የስዬ “ምስጢሮች” (ከተስፋዬ ገብረአብ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ስዬ አብርሃ የፃፈውን መፅሃፍ አነበብኩት።

የተደጋገመውን ዝባዝንኬ እየዘለልኩ እንደምንም ጨረስኩት። የስዬ ወንድሞች የገዟቸው መኪኖች የሻንሲ ቁጥር ምንም ስለማያደርግልኝ እየነጠርኩ አልፌዋለሁ።

ስዬ ላይ አልፈረድኩበትም።

ከነበረበት የስልጣን ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የማንበብ ልምድ እንደሌለው ይታወቃል። በአናቱ የተፈጥሮ እብሪቱ ሲታከልበት ማንኛውም የተጠረዘ ነገር ሁሉ መፅሃፍ ሊሆን የሚችል ቢመስለው አያስደንቅም። ጥሩ አንባቢ ያልሆነ ሰው ለመፃፍ ባይሞክር ይመረጣል። የመፅሃፍ ጥብቅ ወዳጅ ያልሆነ ሰው በድፍረትና በወኔ ወደ መፃፍ ከገባ እንደ ስዬ አብርሃና ካሳዬ አራጋው አይነት ችግር ላይ ይወድቃሉ። ጥሩ አንባቢ ሆነህ ሳለም ታሪክህን የግድ ራስህ መፃፍ ላይኖርብህ ይችላል። ከፃፍክም ደግሞ ጥሩ አማካሪና አርታኢ መፈለግ ይገባ ይሆናል። ሂላሪ ክሊንተን ወይም ኔልሰን ማንዴላ ታሪካቸውን ራሳቸው አልፃፉትም። “ድብቅ ብእረኞች” (ghost writers) ተብለው የሚታወቁ ባለሙያዎች ከጀርባ አሉ። የጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ትረካ ጥሩ የተዋጣለት የፍቅረማርቆስን ብእር ስለተዋሱ ነው። ጃንሆይ እነዚያን ትላልቅ ጥራዞች ራሳቸው አልፃፉዋቸውም። መንግስቱ ሃይለማርያምም በስልጣን ዘመኑ ብእር ሲይዝ ዘባራቂ ነበር። ጋዜጠኛ ከበደ አኒሳ መንግስቱ የሚቸከችከውን ዝባዝንኬ በማቃናት መከራቸውን ያዩ ነበር። አንድ ጊዜ መንጌ ቴክሱ ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጉባኤ የሚቀርብ ንግግሩ ላይ፣ “መሃመድ ጋዳፊ ህዝብ ያስታወከው መሪ ነው” የሚል አረፍተነገር ጨምሮ፣ በመከራ ተለምኖ ነው ያቺ አረፍተነገር የተሰረዘችው።

ስዬ አብርሃ በጎ መካሪ ካጠገቡ ሳያስቀምጥ እንደ ኪም ኢል ሱንግ የህይወት ታሪክ አንድ ትልቅ ጥራዝ ጀባ ሊለን በቃ። ገንዘብ ካለ ምን ችግር አለ? ችግሩ ግን ተነባቢነትን በገንዘብ መግዛት አይቻልም። ስዬ አብርሃ ወንድሞቹ የገዟቸውን የጭነት መኪኖች የሻንሲ ቁጥር በመጽሃፉ ሲደረድር አማካሪዎቹ ዝም ብለው ማየታቸው ለምን ይሆን? የሆነው ሆኖ የስዬ አብርሃ መፅሃፍ ላይ ሂስ የማቅረብ ፍላጎት የለኝም። ጊዜም የለኝም። አንዳንድ ያስገረሙኝን ነጥቦች ብቻ በጨረፍታ ላነሳ ወደድኩ።

ለአብነት ስዬ አብርሃ እንዲህ ይለናል፣

ታምራት ላይኔ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ አለቃዬ ነበር። እኔ ሚኒስትር ነኝ። በመሰረቱ አንድ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስትርን ሊያዝዝ አይችልም።”

ቃል በቃል ባይሆንም ስዬ ይህን ይለናል። ይህችን ያነበበ ፈገግ ብሎ ከማለፍ ውጭ ምን ሊል ይችላል?

ገፅ 155 ላይ ታዲያ የራሱን አባባል እንዲህ ሲል ያፈርሰዋል።

“የብአዴን አመራር የራሱን የቤት ስራ ለመስራት የሚቸገር መሆኑን ከድሮ ጀምሮ አሳምሬ አውቃለሁ።”

እና ታዲያ የራሱን የቤት ስራ መስራት የማይችል ሰው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው የሾሙት?

እንዲህ ይለናል ደግሞ፣

“ትምኒት የቤታችን የመጨረሻ ልጅ ናት። እሷ ብቻ ናት ሴት ልጅ።”

ትምኒት እድሜዋ 34 መሆኑም ተጠቅሷል። በመቀጠል ደግሞ ስዬ ሌሎች ሁለት ወንድሞቹ እድሜያቸው ሁለቱም 33 መሆኑን ይገልፃል። ወንድሞቹ መንታ አይደሉም። እንዴት ሁለቱም 33 ሊሆኑ ቻሉ? ትምኒትስ እድሜዋ 34 ሆኖ ሳለ እንዴት የመጨረሻ ልጅ ሆነች?

ምላሽ የለውም። ፈገግ ብለህ ማለፍ ብቻ ነው።

ገፅ 231 ላይ ደግሞ እንዲህ ይለናል፣

እኔ ከእስር ቤት ስወጣ እናቴ እልልልልል አለች። እናቴን ከ6 አመታት በፊት ተምቤን ላይ ያየሁዋት ነበር። ተጎሳቁላ ጠበቀችኝ። ወዘተ…”

ስዬ አብርሃ ይህንን ማለቱን ረስቶት ገፅ 118 ላይ ደግሞ እንዲህ ይለናል፣

ፍርድ ቤት ስቀርብ እናቴ በትምኒት ተደግፋ መጥታ ነበር…”

በዚህ አያበቃም። ከመታሰሩ በፊት እናቱን ከወንድሙ ከምህረተአብ ቤት (ምህረተአብ የታሰረ ቀን) አግኝቷት እንደነበርና ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ እንደነበር ጭምር ይነግረናል።

ስዬ የሚዋሸው ነገር ለማሳመር ብሎ ይሆን፣ ወይ የውሸት ልማድ ስላለበት አላውቅም። እናቱን በተመለከተ ሶስት የተለያየ ነገር መናገሩ ግን ያስገርማል።
አማካሪዎቹንም ትዝብት ላይ ይጥላል።

ከአንባቢ ርህራሄ ለማግኘት ሲል የሚያሰፍራቸው ማስተዛዘኛ ነገሮችም አሉት።

ለአብነት ስለ ትምኒት ሲገልፅ፣ በ500 ብር ደሞዝ ተቀጥራ የምትሰራ፣ ከደሞዟ ሌላ ገቢ የሌላት ምስኪን ሴት ስለመሆኗ ሊነግረን ሞክሯል። ሱሬ እና ሸሚዝ ብቻ የነበረው የእህቱ ባል ባንድ አዳር እንዴት የሚሊዮን ብር ቼክ ለመፈረም እንደበቃ ግን አይነግረንም።

ገፅ 83 ላይ ደግሞ ስለ ባለቤቱ መኪና መነጠቅ አንስቶ ሲያወጋ፣ የትምኒትን በድህነት መኖር እንደነገረን ረስቶት፣ “እኔ ከታሰርኩ በሁዋላ ባለቤቴ የትምኒትን መኪና መጠቀም ጀመረች” ይላል።

የ500 ብር ደሞዝተኛዋ ትምኒት እንዴት አይነት የቁጠባ ዘዴ ተጠቅማ የ120 ሺህ ብር መኪና መግዛት እንደቻለች ግን አልነገረንም።

