ምን ነው ኢሳት ኸይ! የሚል የጠፋ – ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በተጠቃሹ “የዜና” ማሰራጫ ማዕከል ስራዎች ዙሪያ ስጽፍ ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም። በተለያዩ ጊዜያት ማዕከሉ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን በተመለከተ የሚያሰራጫቸው ሚዛናቸው የሳቱና ግልጽነት የሚጎድልባቸው ዘገባዎቹንና ሐተታዎቹን በማስመልከት ተደጋጋሚ ጽሑፎች ለንባብ መብቃታቸው የሚታወስ ሆኖ በርካታዎቹ ሃያ አራት ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከስፍራቸው እየተነቀሉ ለአንባቢያን እንዳይደርሱ ተደርገዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዜና ማሰራጫ ማዕከሉ ግድፈቶቹን አምኖ ራሱን ከማስተካከልም ይልቅ “ሰምቶ ማሳለፍ!” የሚልዋትን ፖለቲካ ተጋርቶ ባለበት ሲረግጥ እየተስተዋለ ነው። ለነገሩ ከስህተቱ በመማር ፈንታ ጠቋሚ (ለመልካም) ጣቶችን መቁረጥ የሚቀናው የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ መንግሥትም እንደሆነ ያልበጀ መርህ ለሌላም ቢሆን ይጠቅማል የሚል እምነት የለኝም። ሥርዓቱ ዛሬ ለሚገኝበት አጣብቂኝና አስተዳደራዊ ዝቅተት የዳረገ የማያዛልቅ ዲቃላ ፍልስፍና መሆኑን ልብ ላለ ዜጋ ሁሉ የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ እንጅ የሌሎቹም ዕጣ ፈንታ/መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይቸግርም።
እውነት ነው የሕዝብ ጆሮና ዓይን መሆን ማለት “የሕዝብ ጆሮና ዓይን ነን!” በማለት የሞፈከር ያክል ቀላል ነገር እንዳይደለ አንድ የሰከነ ባለ አእምሮ ሰው የማይስተው መሬት የረገጠ እውነታ ለመሆኑ የሚያከራክረን አይመስለኝም። ከላይ ወደ ታች የሚወርደውን ቀጭኝ ትዕዛዝ ከማስተላለፍና ከማስተጋባት አልፈው ለሕዝብ ጆሮ የሌላቸው ደንታ ቢሶች በወቅታዊ ስመ አጠራራቸው “ልማታዊ” በመባል የሚታወቁ መንግስታዊ ልሳኖች/መገናኛ ብዙሐን ኢቲቪም ሆነ ዋልታ ዓይናቸው አፍጥጠውና ደረታቸው ግልብጠው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ነን!” ማለታቸው እስካልቀረ ድረስ ሌላውም እንደሆነ በፊናው “ብቸኛ አማራጭ፣ ገለልተኛ፣ ፈር ቀዳጅ … ” እና የመሳሰሉት ታቤላዎች እየለጠፉ ጡሩንባ መንፋቱ ሕጋዊ ባይሆንም ዝርው መብታቸውን ተጠቅመው የማለት መብታቸው የተጠበቀ ነው። እዚህ ላይ አንድ መገናኛ ብዙሐን ራሱን በፈለገው መልክና ቅርፅ እየቃኘ ማስተዋወቁ አያጣላንም፤ የጽሑፉ ዓላማም አይደለም። በጥቅሉ ከስሙ ባሻገር በተገለጠው ፍሬው/በስራዎቹ አይጠየቅበትም ማለት ግን አይደለም።
በአጭሩ “የዜና” ማዕከሉ (ኢ.ሳ.ት) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በማስመልከት ለሚያስተላልፋቸውና ለሚያሰራጫቸው ዘገባዎች በተመለከተ ግን በምንጭ ደረጃም ሆነ የተፋለሱ መረጃዎችን በመቀባበል ረገድም ስውር ዓላማ ካለው ራሱን የቅዱሳን ማኅበር በማለት ከሚጠራ ትውልድ ገዳይ አገር አጥፊ ስመ መንፈሳዊ ድርጅት መተሻሸቱ እስላቆመ፤ ቀና ቀናውን ማሰብንና መስራትን ትቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን በበሬ ወለደ ዜናና ሐተታ ለማተረማመስ፣ ሁከትንና ሽብርን ለመፍጠር አለሁ ማለቱ እስካልተወ ድረስ ጉዳዮ ተወዳጅነት የማትረፍና ቲፎዞ የመሰብሰብ ጉዳይ አይሆንምና “የዜና” ማዕከሉ ምእራብ ከምስራቅ ሰሜንም ከደቡብ እንደሚርቅ ጽንፍ የረገጠ መሰረት አልባ ዘገባዎችና ዜናዎች በማስመልከት በቃሉ እንደ ተፃፈ እንዲሁ እሬት እሬት ቢለንም እውነት እውነቱ መነገሩ የማይቀር ነው።
