የመንግስት ቅጥ ያጣ የኢንተርኔት ቁጥጥር በቻይና ለቋንቋ እድገት ስተዋጽኦ እያደረገ ነው። (የትነበርክ ታደለ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ቻይና ባለአንድ ፓርቲ መንግስት ያላት ሀገር ናት። የዛሬይቷን ቻይና የፈጠረውም አሁንም የሚመራትም አንድና አንድ ፓርቲ ብቻ ነው። የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ! ይህ ፓርቲ አንድ መሆኑ ብቻ ሳያንሰው የህዝቡን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በወጡ ወረዱ ሁላ የሚከታተላቸው ሁሉን አወቅ ፓርቲ ነው።
እናም ቻይናውያን በምንም የመንግስት ጉዳይ ላይ እንደፈለጉ ሀሳብ መስጠት አይችሉም። ሌላው ቀርቶ መንግስት ስለጫነባቸው የወሊድ ቁጥር እቀባ፣ ስለ ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ፣ ስለ ቤት ስራ ማህበራትና ሌሎች በቀጥታ የሚመለከታቸውን ነገሮች እንኳ እንዲች ብለው መነጋገር አይችሉም። ለምን? በቃ ተብሏል ተብሏል!!
መንግስት ታዲያ ይህን ሁሉ ለመቆጣጠር እንዲያስችለው እያንዳንዱ ቻይናዊ በኢንተርኔት መረብ የተነፈሳትን የፈሳትን ሁሉ ቁጭ ብሎ ያዳምጣል። ለምን? መንግስት ነዋ!!!
ቢሆንም ግን ቻይኖቹ የዋዛ አይደሉም የራሳቸውን የመግባብያ ቃላት በመፍጠር የልብ የልባቸውን በማውራት ላይ እንደሚገኙ ሰሞኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። በአራዳ ቃላት! በዚህ አመት ብቻ ከሀያ አምስት በላይ ቃላት ወደ መዝገበ ቃላት እንደተመዘገበ ተገልጿል።
ለምሳሌ፦ 1
በቻይና ፖሊስ በር ቢያንኳኳ የሚከፍትለት የለም። ያው በሰላም እንደማይመጣ ስለሚታወቅ። እናም ፖሊሶቹ ይህን ስለሚያውቁ የውሀ ቆጣሪዎችን ልብስ እየለበሱ ይመጣሉ። እናም አሁን ቻይናውያን በኢንተርኔት (በፌስቡክ) “ውሀ ቆጣሪ አለመኖሩን አረጋግጠሻል?፡ ብሎ መጠየቅ “ኢንተርኔትሽ እየተሰለለ ነው ወይ ወይም ፖሊስ ባካባቢው የለም ወይ?” እንደማለት ነው።
ምሳሌ፦ 2
ከጥቂት አመታት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ተጠርጣሪ እዝያው ጣብያ ውስጥ ተደብድቦ ሞቷል። ፖሊስ ምክንያቱን ሲጠየቅም “ከእስረኞች ጋር አባሮሽ ሲጫወት ነው።” ሲል መለሰ። ታዲያ አሁን ቻይናውያን “አባሮሽ መጫወትህ ነው!” ካሉ “ፖሊስ እየፈለገህ ነው ወይም ግንኙነታችን ተጠልፏል” ማለታቸው ነው። እናም እንዲህ እንዲህ እያሉ መንግስትና ዜጎቹ በኢንተርኔት አባሮሽ ይጫወታሉ።
ይህም ሆኖ ግን ከቻይና 1.3 ቢሊየን ህዝብ ግማሹ ኢንተርኔት የሚጠቀም ሲሆን 198 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ ዊቦ በተሰኘው የቻይናውያን ቨርዥን ትዊተር ላይ ሙሉ ግዜ ሰጥተው ይጠቀማሉ።