የደጃች ውቤ ልቅሶ – ዳንኤል ክብረት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ዐፄ ቴዎድሮስ በበጌምድር ማንም ለሞተ ዘመዱ እንዳያለቅስ የሚል ዐዋጅ ዐውጀው ‹ሰው ሁሉ ዕንባውን ያጠጣ ነበር፡፡› በዚህ መካከል ደጃች ውቤ ሞቱና ለእቴጌ ጥሩ ወርቅ ወደ መቅደላ መርዶ ተላከ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም ሕዝቡን ‹ለደጃች ውቤ አልቅሱልኝ› ብለው አዘዙ፡፡ ሰውም ሁሉ ዘመዱ ሲሞት የቀረበት ልቅሶ ያን ጊዜ ወጣለት፡፡ ይህንን ያየች የበጌምድር አልቃሽ
የኔታ ደጅ አዝማች ሁልጊዜ ደግነት
ዛሬ እንኳን ለድኻው ዕንባ አስተረፉለት
ብላ ገጠመች ይባላል፡፡
ያን ቀን በበጌምድር ወጥቶ የማያውቅ ሰው አደባባይ ወጥቶ፣ ተለቅሶ የማያልቅ ልቅሶ ተለቀሰ ይባላል፡፡ ከወጣው በጌምድሬ መካከል ደጃች ውቤን የሚያውቃቸው፣ ለደጃች ውቤም ያለቀሰላቸው ጥቂት ነው አሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ያለቀሰው ከዚህ በፊት ለሞተውና ተከልክሎ ሳያለቅስለት ለቀረው ዘመዱ ነበር፡፡ በየማርገጃው የወረደው ሙሾ ደጃች ውቤን ከሚያስታውስ ይልቅ ቴዎድሮስን የሚወቅሰው ይበዛ ነበር አሉ፡፡ በዚህ የተነሣ የደጃች ውቤ ልቅሶ በድምቀቱ ተወዳዳሪ አጥቶ ይኖራል፡፡
ምክንያትና ሰበብ ይለያያሉ፡፡ ምክንያት የአንድ ነገር መነሻ ሥር መሠረቱ፣ ቫይረሱና ጀርሙ፣ መንሥኤውና መብቀያው ነው፡፡ ሰበብ ግን ያ በአንዳች ምክንያት ሲበቅል፣ሲያድግ፣ ሲጎነቁል፣ ሲከካ፣ ሲቦካ የኖረ ጉዳይ የሚገለጥበት ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡ ‹እንኳን እናቱ ሞታ እንዲያውም አልቅስ አልቅስ ሲለው› የኖረ ሰው ‹ዋይ› ብሎ የሚወጣለት ቀን፡፡ የበጌምድርን ሰው በነቂስ ወጥቶ እንዲያለቅስ ያደረገው ምክንያት የደጃች ውቤ መሞት አልነበረም፡፡ የቴዎድሮስ አስተዳደራዊ በደል እንጂ፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ ሞጣ ሄደው ሬሳ በሬሳ አድርገውት ሲመጡ
ሞጣ ቀራንዮ ምነው አይታረስ
በሬሳ ላይ መጣሁ ከዚያ እስከዚህ ድረስ
ተብሎ ተለቅሷል፡፡ ንጉሥ ግን አልሰሙም፡፡ ሸዋ ወርደው የሰውን እጅ እየቆረጡ ገደል ሲከቱትም
ዐፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ
የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነሥተው ሄዱ ተባለ፡፡ ንጉሥ ግን አልሰሙም፡፡
ጎጃም አገው ምድር ሄደው የደጃች ጓሉን ሠራዊት ገጥመው ድል ካደረጉ በኋላ የተማረከውን ስምንት ሺ ሠራዊት እንደ ከብት አሳርደው ባደሩ ጊዜ
አንጥረኛው ብዙ ከንጉሡ ቤት
ባል አልቦ አደረጉት ይኼን ሁሉ ሴት
ተብሎ ተለቀሰ፡፡ ንጉሥ ግን አልሰሙም፡፡
ከጣና ምጽርሐ ደሴት ተነሥተው የደንቢያንና የበጌምድርን ሰው በየቤቱ እያስገቡ እሳት ባነደዱት ጊዜ፤ የበጌምድር አልቃሽ
እግዜርና ንጉሥ ተጣልተው ቁመው
ቅዱስ ሚካኤልን ዳኛ አስቀምጠው
እግዜር በግራ ነው ንጉሡ በቀኝ
በል ፍጅና ስጠኝ ሲሉ ሰማሁኝ፤ ብላ አለቀሰች ፡፡ ንጉሥ ግን አልሰሙም፡፡
የጎጃምም አልቃሽ ሜጫን በዘረፉት ጊዜ
ልብሴንም ገፈፈው ለበሰው እርዘኛ
በሬዬንም ነዳው አረደው ነፍጠኛ
እህሌንም ዘረፈው በላው ቀለበኛ
ንጉሥ የቀረዎ ጥቂት አማርኛ
ምነው ሆድ አይዘርፉ አርፌ እንድተኛ፡፡ አለች አሉ፡፡ ንጉሥ ግን አልሰሙም፡፡
ይህ ሁሉ ብሶት በሕዝቡ ውስጥ ታምቆ ይኖር ነበር፡፡ ብሶቱም እንደ ሙዳየ ምጽዋት በየቀኑ እየተጠራቀመ፣ እንደ ፍግ እሳት ውስጡን እየፋመ፣ እያብተከተከው ኖሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ እንደዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ጋዜጣ፣ ሬዲዮ፣ ፌስ ቡክና ሚዲያ ከመምጣቱ በፊት የብሶቱ ማውጫ፣ የሐሳቡም መግለጫ የልቅሶ ላይ ሙሾ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ይባስ ብለው የከለከሉት እርሱን ነው፡፡ ማንም ልቅሶ እንዳይቆም፣ ማንም ሙሾ እንዳያወርድ አወጁ፡፡ ‹የሚያስቆጣ ነገር ነግሮ አትቆጣ ይለኛል› እንደሚባለው፡፡
ሰውን ከብሶቱ በላይ ሁለት ነገር ይጎዳዋል፡፡ ብሶት ሰሚና ብሶት ማሰማት ሲከለከል፡፡ ሰው ዘመድ ሲሞትበት እንኳ ምን ዘመዱን ከሞት ባይመልሰው ‹አልቅሼ ይውጣልኝ› ይላል፡፡ በትግርኛ ‹ካስለቀሰኝ ይልቅ አታልቅስ ያለኝ ያመኛል› የሚል አባባል አለ፡፡ ሰው አልተናገረም ማለት የሚናገረው ነገር የለውም ማለት አይደለም፡፡ ሰው አላመጸም ማለት የሚያሳምጽ ነገር አልገጠመውም ማለት አይደለም፡፡ ሰው አልተቃወመም ማለት የሚቃወመው ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ ሰው ዝም ሲል ተስማምቷል ማለት አይደለም፡፡ እንደ ደጃች ውቤ ልቅሶ ሰበብ እየጠበቀ ይሆናል እንጂ፡፡
የደጃች ውቤ ሞት የልቅሶው ሰበብ ነበር እንጂ ምክንያት አልነበረም፡፡
በጣልያን ጊዜ ለጣልያን የገባ ባንዳ አራዳ ወርዶ የአራዳን ሴተኛ አዳሪዎች እንደ ጌቶቹ እንደ ጣልያኖች በጥፊና በካልቾ ሲማታ ያዩት የአራዳ ሴቶች
በጥፊም ተማታ
በካልቾም ተማታ
እንገናኛለን የዘመመ ለታ፡፡
ብለው ገጠሙበት አሉ፡፡ አልቀረም፡፡ የጣልያን ዘመን ዘምሞ፣ ዐርበኞችና እንግሊዝ ወደ አዲስ አበባ ሲገሠግሡ ያ ባንዳ መግቢያ አጣ፡፡ የተመካባቸው ጌቶቹም ዘመኑ ለእነርሱም ዘምሞባቸው ነበርና ሊያስጥሉት አልቻሉም፡፡ ወድቀህ ተነሣ የሚለው አጥቶ እሪ በከንቱ ላይ ተገደለ አሉ፡፡
ሰበቦችን ማስተንፈስ ቀላል ነው፡፡ የበጌምድር ሰውም ደጃች ውቤን አመስግኖ የሆዱን ሁሉ አልቅሶ ወጣለት፡፡ ግን ብሶቱ እንጂ ችግሩ አልወጣለትም፡፡ ደጃች ውቤ የልቅሶው ሰበብ እንጂ ምክንያት አልነበሩምና፡፡ የልቅሶው ምክንያት ሳይፈታ፤ የቴዎድሮስም ጭካኔ ከተስፋ መቁረጥ ጋር እየባሰ መጥቶ የመቅደላው ጦርነት እያዘገመ ደረሰ፡፡ የአራዳ ሴቶች ‹የዘመመ ለታ› እንዳሉት የቴዎድሮስ ዘመን ዘመመ፡፡ ሕዝቡ የእርሳቸውን ርዳታ ሳይሆን እርሳቸው የሕዝብ ርዳታ የሚፈልጉበት ዘመን መጣ፡፡ በጀግንነታቸው ካደነቃቸው፤ የንግሥና ዘር የለህም እየተባሉ እንኳን ካነገሣቸው፣ ዛሬም ድረስ ከማይረሳቸው ሕዝብ ጋር ተጣልተው ብቻቸውን ከጥቂት ባለሟሎቻቸው ጋር መቅደላ ላይ ቀሩ፡፡
ከሕዝቡ ጋር ያጣላቸውን፣ ያላግባባቸውንና ቀስ በቀስም ከሕዝብ ልብ እያወጣ ያመጣቸውን የችግሩን ምክንያት ሳይፈቱት፣ ራሱ ችግሩ ተብትቦ መቅደላ ላይ ጣላቸው፡፡ የንግሥናቸው ዘመን በጨመረ ቁጥር ችግሩን ለመፍታት የነበራቸውን እድል እያጡት፣ ችግሩን ከመፍታትም ይልቅም ችግሩን ሕዝቡ እንዳይናገር ወደማድረግ እየገቡ፤ የሚያስለቅሰውን ምክንያት ከማጥፋት ይልቅ እንዳያለቅስ እያወጁ፤ በትልቅ ጉዳይ ወደ ዙፋን የመጡት ቴዎድሮስ በትንሽ ጉዳይ ተሰናበቱ፡፡
ባለፉት ሰሞናት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ያየናቸው የሕዝብ ተቃውሞዎች መተንተን ያለባቸው ሰበብ ናቸው ወይስ ምክንያት? በሚለው መሆን አለበት፡፡ የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ሰበብ ነው ወይስ ምክንያት? ሳይፈቱ ለኖሩ ችግሮች የመገለጫ ሰበብ ሆናቸው ወይስ ጥያቄው ፕላኑ ነው? ‹የአማራና ቅማንት› ጉዳይ ያንን ያህል ያወዛገበውና ደም እስከማፋሰስ የደረሰው የመሬቱ ጥያቄ የችግሩ መገለጫ ሰበብ ነው ወይስ በራሱ ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች የበሽታው ምልክቶች ናቸው ወይስ ራሱ በሽታው ነው፡፡ ያየነው ትኩሳቱን ነው ወይስ ጀርምና ቫይረሱን? ይኼን የመለስን ለት ነው ከመቅደላ የምንተርፈው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህን መሰል አጋጣሚዎች የኖረ ችግር፣ ያልተመለሰ ጥያቄ፣ የተበላሸ አሠራር ወይም የተነፈገ ፍትሕ የመግለጫ አጋጣሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
መልካም አስተዳደር ከስብሰባ ይልቅ ቁርጠኝነት፣ ሥርዓት(ሲስተም)፣ ሳይንሳዊ አካኼድ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድን ይጠይቃል፡፡ አሁን በየመድረኩ የሚነሡት ችግሮቹ አይደሉም፣ የችግሮቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ነገሩ እንደ ደጃች ውቤ ልቅሶ ላልተለቀሰለት፣ ለማልቀስም ዕድል ለታጣለት ነገር ማልቀሻ ነው የሆነው፡፡ የሆኑ ሰዎችን ከቢሮ ማባረር እንደ ደጃች ውቤ ልቅሶ ማስተንፈሻ እንጂ መፍቻ አይሆንም፡፡
ችግሩን ከመሠረቱ አጥንቶ እንዳያዳግም አድርጎ ከመፍታት ይልቅ በስብሰባ ብዛት ለመፍታት መሞከር አሁንም እንደ ደጃች ውቤ ልቅሶ ነው የሚሆነው፡፡ በደጃች ውቤ ልቅሶ የከረመውን ሟች የበላውን እርም እያስታወሰ ብሶቱን ተነፈሰበት እንጂ ሕዝቡ ችግሩን አልፈታበትም፡፡ የሚያይና የሚሰማ ቢኖር ኖሮ ግን የሕዝቡን የምሬት መጠን የደጃች ውቤ ልቅሶ ያሳይ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የደጃች ውቤን ልቅሶ የፈቀዱት ለሕዝቡ ብለው ሳይሆን ለእቴጌይቱ ብለው ነበር፤ ሕዝቡ ለራሱ ብሶት ማስተንፈሻ አደረገው እንጂ፡፡ አሁንም ሰበቡን ትተን ምክንያቱን እንፍታ፡፡ አለማልቀስ አንድም የልቅሶውን አለመፈቀድ፣ አለበለዚያም የልቅሶው መዳፈን እንጂ የሚያስለቅስ ነገር አለመኖርን አያሳይምና፡፡ ተለቀሰ ማለትም የሚያስለቅሰው ነገር ተፈታ ማለት አይደለም፡፡ ሙሾ ወረደ ማለት እንጂ፡፡ ከሰበቡ ወደ ምክንያቱ፡፡