፋፈለም ስለነበር ታማኝነቱ ለግዛቱ ንጉሶች እንጂ ለ አንድ የአማራ ብሄር መንግስት አልነበረም በዚህም ምክንያት አማራ አንድ ጠንካራ የሆነ የብሔር ስሜት መፍጠር ተሳነው፡፡ከ አጼ ሚኒሊክ አስከ ደርግም ባለው ግዜ ሲሰበክ የነበረው ብሔርተኝነት ኢትዮጲያዊነት ነው፡፡በዚህም የሚነገረው ቋንቋ አማርኛ ባህሉም የአማራ በመሆኑ ለአማራ ህዝብ በብሔር አኳያ አንድንነት ፈጥሮ ለ መዋጋት እደል አልሰጠውም፡፡ምንም እንኳን ገዢው መንግስት በኢኮኖሚ ህዝቡን ቢያደቀውም ለአማራ ህዝብ በብሔር ሳይሆን በመደብ በተነሳ በደረሰበት በደል በተለያዩ ግዜያት ተቃውሞውን አሳይቷል፡፡˝ቀደም ሲል ስለ አጼ ቴዎድሮስ ስናወሳ እንዳየነው የአማራ ገዥዎች ወደ ስልጣን ብቅ ማለት ሲጀምሩ ለአማራነት የሰጡት ትርጉም አማራነት እራሱ ለገዢነት በቂ ማረጋገጫ ማድረግ እንደነበር ነው፡፡̋˝ በዚህም የተነሳ የፍርድ ቤቶች ህግ አስፈጻሚ አካላት አማርኛ ቋንቋን በመጠቀማቸው አማራ ውስጥ የተሳለው አማራነት ሳይሆን ኢትዮጲያዊነት ይህ በአስተዳዳሪዎቹ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ለዚህም ነው ሰዎች የአማራ ብሔርነት አሁንም ድረስ ሊዋጥላቸው ያልቻለው፡፡አማራ በኢትዮጲያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ብሔር እንጂ የኢትዮጲያነት ማንነት አይደለም፡፡ ለዘመናት የቀደሙት መንግስታት ያደሩት ድር በቀላሉ እንደማይገፈፍ የታወቀ ነው ነገር ግን በብዙ ስራና ልፋት ግን ኢትዮጲያ ውስጥ ካለው ሁኔታ የአማራውም ህዝብ እንዴት አብሮ መሄድ እንደሚቻል ከስምምነት መድረስ ይቻላል፡፡ ልንረሳ የማንችለው ነገር ቢኖር ግን በአማራው ህዝብ ላይ የደረሱትንም በደሎችንም ነው ˝የጎጃም ህዝብና የጀግናውን በላይ ዘለቀን የብቸናን ሕዝብና ጀፍናውን ውባለ ተገኑን የንዋይ ልጆችን የጎንደሩ አምባሳደር ወርቅንህ ገበየሁን የወሎውን የህዝብ ልጅ ዋለልኝ መኮንን በአጠቃላይ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ሕልፈታቸው በአማረው ህዝብ ህይወት ለትውልድ የሚተላለፍ ሃዘን የተወውን የቡልጋ የምጃር የመንዝ ወጣት ምሁር ፍግት ስናስታውስ ማን ለፍጅቱ በዋነኝነት እንደሚጠየቅ አንረሳም፡፡̋
ምዕራፍ አምስት ለአድማሳዊ ጭቆና የአማራው ምሁር ብቸኛ ምላሽ አድማሳዊ ጸረ ጭቆና ትግል ነበር ይላል በዚም ምእራፍ የሚዳሰሰው ነገር የአማራው የትግል ታሪክ በመዘርዘር አማራው በትግሉ ታሪኩ ያነሳቸው ጥያቄዎች ምን እንደነበሩና በምን መልክ እንደተታገለ ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ ባለፉት ግዜያት እንደ አርበኛና ጀግና የምናያቸው ሰዎች መታገላቸውን ብቻ ሳይሆን ለምን እንደታገሉ በጥልቀት መመርመር ያሰፈልጋል፡፡ብቻ እንደመጣልን እሱ ጀግና ነው ሳይሆን ለምንድን ነው የታገለው? ለምን አለማ ነበር የቆመው? የሚለውን ማየት አለብን፡፡ በመጽሃፉ የተጠቀሱት ሰዎች በመጀመሪያ በ1953 ዓም በታህሳስ ወር መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ የሞከሩትን የንዋይ ልጆች መንግስቱንና ገርማሜን ነው፡፡እንደሚታወቀው ይህ ሙከራ ለኢትዮጲያ ህዝብ አይን የከፈተና ለሚቀጥሉት ህዝባዊ አመጾች ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ደግሞ ብርጋዴር ጀነራል መንግስቱ ነወይ ሊገደል ፍርድ ቤት በቀረበበት ግዜ ያለውን መጽሃፉ ይተርክልናል እንዴት ስለ ህዝቡ ጉዳይ እንደሚያሳስበው እና ያሉበትን የፍትህ አልባ ኑሮ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑ ነው፡፡ለዚያም ነው ይህ ሰው የማይረሳ መሆኑ የሚቀጥለው፡፡ሌላው እነዚህ የመፈንቅለ መንግስት ተሳታፊዎች ያለውን የብሔር ጭቆና ያሳሰባቸው ነበሩ፡፡ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆነው በቅርቡ (መጽኃፉ በተጻፈበት ግዜ መሆኑን ልብ ይበሉ)በምእራብ ሶማሌ የነጻነት ግንባር ተወካይ የመንፈቅለ መንግስቱን ዋነኛ መሪ የሆነውን ገርማማ ነዋይን አስመልክቶ የጻፉትን ደብዳቤ ማየት ይቻላል፡፡ከምእራብ ሶማሊያ የነጻነት ግንባር ተወካይ የተጻፈው የድርጅቱ ማህተም የያዘው ደብዳቤ˝ኦጋዴንና ታላቁ ሰው ገርማሜ̋˝በሚል ርእስ ገርማሜ ንዋየ በኦጋዴን አስተዳዳሪ በነበረበት ወቅት የሰራቸው ስራዎች በዝርዝር የሚያስቀምጥ ነው፡፡እነዚህ ስራዎች አስተዳደርን የመሰረት ልማት ግንባታን ፍትህ ስርአትን ሌሎችን የገርማሜ ነዋይ ስራዎች ናቸው፡፡ከእነዚህ ውስጥ የአስተዳደር ሰዎችን በተመለከተ የነጻነት ግንባሩ ያሉትን እንይ፡፡˝ገርማሜ ህዝቡ በራሱ ሰዎች እንዲተዳደር እነዚህም ሰዎች የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን መሆን አለባቸው የሚል አቋም ነበረው፡፡በዚህ አቋሙ መሰረት ንጉሰ ነገስቱ በባላባትነት መጠሪያ ብቻ በህዝቡ ላይ ያስቀመጧቸውን ወረዳና ምክትል ወረዳ ገዢዎች በእራሱ ውሳኔ በመሻር ከአውራጃ ጽ/ቤት ጀምሮ አስከታች ያለውን የአስተዳደር ሰንሰለት በአካባቢው ምሁራን በመተካት እስከ ንጉሰ ነገስቱ ድረስ በአደገኛነቱ የተሰማውን እርምጃ ወስዷል፡፡̋ ˝ ˝ ስለዚህ አነዚ የምናደንቃቸው ሰዎች ስለብሔር ጭቆና የገባቸው እና ስለብሔር ጭቆና የታገሉ ናቸው፡፡አነሱን ከወደድን ሃሳባቸውን ትግላቸውንም እንውደድ፡፡2ኛ ደግሞ ከ 1966 በውኃላ አፋኙ የደርግ መንግስት ስልጣን ከያዘበት በውሃላ በኢህአፓ የሚመረው የተማሪው እንቅስቃሴ ነበር ፡፡ስለ ኢህአፓ ብዙ ተብሎአል ግን ኢህአፓን እንደግፋለን ስንል የነበርን ይህንን እናዋውቃለን?˝ኢህአፓ የተማሪው እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ውጤት ስለነበር በነሃሴ ወር 1967 ዓ.ም ባወጣው ፕሮግራሙ ላይ ተማሪውና ምሁሩ ለዘመናት የታገለላቸውን የመሬት ለአራሹ የብሔርሮችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መንገንጠል ያልተገደበ የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብት መከበርን በማያሻማ ቋንቋ በፕሮግራሙ የተቀረጸ ድርጅት ነበር፡፡ ̋ ስለዚህ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ከድሮም ጀምሮ አሳሳቢ የነበረና ብዙ ደምም የፈሰሰለት ብሄር ብሔረሰፖች ዴሞክራሲያዊ መብቶቸቸው አስከ መንገጠል እንዲከበርላቸው ነን ፡፡ስለዚህ ለ ያ ትውልድ አድናቂዎች ሁሉ ያ ትውልድ የብሔር ጭቆናን መኖሩን የሚቀበልና የብሔር ብሔረሰቦች የራስን አድል በእራስ መወሰን የሚየከብር ነው፡፡ ስለዚህ ከላይ እንዳየው የእነዚህ ጀግኖች አባቶቻችን ደም የፈሰሰው ለሁሉም እኩል መብትን እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡ በዚያላይ መንግስቱና ገርማሜ በ ያትውልድ ውስጥ ያለፉትም የኢሀአፓ ኮከቦች ሁሉ ከአማራ ብሔር የመጡ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ስለዚህ የአማራው ብሔር የገዢው መደብ ብቻ ሳይሆን ለ ብሔር ነጻነት የታገለም ህዝብ የወጣበት ነው ፡፡እዚህ ጋር አጥብቄ መናገር የምፈልገው የብሔር ጉዳይ አሁን የመጣ ሳይሆን የድሮ አባቶችም የተዋጉለት ነው ስለዚህ ስለድሮ እያሰብን አባቶችን ስናመሰግን የቆሙለትን አቋም አንዘንጋ ለማለት ነው፡፡3ኛ ገራሚው ሰው ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡ ዋለልኝ አእምሮ ከዘምኑ እጅግ ያለፍ ጠቢብ ሰው ነው፡፡ስለብሔር ጭቆና የገባውና ከመሰሎቹም ጋር ይህንን ክፉ ተግባር ለማስወገድ የጣረ ሰው ነው ካደነቅን ይህንን ሰው ማድነቅ ነው፡፡˝በአደባባይ ስለመብታቸው የመከራከር ባህል ባልነበረበት በዚያ አስከፊ የጨለማ ዘመን የጭቁኑን ብሔሮች ቀንበር እንደተሸከሙ መስዋትነትን ከተቀበሉ የአማራ ምሁራን መሃከል አንዱን ዋለልኝ መኮንን ብቻ መጥቀስ ይበቃል፡፡̋˝ዋልልኝ በእንግሊዘኛ የጻፈው ̋የብሄር ጥያቄ ላይ˝ይህንን ብሎ ነበር ˝ጭቆናን በመቃወም ለሚነሱ አመጻዎች አንድ አይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል፡፡የጎጃም ህዝብ ሲያምጽ ማጨብጨብ የባሌና የኤርትራ ህዝቦች ሲያምጹ ዝም ማለት የመንግስቱ ንዋይን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማወደስ ነገር ግን የታደሰ ብሩን ሙከራ መንቀፍ ምን ማለት ነው?አማሮች ብቻ ሲያምጹ ብቻ መደገፍ አማራውን የሚመራው አመጽ ከሆነ ማወደስ ኦሮሞውና ኤርትራዊ ከሆነ ግን የማይዋጥልን ለምንድን ነው?ለሌሎች ህዝቦች ያለንን ብሄራዊ ንቀት ከማሳየት ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ለጸለ ጭቆና እስከቆምን ድረስ ጭቆናን ተቃውሞ ማንም የትም ይነሳ ሁሌም ልንደግፈው ይገባል፡፡እያንዳንዱ ጸረ ጭቆና አመጽ የኢትዮጲያ ህዝቦች የነጻነት ቀን የሚያቀርብ እርምጃ ነውና፡፡̋˝ የተባረከ አእምሮ!!!
