የገሃነም ቅጥረኞች
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የመፅሐፉ አርእስት – “የገሃነም ቅጥረኞች”
ደራሲ – መሳይ ጫኔ ዘገዬ
የመፅሀፉ አይነት – የግጥሞች ስብስብ
የታተመበት ቦታ – አትላንት ጆርጅያ (አሜሪካ)
የታተመበት ቀን – ነሐሴ 2010 እ.ኤ.አ
የገበያው ተመን – አስር የአሜሪካ ብሮች
“ግጥም ሰዋዊ ባህርይ ነው . . .” ይለዋል እዉቁ ኢትዮጵያዊ የስነፅሁፍ ሊቅ ብርሃኑ ገበየሁ ይቀጥልና “ህፃናት በግጥማዊ ጨዋታ፣ በአሊ ሆይ አላሊ ሆይ፣ በምላስ አድጥ፣ በእንግቼ እንግቼ አፋቸውን ይፈታሉ አንደበታቸውን ያቀለጥፋሉ”። ይላል
ግጥም ተወዳጅ ያሚያደርገው ሲነገር የሚፈጥረው ዜማ ብቻ አይደለም። ያዝናናል፣ ያጥናናል፣ የጀግናን ልብ ያጀግናል፣ ፈሪን ያስደፍራል መልሶም ያስፈራል፣ ተፈጥሮን እንደ ስዕል ሲገልጥ የሰውኛ ስሜቶችን ያጭራል፣ ደስታን ሃዘንን፣ መደኽየትን መበልፀግን፣ መታመምን ጤነኛ መሆንን፣ ማፍቀርን መጥላትን አረ እንዲያዉም ሞትን ሁሉ የሚገድል ወብ ማሰሪያ ግጥም ነው። የተለያዩ አንጋፋ የኢትዮጵያ ሃያስያን ስለግጥም የራሳቸውን አስተያየት አኑረዋል።
– ሰለሞን ደሬሳ
“የግጥም ፈንታ የሰው ልጅ (የኑሮ አላማዉን ለማሳካት የሚያደርገውን) ግላዊ ምፍጨርጨር . . . ከዚህ አላማ ችላ ባይነት ጋር አያይዞ ማብላላት ይመስለኛል ይልና ቀጥሎ ማፎጨት እያፎጩ ተቃራኒዎችን ማጣመድ ተመሳሳዩችን ማለያየት። ከነግጭታቸው ላንዳፍታ እንደበራሪ ኮከብ የሚታይ ግልጥ መፍትሔ ማዋለድ . . .” እያለ ይቀጥላል።
– ገሞራው ሃይሉ ገ/ዩሐንስ
“የአካባቢ ልዩ ሃይሎች በመንፈስ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በሚያስከትሉት የሕሊና ጭንቀት የተለየ ሃሳብ በልቦና ውስጥ ይፀንሳል። ያም ፅንሰ ሃሳብ ሲብላላና ሲጋጋል ከቆዬ በኋላ በልዩ ልዩ መልክ ከአንደበት በኩል ይፈነዳል። አንደበት ሐሳብን ከሚገልፅባቸው አይነቶች ግጥም አንዱ ነው”።
ይህንን ያህል እጅግ በጥቂቱ ስለ ግጥም ካልኩ በኋላ ወደ ተነሳሁበት መፅሐፍ ግምገማ ልመለስ። የአንድን ገጣሚ የአእምሮ ልጆች አንብቦና ተረድቶ ትንታኔ መስጠት ምንኛ ከባድ ሥራ እንደሆነ ሳትረዱት አትቀሩም። የኔም የዛሬው ግምጋሜ ሁሉን የመፅሐፉን ጥንካሬና ግድፈቶች የሚነክስ አይሆንም። ከመደምደሚያዬ ለመጀመር የገሃነም ቅጥረኞች ወጣት ፀሓፊ በርታ ሊባል የሚገባው ደራሲ ነው።
ከላይ እንደ ጠቀስኩት የመፅሐፉ አርዕስት “የገሃነም ቅጥረኞች” የተሰኘ ሲሆን አንድ መቶ ስምንት ቅጠሎች ወይም ገፆች አሉት። ከመታሰቢያ ምስጋናና ማውጫ ውጭ መፅሐፉ በመቶ ሁለት ገፆች በስድሳ ዘጠኝ አርእስቶች የተሰደሩ ግጥሞችን አካቷል። በመፅሐፉ ጀርባ ስልጣኔ እንደፈጠረው ሰላሳ ሁለት የሚደርሱ በመፅሐፉ ላይ የታተሙ ግጥሞችን በሙዚቃ የታጀቡ፤ በፀሀፊው አንደበት ተነበው የተቀረፁ ሲዲ ተዘጋጅቶለታል።