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ሲገልፅም እንዲሁ በርካታ አስቂኝ ወጎችን አግኝቻለሁ። ገፅ 19 ላይ ከኤርትራ ጋር ለተደረገው ጦርነት የኮማንድ ፖስት አባላት ተብለው የተመረጡ ሰዎችን ስም ይዘረዝራል። እነሱም፣ “ተወልደን ጨምሮ የማእከላዊ ኮማንድ ፖስቱ አባላት መለስ፣ ተፈራ፣ ፃድቃን፣ አባዱላ፣ አበበ (ጆቤ)፣ እና እኔ ነበርን” ይላል።

ስዬ ሳያውቀው ሕወሃት ለሚታማበት ዋና ጉዳይ ማረጋገጫ እየሰጠ ነበር። እዚያው በዚያው ገፅ 49 ላይ፣ “የአባዱላ ፓርቲ በመለስ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው” ሲል ያረጋግጣል። ብአዴንንም “የቤት ስራቸውን የማይሰሩ” ይላቸዋል። ደቡቦችን ደግሞ፣ “አባተ ኪሾን እውነቱን ካወጣህ ስልጣንህን እንድትቀጥል እናደርግሃለን አሉት” እያለ የሃገሪቱ አጀንዳ ሁሉ በህወሃት ፍላጎት የሚሰራ መሆኑን እያረጋገጠ፣ ያረጋገጠውን ደግሞ መልሶ ለማፍረስ ይሞክራል።

ከመነሻው ኮማንድ ፖስቱ ውስጥ አባዱላና ተፈራ እንዲገቡ የተደረገው አማራና ኦሮሞ በሃገር ደረጃ ተወክሎአል እንዲባል ለተመልካች ለማስመሰል መሆኑን ስዬ አያምንም። እውነቱ ግን ያ ነው። በኮማንድ ፖስቱ በሙሉ ትግሬዎች እንዲሆኑ የተደረገው በመላ ሃገሪቱ ዋና ጉዳዮች ላይ ብቸኛው ወሳኝ አካል ህወሃት ብቻ ስለሆነ መሆኑን ማስረጃ ማቅረብ አያሻውም። ስዬ ግን በተዘዋዋሪ ራሱን ያጋልጣል እንጂ ይህን ማመን አይፈልግም። በኤርትራ ጦርነት አመራር ሌላው ኢትዮጵያዊ ለመሞት ብቻ እንጂ አጀንዳው ላይ ለመወያየትና አሳብ ለመስጠት እንዳልተፈቀደለት ስዬ በተዘዋዋሪ አረጋግጦታል። ከዚያም ባሻገር ስዬና ተወልደ የመንግስት መዋቅር ውስጥ አልነበሩበትም። በምን ህግ? በየትኛው አሰራርና ደንብ? በየትኛው የህገመንግስቱ አንቀፅ መሰረት ይሆን ያ ማእከል የተዋቀረው?

የሃገሪቱ ቁልፍ ቦታዎች ሁሉ በትግሬዎች መያዛቸውን ስዬ ብዙ ቦታ በተዘዋዋሪ ገልፆልናል። አምቼ በተባለው ኩባንያ፣ የህግ አማካሪው፣ ኮንሰልታንቱ፣ የመንግስት ወኪሉ፣ ሶስቱም ትግሬዎች ናቸው። ኢዮብ ሃጎስ፣ ፀሃዬ ነጋሽ፣ እና ፍጡርዘአብ ይባላሉ። እነዚህ ሰዎች የያዙት ቦታ ደግሞ ግዢ ለመፈፀም ቁልፍ ቦታ ነው። ሁሉም እዚያው በዚያው በስልክ ያልቃል። በተለይም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ዝርፊያው በተሳካ መንገድ መቀጠል ችሎ ነበር። ገፅ 365 ላይ በተመሳሳይ በተዘዋዋሪ ራሱን ያጋልጣል። ስለ 600 መኪኖች ግዢ ለማንሳት ተገዶ ነበር። በዚያ ሰበብ ከባንክ ብድር ተፈቅዶላቸው በአንድ አዳር ባለሃብት ስለሆኑ ትግሬዎች ጉዳይ ግን ሳይጠቅስ ሸፋፍኖ አልፎታል።

ገፅ 22 ላይ ደግሞ፣ “ሰራዊታችን ወደ ኤርትራ የሚያደርገው ግስጋሴ ቆሞ ሻእቢያ ከመደምሰስ የተረፈበትን ስንክሳር ወደፊት ታሪክ ያወጣዋል” ሲል ገልፆአል። ሌላ ቦታም እንዲሁ፣ ሰንአፌን አልፎ የሄደው ጦር እንዴት እንደተገታ “እንቆቅልሽ ነው።”

ምን ይሆን ይሄ እንቆቅልሽ? ምን ይሆን ይሄ ስንክሳር?

ስዬ ለምን እዚያው ፍርጥርጥ አድርጎ ሳይነግረን ቀረ? እንቆቅልሹስ ከማን ነው? ስዬ የላይኛው ኮማንድ ቀለበት ውስጥ በአመራር ደረጃ ላይ ነበረ። እንዲያውም መለስ በድምፅ ተሸንፎ፣ ‘የመለስ ደጋፊ ካሱ ይላላ ብቻ ነበር’ ብሎ ራሱ ስዬ ይነግረናል። እና ይሄ እንቆቅልሽ እና ስንክሳር ምን ይሆን? ለምን ስዬ ሳይነግረን ዘለለው? ለመቼ ነው የሚያቆየው? ‘አላውቅም’ ሊል አይችልም። እሱ ነው የላይኛው ከፍተኛ አካል። “መለስን ወይም ኢሳይያስን አሊያም ሲአይኤን ፈርቶ ነው የማይናገረው” ልንል አንችልም። ታዲያ አስመራን ከመቆጣጠር ያገዳቸው እንቆቅልሽና ስንክሳር ምን ይሆን? ስዬ ይህን ሳይነግረን መፅሃፉን ዘጋ። ወደፊትም አይነግረንም። ‘ለምን?’ ቢባል ምንም ስንክሳርና እንቆቅልሽ አልነበረም።

ይህን ጉዳይ፣ “የደራሲው ማስታወሻ” ላይም ገልጬዋለሁ።

በቀጥታ ለመናገር ስዬ እየዋሸና እያጨበረበረ ነው። በጦርነቱ የተቻላቸውን ሁሉ ሞከረዋል! ስላልተቻለም ተመልሰዋል! ሌላ ሰበብ ማብዛት ለምን አስፈለገ? ወያኔ ሰራዊት ባረንቱ ከገባ በሁዋላ ሰራዊቱን አስከትለው 5000 የትግራይን ገበሬ ለዘረፋ አሰማርተዋል። በዚህ ዘረፋም ጀበናና ማርገብገቢያ ብቻ ሳይሆን ማሳ ላይ የነበረ ጥቅል ጎመን ሳይቀር በአህያ እየጫኑ ወስደዋል። ከዘረፋው በሁዋላ ሰራዊቱ ተመልሶ ወጣ። ስለዘረፋው ባረንቱ ሄጄ ከገበሬዎች የሰማሁ ሲሆን፣ “ከእነዚህ ጋር ሲወዳደር የደርግ ሰራዊት ጨዋ ነበር።” ብለው ነግረውኛል።

ውጊያውን በተመለከተ ወደፊት ይፋ የሚሆን ምንም እንቆቅልሽ የለም። ቢኖር እስካሁን እናውቀው ነበር። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ስዬ የማያውቀው ምንም መረጃ የለም። የሻእቢያ የውጊያ ስልት በወያኔም ሆነ በደርግ በግልፅ ይታወቃል። ሻእቢያ ሃይል ሲበረታበት አንድ እግር በመሬት እያደረገ ማፈግፈጉ አዲስ ስልት አይደለም። ስለዚሁ ጉዳይ መንግስቱ ሃይለማርያም ደጋግሞ ሲናገር ተሰምቶአል። “በየቀኑ በሚደረግ ውጊያ ተራራ እየተነጣጠቅን ስንዋጋ ነው የኖርነው።” ብሏል። ደርግ ከመውደቁ በፊት ሻእቢያ ምፅዋና ከረንን በጦነት ይዞአቸው መልሶ ለቆአቸዋል። የሰው ሃይል እጥረት ያለባቸው ተዋጊዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ስዬ በመፅሃፉ ይህን በግልፅ ከመናገር ይልቅ አንድ ትልቅ የሚያውቀው ምስጢር ያለ ለማስመሰል ሞክሯል።

“ይህን ምስጢር፣ ይህን ስንክሳር፣ ይህን እንቆቅልሽ ወደፊት ታሪክ ያወጣዋል” ሲል ፃፈ።

ምንድነው ያ ምስጢር?

“መለስ ዜናዊ የተባለው ሰው ለሻእቢያ ምስጢር ያቀብል ነበር!? ኢሳይያስና መለስ በምስጢር ይገናኛሉ? የኢትዮጵያን ሰራዊት ያስጨረሰው ሆን ብሎ መለስ ዜናዊ ነው? የሲአይኤ እጅ አለበት? ወይስ ሌላ ወሬ አለ?”

ስዬ አብርሃ ያልነገረን ምስጢር የት ይሆን ተፈልጎ የሚገኝ? በርግጥ ምስጢር ካለ መለስን ለማጋለጥና እድሜውን ለማሳጠር ጊዜው አሁን ነው። የነፃነት ትግሉን ያጣድፍልናል። ስዬ ያልነገረን፣ “ጊዜ ይመልሰው” የተባለው መረጃ ከተጋለጠ፣ ለመለስ ድጋፍ እየሰጡ ስቃያችንን ያራዘሙ አጎብዳጆችም ወደ ሰፊው ህዝብ ጎራ እንዲመጡ ባገዘ ነበር። በተቀረ ስለ እንቆቅልሽ ማውራት መብት ያለው ከአዛዥነቱ ቀለበት ውጭ ያለ ብቻ ነው።

መቼም የስዬ መፅሃፍ ሳይታወቀው አንዳንድ ምስጢር ማሾለኩ አልቀረም።

አንድ ቦታ ላይ ስዬ፣ “ሾፌሬ ታሰረ። መኪናዬንም ተነጠቅሁ” ሲል ይገልፃል።

ሾፌሩ ስሙ ተከስተ እንደሚባልና የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑንም ይጠቅሳል። እንዴት ነው ነገሩ? ስዬ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የለበትም። የመከላከያ አባልም አይደለም። ሰራዊቱም የፓርቲ አባል አይደለም። እንዴት ነው ታዲያ ስዬ በመከላከያ በጀትና የሰው ሃይል የሚጠቀመው? የወያኔ ህገመንግስት መቼም በየቦታው እርቃኑን እንደቀረ ነው። እና ስዬ ልቡን ሞልቶ የመፅሃፉን ስም፣ “ፍትህና ዳኝነት” ሲል ሰይሞታል።

ሌላ ቦታ ደግሞ ሌላ ታሪክ ያመጣል።

በታሰረበት እለት ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ግርማይ ማንጁስ የተባለውን የፖሊስ አዛዥ፣ እንዴት እንዳስፈራራውና እንዳንቀጠቀጠው ሊነግረን ይሞክራል።

ስዬ ማን ስለሆነ ይሆን ያን ማድረግ መቻሉ? ምን እንድናስብ ይሆንን ይሄን የሚነግረን? “ቤተኛ ነኝ” ለማለት ነው? ምን ለማለት ነው?

ሌሎች ኢትዮጵያውያን ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ፖሊሱን በሃይለቃል አይናገሩም። እሱ ያን በማድረጉ፣ “እንዴት ያለ ጀግና ነው!?” ብለን እንድናደንቀው ይሆን የፈለገው?

“ፖሊስ ጣቢያው በር ላይ ቆምኩና ‘ስዬ በር ላይ ቆሞአል።’ ብለህ ንገረው አልኩት። ወዲያው ግርማይ ማንጁስ ወደ ውስጥ እንድገባ ፈቀደ” ሲል ይነግረናል። ታምራት ላይኔን ግን ትግሬ ፖሊሶች በጥፊ ይመቱት ነበር። ይህ ልዩነት እንዳይኖር የሚደረገውን ትግል ስዬ የተረዳው አይመስልም። ሱፐርማን እና ስፓይደርማን ለመሆን ይሞክራል። እንደ ሸዋዚንገርም ጡንቻውን ያሳየናል። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀው ማንም ማንንም የማያስፈራራበት፣ የህግ የበላይነት የሚከበርበት ስርአት እንዲመጣ አይደለምን?

ሌላ ቦታ ደግሞ EFFORT ከአምቼ 173 መኪኖች መግዛቱን ይገልፅልናል። ገንዘቡ ከየት መጣ? ይህንን አይናገርም።

እንደ EFFORT ስማቸው የደበዘዘና ከመቃብር በላይ ያሉ ለስሙ የአማራውና የኦሮሞውም የንግድ ድርጅቶችም ነበሩ። እነሱ በቅናሽ ከአምቼ መኪና ሊገዙ ጠይቀው እንዳልተፈቀደ ግን ትንፍሽ ሳይል አልፎአል። የዲንሾ ሊቀመንበር የነበረው ዱባለ ጃሌ በራሱ ስልጣን ለዲንሾ መኪኖች በመግዛቱ፣ በስዬ አብርሃ የውርደት ስድብ ደርሶበት ለአእምሮ መቃወስ መብቃቱን “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ መተረኬ ይታወሳል። በግልባጩ ስዬ ወንድሞቹ በቅናሽ መኪና መግዛታቸው ህጋዊ መሆኑን ሊያሳምነን 500 ገጽ ፃፈ።

ለEFFORT የተገዙት 173 መኪኖች የመገጣጠሙ ስራ ለመስፍን ኢንጂነሪነግ ስራው መሰጠቱንም ስዬ ፅፎአል። መቀሌ ላይ የተተከለው የመስፍን ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ስራውን የጀመረባቸውን ግዙፍና ውድ ማሺኖች ከየት እንዳመጣ ግን ስዬ አልገለፀም። ወደፊትም አይገልፅም። የፋብሪካው ከፊል ማሽኖች መንግስቱ ሃይለማርያም ለመከላከያ ኢንጂነሪነግ ደብረዘይት መኮድ ላይ ያከማቻቸው ማሽኖች መሆናቸውን የምናውቅ ከጥቂት በላይ ነን። እነዚህን ማሽኖች በሌሊት እየጫኑ የመውሰዱን የዝርፊያ ስራ ያስፈፀመውና የመራው ስዬ ራሱ ነው።

“ለከፈልነው ደም የሚገባን ድርሻችን ነው” ሲል አልነበረም እንዴ?

መስፍን ኢንጂነሪንግ ሲመረቅ፣ “ይህ ብረታ ብረት ለከሰከስነው አጥንት ምትክ ነው” ብሎ የተናገረው ማነው?

መንግስቱ ሃይለማርያም በብድር ያመጣቸውን ማሽኖች እዳ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍሎታል። ንብረቱ ግን ወደ EFFORT ነው የተላለፈው። EFFORT የመንግስት ተቋም አይደለም።

እዚህ ላይ ታዲያ ፍትህ የታለ? ስዬ ይህን መሰል ነገሮችን በመፅሃፉ ሳይነካ ዘሎታል። ይህን ስለ መሰለ ራሱ ስላስፈፀመው የወያኔ ዘረኛ ቅሌት አንድ ገፅ እንኳ የይቅርታ ቃል ሳይተነፍስ ስለ ወንድሞቹ ንብረት ጉዳይ 500 ገፆች መከመሩ ሳያስደምመኝ አልቀረም።

ሌላ ቦታ ደግሞ ስለ ወንድሙ ስለ አሰፋ አብርሃ ታስሮ መቆየት ሲፅፍ፣

“አሰፋ አብርሃ እስር ቤት እያለ እናታችን ብትሞት መዘዘ አለው?’ ብዬ ለመለስ ዜናዊ መልእክት ላክሁበት” ይለናል።

እና ብዙም ሳይቆይ አሰፋ አብርሃ ተፈታ። የሚደንቅ ነው። እስኪ ይሄን ገልበጥ አድርገን እንመልከተው? ብርቱካን ሚደቅሳ እስር ቤት እያለች እናቷ ቢሞቱስ? መዘዝ የለውም?

“ስዬ ማን ስለሆነ ነው መለስን እንዲህ ማስፈራራት የቻለው?” ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ “ስዬ አሁንም ህወሃት ነው” የሚል ይሆናል። ለመሆኑ ስዬ ለ“ትግል ጓዱ” ለብርቱካን ያን አይነት የማስፈራሪያ መልእክት ለመለስ ለምን ሳይልክ ቀረ?

ምክንያቱ ግልፅ ነው። የብርቱካን መታሰሯ ሳይሆን መፈታቷ ሆነ መዘዙ። የብርትኳን መፈታት የዘገየው መለስን የሚያስፈራራ እንደ ስዬ ያለ “ጀግና” ስለጠፋ ይሆን? “መዘዝ አለው!” ብሎ መለስን በሃይለቃል የሚናገረው ሰው ጠፋ? ስዬ እንዲያ እያለን ነው። የቤተሰብ ጥል እና የባዳ ጥል መሆኑ ነው እንግዲህ…

በህወሃት ዙሪያ በሃብት የተተኮሱ ቤተሰቦችና የኢትዮጵያ ህዝብ የሁለት አለም ሰዎች ለመሆን መብቃታቸውን ማስተዋል ይቻላል። አጀንዳዎቻችን ተለያይተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ “ፍትህ” ሲልና እነ ስዬ “ፍትህ” ሲሉ ለየቅል ቢሆኑም ተመሳስለው ለመምጣት እየጣሩ ይመስላሉ።

ስዬ 6 አመታት ቢታሰርም ከህወሃት የአስተሳሰብ ቀለበት አለመውጣቱን በዝባዝንኬ ከታጨቀው መፅሃፉ ማጤን አይገድም። አሁንም ወደዚያው ጀምሮት ወደ ተቋረጠበት የአገዛዝና የቅንጦት ህይወት ለመመለስ የቤት ስራውን እየሰራ ነው። ሰይጣን ካገዘው ይሳካለት ይሆናል።

ርግጥ ነው፣ ስልጣን ያባልጋል።
ካልተሳሳትኩ ለገሰ አስፋው ላይ አንድ ቀልድ ተቀልዶበት ነበር መሰለኝ፣
“ጮማውን እንዴት ለመዳችሁት?” ሲባል፣
“በመከራ” አለ አሉ።

የወያኔ የላይኛው ቀለበት ከባዶ ወደ ቢሊዮን ተተኩሰዋል። ይህ ሃብት አስደንግጧቸዋል። ሰው በጠባዩ ሃብት ሲበዛበት ስግብግብና ጨካኝ እየሆነ ይሄዳል። ሞቡቱ ሴሴሴኮ የጭካኔና የስግብግበነት ምሳሌ ነበር። ጁሌስ ኔሬሬ ባዶ እጁን ወደ ምድር መጣ፤ ባዶ እጁንም ወደ መቃብሩ ሄደ። ስሙም የተከበረ ሆነ። እግዚአብሄር ለእኛም እያለቀስን የምንቀብረውን መሪ ይስጠን።

(ጸሀፊውን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል [email protected])