ፓርላማ ለእንቦሳ! (የትነበርክ ታደለ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
….እንግዲህ 547 ጎጆ ወጪዎች ወደ ጎጆዋቸው ሊገቡ ነው!….. የአምስት አመት የኮንትራት ኑሯቸውን ይጀመራሉ!……547ቱ የፓርላማ አባላት ናቸው ጎጆ ወጪዎች!…..ደግ አደረጉ በደህና ጊዜ ስማቸውን አስቀየሩት!….. ባይሆንማ ኖሮ መደበኛው ስማቸው ‘የህዝብ እንደራሴ” ነበር!…. እነሱስ አውቀውበታል!….እንደራሴ ብሎ ነገር የለም!…. ጭራሽ የህዝብ እንደራሴ!….ሆሆ!. የምክርቤት አባል ብለው ማሻሻላቸው በእውነቱ ቀጣዩን አምስት አመት ማንም ህዝብ እንዳሻው እየተነሳ እንዳይጨፍርባቸው ይረዳቸዋል!….እንደራሳቸው ሆነው ገብተው ይወጣሉ!…… እስኪ እንመርቃቸው!…. ቆይ ከመመረቃችን በፊት ትንሽ ታሪክ እንመርምር…… የዛሬዎቹ 547 የምክር ቤት አባላት ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ 546 የተከበሩ ታላላቆቻቸው እዚሁ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር!…አንዱ የተከበሩት አባል ትንሽ ያስቸግሯቸው ነበር!….ክርክር ያበዛሉ!….ለድጋፍ የሚቆጠረውን የእጅ ብዛት ያጎድሉ ነበር!….እነሆ ዘንድሮ እንዲህ አይነት ቅይጥ የለምና….መስኩ ለምለም ነው!…ተራራው ቀንቷል!……እጅ እንደ አቋቋም ቤት የመሪጌቶች መቋምያ አንድ ላይ ይወጣል አንድ ላይ ይወርዳል!….ዜማውም ከበጋ እስከ ክረምት አንድ አይነት ነው!……እንደ አንድ ልብ መካሪ! እንደ አንድ ቃል ተናጋሪም አይደል መጽሀፉም የሚለው?!…… እንግድያሳ!?..ልዩነት የለም!..በሉ በሰላም ወደየወንበራችሁ ግቡ!…….
((እኛ ግን ሀገሬውን እንመርቃለን፣ ምድሪቱን ለሚገዛ አምላክ ጸሎታችንን እናቀርባለን!)
* ወገኖች ሆይ! በልዩነትም በአንድነትም ኑሩ!….. የሰው ሀሳብ አትጠየፉ!….እርስ በርስ አትዘላለፉ! አትናናቁ!….ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አትሂዱ!… አትፍሩ!…ማንም ከማሰብ ወይም ሀሳቡን ከመግለጽ አይቆጠብ!…ተከራከሩ!… በሀሳብ መሸነፍን እንደ ወርደት አትቁጠሩ!…ራሳችሁን ዛሬ ከሰለጠኑት ሀገራትና ህዝቦች ጋር እንጂ ቀድሞ ባልሰለጠነው ዘመን ከነበሩት ጋር አታወዳድሩ!…. ስትሰሩ ከልብ..ስታወሩም ከእውነት ይሁን!…. ተወያዩ፣ ጻፉ፣ አንብቡ፣ ተማሩ፣ ጠይቁ!…አንዳችሁ የአንዳችሁ እንደራሴ አድርጋችሁ ሹሙ!…ተያያዙ እንጂ አትላቀቁ!…
በሉ እንጸልይ!…
* አባታችን ሆይ ሀገራችንን ባርክ!…..እስከዛሬ የሆነብንን ሁሉ አይተሀልና እንግዲህ ዳግም እንዳይሆንብን በቃችሁ በለን… ማንም በስደትና በረሀብ አይሙት!….በስራ ማጣት የሚንከራተተውንም አስብ…..ክብራችንን መልስልን!…ፍቅራችንንም መልስ….እንግዲህ አንተ እንደሰው አይደለህምና ብዙ አንነግርህም!…. ዳግም ለስራ አንሳን! አለምም እንደሚያውቀን ይወቀን!