እንደ ማንኛውም መገናኛ ብዙሐን ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ አንዳች ነገር አይባል/አይዘገብ አይነት ጭፍን መልዕክት እያስተላለፍኩ አይደለም። በእርግጥ ለማለት የተፈለገው ምን እንደሆነ አንባቢም ሆነ ተደራሲው ያጠዋል የሚል እምነትም የለኝም። ነገሩ ግልጽ ለማድረግ የተፈለገ እንደሆነ ግን ግመልን የሚያክ እውነት ወደጎን እየተተወ ትንሽዋን በማስፋት፣ በመለጠጥ፣ በመወጠርና ከዚህም አልፎ የሌለውን በመፍጠር የሚሰራ የግብር ይውጣ ስራ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይቁም! ነው። ሰው አይሳሳትም አይባልም። ሰው ስራ እስከሰራ ድረስ ስህተት መስራቱ የማይቀር ነው። በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳይ ከአንዴም ሁለቴ ሶስት አራት ጊዜ ተደራራቢ ጥፋት መፈጸም ግን ስህተት ሳይሆን ንቀት ነው የሚባለው።
ይኸውና November 11 2012 “የዜና” ማእከሉ ያሰራጨው “ዜና” እንደሚከተለው ይነበባል “እርቅን ለማውረድ በቀጠለበት በአሁን ወቅት የዓቃቤ መንበረ ፓትሪያርኩ ጥረት የሚያሰናክሉ ወገኖች መነሳታቸው ተገለጸ” ይላል። መቼም ኢሳት ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግን ወገን ብሎ እንደማይጠራ የታወቀ ነው። ታድያ ይህ ወገን የተባለ አካል ማን ነው? በማለት የጠየቅን እንደሆነ “… ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ በራሱ እየተንቀሳቀሱ ነው ከሚለው ወቀሳ ጀምሮ አቡነ መርቆርዮስን አንፈልግም እስከሚለው ድረስ ከመንግስት ጋር ቅርበት ያላቸው ጳጳሳትና ሌሎች ወገኖች ችግር እየፈጠሩ መሆናቸው ተረጋግጠዋል::”ከንባቡ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ችግር ፈጣሪዎቹ ቀደም ብሎ “ወገኖች” ተብለው የተጠሩ ሊቃነ ጳጳሳት ጨምሮ ማንነታቸው በግልጽ ያልሰፈረ ግለሰቦች/ሃይሎች የሚያጠቃልል ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ማኅበረ ቅዱሳን” ከመጋረጃ በስተጀርባ ተቀምጦ ከሚዘውራቸው የሁከትና የበሬ ወለደ ልሳኖቹ መካከል የሆነው “አንድ አድርገን” በመባል የሚታወቀው መካነ ድር ጥቅምት 30 2005 ዓ.ም“በፓትርያርክ ምርጫ ላይ መንግስት ተጽህኖ ለማሳደር የራሱን ቡድን መሰረተ“ሲል በዘራው የፈጠራ ወሬ እንዲህ ብሎ ነበር“የቀድሞ ፓትርያርክ ከአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ ብዙዎችን እያነጋገሩ ካሉት ነገሮች ውስጥ ስለ ቀጣይ ፓትርያርክ ምርጫ እና እርቀ ሰላም ይገኙበታል ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በፌደራል ጉዳዮች አማካኝነት የራሱን ተጽህኖ ማሳረፍ የሚልች 7 ሰዎችን የያዘ ቡድን በሚስጥር መመስረቱ ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ሰዎች ተሰምቷል“በማለት የራሱን ሐጢአት በሌሎች ሲያሳብብና ሌላውን ሲወነጅል ከጥቂት ቆይታ በሃላ ደግሞ ኢሳት “የማህበረ ቅዱሳን” ደጀን በመሆን ይህንን አሉባልታ በመጋራት መጠነኛ የቃል ማሻሻያም በማድረግ “በዜና” መልክ ይዞ ለመቅረብ መድፈሩ በራሱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ያለውን ቁልጭ ያለ ንቀት የሚያሳይ ነው።
“ዜና” አንባቢው አክሎ “.. አቃቤ መንበር ብጹእ አቡነ ናትናኤልና በርካታ ጳጳሳት በብጹእ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲመለስ የሚፈልጉ ቢሆኑም መንግስት አዲስ ፓትሪያሪክ አንዲመርጡ እየገፋ መሆኑን እየተሰማ ነው” ሲል እንዳነበበው “የዜና” ማእከሉ ምን ያህል ከእውነት እየራቀ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መሪዎች አንድ አለመሆንና አለመግባባት የተነሳ በሚፈጠረው ሁከትና ግርግር የልዩ ጥቅም ተካፋይ/ተጋሪም አስመስሎታል። (ሙሉውን የዜናው ይዘት ለማድመጥ የሚከለተውን ሊንክ ይጫኑ (ESAT DC Daily News November 11 2012 https://www.youtube.com/watch?v=ukRoOPD2cbM&feature=plcp)
በመሰረቱ የአገር ቤቱ ሲኖዶስ አዲስ ፓትሪያሪክ እንዲመርጥና እንዲሾም እየገፋፋና ቅጥረኞች አሰማርቶ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እያተራማመሰ እንዲሁም ሌቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እያመሰ ያለው ማን ነው? ምን ነው ሕዝብ በተጨባጭ የሚያውቀውን እውነት በጠራራ ፀሐይ ለማድበስበስና የጥላሸት ለመቀባት የተነሳችሁ? ለመሆኑ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱም ወደ ቀድሞ አንድነትዋ እንይመለሱ የማይፈልግ ማን ነው? እውነት በእውነትነቱ መነገር: መዘገብና ማታተት ማንን ገደለ ነውና መንግሥት ባልዋለበት የሚወነጀለው? እውነት የማይጥማችሁ ከድርጅቱም አላማ ፈጽሞ የማይገጥም ከሆነም የሀገሬ ሰው “ዝም ያለ አፍ ዝንብ አይገባበትም” እንዲል ሁሉንም ሳይሉና ሳይነካኩ አርፎ መቀመጥ ነው:: በተረፈ ግን በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በኩል እየተኬደ ያለውን ጸረ ሰላም አካሄድ ዋና አቀንቃኝና አራጋቢ በሁከቱ ቀዳሚ ተጠቃሚ የሆነው ራሱን “ማህበረ ቅዱሳን” ብሎ የሚጠራ የጥቁር ራስ ስብስብ ሆኖ ሳለ በመንግስት ማላከኩ ዝናብ የሌለው ደመና ይፈጥር እንደሆነ እንጂ ዝናብ አያወርድም።
የመረጃ እጥረት ያለባችሁ/ድርቀት የገጠማችሁ እንደሆነም ስለምትዘግቡት ዘገባም ሆነ ሰፊ ሽፋን ሰጥታችሁ ስለምታትቱት ሐተታ በመጠኑም ቢሆን ግንዛቤ ይኖራችሁ ዘንድ ይህን ላስታውሳችሁ። ወቅታዊና ነባራዊው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሃይማኖት መሪዎች ሁኔታ በተመለከተ በተለይ በአሁን ሰዓት እዩኝ እዩኝ ማለት ያበዙና ፎቶ ግራፋቸው በየጎዳናው እየበተኑ የሚገኙ መነኮሳት (“ሊቃነ ጳጳሳት“) ምንነት ሐቁ ቁምነገር ኑሮባቸውና የሚረቡ ሆነው መንግሥት የሚያክ ግዙፍ አካል የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች ሳይሆኑ በአንድም በሌላም መንገድ ሳይገባቸውና ሳይገባቸው የተቀራመቱትን ወንበር ለመጠበቅ ሲሉ ብቻ የመንግሥት ድጋፍና እርዳታ በብርቱ የሚሹ: ደጅም የሚጸኑ ለመሆናቸው ግልጽ ሳደርግላችሁ በአክብሮት ነው። በተረፈ የሐሰት አባት ከሆነው የራሱ ነገር የሌለውና ራሱንም እንደ ባለጸጋ የሚጠራና የሚቆጥር ሌባ፣ አታላይ፣ ደም አፍሳሽና ነፈሰ ገዳይ ከሆነው ከዲያብሎስ ጋርም በደም ቃል ኪዳን ተሳስረውና ተማምለው አብረው ለመስራት የማይመለሱ ከማንም በላይ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት የሚያስፈልጋቸው ሕዝብን በሃጢአት፣ የጥፋት በሆነው መንገድ እየመሩ የሚገኙ ህይወት የሚያስፈልጋቸው የደረቁ አጥንቶች ናቸው።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail [email protected]
United States of America
November 16, 2012