ተቃውሞው ችላ ተብሏል ………. ጥር 23 ጀምሮ በስስ ፌስታል እቃ መያዝ ሆነ መሸጥ በህግ ያስቀጣል !

ጥር 23 ጀምሮ በስስ ፌስታል እቃ መያዝ ሆነ መሸጥ በህግ ያስቀጣል !

” ህጉ ወጥቷል ፤ ማህበረሰቡ ማክበር አለበት ፤ ካላከበረ ህግ አስከባሪ ሁሉ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት ” – ባለስልጣኑ

⚫️ ” አዋጁ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ነገ ከመሆኑ፣ እሱም ጊዜ ከመድረሱ ውጭ ከየትኛውም አካል በኩል የተለየ የተሰጠን ማብራሪያ የለም ” – ማህበሩ

በስስ ፕላስቲክ (ስስ ፌስታል) እቃ ይዞ የተገኘን ሰው ለመቅጣት የወጣው ህግ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግና እስካሁን ባለው መረጃ የተራዘመም ሆነ የተሻሻለ ነገር እንደሌለ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸ።

ጉዳዩን ከሚያስፈጽሙት ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣  ” ከጥር 23 ጀምሮ ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶችን (ስስ ፌስታል) መጠቀም፣ ማምረትና ወደሀገር ውስጥ ማስገባት አይቻልም ” ማለቱ ይታወሳል።

– ማንኛውም ግለሰብ ፌስታል በእጅ ይዞ ከተገኘ ከተጠቀመ፣ ለመጠቀም ከሞከረ ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር ይቀጣል።

– አምራቾችና አከፋፋዮች፣ አስመጪዎችና አከማቾች ከ50 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር እንዲሁም የ5 አመት ጽኑ እስራት ይቀጣሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ጉዳዩ ተፈጻሚ ሊሆን ነው ወይስ የተለየ ነገር አለ ? ሲል በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባን ዛሬ ምሽት ጠይቋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ምን መለሱ ?

” አዎ ምንም የተራዘመ ነገር የለም። በዚያው ጸንቷል። በፌደራል ፓርላማ ነው ይሄ ህግ የወጣው እኛ ማስፈጸም ነው ያለብን።

ቀነ ገደቡንም የሰጠው፣ ህጉንም ያወጣው የአገሪቱ ፓርላማ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት አባላት የጸደቀ ደንብ ነው። ከዚህ ያሉ ሰዎች ማሻሻል አይችሉም።

የደንብ አስከባሪዎች፣ የፓሊስ አባላት ፣ የባለስጣኑ ሠራተኞች ሆነው ህጉን ያስፈጽማሉ። ” ብለዋል።

ዜጎች ደግሞ ከወዲሁ፣ ” በምን ልጠቀም ነው ? የተተካ ነገር አለ ?” የሚሉ አስተያየት አዘል ጥያቄዎችን እየሰጡ ሲሆን፣ እኝህ የባለስልጣኑ አካል ግን፣ ” ይህ ህግ የወጣው ህዝቡን ለመጥቀም ነው። አሁን ያለውንም ቀጥሎ የሚመጣውንም ትልውልድ የሚጠቅም ነው ” ብለዋል።

አክለው ፥

” የተበላሸ መሬት ለትውልድ ከማስተላለፍ የወጣውን ህግ አክብረን ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆበትን መንገድ ነው መከተል ያለብን። ህጉ ወጥቷል፤ ማህበረሰቡ ማክበር አለበት። ካላከበረ ህግ አስከባሪ ሁሉ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት። ብዙ ይሄን (ፕላስቲክን) ሊተኩ የሚችሉ ከወረቀት፣ ከጨርቃጨርቅ የሚሰሩ ነገሮች እየተሰሩ ነው ያለው።

የ6 ወራት የጊዜ ገደብ ቢሰጥም ‘ብክለት ይምጣ ወይስ ውበት ይምጣ?’ በሚል የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ ከወጣው ንቅናቄ ጀምሮ ፕላስቲክ ላይ፣ ብክለት ላይ እየሰራን ነው የነበረው። ከዚያ በፊትም ስስ ፌስታል ለአገልግሎት እንዳይውሉ ህግ ወጥቶ ነበር። አሁንም ስስ ፌስታሎች ናቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የታገደው።

ስለዚህ ለአብዛኛው ህዝብ ጥቅም ሲባል የወጣ ህግ ስለሆነ በስራ ላይ ይውላል። ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል መባሉ ትክክል ነው። ደንብ ተጥሶ ሲገኝ ደንብ አስከባሪው እርምጃ ይወስዳል።

ስለዚህ ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ፣ ከአንድ አገልግሎት በኋላ የሚጣሉ፣ ከተጣሉ በኋላ ለመሰብሰብም የማይመቹ፣ በቱቦ፣ በእርሻ ማሳ ንፋስ የሚወትፋቸውና የጎርፍ አደጋ የሚያስከትሉ ስስ ፌስታሎችን (ስኳር፣ ጫት፣ ስጋ የሚያዝባቸው) መያዝ ታግዷል ” ብለዋል።

የቅጣቱም መጠኑም ቢሆን ከዚህ ቀደም የተነገረው ተግባራዊ እንደሚደረግና የተሻሻለ ነገር እንደሌለ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር ምን አለ ?

ማህበሩ ” አዋጁ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ነገ ከመሆኑ፣ እሱም ጊዜ ከመድረሱ ውጭ ከየትኛውም አካል በኩል የተለየ የተሰጠን ማብራሪያ የለም ” ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

በውሳኔው ላይ ያለውን አስተያየት በመግለጽም፣ አሁንም ” ጉዳዩ በድጋሚ እንዲጤን ” የጠየቀ ሲሆን፣ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጠው ሙሉ ገለጻ በቀጣይ ይቀርባል።