የወይንሸት እምባ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኤርትራ መንግስት ለረዥም ጊዜ የቁም እስረኛ ሆነው የከረሙትና ላለፉት 4 ዓመታት የደረሱበት ያልታወቀው የነፃነት ታጋዩ የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ልጅ፦ “አባቴን ታደጉኝ! ወገኖቼ ድረሱልኝ!” ስትል በለቅሶ ለኢትዮጵያውያኑ ጥሪ አቀረበች።

በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ወይንሸት ታደሰ ለመጀመሪያ ይህን ጥሪ ለህዝብ ያቀረበችው በታህሳስ ወር 2010 ነበር። በወቅቱም በግንቦት 97 ምርጫ በወያኔ ታጣቂዎች የተጨፈጨፉትን ሰማዕታት ለመዘከር በአምስተርዳም ለተሰባሰቡት በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ “የአባቴን ነገር መላ በሉኝ፤ ምን ላድርግ? መሄጃ መንገዱ ጠፋኝ፤ ወዴት ነው አቤት የሚባለው? እባካችሁ ወገኖቼ አባቴን ታደጉኝ!” በማለት ሲቃ በተመላበት ለቅሶ ጥሪ አቅርባለች።

ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ በቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንጋፋ አብራሪ ከመሆናቸው ባሻገር፣ በሀገር ውስጥ፣ በአሜሪካን ሀገርና በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት በአገኙት ከፍተኛ ሥልጠና፤ የጄት አብራሪዎች መምህር (pilot instructor) እንደነበሩ ይታወቃል።

ኮሎኔሉ የውጊያ አውሮፕላኖች የቴክኖሎጂ ሙያ ሀገራቸውን በማገልገል ላይ እያሉ ወያኔ/ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ እንደወጣ በፈፀመባቸው ይህ ቀረሽ የማይባል ተደራራቢ ጥቃት ሀገራቸውን ለቀው፤ አምባገነናዊውን የወያኔ አገዛዝ ለመታገል በኡጋንዳ በኩል አድርገው ወደ ኤርትራ አመሩ። እዛም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን በመመሥረትና በመምራት የአርበኝነት ተጋድሎአቸውን በብቃት፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሲወጡ የቆዩ ኢትዮጵያዊ ጀግና ናቸው።

በአምስተርዳሙ የሰማዕታት መታሰቢያ ላይ የተገኘውና ቀድሞ የአርበኞች ግንባር አባል እንደነበረ የገለፀው ወጣት ብርሀነ-መስቀል በበኩሉ እሱም አስመራ በነበረበት ወቅት ከእስራት ጀምሮ ሌሎች ስቃዮች እንደደረሱበት በመጥቀስ፤ “ኮሎኔል ታደሰ የአገዛዙ ሰለባ የሆኑት አንዲት ኢትዮጵያ የሚለውን ፅኑ እምነታቸውን አሳልፈው ስለማይሰጡ ለመሆኑ እናውቃለን” ብሏል።

በማከልም፦ “ሌሎች በተለያዬ ጊዜ የአርበኞች ግንባር አመራር ሆነው ተመርጠው የነበሩ ሰዎች ወደ ውጭ አገራት ለስብሰባ ሲላኩ በዚያው የውሀ ሽታ ሆነው ነው የሚቀሩት፤ አይመለሱም። ኮሎኔል ታደሰ ግን ከአንድም ሶስት ጊዜ አሜሪካ ለተለያየ ስራ መጥቶ አንዳንዶች በዛው እንዲቀር ሲመክሩት፦ “እምነት የጣለብኝን አርበኛ ትቼ የት ነው የምቀረው?” በማለት የተመለሰ ለአገሩ ከፍተኛ ፍቅር ያለውና እንደሌሎቹ በማሰፈራራትና በጥቅም ከግንባሩ አላማ ንቅንቅ የማይል ጀግና ነው” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷ ል።

አርበኛ ብርሀነ-መስቀል በማከልም በከፍተኛ ቁጣና እልህ ውስጥ ሆኖ፦ “የኤርትራ ደህንነቶች ኮሎኔል ታደሰን ለምን እንዳሰሩት እናውቃለን! አርበኛውን በዘር እየከፋፈሉ በማደራጀት የሚያደርጉትን አሰራር ስለተቃወማቸው ነው! ሌላ ጥፋት የለውም። ይህን ሁላችንም ከድሮ ጀምረን እናውቃለን። በጣም የሚያሳዝነኝና የሚያሳስበኝ ግን በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት እንታገላለን የሚሉ አንዳንድ ድርጅቶች በኤርትራ በኩል ለመሞከር ማሰባቸው ነው” ብሏል።

ሌሎች ተሰብሳቢዎች ደግሞ በተፈፀመው ድርጊት ከልብ ማዘናቸውን በመጥቀስ፤ “ኮሎኔል ታደሰ እንደ ታላቅ አርበኛነታቸው ይህ ድርጊት ሲፈፀምባቸው እንደኢሳት ያሉት ሚዲያዎች ዝም ማለታቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።

“ወያኔ ቢያስራቸው ኖሮ ሰማዕት፣ ጀግና፣ ሂሮ… እያልን እንዘምርላቸው ነበር፤ ምን ያደርጋል? ሻዕቢያ ስላሰራቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት ቆመናል የሚሉ አንዳንድ ሚዲዮዎች ስምታት መምረጣቸው ያሳፍራል” ሲሉም አንድ ተሳታፊ ለኢትዮ-ፎረም ዘጋቢ በሰጡት አስተያዬት የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።

የጥቁር አንበሳ ከፍተኛ ኒሻን ተሸላሚ የሆኑትና በተለይ በዚያድ ባሬ ወረራ ወቅት ሲያበሩት የነበረው ሚግ ሲመታ በፓራሹት በመውረድ ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው የተመለሱት ኮሎኔል ታደሰ፤ በወቅቱ የወጣትነት ዘመናቸው በፓራሹት ሲወርዱ ይሰማቸው የነበረው መጠነኛ ህመም አሁን ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ እየባሰባቸው መጥቶ እያሰቃያቸው እንደሚገኝ አርበኞች ጓደኞቻቸው ይናገራሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ የቅርብ መረጃ እንዳላቸው የጠቀሱ ወገኖች የተለያዩ ድርጅቶች ኮሎኔል ታደሰን ለማስፈታት ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቀጥታ ደብዳቤ ከመፃፍ ጀምሮ የተለያዬ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል።