ኦሮሞና አማራ የሚለው ነገር – ‪ግርማ ካሳ‬

ኦሮሞና አማራ የሚለው ነገር – ‪#‎ግርማ_ካሳ‬

ሁለት ነጥቦችን እንዳነሳ ይፈቀድልኝ

1. “የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን መተባበር አለባቸው፣ አማራዉን አሮሞው አንድ መሆን አለበት ..” እየተባለ ነው። ይሄ አነጋገር በጣም አይመቸኝም። አንደኛ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዘራችን ኢትዮጵያዊነት ነው የሚሉ አሉ። አማራነት ሆነ ኦሮሞነት የማይወክላቸው። እንደኔ ያሉ። ሁለተኛ እንደ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ሃዲያ፣ አፋር ያሉ አሉ። አማራና ኦሮሞ ያልሆኑ አሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሶስተኛ ናቸው። ታዲያ እነዚህ የአገራችን ማህበረሰብ ክፍሎች ማግለል አይህንም ወይ? “ኢትዮጵያዉያን ሁሉ መተባበር አለባቸው” ቢባል እመርጣለሁ።

2. በኦሮሞው ያለው እንቅስቃሴና በአማራው ክልል ያለው እንቅስቃሴ በአንድ በኩል መያያዝ ጀመሯል። በኦሮሚያ “አማራ የኛ ነው” ሲባል በአማራው ክልል ደግሞ “የኦሮሞ ወገኖቻን ደም የኛ ደም ነው” ሲባል ነበር። ይህ በጣም ሲበዛ አስደሳች ክስተት ነው።

ሆኖም ግን አሁንም እነዚህ ህይሎች የሚያራርቅ ነገር እንዳለ መርሳት የለብንም። ለምሳሌ የአማራው ተጋድሎ እንቅስቃሴ ከአማራው ክልል ዉጭ ኦሮሚያን ጨምሮ በደልን ግፍ የሚፈጸምባቸው አማርኛ ተናገሪዎች ጉዳይ አንዱ አጀንዳው ነው። የኦሮሞ እንቅስቃሴ ኦሮሚያ ለኦሮሞ የሚል ነው። ይህ መሰረታዊ ልዩነት ነው።

ሌሎች በርካታ የፖለቲካ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላል። ፌዴራል አወቃቀሩ እንዴት ይሁን ? የመሬት ፖሊሲው እንዴት ይሻሻል ….ወዘተረፈ። ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲዘረጋ ወደፊት በሕዝብ ድምጽ ይፈታሉ። ሆኖም ግን መሰረታዊ የሆኑ የሕልዉና ጥያቄዎች ግን ምላሽ ማግኘት አለባቸው። በኦሮሚያ ያሉ የሌሎች ማህበረሰቦችን የሕልዉና ጥያቄዎችና የኦሮሞ ጥያቄዎችን ማጣጣም ባልተቻለበት ሁኔታ እነዚህ ሁለት እንቅስቃሴዎች መጋጨታቸው አይቀርም።

በዚህ ዙሪያ እነዚህ ሁለት ማሀብረሰቦች አብረው እንዲሰሩና እንቅስቃሴያቸውም ዘለቄታ ያለው እንዲሆን ፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ በመሰረታዊ ልዩነቶቻቸው ላይ መግባባት መድረስ አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ ላለፉት 25 አመታት አማርኛ ተናገሪዎች በገፍ የዘር ማጽዳት ወንጀልተፈጽሞባቸዋል። አገሩ የኦሮሞ ነው በሚል በብዛት በሃረረጌ፣ በምእራብ አርሲ (አኖሌ ሃዉልት ያለበት) በመሳሰሉ ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ አማርኛ ተናጋሪዎች መኖር አልቻሉም። በኦሮሞያ የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ በመሆኑ ብዙዎች አፋን ኦሮሞ ስላልቻሉ የሚኖሩበትን ለቀው ወጥተዋል።

ታዲያ በኦሮሚያ የሚኖረውን ኦሮሞ ያልሆነው ማህበረሰብ፣ ላለዉ የሕልዉና ጥያቄ የኦሮሞ ተቃዉሞ መሪዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው ? በኬንያ እንደሚኖሩት ኢትዮጵያዉያን በሰላም ትኖራለችሁ ከሚል ዉጭ የሰማነው ነገር እስከ አሁን የለም። በኦሮሚያ የሚኖር ኦሮሞ ያለሆነ ማሀበረሰብ አለ። የዜግነት መብቱ የተረገጠ። ይህ ማህበረሰብ ከኦሮሞው እኩል መብቱ በህግ ሊከበርለት ይገባል። በዚህ መስማማት ካልተቻለ አብሮ ለመስራት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

በዚህ ረገድ ሁለት አማራጭ ሐሳቦች አሉኝ፡

1. ክልሎችን እንዳለ አፍርሶ፣ ዞኖችን ከፌዴራል መንግስት ቀጥሎ የመንግስት አካል ማድረግ አንዱ ነው። በዞኖች ከ10% የዞኑ ነዋሪ አንደኛ ቋንቋ የሆኑ ቋንቋዎች የዞኑ የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ። ዞኑ የአንድ ወይም ሁለት ብሄረሰቦች ሳይሆን የየዞኑ ነዋሪዎች ነው። ዞኖችን በፍላጎታችው ተዋህደው አንድ ተለቅ ያለ ዞን ሊፈጥሩ ይችላሉ።ለምሳሌ መራብ ትግራይ ዞን፣ ሰሜን ጎድነር ዞን እና ደቡብ ጎንደር ዞን ተዋህደው በጌምድር የሚል ዞን ሊፈጥሩ ይችላሉ። የወለጋ አራቱ ዞኖች መዋሃድ ይችላሉ።

2. አይ አሁን ያለው አከላለ ለጊዜ ይቀጥል ከተባለ ደግሞ ሌላው ቢቀር ዘላቂ መፍትሄ እስኪመጣ፣ ክልሎች በአዲስ መልክ እስኪዋቀሩ፣ በኦሮሚያ ከአፋን ኦሮሞ ጋር አማርኛም የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት። ሁለተኛ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ሳይሆን የኦሮሚያ ነዋሪዎች መሆኑን በግልጽ መረጋገጥ አለበት።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE