የግንቦት 7 የእቃ እቃ ጨዋታ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ይህ አዲሱ 2008 የኢትዮጵያ አመት ከዋዜማው ጀምሮ ፤ በየሳምንቱ አዳዲስ ክስተቶችን እያሳየን ነው ። የሐረር ሰው “አጃኢብ” ይላል ፤ ነገር አልጥም ሲለው ። ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆኑኝ ፤ ከጁላይ 18 ቀን ጀምሮ እያስተዋልኩ ያለሁት ጉዳይ ነው ። ጁላይ 18 ቀን 2015 እ.አ.አ ፤ በኢሳት ሰበር ዜና ፤እንዲህ ሰምተን ነበር ። “ወደትግል ለመግባት የመሪዎችንም መስዋእትነት ይሻልና የግንቦት 7 መሪዎቹ ወደ ትግል ገቡ” ነበር የተባለው ።“የግንቦት ሰባት አመራር ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ትግል ሜዳ ገባ” ሲባል ፤ በሁሉም አቅጣጫ ጭብጨባው ሰማይ እንዲደርስ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም ። የጉዳዩን ታላቅነት ለመግለፅ ፤ የግንቦት ሰባቱ መሪ ደመወዛቸው ሁለት መቶ ሺህ ፤ ማእረጋቸው ፕሮፌሰር ፤ ችሎታቸው ከሰው የበለጠ ፤ እየተባለ ተጋኖ ተወጋ ። ወደዚህ ትግል የገቡትና በፎቶም ያየናቸው የግንቦት ሰባቱ ሊቀ-መንበር ብቻ ሳይሆኑ ፤የኢሳቱም ዳይሬክቲንግ ማናጀር ነበሩ ። ዜናውን ለማስታወስ ሊንኩን ይጫኑ ።
https://www.youtube.com/watch?v=MoRdJ9nGCYY
አሁን ደሞ ያ ሁሉ ጭብጨባ ተደርጎ ፤ ጉሮ ወሸባዬ ተዘፍኖ ሄደው ፤ ዛሬ የተመለሱት ዘማች አቶ ነአምን ዘለቀ ፤ እንደነገሩን የዘመቻ ተልእኳቸውን አጠናቀዋል። በዘመቱ በሁለተኛ ወራቸው በረኃ የገቡት ዘማች “ተልእኮዬን ጨርሻለሁ” ብለው ሲመለሱ ትንሽ ግር ማለቱ አልቀረም ። ተመላሹ ዘማች ፤ ገና እግራቸው አሜሪካን እንደረገጠ ፤ አንድ ወጥ የሆነ ቅጂ ፤ ቃለ- መጠይቅ በኢሳት ራዲዮ የተደረገ ነው ሲሉ በየድረ-ገፁ በተኑ ። ውለው ሳያድሩ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮም ቀርበው እንዲሁ ሌላ ቃለ-መጠይቅ አደረጉ ። የሚዲያውን መስክ የምንረዳ ሰዎች ይህን መሳይ ጉዳይ ሲከሰት ፤ “የሚዲያ ወከባ” እንለዋለን ። ያፈጠጠን ጉዳይ ለማስቀየስ ወይም ሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ ፤ በሌለ ጉዳይ ላይ አቧራ ማስነሳት ማለት ነው ። ላብራራ።
ተመላሹ ታጋይ የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የአርበኞች ግንቦት ሰባት የውጪ ጉዳይ ሃላፊ፤ ጓዜን ጠቅልዬ ለትግል ገባሁ ብለውን በሰበር ዜና ሰምተን ነበር። ሰው ምነው ለድል ሳያበቁን ተመለሱ ብሎ ህዝቡ መጠየቁ አይቀርምና ፤ አስቀድመው በየሜዲያው ላይ ፤ ወከባ መፍጠር ተገቢ መስሎ ታይቷቸዋል ። “ጉሮ ወሸባዬ ባልዘፈንሽ ፤ ዘንድሮ ባላፈርሽ” ይላል የአገሬ ሰው። ምናልባት ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ፤ በራሳቸው ፈቃድ ፤ ይሸወዱ እንደሆን ነው እንጂ ፤የሚዲያ ወከባው ፤ በነቃው ሕ/ሰብ ዘንድ ውኃ አልቋጠረም ። ዛሬ ሰው ፤ እንደድሮው ዝም ብሎ “ይሁን እስቲ” እያለ ማለፉን ትቶታል ። መጠየቅ ጀምሯል ። እኔም እንዲሁ አንዳንድ ጥያቄዎችን ላነሳ ነው ። በአሜሪካ ድምፅ ከተላለፈውም ሆነ ፤በኢሳት ተደረገ ፤ ከተባሉት ቃለ-መጠይቆች ፤ ባዶ የሆኑትን ስሜት የማይሰጡ ፤ አባባሎች ትቼ ፤ የተወሰኑ ነጥቦችን ቀጥዬ አነሳለሁ ።
