የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐረፉ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


  • ሥርዓተ ቀብራቸው ከነገ በስቲያ በአሰላ ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ይፈጸማል
  • በታኅሣሥ 1966 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ኾነው ተሹመው ነበር

በአሰላ መኖርያ ቤታቸው በቅርብ በሚረዷቸው ወዳጆቻቸው እንደተከበቡ በሰላመ እግዚአብሔር ያረፉት ብፁዕነታቸው፣ ከኩላሊትና ስኳር ሕመም ጋር በተያያዘ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፤ ከሕመማቸው አገግመው በመልካም ጤንነት ላይ እንደነበሩ የተነገረ ሲኾን፣ ከዕረፍታቸው ሦስትና አራት ቀናት በፊት ምግብ መወሰድ አቁመው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ መዓዛ ቅዱሳን ገብረ ሕይወት የሚባሉት ብፁዕነታቸው፣ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ከተሾሙት 13 ኤጴስ ቆጶሳት አንዱ ሲኾኑ ምድብ ሀገረ ስብከታቸውም በቀድሞው አጠራር ትግራይ ክፍለ ሀገር ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ከዐሥር ዓመት በፊት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አብርሃም ቤት ዓምድ በሰጡት ቃለ ምልልስ፥ “በመንግሥት ሥራ የባህል ሚኒስቴር ሲቪል ሰርቫንት ኾኜ እየሠራኹ በመናኙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን ለጵጵስና ታጨኹ፡፡ እኔ ጵጵስና ለመሾም ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ ያኔ የነበረኝ ዓላማ በመጽሐፍ መምህርነቴ ጉባኤ አስፍቼ እንዳስተምር ነበር የምፈልገው፡፡ ምንኵስናን ተቀብዬ እንኳ ለጵጵስና ጉጉቱም ፍላጎቱም አልነበረኝም፤” ብለዋል፤ ለመምህርነት ሞያ ከፍተኛ ፍቅር እንደነበራቸው ሲያስረዱ፡፡

ነገ ቤተ ክርስቲያን ይከፍታል ብሎ ያሳደገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የአቅሜን ያኽል ተምሬአለኹ፤ ቤተ ክርስቲያን አሳድጋኛለች፤ ባለውለታዬ ነች፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ውለታ አኹንም አልከፈልኩም፤ እስከ ሞት ቢኾን ውለታዋን ተሸክሜ ወደ መቃብር ከመግባት በስተቀር ውለታዋን አልከፈልኩም፤ ይኼን የምናገረው ከልቤ ነው፤ ኹሉም ውለታ አለበት፤ የቤተ ክርስቲያኑን ውለታ መመለስ አለበት፡፡ – ብፁዕ አቡነ ናትናኤል