ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን! ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አይተጣጡም በየትም ሥፍራ መገናኘታቸው የማይቀር ነው። በለቅሶ ቤት፣ በገበያ፣ በቤተ – መቅደስ፣ መንገድ ላይ ኢየሱስና አይሁድ የእስራኤል ምድር “ውበት” ናቸው። አይሁድ እርስ በርሳቸው – “ከእኛ በላይ አዋቂ!” ሕዝብ ጋር ሲደርሱም “እኛ እናውቅልሃለን!” ማለታቸው አይተዉም። ኢየሱስም እንደሆነ የመጣበት ዓላማ ነውና ጉድጓድ ቢቆፈር፣ ሰይፍ ቢሳል፣ የረቡኒ መዓት ቢሰባሰቡ ስምና ጺም በልቡ ቦታ አይሰጥም ነበርና (የአይሁድ መምህራን አንዱ መለያቸው ረጅም ጺም፣ ዘርፋፋ ቀሚስ ነው) “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ፣ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፣ አንተ ልጅ አይዞህ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ፣ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፣ እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ ገበሬውም አባቴ ነው …” እያለ አገር ምድሩን ሲያስስ የአይሁድ ቤተ- መቅደስ የሸረሪትና የአይጥ መቀለጃ እስኪሆን ድረስ ባዶውን በማስቀረት የምድሪትዋ ሕዝብ ኢየሱስ ሲከተል ያኔ ነበር የአይሁድ ዓይን ደም መቋጠር የጀመረው።
አይሁድ ለተንኮል ሴረኞች ከመሆናቸው በላይ ሰውን ለመግደል ጾም ጸሎት የሚይዙ ሱባዔ የሚገቡ ዓይነት ሰዎችም ናቸው። ይህ መታወቂያቸው እንዳለ ሆኖ ኢየሱስ በቀን መልካም ዘር በዘራበት ሰፈር እየተገኙ በሌሊት እንክርዳድን መጣል ሆነ ብለው የተያያዙት ተደራቢ ስራቸው ነበር። ኢየሱስ በሚያስተምርበት ስፍራዎችንም በመገኘት የሕዝቡ ብቸኛ ጋሻ፣ ጠበቆችና ተቆርቋሪዎችንም በመምሰል በአደባባይ የራሳቸውን ጥያቄ የሕዝብ ጥያቄ በማስመሰል ዳህጸ ልሳን ጠብቀው ከሕዝቡ ልብ ለማስወጣትና በሮማ መንግሥት ጥርስ ውስጥ ለማስገባት የተለያዩ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በመሰንዘር ኢየሱስን ማዋከብ ሌላ ሁነኛ ዜድያቸው ነበር። ከማን ጋር እንደገጠሙ በውል ባይረዱም!
ይሄው እንደ ወትሮው ተገናኝተዋል (ጌታና አይሁድ) እስቲ ከውሎአቸው መካከል በጥቅቱ አንዱን እንመለከት፥ በዚህ አጋጣሚ ከጽሑፉ ባህሪ የተነሳ አንባቢ ውስጠ ወይራውን አንብበው ይረዱ ዘንድ ሃላፊነት መሸከማቸውን በአክብሮት ለማሳሰብ እወዳለሁ።
ዮሐንስ እንደ ጻፈው፥ (ዮሐ. 8፥ 31-59)
ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፥ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።
አይሁድም፥ መልሰው የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት
ኢየሱስ መለሰ፥ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። የአብርሃም ዘርመሆናችሁንስአውቃለሁነገርግንቃሌበእናንተአይኖርምናልትገድሉኝትፈልጋላችሁ። እኔበአባቴዘንድያየሁትንእናገራለሁ፤እናንተምደግሞበአባታችሁዘንድያያችሁትንታደርጋላችሁ።
አይሁድም መልሰው፥ አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት።
ኢየሱስም፥ የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው።
አይሁድም፥ እኛስከዝሙትአልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት።
እዚህ ስፍራ ላይ ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ሲል ስለሚናገረው እውነት ከራሱ ማንነት ጋር የተቆራኘ ለመሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር እውነትን ማወቅ ኢየሱስን ማወቅ ነው ይህ ደግሞ ከሃጢአት ባርነት ከሰይጣን እስራትና ከዚህ ዓለም ቀንበር የሚፈታ ነው። ለእናንተም የሚያስፈልጋችሁ ይህ ነው ይኸውም እኔን ማወቅ ነው ይላቸዋል። ታድያ በሌላቸው ነገር ሁሉ መኮፈስን ከደማቸው ጋር የተወሃዳቸው አይሁድ እንደ ልማዳቸው ዘራፍ! ማለት ይጀምራሉ ኢየሱስም በሉ እንግዲህ በድንብ ለመዝረፍም እንዲያመቻችሁ አጥብቃችሁ ስሙኝ በማለት ይመስል ልክ ልካቸውን ሲነግራቸው አይሁድ ገና አሁን የአመለካከት ልዩነት ከፈጠረው የሃሳብ ሙግት አፈንግጠው በመውጣት ወደ ኢየሱስ የግል ህይወት በመግባት “እኛስከዝሙትአልተወለድንም” ሲሉ የሽሙጥ አነጋገር ጀምሩ። “እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም” ማለታቸው “ድሮም እኮ አንተ ማለት አጭበርባሪ ነህ! ከድንግል ተወልጃለሁም ትላለህ እንጅ በዝሙት የተገኘህ የዘማ ልጅ ነህ” ነው አነጋገሩ።
ልብ ይበሉ! ይህ አነጋገር በሕዝቡ ዘንድ ሊፈጥረው ስለሚችለው ውዥንብርና ብዥታ ቀላል ላለመሆኑና ምን ያክልም መርዛማ አነጋገር ለመሆኑ የአይሁድን ባህል፣ ወግና ልማድ ማወቅ ይጠይቃል። በአይሁድ ባህል ዘንድ ዝሙት እጅግ ጸያፍ ተግባር/ድርጊት ነው። በህጉም መሰረት (በሙሴ ሕግ ማለት ነው) አድራጊው ያለምንም ርህራሄ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት ነው የሚለው። ታድያ ኖረው ኖረው አይሁድ አጋጣሚ በሚመስል ሁኔታ ይህን ያሉበት ምክንያት ምንድነው? በማለት እንጠይቅ ይሆናል።[1] በዋናነት አይሁድ ከመወያያው ርዕስ በመውጣት የጀመሩትን ዘለፋ የሽንፈታቸው ምልክት ለመሆኑ ማስተዋል ያስፈልጋል። ተለላ ሰው የአመለካከት ልቀትና ብልጫ ባለው ሰው ሲሸነፍ እጅ ላለመስጠት በሚያደርገው ትግል ውስጥ የመጀመሪያው እርምጃ ግለሰቡ ማንንነት ላይ ያነጣጠረ ጦር አነጣጥሮ መወርወር ነው። በተጨማሪም ለመማር፣ የሌላውን ወገን የተሻለ አመለካከት የመቀበል፣ ዝቅ የማለት፣ በእወቅትና በጥበብ ታላላቆች የሚሆኑትን ራስን የማስገዛት ልብና ስብእና የሌለው ሰው ሁል ጊዜ ቃላትን አለ ጊዜውና አለ ቦታው መጠቀም ሁነኛ መታወቂያው ነው። ሽንፈቱንም ለማካካስና ለማድበስስበስም ጭብጥ በሌላው ተራ ወሬና አሉባልታ የሰውን ስምና መልካምን ዝና የጥላሸት መቀባት ነው።
ሌላው አንኳር ነጥብ አይሁድ “እኛስከዝሙትአልተወለድንም” ያሉበት ምክንያት ከላይ በሰፊው የተመለከትነውን ትንታኔ የተያያዘ ሆኖ በተለየ መልኩ ሕዝብ ልብ ላይ ያነጣጠረ ጦር ነው። በሌላ አገላለጽ አይሁድ እያሉ ያሉ “ሕዝብ ሆይ! ለመሆኑ የማንን ቃል እየሰማህ እንዳለህና ማንንስ እየተከተልክ እንዳለህ ልብ ብለሃልን? ይህ ሰው እኮ (ኢየሱስን ማለት ነው) በዝሙት የተገኘ የዘማ ልጅ ነው፣ በሙሴ ህግም መሰረት እርኩስ ነው” ነው አነጋገራቸው። እንዲህ ያለ የሰሚን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ ደግሞ ዘወትር የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በማለት በሚከተለውን ሕዝብ ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን ወከባ ቀላል አይደለም። ይህን የሚሰሙ አይሁድ: ቆመው ቃሉን ሊያደምጡት፣ ከሄደበት ሊከተሉትና ከዋለበት ሊውሉ ይቅርና ኢየሱስ ባለፈበት እንደማያልፉ በመተማመን የሕዝቡን ልብ ለመክፈል ሆን ተብሎ በቀመር የተነገረ አነጋገር ነበር። “አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው” ሲሉ ለተናገሩት ደግሞ እንደሚከተለው ይመልስላቸዋል።
ኢየሱስም አላቸው፥ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና ንግግሬን የማታስተውስ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። እናንተከአባታችሁከዲያብሎስናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪ ነፍሰ ገዳይ ነበረ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም። ይላቸዋል
አንድ ሰው ከዚህ ቀደም አግኝቶት/አይቶት የማያውቅ እንግዳ የሆነ ሰው ሲገጥመው ቀድሞም በደንብ ከሚያውቀው ሰው ጋር የሆነ ነገሩ የተመሳሰለበት እንደሆነ ወይ መመሳሰል! እናንተ ቁርጥ እገሌን/እገሊትን ይመስላል! እንደሚል ሁሉ አይሁድ ምንም እንኳ ከአብርሃም ዘር ነን በማለት ቢመኩና ቢያናፉም ኢየሱስ ሲያያቸው ግን/የሚገልጻቸው እናንተ ምን አለፋችሁ! ቁርጥ አባታችሁ ዲያብሎስን ትመስላላችሁ በማለት ነው። ይኸውም በተጨባጭ አባታቸው ዲያብሎስ ምን እንደሚመስል በመግለጽ “ሐሰትን ሲናገር ከራ ይናገራ ሐሰተኛየሐሰትምአባት ነውና” እንዲል። ሩቅ ሳንሄድ ይህንን የአይሁድ ነጭ ውሸት ላሳያችሁ። በቁ. 31 ላይ ኢየሱስ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት ሲናገራቸው አይሁድ የመለሱለት መልስ እንደሚከተለው ነበር “ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም” እንግዲህ ተናጋሪዎቹ ይህን የሚሉት በሮማውያን ቀኝ አገዛዝ ስር እየማቀቁ ነው። አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማ ይሉት እንዲህ ያለውን ነው!
ኢየሱስ የተነሳበትን ርዕሰ ጉዳይ እንደጠበቀ አይሁድ ደግሞ የሚዙትንና የሚጨብጡት አጥተው አራንባና ቆቦ እየረገጡ እዚህ ደርሰዋል። ሙግቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ታድያ ኢየሱስ እሳት እሳት እየሸተተ እሳት ሲተፋባቸው አይሁድ በአንጻሩ ምንም እንኳን ነገራቸውን ሁሉ እንዳለቀባቸው በውል ቢረዱና ቢገነዘቡም በንስሃ ከመመለስ ይልቅ ይቀረችውን ካርታ በመምዘዝ ለመጫወት ወስኖዋል። የቀረችውን የአይሁድ ጥይት ምን ትሆን? ዒላማዋንስ ትመታ ይሆን? ወይስ … እንግዲህ የሚፈጠረውን አብረን እንከታተል።
አይሁድ መልሰው፥ ሳምራዊእንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን? አሉት
ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል እኔስ ጋኔን የለብኝም ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ። እኔ ግን የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም።
አይሁድ፥ ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም፤ አንተም። ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም ትላለህ። በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ? አሉት።
ኢየሱስም፥ አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።
አይሁድ፥ ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት።
ኢየሱስም፥ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።
አይሁድም፥ ስለዚህ ነገር ሊወግሩትድንጋይአነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
የሥነ ባህሪ ተመራማሪዎች ሰዎች ተሟግተው መርታት ሲያቅታቸውና በፈንታውም ሲረቱና ሽንፈትን ሲከናንነቡ አፋቸው ባይናገርም ፊታቸው ይመሰክርባቸዋል በማለት ኪሳራ በተከናነቡ ሰዎች ፊት ላይ የሚታየውን ምልክት አንድ በአንድ እንደሚዘረዝሩ ሁሉ በወቅቱ የአይሁድ ፊትና ዓይን ምን ይመስል እንደነበረ ለማየት ባይቻለንም በቃል ከሰፈረው እውነታ በመነሳት ግን ብሽቀታቸውን ለመረዳት አይዳግተንም።
ኢየሱስ አይሁድን ከእግዚአብሔር አለመሆናቸውን እና የእግዚአብሔር የሆነ ነገር ሊሰሙ እንደማይችሉ እንቅጭዋን ሲነግራቸው ሃሳብን በሃሳብ ተሟግተው ማሸነፍና መርታት ሲያቅትቸው ሽንፈታቸውን ለማደባበስ አይሁድ እውነታውን ለማዳፈን የወሰዱት እርምጃ ከፍ ስንል በዝርዝር የተመለከትነውን ጭብጥ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪ የሰሚ ሕዝብ ልብ ለማወክና ለመክፈል ብሎም ኢየሱስን ከጨወታ ውጭ ለማድረግ የቀረችውን ጥይት ዘሩን ቆጥረው መናገር ነበር። “ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን?” በማለት እስከ አሁን የኢየሱስ ቃል እየሰሙና በአንድም በሌላም ምክንያት እየተከተሉትም የመጡትን እስራኤላውያንን በጎሳ ፖለቲካ ለመክፈል ይህን አደረጉ።
ልብ ይበሉ! “ሳምራዊ እንደ ሆንህ” የምትለዋን የአይሁድ አነጋገር የመጨረሻና ከምን ጊዜም በላይ የከፋች በቀላሉ የትልቁም ትንሹም ልብ የምታሸፍት መርዛማ አነጋገር ናት። “ይቀላቅላል፣ እብድ ነው፣ ውሸቱ ነው ከድንግል አልተወለደም፣ የእግዚአብሔር ልጅም አይደለምና አትስሙት” ሲባል የአይሁድ ምህጽንታ ሳይበግረው እዚህ የደረሰ ሕዝብ አሁን ግን ሆነም አልሆነም ኢየሱስ “ሳምራዊ” ነው የሚል ሰምቶ የቀረ ይቀራል እንጅ የማይበረግግ ቤተ- እስራኤል ማንም የለም። ምክንያቱም በአይሁድና በሳምራዊያን መካከል ከፍተኛ የሆነ ክፍተትና የማይበርድ ጸብ እንደነበራቸው መጻህፍትን በአግባቡ በማጥናት ለማወቅ ይቻላል። ይህንንም ታሪክ ትልቁም ትንሹም የአይሁድ ዘር ያለበት ሁሉ ጠንቅቆ ሲለሚያውቅ ኢየሱስን ጥለው ለመሄድ ሌላ ከዚህ በላይ ተጨማሪ ምክንያት አይስፈልገውም:: አይሁዳውያን ምንም ቢሆን ምን ለሳምራውያን ቅንጣት ታክል ክብር የላቸውም:: ይህም ሊሆንበት የቻለበት ዋና ምክንያት ደግሞ ምንም እንኳን ታሪኩ ሲፊ ቢሆንም በመጠኑም ቢሆን እንደሚከተለው ይመስላል።
በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 17: 5 ላይ “የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፥ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት” ተብሎ ተጽፎ እንደምናገኘው ሰማሪያ በአሶራውያን ተከባ በቁጥጥር ስር ለመዋልዋ ለማወቅ ይቻላል። መጽሐፉ ወረድ እያልን ባነበብነው ቁጥርም የበለጠ ታሪኩ ግለጽ ያደርግልናል። በተለይ በተመሳሳይ ምዕራፍ ቁ. 24 ላይ “የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፥ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ።” የአሶር ንጉስ የሰማርያ ሰዎችን አፍልሶ በምትካቸው ከባቢሎን አምጥቶ ሰው እንዳሰፈረበት ነው የምንመለከተው። ከዚህም የተነሳ እነዚህ በአሦር ንጉስ አማካኝነት ከሌላ ስፍራ ፈልሰው በሰማሪያ ይሰፈሩትን ሰዎች ከጊዜ በሃላ ሳምራውያን ተብለው እንደሚጠሩና ይህም ሆኖ ግን እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳን ሳምራውያን ተብለው በስም ይጠሩ እንጅ ከእግዚአብሔርም ሕዝብ ጋር ግን ምንም እድል ፈንታ እንደሌላቸው፣ በተጨማሪም ልዩ ወገን ተብለው ይታወቃሉ እንጅ ከአብርሃም ዘርም እንደማይቆተሩ አህዛብ እንጂ የእስራኤል ወገን እንዳልነበሩ ሀዲሳትንና ብሉያትን በሚገባ በጥንቃቄ በማጥናት የታሪኩን ሙላት መረዳት ይቻላል።
ቁምነገሩ ይህን ያክል የተወሳሰበና ግዙፍ ልዩነት ያለው የጎሳ ልዩነት ያለን ዜጎችም ባንሆንም በአቅማችን አማራ፣ ትግሬ፣ አሮሞ፣ ጉራጌ፣ ደቡብ፣ … ነው እየተባለ ሰውን ለማሳጣት የሚደረግ ፖለቲካ በደንብ “ተክነንበታል”። በአጭሩ እዚህ ላይ አጽንዖት ሰጥቼ ማስተላለፍ የምፈልገው ነጥብ ቢኖር በእንዲህ አይነቱ የመከፋፈልና የማሳጣት በሽታ የተለከፉና ታጥቀው የተሰማሩ ጥቂት ሰላማዊ አጀንዳ የሌላቸው በግርግርና በሁከት የሚያምኑ ግለሰቦች ሌላ የሚፈጥሩት ተአምር ኖሯቸው ሳይሆን ሽንፈታቸውንና ውድቀታቸውን የሚያሳይ እንዲሁም ደካማነታቸውን የሚያጋልጥ መሆኑን ተረድተን በእንደዚህ ዓይነቱ የማሳጣት ዘመቻ ሳንበገርና ሳንበረከክ በጊዜውም አለጊዜውም አንድ ሕዝብ! አንድ ወገን! በማለት አንዱን ከሌላው ከቋንቋው ከባህሉና ልማዶቹን የተነሳ የተለየ መልክና ገጽታ ሳንሰጥ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ በሚደረገው ሰላማዊ የሆነ ትግል መልካም ተጋድሎአችንን ከምን ጊዜም በበለጠ አጠናክረን እንገፋበት ዘንድ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
ሌላው “ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን” የምትለዋን ከቁብም የማትቆጠር ከከሰረች ነፍስ የአንደበት ፍሬ የምትገኝ ናት። ነገሩን ለማሳጠር ያክል እውነት ኢየሱስ፥
ü ጸበል የሚያስፈልገው:
ü ጨርቁን የጣለ:
ü የሚደርስለት ሁነኛ ዘመድ ያጣ:
ü ቤተ-ሰቡ የረሳው/የዘነጋው:
ü የሚናገረውን በውል የማያውቅ:
ü እብድና ጋኔን ያለበት/ያደረበት ሰው ነበር ወይ ነው ጥያቄው? ለመሆኑ ያበደ/ጋኔን ያለበት ሰው ምልክቱ ምንድ ነው? አእምሮን የሚያልፍ ቃል/እውቀት? ጋኔን አለብህ ያስባለውስ ምንድን ነው? ተናግሮ አለመረታቱ? የተናገራትን ቃል እንዲሁ አየር ላይ የማትቀርና በሰው ልብ ስራ መስራትዋ ነው? ውድ አንባቢ! አሁንስ አወቅንህ ሲሉ በኢየሱስ ላይ “ጋኔን አለብህ ሲሉ” የተናገሩትን አይሁዶች እውነት አውቀውታል ብለው ያምናሉ? እንግዲህ መስማት የማንፈልገው ዳሩ ግን የሚበጀንን፣ ሚዛናዊና የመፍትሔ ሃሳብ የሚያቀርብ ሁሉ እብድ ነው ከተባለ የመጀመሪያው ዕብድ ኢየሱስ መሆኑን ሳይዘነጉ በአመለካከት የማይመስሎትን ሰውን ሁሉ “ዕብድ ነህ!” ይበሉ።
እብዶች ብንሆን ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን ለእናንተ ነው!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America
May 31, 2012
[1] እንዲህ ዓይነቱ ፖለቲካ በሦተኛው ዓለም ብዙ ጎልቶ የሚታይ ባይሆንም በምእራቡ የዓለማችን ክፍል በተለይ በአሜሪካን አገር ወደ “ሃይት ሃውስ” ለመግባት በሚደረገ የምረጡኝ እንቅስቃሴ በዚህ ወቅትም አንዱ ሌላውን ለማሳጣት በሚደረገው ፍኩክር የማይመዘዝ ፋይልና የማይሰማ ጉድ የለም። እንዲህ ያሉ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማወቁ ይህ ክፍል ስለ ምን እየተናገረ እንዳለ በቀላሉ መልዕክቱ እንድናገኘው ይረዳናል።