ኤርትራ ጋር ተስማምተን ነው የምንሰራው ። ነው ያሉን ከዘመቻ ተልእኳቸውን ጨርሰው የመጡት ፤ የኢሳት ሜዲያ ዳይሬክተር ። ይህ አባባል በራሱ ፤ዋጋ የሚያስከፍልበት ግዜ ሩቅ አይደለም ። ከኤርትራ ጋር ያላቸውን ስምምነት አስታክከው ፤ የወያኔ አገዛዝን ፤ “ይህ ዘረኛና ዘራፊ አገዛዝ” ብለው ያወግዙታል የኢሳት ሜዲያ ዳይሬክተሩ ። ወያኔ ዘረኛ ስለሆነ ወይም ዘራፊ ስለሆነ ፤ ግንቦት 7 ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሻእቢያ ጋር መስማማት አለበት ? የተደረገውስ ምን አይነት ስምምነት ነው ? እኝሁ የዘመቻ ተመላሽ ሰው ይባስ ብለው ፤ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ ፤ ሻእቢያ ወይም ኤርትራ ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የStakeholderነት
( ባለድርሻ አካልነት) መብት አለው ሲሉ ተናግረዋል ። ይህን ሊያሰኛቸው የቻለ አንድ ምክንያት መኖር አለበት ። በኢትዮጵያ ጉዳይስ ሻእቢያ ምን አይነት ባለድርሻ አካል ነው ? ሁሉም ኢትዮጵያዊ የማወቅ መብት አለውና ስምምነቱን ግልጽ ልታደርጉት ይገባል ። አንባቢ ሆይ ፤ የራስዎን ፍርድ ይሰጡ ዘንድ ፤ የአሜሪካ ድምፁንም ሆነ የኢሳቱን ቃለ- መጥይቆች በዚህ ሊንክ ላይ ያዳምጡ።
እኔም ሆንኩ ፤ ሻእቢያን ከጠዋቱ በሚገባ የሚያውቁ ወገኖች ብሎም ከልብ አገራቸውን የሚወዱ ሰዎች ፤ ደግመን ደጋግመን ያስጠነቀቅነው ጉዳይ አለ ። ሻእቢያ የኢትዮጵያን መፈራረስ ሳያረጋግጥ እንቅልፍ ባይኑ አይዞርም ብለናል ።
ለዚህም ሻእቢያ ምክንያት አለው ። ኤርትራ ዛሬ አንድ ነፃ ሐገር ነች ። ኤርትራ ፤ ኢትዮጵያን ያህል ግዙፍ አገር ከጎኗ አስቀምጣ ሳትባንን የምታድርበት ሌሊት በፍፁም አይኖርም ። የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር ፤ውሎ አድሮ የባህር በር ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ይሆናል ። ስለዚህ ሻእቢያ የኤርትራን ነፃነት ለማረጋገጥ ፤ ኢትዮጵያ ብትንትኗ ወጥቶ በጥቃቅን መንግስታት እስክትከፋፈል ድረስ እንቅልፍ አይወስደውም ።
ግንቦቶች እንደግንቦት 7 ድርጅት ፤ ከሻእቢያ ጋር የመሰረታችሁት ፍቅር የራሳችሁ ሊሆን ይችላል ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፤ ከማንም ጋር ለመስማማት ግን ፤ ምንም አይነት ስልጣንም Mandate እንደሌላችሁ በግልፅ ልታውቁት ይገባል ። ተስማምታችሁ በምትሰሩበት ስምምነት ላይ “ባለ ድርሻ አካል” ተብሎ በአቶ ነአምን የተገለፀው ፤ ሻእቢያ ድርሻው ምን ያህል ነው ? ሻእቢያን የምናውቀው ሰዎች ደግሞ ፤ ምን ድርሻ ሊጠይቅ እንደሚችል መገመት አያቅተንም ። ኋላ ሂሳብ ማወራረድ እንዳይመጣ ፤ በኢትዮጵያ ላይ ያላችሁን ኢምንት የሆነ ድርሻ ፤ አግዝፋችሁ እንዳትመለከቱት እንመክራለን ። በኋላ ውርድ ከራሴ ።
አንባቢ እንዲያስተውለው የምፈልገው ጉዳይ የሚከተለው ነው ። ግንቦት ሰባት ሻእቢያን ባለድርሻ አካል ካደረገ ፤ ዋና ፅ/ቤታቸውን አስመራ ያደረጉት የኦሮሞ ነፃ አውጪና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባሮች ፤ የመገንጠል ጥያቄ ባቀረቡባቸው የኢትዮጵያ ግዝቶች ላይ ፤ ለሻእቢያ ምን ያህል ባለ ድርሻነት ሰጥተውት ይሆን ?
ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ በኢሳት ሜዲያ ዳይሬክትር አቶ ነአምን ዘለቀም ሆነ በዶክተር ብርሃኑ ነጋ የተሰጡት ቃለመጠይቆች ፤ እንደ አሸኛኘታችሁና ፤ እንደ ተመልሶ አመጣጣችሁ አስቂኝ ነው የሆነብኝ ።
ድሮ ልጆች ሆነን ከበደ ሚካኤል ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የአማርኛ መመሪያ መጻህፍት ያዘጋጁልን እንደነበር ብዙዎቻችን የምናስታውስ ይመስለኛል ። እነዚህ መፃህፍት በተረቶች የተሞሉ ስለነበር ፤ የዚያ ዘመን ልጆች ፤ በደስታ እናነባቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል ። ከነዚህ ተረቶች አንዷን በአጭሩ ላስታውስ ።
ቀበሮዋ በመንገዷ ላይ ስትጓዝ አንድ አጥር ግቢ ውስጥ የወይን ፍሬ ታያለች ። የወይን ፍሬው ያስጎምጃታል ። ቶሎ ወደ ግቢው ትገባና የወይን ፍሬውን ተንዠርጎ ከተሰቀለበት አልጋው ላይ ታየዋለች ። በጣም ጎመጀች ። አፏ ውኃ ሞላ ። ፍሬውንም ለማውረድ ወደ ላይ መዝለል ጀመረች ። ዘለለች ፤ ዘለለች ፤ ፍሬው ላይ ለመድረስ ግን አልቻለችም ። በመጨረሻ ፍሬውን እንደማታገኘው ስታረጋግጥ ፤ “ድሮም ዝም ብዬ ነው የለፋሁት ፤ ይህ የወይን ፍሬ እኮ አይጣፍጥም” ብላ መንገዷን ቀጠለች ፤ ይባላል ።
ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ ፤ ከዶክተር ብርሃኑ ነጋም ሆነ ከአቶ ነአምን ዘለቀ የሰማነው ፤ ኩብለላው እንኳን አሁን ሆነ የሚል ነው ። ጉዳዩን አስመልክቶ ዶክተር ብርሃኑ ትንሽ ቅመም ቢጤ ጣል አድርገውባታል ። “ይህ ክስተት ወደፊት አገር ውስጥ ሲገባ ቢሆን ኖሮ አደጋው የከፋ ይሆን ነበር” ፤ ብለዋል ። ይህች ቅመም ሻእቢያን እዘለኝ ተብሎ አገር ቤት ለመግባት ታስቦ እንደሆነ ፤ ሻእቢያ እንኳን እናንተን ሊያዝል ለራሱም መቆም ያቃተው ፤ እየፈራረሰ ያለ ፤ ለራሱ ህዝብ እንኳ መሆን ያቃተው መንግስት ነው ።
አዲሱ አመት መባቻ ላይ ፤ የንቅናቄውን ጥንካሬ ፤ የብዙሃኑን የመተባበር ጥያቄ የመለሰ ፤ እንዳይፈርስ መጠበቂያ የተደረገለት ፤ በፀና መሰረት ላይ የቆመ ፤ ሌላም ሌላም ያሉት ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሴፕቴምበር 9 ቀን 2015 ከንቅናቄው መመስረት በኋላ የሰጡትን ቃለ-መጠይቅ በሚቀጥለው ሊንክ ያዳምጡ ።
https://www.youtube.com/watch?v=p1SNkU4giLA
እንደገና ከሳምንት በኋላ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በሴፕቴምበር 9 ቀን 2015 ላይ ፤ 2ኛ ኢንተርቪው ከንቅናቄው መናድ በኋላ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ ደግሞ ፤ በሚከተለው ሊንክ ላይ ያዳምጡ ። ወደ ሊንኩ ከመሸጋገራችን በፊት ፤ በፊት አንድ ነገር ልበል ።