በመፅሀፉ በአብላጫው ደራሲው በአጭር በአጭር የተቀኘባቸው ስራዎቹ ይነበባሉ። ይህ የፀሐፊው ፊርማ ሆኖ በአጫጭር አባባል አገር ያክል ትንታኔ መስጠት የቻለበት ጠንካራ ገፅታው ነው። ፀሐፊው በረጅምም መቀኘት እንደሚችል ለማሳየት ይመስላል እንደ የአንድ ዘመን ሺዎች (ገፅ 79) እና የአውዳ አመት ዉሎ (ገፅ 75) አይነት ግጥሞች ጣል ጣል አርጐልናል።
ኳስ ተጫዋች መጥኖ የለጋት ወይም የነረታት ኳስ መረብ ላይ ታርፋለች። ያነዜ ግብ ገባ እንላለን። ገጥሚም ቃላቶችን መጥኖና መዝኖ ሲያቀርባቸው ድምፅ ይፈጥራሉ። ይህም ለንባብ ምቾትን ለጆሮም የደስ ደስን ይፈጥራል። በዚህ ጊዜ ገጣሚውና ግጥሙ ያለመውን አደረስ ይባላል። ይህንን ለማጠንከር የተለያዩ አንጋፋ ሃያሲያን ምሳሌ ለመጥቀስ
“ታመህ ባልጠይቅህ ከቶ እኔን አትውቀስ
መሃሪው ይማርህ እስክመጣ ድረስ”። (ዩፍታሔ ንጉሴ)
“እንቢኝ አሻፈረኝ አሻፈረኝ እንቢ
መቅደስ ነው ሃገሬ ቅዱስ ነው ሃገሬ . . .” (ገ/ክርስቶስ ደስታ)
“ያ ዶሮዬ ጮኸ መንጋቱን ሊነገርኝ
በዛሬው ቀን ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ”። (ታገል ሰይፉ)
እነኝህን ግጥሞች ስንመለከት ገጣሚያኑ ቃላቶችን መጥነው ሰለአገጣጠሟቸው ለአንባቢ ሲጣፍጡ ለጆሮም የደስ ደስ ሰጥተው መልዕክታቸውን እንዳይረሳ አድርገው ያሻግራሉ። “የገሃነም ቅጥረኞች” ደራሲም ይህንን መላ አጠንቅቆ ተጠቅሞበታል። ገጣሚ ቃላት ከቃላት እያቁላላ ማዘፈን ይችላል። ቃላትን በቃላት ቆልፎ እስር ቤት ይፈጥራል፣ እስር ቤት ይከፍታል፣ ገጣሚ ቃላትን ያስፎክራል ያስጐደፍራል፣ ያስለቅሳል ያስቃል ሲለውም ደግሞ ዝም ያሰኛቸዋል። “የገሃነም ቅጥረኞች” መድበል ደራሲ በቃላት መጫወትና መፈላሰፍ ችሏል። የፃፈበትን ቋንቋ አሳምሮ እንደሚያወቀውና እንዳደገበት አስመስክሯል። የገሃነም ቅጥረኞች በአንድ ቁጭታ ተነባና ተለብልባ፣ ተውጣና ተሰልቅጣ ወደ ጐን የምትቀመጥ መድበል አይደለችም። ቀስ እያሉ እየቆነጠሩ የሚቅሟት ጊዜ ወስደው የሚያጣጥሟት ሥራ ነች። በዚች መድበል ከተካተቱት ግጥሞች አንዳንዶቹ ወዲያዉኑ ደስ የሚሉ ወዲያዉኑ መረዳት የምንችላቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ይህ ሞንጫሪ ምን አለ? አስብለው የሚስደምሙ ስራዎችን አካትቶል።
ለምሳሌ
“ስሄድ ተከትሎኝ – ስቆም አብሮ ቆሞ
ስሮጥም ሮጦ – ሳመልጥም አምልጦ
ከውልደት ጊዜዬ – ከድሮ ጀምሮ
በሄድኩበት ሁሉ – ሲከተለኝ ኖሮ
ዛሬ ግን ሆነብኝ- ስሜ ከዳተኛ
ፊቱን አዞረብኝ – ካፈሩ ብተኛ”። (“የገሃነም ቅጥረኞች” “ስሜ” የተሰኘው ቅኝት ገፅ 8”
ይህንን ቅኝት ለመረዳት ቆም ብሎ ማሰብ ወይም ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልገዋል።
በአንፃሩ
“አንዴ ከፊቴ – ከዛም ከኋላዬ – ለጥቆ ከጐኔ
ዙሪያዬን ሲዞረው – አካሌን ሲያካለው – አብሮኝ እንደዋለ
በእኔ እንደዋለለ
ሳርፍ አብሮኝ አረፈ
ቀኑን ሙሉ ከእኔ አብሮ እንደከነፈ”። (“የገሃነም ቅጥረኞች” “ጥላዬ” የተሰኘው ግጥም ገፅ 32)
ሲል ፊትን በፈገግታ አልብሶ እዉነትም የሚያስብል ቀለል ያለ ቅኝት ነው።
ስጀምር እንደገለፅኩት ከያኒ ለቃላቶች አስካክ ጠንቃቃ ነው። በ”ገሃነም ቅጥረኞች” ደራሲው ቃላቶችን ሲለጣጥፍ ችሎታውን ካሳየበቻው መስመሮች ምሳሌ ብጠቅስ
ገፅ 58 “ድሪያ” የሚለው ግጥም ውስጥ
“የስጋው ገበያ ደርቶ ብመለከት
ገባሁበትና ነፍሴን አጣሁበት”።
ሁለት ስንኝ ድንቅ ቅኝት የዘመኑን የአለማችንን ተውሳክ (የኤይድስን በሽታ) እጥር ባለ ቅኔ ዳሰሰው።
ገፅ 6 “ስምና ወርቅ” የሚል ግጥሙ
የቅኔ ዝቃጭ ወርቁ – የህብረ ቃል ጠለል ስሙ
የቤት መምቻ – መድፊያ ደሙ . . .” ይላል።
ገፅ 83 “የገሃነም ቅጥረኞች” የሚለው አርእስት ስር
ቂም ፀብን ቀብትቶ . . . .
በወንድሙ ቆዳ . . . .
በዜጋ ሲቀብጡ . . .
ያ መንቻካ ዘመን . . .
የሚጣፍጡ የቃላት አገጣጠሞችን ማንበብ ይችሏል።
“የገሃነም ቅጥረኞች” መድበልን እየገላለጥኩ ከበስተጀርባው የተለጠፈውን ሃያሲው በሙዚቃ እየታጀበ በልሳኑ ያንቆረቆራቸውን ግጥሞች ስሰማ፤ ገጣሚው ለግጥሞቹ ፍትህ የበየነው በእራሱ አንደበት ሲያነባቸው የተሰማኝና የሰጠኝ ደስታ ነው። ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው አንደኛው የመድበሉ ጠንካራ ገፅታ ለየግጥሞቹ የተመረጠው አርእስት እየሆነ የተሰለፈው መጀመሪያ ነው። በስነ ግጥም ስርዐት (ያልተቀመረ ደንብ ሊሆን ይችላል) ግጥሞቹን የሚገልፃቸው ትልቁ በትር አርእስታቸው ይሆናል። ይህ አርእስት (ሌላ ስም ይኖረው ይሆን?) ተብሎ የተሰየመው ነገር የግጥሙ ጭንቅላት፣ ፈርስ፣ ጭራና ማረፊያ በርጩማ መስለጡን ሊያሳብቅ የሚገባው መሳሪያ ነው። የ”ገሃነም ቅጥረኞች” ደራሲ ይህንን ቀመር በአብላጫው በቅጡ ጠብቋል እላለሁ። መፅሃፉ ውስጥ የሚታዩት አንዳንድ የቃላት ግድፈቶች ደራሲው ሊማርባቸው የሚገባ ግድፈቶች ናቸው።
ለማጠቃለያ ይህ ግምገማ የመፅሐፉን ጠንካራና ደካማ ጐኖች ባይዳስስም መጠነኛ በሆነ ጐኑ የመድበሉን ይዘትና የደራሲውን ችሎታ ይዳስሳል። “ግጥም ሰዋዊ ባሕርይ ነው . . .” ብዬ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ሊቅና መምህር ከብርሃኑ ገበየሁ ጠቅሼ ወደጀምርኩት ስመለስ፤ የ”ገሃነም ቅጥረኞች” ደራሲ በዚህ የግጥም መፅሐፍ ሰዋዊ ባህርይውን ማለትም ተፈጥሮ የሰጠዉን ፀጋ ተጠቅሞበታል። አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ የደራሲነት ማዕረግን ተጓናፅፎል። የወደፊት ስራዎቹ ከዚህ የበሰሉ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ።
(ለምሳሌ የተጠቀምኩባቸውን ማጠንከሪያዎች የወሰድኩት ብርሃኑ ገበየሁ ስለአማርኛ ስነ ግጥም መመሪያ ይሆን ዘንድ ካዘጋጀው ብርቅዬና ብቸኛ መድበል ነው)።
ገርመው መርጊያ፣ [email protected]