ምዕራፍ ስድስት አዲሱ እውነታና የአማራው ህዝብ የውክልና ጥያቄ ጥሩ ነጥቦችን ያነሳል በአጭሩ አማራውን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች በመጀመሪያ ደረጃ አማራነታቸውን መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ በመቀጠል ስለ ብሔሩ ቆዳ ስፋት ኢኮኖሚ የትምህርት ሁኔታ ሁሉ ጠንቅቆ በማወቅ ለህዝቡ የተሸለን ኑሮ ማሰብ ይኖርበታል፡፡እንደሌላው ብሔር ብሄርተኝነቱን ለማጥበቅ ባይታደለም አሁን ባሉ ግዜያቶች ግን እራሱን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
በምእረፍ ሰባት እንደማጠቃለያ ቅርብና ሩቅ ላላችሁ አማራች በሙሉ ይላል አማራው ህዝብ አሁንም ጥሩ የማይባል ኑሮ እንደሚይኖር ይገልጻል፡፡የአማራው ህዝብ የብሄር ጭቆና ባይደርስበትም ነገር ግን እንደሌላው ህዝብ በኢኮኖሚ ብዙ ተጎድቷል፡፡ ስለዚህ ለዚህ እራሱን በመጠናከር መፍትሄ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡
እንግዲህ ኢትዮጲያውን ፍለጋ የሄድኩት ጉዞ አሁን መልስ አግኝቷል፡፡ ኢትጲያዊው ይህንን ይመስላል፡፡ኢትዮጲዊው ብዙ መልክ አለው ብዙ ብሔር ብዙ ሙዚቃ ብዙ ሀይማኖት አለው፡፡ኢትዮጲያዊው ብዙ ነው ትልቅም ነው፡፡ቢገባን ትልቅነቱ ለጥቅም ነው፡፡ ተቻችለንና ተግባብተን ስለ ብሔራችን ጥቅም በአግባቡ አውጥተን አውርደን በሌሎች የምትፈራ ጠንካራ ሃገር ኢትዮጲያን መገንባት እንችላለን፡፡ነገር ግን የእስራኤል ህዝብ ከአምላኩ እስኪስማማ ድረስ አርባ አመት በርሃ እንደተንከራተተው ይህ ብዙህነት እና እኩልነት እስካልገባን ድረስ በድህነትና እርስ በእርስ ጉሽሚያ ዘመናትን ማሳለፋችን የማይቀር ነው፡፡አንድ ጥሩ ምሳሌ ልንገራችሁ ሁለት ሰዎች ነበሩ አሉ፡፡ ሁለቱም ጠዋት ተነስተው መንገድ ጀመሩ፡፡ድንገት በአንዲት ጠባብ መንገድ ላይ ፊት ለፊት ተጋጠሙ፡፡አንደኛው አንደኛውን ዘወር በልልኝ ይለዋል አይ እኔ ዘወር አልልም አንተዘወር በል ይላል ደግሞ ሌላኛው፡፡አንዲ ሲነታረኩ ቀኑ መሸ ሁለቱም ፈቀቅ አላሉም፡፡ክረምት መጣ በጋ ሄደ አዚያው እንደቆሙ በላያቸው አደባባይ ተሰራ ዙሪያቸው በፎቅ ቤቶች ተገነቡ መንገዶች ተሰሩ ሃገር አደገ አነርሱ ግን ፈቀቅ አልል ብለው አዚያው እንደተፋጠጡ ቀሩ፡፡እኛ ስለ ብሔር ለዘመናት ስንነታረክ አለም ጥሎን ሄደ፡፡ ትልልቅ ሃገሮች በቴክኖሎጂ በኢኮኖሚ ከኛ ብዙ ራቁ ሄዱ፡፡ሃገራት ስለ ኒውክሌር በሚያወሩበት ግዜ እኛም እነርሱ በፈጠሩል መገናኛ ዘዴዎች እሩቅ ለሩቅ ስንሰዳደብ እንኖራለን፡፡ምናለባት ሰዎቹ እንደሚሉገት የአምላክ ቁጣ የሆን?እላለሁ፡፡ብቻ እኩልነታችን ተረገግጦ ብሔር ብሔረሰቦች ሰላማቸው ተጠብቆ ለማየት ያብቃን፡፡
ኢትዮጵያ ለሁሉም ሁሉም ለኢትዮጵያ!!!
በያቤፅ ካሳ ግችሌ
መስከረም 2008