ለ ‹‹ቀጣይ›› ትግል ያሉትን አማራጮች እንፈትሽ // Girma Bekele
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የዚህ መነሻ የሆኑኝ ከማከብራቸውና የእስከዛሬውን የፖለቲካ ተሳትፎዬን ከሚደግፉና ከሚያበረታቱኝ (የፖለቲካ አባላትና አመራሮች፣በፖለቲካ ፓርቲ ያልታቀፉ ለውጥ ፈላጊ ደጋፊዎች፣ እንዲሁም በማሕበራዊ ግንኙነታችን የቅርቤ የሆኑ) ወዳጆቼ ያለአንዳች ስስትና ያልተሸረፈ ግልጽነት በተደጋጋሚ ጊዜ በተናጠል በግንባር፤ በኢንቦክስና በስልክ ከሚቀርቡልኝና አንዳንዴም በጋራ ስንወያይ ከሚነሱ በዋነኛነት በሁለት ሊጠቃለሉ የሚችሉ ኃሳቦች/ አስተያየቶች ናቸው፡፡
አንደኛው ወገን– ‹‹… 24 ዓመት ሙሉ የትብብር ትግል ሲወድቅ ሲነሳ ሳይዘምንና ሳይሳካ የዘለቀው የማይተባበረውን ለማስተባበር፣ ለዚህም ፖለቲካ በሚፈልገው እና የአገራችን ፖለቲካ በለመደው ቅመም ‹‹ ማስመሰልና መሸካከም፣ መገለባበጥና የዓላማ ጽናትን በወቅታዊ ጉዳዮችና ፕሮፖጋንዳ ጥቅም መሸርሸር፣ የፓርቲዎች በአመራሮች/መሪው መዳፍ ሥር የመሆናቸው….›› መካከል ያለውን ልዩነት ካለመረዳት/ካለመቀበል ነው፤ እንዲሁም የአገራችን የፖለቲካ ትግልና የህዝቡን የፖለቲካ አረዳድና ተሳትፎ ደረጃ ካለመረዳት፣… የተነሳ ነው፡፡ በመሆኑም ለአብሮነት መገጣጠም የተሞከሩት እንኳን ለመተባበር በራሳቸው ውስጥም አብረው ለመቆም ጽናቱ የሌላቸው፣ ኅልውናቸውም ከምርጫ ቦርድ ሰርቲፊኬት ውጪ የሌሉትን ግን ለማበላሸት/ለማክሸፍ የማያንሱትን ሁሉ በማካተት (በህዝብ ውስጥ የሌሉትን ፣ምንም የፖለቲካ ተጽዕኖ የሌላቸውን)ነውና ፣ተሳክቶ ቢሆንም የተገጣጠሙት ‹‹ድሪቶዎች›› ስለሆኑ ከ‹‹ድርቶዎች›› ስብስብነት አልፈው ለትግሉ የሚመጥን ቅርጽም ሆነ ይዘት ሊኖራቸው አይችልም ነበር፣ በቀጣይም አይችልም …. ፡፡›› ስለዚህ ይላሉ እነዚህ ወገኖች ‹‹ አሁን ላይ የፖለቲካው መድረክ ፓርቲዎች ራሳቸውን መርምረው አንድም ከገቡበት በጎ/ ቀና ግን የማይጨበጥ የትብብር ‹‹ ምኞት›› ወጥተው የራሳቸውን የውስጥ ዲሞክራሲና ውጤታማ የአመራርና አሰራር ሥርዓት ገንብተው ወደ ህዝብ ለመድረስ አደረጃጀታቸውን በተጨባጭ አስፍተው አዎንታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር ለትግል (ገቢራዊና ውጤታማ ትብብርን ጨምሮ) መቀጠል አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ እንኳን ለ40 ዓመታት ትክክል ተብሎ በተወሰደው ‹‹የሴራ ቦቶልካ›› ውስጥ እየተገላበጡ የቆዩትና የጭቃ ውስጥ እንቅልፍ ላይ ካሉት ቀርቶ ‹‹ወጣቶችም ›› ከሴራ ቦቶልካው በተጋቦሽ ተጠቂ እየሆኑ ነውና ከዚህ እስካልተላቀቁ/እስካልተፈወሱ ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብና አመራር ሊያመጡ ስለማይችሉ ሁሉም አርፈው ይቀመጡና አይቀሬውን ለውጥ ይጠባበቁ እንጂ ታጋዩንና ህዝቡን ለውጤት በማያበቃ ‹‹ትግል›› አላስፈላጊ ዋጋ አያስከፍሉ›› የሚሉ ናቸው፡፡
ሁለተኛው ወገን፡– ‹‹… ዛሬ ላይ የአገራችን ፖለቲካ የደረሰበት ደረጃ 24 ዓመታት ለመተባበር ከተሞከረበት በጣም የተለየ፣ እንዲያውም የ24 ዓመታቱ የትብብር ስብከትና ጥረት ‹‹ትክክል›› እንደነበር የተረጋገጠበት ነውና ከዚህ በፊት ከተደረጉት በመማር የትብብሩን ዓላማና የተዋናዮቹን ህልውናና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አጥርቶ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ትግሉ ከነበረበት ወደ አንድ ከፍ ያለ ደረጃ መሸጋገር የግድ ባለበት ጊዜ የተናጠል ፓርቲ ፖለቲካ መቀጠል ውጤታማ አያደርግም ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን ከፓርቲ ፕሮግራምና ዓላማ ያለፈ ፓርቲዎች የየፓርቲ ዓላማቸውንም ማስፈጸም የሚችሉበትን ከስልጣን ጥያቄ በመለስ አገራዊ የጋራ አጀንዳ ለመቅረጽ (እንደ ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ-/በቅድሚያ/ በራሳቸው ተቃዋሚዎች መካከል) የሚያስገድደውን ተጨባጭ ሁኔታ መቀልበስ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱ ውስብስብ ችግሮች እንኳን በአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ይቅርና 24 ዓመታት በአገዛዝ ከቆየው የገዢው ፓርቲ የመሸከም አቅም በላይ ነው፡፡ ›› ይላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ስለሆነም ‹‹ የትብብር ጥረት በጠራ ኃሳብ/ ለምን፣ በእነማን፣ እንዴት፣…/ ለሚሉት ጥያቄዎች ግልጽ መልስ በመስጠት በአንድ የጋራ ዓላማ እና አገራዊ አጀንዳ ላይ ከዚህ በፊት ከተለመዱት ግንኙነቶችና በምርጫ ቦርድ ከተፈቀዱት (ቅንጅት፣ግንባር ፣ውህደት) ውጪ የሆኑ እንደ ‹‹33ቱ›› ፣ ከዚያም ሊሰፉ የሚችሉ እንደ 86ቱ ግዮን ጉባኤ (ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውጪ ያሉ ባለድርሻዎችን የሚያካትት) ያሉ አማራጮችን ጭምር ከግምት በማስገባት በጋራ የሚቆሙበትን የትግል መድረክ ለመፍጠር ጥረቱ መቀጠል አለበት፣ ግንኙነቱ ዛሬ መጀመር አለበት ›› የሚል የመፍትሄ ኃሳብ ያቀርባሉ፡፡
ከነዚህ በተጨማሪ ከዋነኞቹ ጋር ሊጣመሩ የሚችሉ ‹‹እስከዛሬ ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል አልተደረገምና ሰላማዊ ትግል ‹‹ሀ›› ብሎ ስለሚጀመርበት እንዴትነት መወያየት /መነጋገር እንጂ ስለፓርቲ የተናጠል ፖለቲካም ሆነ የትብብር ትግል ማውራት ከንቱ ድካም፣ አላስፈላጊ ዋጋ መክፈልና በተለመደው መንገድ ተጉዞ/የሌለውን እንዳለ በሚቆጥር አካሄድ፣ባልጠራ ሃሳብ/ የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው፤›› ከሚለው በመነሳት ‹‹ፓርቲ በሌለበት ስለ‹‹ትብብር›› ማውራት ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ›› ነው›› እስከሚል የሚደርስ ነው፡፡ በሌላ በኩል ‹‹የአገራችን ሰላማዊ ፖለቲካ ትግል እስከዛሬ በስሜት እንጂ ዘላቂ መፍትሄ በሚያስገኝ የፖለቲካ አስተሳሰብና አመራር አልተመራም፤›› በማለት ‹‹የአገራችን ፖለቲካ ትግል ዋናው ችግር የአመራር እንጂ ትግሉም አለ፤ ፓርቲዎችም አሉና መፍትሄው በሳልና ብቃት ያለው አመራር ማውጣት ላይ ማተኮር አለበት ›› የሚሉም ይገኙበታል፡፡
ከነዚህ ውጪ ደግሞ ‹‹በአፍሪካ ምድር በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማሰብ አይቻልምና አርፋችሁ ተቀመጡ ፣ በ‹‹ሁለገብ ትግል ›› ለተሰማሩት ጋሬጣ/እንቅፋት አትሁኑ፣ ህዝቡን አታዘናጉት፣ተስፋችን አታደብዝዙት፤›› ከሚሉት በሁሉም ተስፋ ቆርጠው ‹‹መፍትሄውን ለፈጣሪ መስጠት ነው›› እስከማለት የደረሱም አሉ፡፡
ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች በሁለት ነገሮች ይስማማሉ፡፡ አንዱ – ህዝቡ በገዢው ፓርቲ አመራር ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ በመሟጠጡ አመጣጡ አሳሳቢ ቢሆንም በአገሪቱ ለውጥ አይቀሬ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ስለመሆኑ፤ ሌላው ህዝቡ በምርጫ ለውጥ ይመጣል የሚለው በተደጋጋሚ ስለከሸፈ ተስፋው ተሟጦ ያበቃ በመሆኑ በተቃውሞ ጎራው ከተለመደው የተለየ አስተሳሰብና አመራር ካልመጣ የህዝቡን ሰላማዊ ትግል ስሜት ማነሳሳትና ተሳትፎውን ማሳደግ አይደለም ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ እንኳ እጅግ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠይቅ፡፡ በዚህ ጉዳይ እናንተስ ምን ትላላችሁ? በቸር ያገናኘን//