መርካቶን ከነግሳንግሷ የምታውቁ ፤ አለያም እንዴት የጩልሌ ሰፈር እንደሆነ የተነገራችሁ ወይም የስማችሁ ሁሉ የምታውቁት አንድ ነገር አለ ፤ መርካቶ መግዣ ፤ መርካቶ መሸጫ ። መርካቶ ማለት በቃ መግዛት መሸጥ ፤ መግዛት መሸጥ ማለት ነው ። ታዲያ የመርካቶ ሻጮች ፤ አንድ ነገር ለመግዛት ሄደህ እቃውን ሲሸጡልህ ፤ የእቃውን ጥራት ፤ ረዥም እድሜ ፤ የተሰራበትን አገርና ማቴሪያሉን ጭምር አጋነው ፤ ሰማይ አድርሰው ፤ዋጋውን ከፍ አድርገው ይሸጡልኻል ። ያንኑ እቃ ሳትጠቀምበት ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መልሰህ ግዙኝ ብትላቸው ፤ እቃው የማይረባ ፤ርካሽ ፤ የተሰራበት ማቴሪያልም እድሜ ቢስ ፤ ሰሪው አገርም ከአለም ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን ፤ ሳያፍሩ አይንህ ላይ ይነግሩሃል ። ይህን ምሳሌ የተጠቀምኩት ፤ ከላይ ያለውንና ቀጣዩን ቃለ-ምልልሶች እንድታነፃፅሩበት ነው ።
https://www.youtube.com/watch?v=ELft4T0NIZY
ነአምን ዘለቀ ከኤርትራ ዘመቻ መልስ ትግሉ እመር ብሏል ፤ ብለውናል ። አድማጮችዎን እንዴት ቢገምቷቸው ነው ?
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ፦
1ኛ) ተማምናችሁበት የነበረው ፤ የዴምህቱ መሪ ሞላ አስገዶም 683 የሚሆን ተዋጊ ጦሩን ይዞ ሄዶ ፤
2ኛ) ትብብሩ ተቋቋመ በተባለ ማግስት ከሞላ መሄድ ጋር ፤ ፍርክስክሱ ወጣ ፤
3ኛ) ጓዛቸውን ጠቅልለው ለትግል ወደ ሜዳ ገቡ የተባለልዎት ታጋይ ፤ እርስዎ ራስዎ ፤ ከሁለት ወር ቆይታ በኋላ ተልእኮዬን ጨርሻለሁ ብለው ተመልሰዋል
4ኛ) የአማራውና የአፋሮቹ ንቅናቄዎች ፤ መሪዎች ወጣ ብለው ፤ እንደተባባሪ ድርጅት ፤ አንዲት ቅንጣት መግለጫ እንኳ ባልሰጡበት ሁኔታ ፤ መኖራቸው እንኳ አይታወቅም ፤ ታዲያ እንዴት ነው ትግሉ እመር ያለው ?
በነገራችን ላይ የዴምህት ሰራዊት ከሞላ አስገዶም በኋላ አሁንም እየተናደ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለ ሰራዊት ነው።
ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ሞላ አስገዶም ይዞት የሄደውን ተዋጊ ኤርትራ ቀርቷል እየተባለ ከሚነገረው ፤ ሰራዊት ቁጥር ጋር በማወዳደር ፤ እዚህ ግባ የማይባል ነው ፤ በማለት መከራከሪያ ለማቅረብ ይከጅላቸዋል ። ለመሆኑ ፤ እነዚህ ሰዎች ፤ የዴምህት ሰራዊት ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ሊነግሩን ይችላሉን ? አንዳንድ ሰዎች ዩናይትድ ኔሽን 20 ሺህ ይገመታሉ ብሏል ይሉናል ። ዩናይትድ ኔሽን አስመራ ሄዶ ተዋጊዎቹን አስልፎ ቆጥሯል ? ወይስ ከዚህ በፊት ወደ አስመራ ሄደን ከነበርነው ሰዎች ከሚገኙ የፅሁፍና አንዳንድ የንግግር መረጃዎች ፤ ተነስተው ነው ይህን ግምት የሚሰጡት ? ይህም ቢሆን ግምት ነው እንጂ የተረጋገጠ ቁጥር አይደለም ። የአለም አቀፍ ድርጅቶች ፤ የሚሰጡት የግምት ቁጥር ሁሉ ፤ ትክክል ነው ብለን የምናምን ከሆነ ሞኝነት ነው ። የአንድ ነገር ቁጥሩ ከፍም ዝቅም የሚደረገው ፤ የአለም አቀፉ ድርጅት ፤ አሳዳሪ ከሆነው መንግስት ፤ ፍላጎት ጋር እየተጣጣመ ነው ።
ከዚህ ሌላ የሞላ አስገዶም ወደኢትዮጵያ መግባት ፤ ቀሩ የሚባሉት ተዋጊዎች ላይም ቢሆን የሚያሳድረው የስነ-ልቡና ተፅእኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም ። በታሪክ እንደምናስታውሰው ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረጉ ጦርነቶች ላይ ፤ የደርግ መኮንኖች እየከዱ ወደ ጠላት ወገን ይገቡ በነበረበት ወቅት ፤ አይደለም ወታደሩ ፤ ሲቪሉ ህዝብ ላይ ፤ ይፈጠር የነበረው የሞራል ውድቀት በቀላሉ የሚገመት እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ። የኢትዮጵያ ሰራዊትስ ብትንትኑ የወጣው ፤ ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ወደ ዚምባቡዌ ከኮበለሉ በኋላ መሆኑ እስካሁን ድረስ በብዙዎቻችን ዘንድ አሻራው ያልጠፋ ጉዳይ ነው ። ስለዚህ ዴምሕት አሁንም አለ እየተባለ የሚነገረውን ለማመን የምቸገርበት ደረጃ ላይ እገኛለሁ ። ሁሉንም በሂደት የምናየው ይሆናል ።
በመጨረሻም አቶ ነአምን እንዲያውቁልኝ የምፈልገው ፤ እኛ በሬ ወለደ ብለን ፅፈንም ፤ ተናግረንም እንደማናውቅ ነው ። በሬ ወለደ ብሎ ለመናገር ሻእቢያ የከፈለን ቤሳ ቤስቲን የለም ። እርስዎ በዳይሬክተርነት የሚመሩት ፤ ኢሳት ሜዲያ ግን ፤ ከሻእቢያ በየአመቱ $400,000 ሺህ ዶላር እንደሚያገኝ ፤ ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ ሾልኮ በወጣባቸው የድምፅ ቅጂ ላይ መስማታችን ፤ ፀኃይ የሞቀው ጉዳይ ነው ። ስለዚህ በሬ የሚያሳወልደው እየተከፈለው የሚሰራ ነው ።
በተጨማሪ አቶ ነአምን ዘለቀ ፤ እኛ እንድንመከር ያስተላለፉልን መልእክት ሰማሁ ። ያልተረዱትን ነገር እንዳለ ግን ልግለጽልዎ ። እኛ ሻእቢያን ሄደን አይተነው በተግባር ተመክረናል ። ይቻል እንደሁ ብለን እናንተን እየመከርን ነው ። ካልተቻለ ደግሞ እንዲህ እንደሰሞኑ የዘመቻ ጉዞዎ ፤ በየምክንያቱ ፤ በየሁለት ወራችሁ እየተመለሳችሁ የኔ ተልእኮ ይህ ነበር ፤ ያ ነበር ፤ ነገም ልሄድ እችላለሁ ፤ ልትሉን ትችላላችሁ ። ከዚያም የሚዲያ አቧራ በማስነሳት ልታስቀይሱ ትሞክራላችሁ ። እንዳው ለመሆኑ ግን ፤ ለምን መጀመሪያ ስትሄዱ ተልእኳችሁን አትናገሩም ነበር?
ባለፈው ሳምንት ፅሁፌ ላይ ፤ ከሚቀጥለው የኢትዮጵያውያን አዲስ አመት በፊት እንደምትመለሱ ተንብዬ ነበር ። እርስዎ ይህን በተናገርኩ በሁለተኛው ቀን ከአስመራ ከተፍ ሲሉ በእጅጉ ደነቀኝ ። ነገሩ ሁሉ የእቃ እቃ ጨዋታ ሆነ እንዴ ? ብዬም ታዝቤአለሁ ። ከዚህ ሌላ ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመለሱበትን ቀን ባለፈው ፅሁፌ ላይ ያስቀመጥኩት የጊዜ ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ የሚመለሱበትን ምክንያት ደግሞ ፤ ለእርስዎም ሆነ ለአንባብያን ልተንብይ ። በእቅድ የተያዘችው ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ፤ ሊመለሱ የሚችሉባት ምክንያት ፤ “የጤና እክል ደረሰብኝ” የምትል ትሆናለች ። ይህንን መረጃ ፤ ያገኘሁት ደግሞ ራሳቸው ዶ/ሩ የተናገሩትን በማጤን ነው ። መፃኢውን አዲስ አቧራ ደግሞ እንጠብቃለን ።
ሴፕቴምበር 26 2015 እ.አ.አ.
ላስ ቬጋስ ኒባዳ ።