የዴምህቱ መሪ ሞላ አስገዶም ከትናንት በስቲያ እስከ ዛሬ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ
ኢትዮጵያ ውስጥ አዲሱን የ2008 ዓ.ም አመት ለመቀበል ሁሉም በየቤቱ እንደአቅሙ ሽር ጉድ እያለ ነው ። በመላ ሃገሪቷ ሜዳና ሸንተረር ፤ ሸለቆና ሜዳ ፤ አደይ አበባው ፈንድቷል ። ለጥቅምት የሚሆነውን ማር ንቦች ለመቅሰም በነፃነት ካንዱ አደይ አበባ ወደሌላው ውር ውር ይላሉ ። አገር ምድሩ እንዳቅሙና እንደተለመደው በአሉን ለማክበር በየቤቱ ተዘጋጅቷል ። የጠላው ፤ የጠጁ ፤ የዳቦውና አንባሻው መአዛ የአገር ምድሩን አየር አጥኖታል ። በዚህ አውደ-አመት ዋዜማ ላይ ሻእቢያም የራሱን የአዲስ አመት ስጦታ ለአገራችን አዘጋጅቷል ።
ኤርትራ ውስጥ ተቋቋመ የተባለው “አገር አድን ንቅናቄ” ምስረታ ዜና ከተናኘ በኋላ ፤ ሞላ አስገዶም በሻእቢያ ተልእኮ ጠሰጥቶታል ። ተልእኮው ስድስት መቶ የሚደርሱ የዴምሕት ወታደሮቹን ይዞ ኢትዮጵያ ወስጥ በመግባት የአዲሱ አመት ዋዜማ ላይ አደጋ መጣል ነው ። በውጊያ ላይ እነሞላ አስገዶምን ሊከዱ ከሞከሩ በቅርብ የጥይት ርቀት ላይ የሚጠብቁ የሻእቢያ አልሞ ተኳሾች (Snipers) እንደተለመደው አብረዋቸው እንዲገቡ ተዘጋጅተዋል ።
ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አደጋ ለመጣል አመቺው ስፍራ ደግሞ በኦምሃጀር በኩል ወደ ሱዳን ግዛት በመግባት ፤ በፍጥነት ወደ ግራ በመታጠፍ ኢትዮጵያ ግዛት ላይ መዝለቅ ነው ። የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ከነመሰል ጥይቶቹ ፤ ለእያንዳንዱ የዴምሕት ተዋጊ ታድሎታል ። መትረየስ ተሸካሚዎች ከነዝናራቸውና ከነረዳቶቻቸው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፤ በሞላ አስገዶም የሚመራው ስድስት መቶ ጦር በሱዳን ድንበር በኩል ገብቶ በፍጥነት ወደኢትዮጵያ ግዛት እጥፍ ይልና አስፈላጊውን ጥቃት ይፈፅማል ። ይህ ለኢትዮጵያ የአዲሱ አመት ስጦታ ተብሎ በሻእቢያ ታስቦ ነበር ።
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ ሞላ አስገዶምም የራሱን የአዲስ አመት ምኞት ፤ በተግባር ላይ ለማዋል ሃሳቡን በልቡ ቋጥሮ ተዘጋጅቷል ። ከተዋጊዎቹም ውስጥ እንዲሁ የአዲስ አመት ህልማቸውን እውን ለማድረግ የተዘጋጁና ሚስጥሩ የተነገራቸው ተዋጊዎች ፤ ከሻእቢያ ነፃ የሚወጡበትን ደቂቃዎች ጭምር እየቆጠሩ ናቸው ። ይህ እቅድ ደግሞ የሞት የሽረት ጉዳይ ነውና በሁሉም ተዋጊዎች ደረት ውስጥ ልባቸው ክፉኛ ይመታል ። እቅዱ ሌላ አማራጭ የለውም ። ነጻነት ብቻ ።
የመጨረሻው ሰአት ደርሶ ሻእቢያ ትእዛዝ ሰጠ ። ትእዛዝ የተሰጠው ጦር ውስጥ ከየአቅጣጫው ግርግር ተፈጠረ ። ከዚህም ከዚያም ጥይት ተተኮሰ ። እነሞላ አስገዶምን በጥይት ርቀት እንዲጠብቁ ፤ ትእዛዝ የተሰጣቸው የሻእቢያ አልሞ ተኳሾች (Snipers) ፤ ከተዋጊዎቹ በሚተኮሱት ጥይቶች ሬሳቸው እዚህም እዚያም ጠብ ጠብ ማለት ጀመረ ።
በዚህ አይነት ፤ በአዲሱ አመት ፤ በኤርትራ ሱዳን ድንበር ላይ ፤ የሻእቢያን የአዲስ አመት ስጦታ ፤ ተዋጊዎቹ ዘፍ አደረጉት ። በዚህም የነጻነታቸውን ብስራትና የአዲሱን አመት ችቦ ኤርትራና ሱዳን ድንበር ላይ ፤ ተዋጊዎቹ በጥይት ለኮሱ ። ይህ በሞላ አስገዶም የሚመራ ጦር ቀደም ብሎ በሁኔታው ተዘጋጅቶበት ነበርና ሻእቢያዎቹን እዚያው አስቀራቸው ። ጦሩ መሳሪያውን እንደታጠቀም ወደ ሱዳን ገባ ። ይህን እቅድ ፤ ሞላ አስገዶምና ጥቂት የሻእቢያ ጠባቂዎችን ወሳኙ ሰአት ላይ እንዲጥሉ ፤ በሚስጥር ከተዘጋጁ ሰዎች በስተቀር ፤ ማንም የሚያውቅ አልነበረም ። ሆኖም አጋጣሚው ከተገኘ ከሻእቢያ ለማምለጥ ይማይመኝ ተዋጊ ኤርትራ ውስጥ የት ይገኛል ? ይህ ካልሆነ እንዴት ስድስት መቶ ተዋጊ ወታደር በአንድ ልብ ሆኖ ለማምለጥ ሊተባበር ቻለ ?
ሞላ አስገዶም በመራው በዚህ ዘመቻ ላይ ያልተመደቡና ሃሬና ካምፕ የቀሩ ተዋጊዎች ፤ ለዘመቻ በተላኩት ወንድሞቻቸው እድል እንዴት እንደሚቀኑ መገመትም ይቻላል ።
ከዚህ በፊት “ዴምህት የሻእቢያ የትሮ ፈረስ” በሚለው ጽሁፌ ላይ ድርጅቱ ውስጥ ያለውን መንፈስ እንዲህ ብዬ ገልጬው ነበር ።
“…… ያም ሆኖ ታዲያ በደንብ ላስተዋለ በ“ዴምሕት” ሰራዊት ወስጥ ያለ ሰብአዊ ስሜት-አልባነትና የዝምታ ድባብ እጅግ ጠንካራ ነው ። ይህ ሁኔታ በአርበኞች ግንባርም ወስጥ ያለ ቢሆንም እንደ “ዴምሕት” ግን ጎልቶ አይታይም ። የ “ዴምሕትን” ወታደሮች አይናቸውን አትኩረህ ስትመለከት፤ በተለይ የትግራይ ተወላጆቹ በአብዛኛው አንድ ስውር ጥቁር ጥላ ይከተላቸው ይመስል ባስቸኳይ አይናቸውን ይሰብራሉ ።…ለእርሻ ፤ለከብት ጥበቃ ፤ ውሃ ለመቅዳት ወይም ለገበያ በጠዋት ወይም አመሻሽ ላይ የወጡ ወጣቶችን እንደባሪያ እየፈነገሉ በፍጥነት ድንበር እንዲሻገሩ ያደርጓቸዋል ። ተፈንጋዮቹ እነማን እንዳፈኗቸው ወዴትስ እንደሚወስዷቸው ምንም አትነይ ግምት የላቸውም ።….ከአመት ላላነሰ ጊዜ በዚህ አይነት እንዲሰሩ ተደርገው ፤ ቅስማቸው ፤ ማንነታቸውና ሰብዕናቸው ተሰብሮ ተስፋ ቆርጠው ሳለ ለነዚህም ሻእቢያ አዲስ አማራጭ ይሰጣቸዋል ፤ የዴምሕት ወታደር መሆን ። ሌላ ተስፋም ስለሌላቸው የዴምሕት ወታደር መሆን ይገደዳሉ——-።
ይህን የመሰለ የሻእቢያ ጭቆና እንዴት የሰዎችን ልብ በአንድነት አያስር ? የሰው ልጅ በእግዚአብሄር የተሰጠው ፤ማንነቱና ሰብእናውና ተደፍሮ ቅስሙ ተሰብሮ መኖሩ ፤ እንዴት በአንድነት አያስተባብረው ?
ሞላ አስገዶም ኤርትራ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችል ሰው ነው ። ገንዘብም ሆነ የግል ፍላጎቱን ሊያሟላ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ያለው ሰው ነው ። መኪናም ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ሰው ነው ። ሆኖም ግን ኤርትራ ውስጥ አሻንጉሊት ሆኖ በሻእቢያ ትእዛዝ መንቀሳቀስና የመንፈስ ነጻነት ማጣት ከሁሉ የከፋ እንደሆነ ፤ ከዚህ ከሞላ አስገዶም ሁኔታ መገመት ይቻላል ።
ያለፈው የ2ሽህ 7 ዓ.ም የመጨረሻ ሳምንት ፤ የዜናውን አየር በሙሉ ሰበር ዜና በሰበር ዜና አድርጎት አልፏል ። በኢሳት ቴሌቪዥን እንደሰማነው ፤ ከሶስት ቀን በፊት ፤ የአራቱ ድርጅቶችን “አገር አድን ንቅናቄ” “ሰበር ዜና” ምሥረታ ተነገረን ። ሞላ አስገዶም ምክትል ሊቀ መንበር ሆኖ መመረጡንም አብሮ ተወሳ ።
በማግስቱ የአዲሱ አገር አድን ንቅናቄ አዲሱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሐኑ ነጋ ፤ ካለፉት ጥምረቶች ሁሉ በተሻለ ሁኔታ ፤ እንዳይፈርስና ዘለቂ እንዲሆንም አስፈላጊው መጠበቂያ ተደርጎለት አገር አድኑ ንቅናቄ ተቋቁሟል ሲሉ በቃለ መጠይቅ ላይ ገለፁ ። የዛኑ እለት ዶክተሩ ድምፃቸው በአየር ላይ ገና እየተንሳፈፈ እያለ ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ሰበር ዜና ሰማን ። የአዲሱ “የኢትዮጵያን አገር አድን የጋራ ንቅናቄ” ምክትል ሊቀመንበር ፤ አቶ ሞላ አስገዶም ስድስት መቶ ሰራዊት ይዘው መክዳታቸው ተሰማ ።
ስለ ኢትዮጵያ ዜናዎች በየቀኑ የሚከታተለው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፤ ከተለያዩ ሚዲያዎች ዜናውን ቀድሞ ሰማው ። ከዚህ በኋላ የኢሳት ቴሌቪዥንም ዜናውን በራሱ መንገድ አሰራጨው ። ለመሆኑ ኢሳት ከዚህ ሌላ ምን አማራጭ ነበረው ? ኢሳት ቴሌቪዥን ልሸፍነው ቢልስ በምንስ ሊሸፍነው ይችል ነበር ? እኛም ሆንን ሌሎች ታዛቢዎች እንዳስተዋሉት ፤ የአዲሱ “አገር አድን የጋራ ንቅናቄ” እውነተኛ ገፅታ በሞላ አስገዶም ፍንትው ብሎ ወጣ ።
ከላይ በገለፅኩት ዴምህት የሻእቢያ የትሮይ ፈረስ ፅሁፌም ላይ የዚህን “አገር አድን የጋራ ንቅናቄ” መቋቋም አስመልክቶ ፤ የሚከተለውን ትንበያ አድርጌ ነበር ።
“የአዲሱ ትብብር ሊቀ-መንበርነት ስልጣን ለቀድሞው ግንቦት 7 መሪ ይሰጣል ። የወታደራዊ አዛዥነት ስልጣኑን ደግሞ ዴምህት የ(ሻእቢያ የትሮይ ፈረስ) መሪ እንዲይዘው ይደረጋል ።…… የትብብሩ ፀሃፊነትም ለቀድሞዎቹ አርበኞች ግንባር አንድ አባል ሊጨመር ይችላል ። የውጪ ጉዳይ ሃላፊነቱ ስልጣን ደግሞ አዲስ ከአሜሪካ ከሄዱት እንግዶች ላንዱ ለቀድሞው ግንቦት 7 አመራር ሰው ይታከልለታል ።”
“የአገር አድኑ የጋራ ንቅናቄ” ከሊቀ-መንበሩና ከምክትል ሊቀ-መንበሩ ስልጣን በስተቀር ፤ የሌሎች ስልጣን ተዋረድ ባይገለፅም፤ ከሞላ ጎደል የሆነውም ይኸው ነው ። (ይህን “የጋራ አገር አድን ንቅናቄ” በተመለከት ተመልሼ ሰሞኑን በሌላ ጽሁፍ የምመጣበት ጉዳይ ይሆናል ።)
የኢሳት ቴሌቪዥን ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ በበተነው ዜና ላይ ፣ ሞላ አስገዶም የከዳው በጋራ ንቅናቄው ላይ ልዩነት ነበረው የምትል ዜናም አብራ ተሰንቅራ ተነግራለች ።
ጥያቄዎች ልጠይቅ !
ጥያቄ አንድ፦ ሞላ አስገዶም በጋራ ንቅናቄው ላይ ፤ ልዩነት ከነበረው እንዴት ተደርጎ የንቅናቄው ም/ሊቀመንበር ሆኖ ሊመረጥ ቻለ ? ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቃለ-መጠይቃቸው ላይ ፤ በመርህ ላይ የተመሰረተና ፤ እንዳይፈርስ ሆኖ የተዋቀረ ነው ያሉት ፤ ይህን በልዩነት ላይ የተገነባ ካብ ነው እንዴ ?
ጥያቄ ሁለት፦የተዋጊ ድርጅቶችን ባህርይ በሚገባ የሚያውቁና በውጊያ ልምድም ያለፉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ፤ “የዴምሕት” መሪና ተዋጊዎቹ ፤ የነጻነት ትግል ያደርጉ ከነበረ ፤ትግላቸው በመርህ ፤ በአላማና በእምነት ላይ የተመሰረተ አልነበረም ማለት ነው ? ወይስ የሚታገሉት በእምነት ሳይሆን ከኋላ ለሚገፋቸው ልዩ ሃይል ነበር ማለት ነው ?
ጥያቄ ሶስት፦ኢሳት ስለ ሞላ አስገዶም የነዛው ዜና አቢይ አላማ ፤ የሞላ አስገዶምን ሰብእና በማጠልሸት የእስፖንሰርን (ሻእቢያን) ሞራል ለመጠበቅ? ይህን ያሰኘኝ ጥያቄ ደግሞ የሚከተለው ነው ።
ጥያቄ አራት፦ የሞላ አስገዶም እናት ድርጅት “ዴምሕትም” ሆነ ፤አዲስ የተቋቋመው “አገር አድን ንቅናቄ” ምንም አይነት መግለጫ ሳያወጣ ፤ኢሳት የልዩነቱን ዜና ከየትና ከማን አገኘው ?
ጥያቄ አምስት፦ኢሳት በየጊዜው የሚያወጣቸው “ሰበር ዜናዎች” ገና ከመውጣታቸው ቀናት እንኳ ሳያስቆጥሩ ፤ለምንድነው ደጋግመው ፍርስርስ የሚሉት ?
ጥያቄ ስድስት፦ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ፤ የነካቸው ወይም የተጠጋቸው ሁኔታዎች ሁሉ ፤ ለምንድነው በየጊዜው አደጋ የሚያገጥማቸው ?
ከነዚህ ጥያቄዎች በኋላ ወደዜናው ልለፍ ።
ይህን ዜና በማጠናቅርበት ወቅት ሞላ አስገዶም የኢሳት ቴሌቪዥን ዜና እንዳለው ሳይሆን ፤የሚገኘው ሱዳን ግዛት ውስጥ ነው ። ወደ ሱዳን ከመግባታቸው በፊት የኤርትራን አልሞ ተኳሾች (Snipers) እዚያው ኤርትራ ውስጥ አደጋ ጥለው ገድለዋቸዋል ። ሞላ አስገዶም ስድስት መቶ የታጠቁ ወታደሮችን ይዞ ነው ወደ ሱዳን ግዛት የገባው ። ሱዳን በግዛቱ ውስጥ ያለፈቃድ የታጠቀ ጦር ይዞ የገባን ግለሰብ ሁኔታ በራሱ ህግ የሚያይበት ሁኔታውች አሉት ። የሱዳን መንግስትም እንደ መንግስት ማሟላት የሚገባው ፎርማሊቲዎች ስላሉት ያን ካሟላ በኋላ ነው ፤ በሞላ አስገዶምና በቀሩት ተዋጊዎች ላይ ፤ ህጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚችለው ። ስለዚህ ሞላ አስገዶም ፤ ይህን ጽሁፍ እስከማዘጋጅበት ጊዜ ድረስ የሚገኘው ሱዳን ውስጥ ነው ። ከዚህ በተጨማሪ ፤ ከስድስት መቶዎቹ ተዋጊዎች ውስጥ ፤ የተወሰኑ ተዋጊዎች ነፃነታቸውን ከሻእቢያ እንዳገኙ ካረጋገጡ በኋላ ፤ በተፈጠረ የደስታ ስሜት ምክንያት ጊዜ ሳያጠፉ በተዘበራረቀ መልኩ ገስግሰው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ።
ከሻእቢያ ያመለጡት የዴምህት ተዋጊዎች። ሱዳን ድንበር ላይ በትራክተር ተጓጉዘው ከነትጥቃቸው ከሱዳን ወታደር ጋር ።
ወንድሜ ሞላ አስገዶም አንተም ሆንክ አብረውህ ያሉ ተዋጊዎች ፤ እንኳን ከሻእቢያ ገሃነም ወጥታችሁ ለነፃነት በቃችሁ !!
አዲሱ አመት የሰላም እንዲሆንላችሁ ምኞቴ ነው ። እግዚአብሄርም የምታስቡትን ሁሉ ያሟላላችሁ ዘንድ እፀልያለሁ !!
ውድ አንባቢዎቼ እናንተንም እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ እላለሁ!!
ሰፕቴምበር 12 ቀን 2015 እ.ኤ.አ.
ላስ ቬጋስ ኒባዳ ።