ጥር 23 ጀምሮ በስስ ፌስታል እቃ መያዝ ሆነ መሸጥ በህግ ያስቀጣል !
” ህጉ ወጥቷል ፤ ማህበረሰቡ ማክበር አለበት ፤ ካላከበረ ህግ አስከባሪ ሁሉ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት ” – ባለስልጣኑ
⚫️ ” አዋጁ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ነገ ከመሆኑ፣ እሱም ጊዜ ከመድረሱ ውጭ ከየትኛውም አካል በኩል የተለየ የተሰጠን ማብራሪያ የለም ” – ማህበሩ
” ህብረተሰባችን፣ ሰፊው የንግድ ማህበረሰብም የተቀመጠለት መፍትሄ የለም። ዓይን ጨፍኖ እየተገባበት ነው። አሁንም ቆም ተብሎ ቢታሰብበት መልካም ነው ” – ማህበሩ
ከዛሬ ጀምሮ እቃን በፌስታል ይዞ መንቀሳቀስ ያስቀጣል።
የፕላስቲክ ኢንዱስትሪው ከስራው እንዲወጣ መደረጉ በ100 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን የሚጎዳ በመሆኑ “በድጋሚ እንዲጤን” የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር አሳስቧል።
የማህበሩ አባል እና ጉዳዩን በሚደነግገው አዋጅ ምክንያት የተቋቋመው ኮሚቴ ጊዚያዊ ሰብሳቢ አቶ በረከት ገ/ህይወት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ ” አሁንም ቆም ተብሎ ቢታሰብበት መልካም ነው ” ብለዋል።
አቶ በረከት በዝርዝር ምን አስተያየት ሰጡ ?
” የሚፈጠረውን አብረን እናያለን። ከዚህ በፊት በአጽንኦት ያሳሰብናቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፤ የተኪ ምርቶች ሁኔታ በአግባቡ አልታየም።
ኢንዱስትሪዎች በቂ የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ካልሆነ ይከስማሉ፣ ሠራተኞች ይበተናሉ፤ ለሀገርም የምናበረክተው አስተዋጽኦ በዜሮ ይባዛል። ህብረተሰባችን ምቹና ተመጣጣኝ የሆነ ሸቀጦችን የሚሰበስብበት ግብዓትን እንዲያጣ ይደረጋል፤ በዚህ ምክንያት ላላስፈላጊ የኑሮ ውድነትም ይጋለጣል።
ተኪ የሚባል ነገር ቢገኝ እንኳ (አሁን ባለው ሁኔታ እሱን የሚያሳይ ነገር ባይኖርም) በዋጋ፣ በቅልጥፍና፣ በምቾት፣ ሁሉንም አይነት እቃ ለመያዣነት የማገልገል ባህሪ ስለሌላቸው ሌሎች ማሸጊያዎች ህብረሰተባችን፣ ሰፊው የንግድ ማህበረሰብም የተቀመጠለት መፍትሄ የለም። ዓይን ጨፍኖ እየተገባበት ነው ያለው።
ይመጣሉ ካልናቸው ችግሮች የደረሱ አሉ። ወደ ፊት የሚያጋጥሙትን አብረን የምናያቸው ይሆናል። ስለዚህ አሁንም ቆም ተብሎ ቢታሰብበት መልካም ነው ” ብለዋል።
ቲክቪህ ኢትዮጵያም፣ ተተኪ ምርቶች እንደሚመረቱ በመንግስት በኩል ተገልጿል፤ ለዚህም ” ጊዜም ተሰጥቷል” ተብሏል። ተተኪ ምርቶቹን ለማምረት የምትችሉበት ሁኔታ አለ ? ሲል አቶ በረከትን ጠይቋል።
ምን መለሱ ?
” የለም። ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል እኮ ተነጋግረናል። የፕላስቲክ ከረጢት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እነርሱ የሚሏቸውን ሌላ ተኪ ምርቶች ሊያመርቱበት የሚችል ቴኪኒክ በፍጹም የለም፤ ያ ሊሆን አይችልም ማለቴ ነው።
ስለዚህ ሌላ ኢንዲስትሪ ነው የሚቋቋመው ይሄንን ወደዛ Shift ማድረግ አይቻልም። ቴክኒካሊ የተዘጋ ዜሮ ነገር ነው። በዛ ላይ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ተሰጥቷቸው ወደዛ ገብተዋል የሚባለው ምንም መሰረት፣ ሐቅ የሌለው ነው።
በማህበራችን የተጠለሉ በርካታ አምራቾች አይደለም አንድ በነጠላ ደረጃ ወደሌላ ኢንዲስትሪ የተሸጋገረ የለም። ወደ ኢንዱስትሪ የሚገባው ደግሞ በ6 ወራት ውስጥ አይደለም። ወደ ሌላ ኢንዱስትሪ ለመግባት ጥናት፣ Supplayer መለየት፣ ማሽን መምረጥ ያስፈልጋል። ለዚህ የማያስፈልግ Resource Allocate ማድረግንም ይጠይቃል።
አብዛኛው ከውጭ የሚመጣ ቴክኖሎጂ ስለሆነ፣ የጉምሩክ እና ሌሎች አጠቃላይ ስራዎች ሲደመሩ በ6 ወራት የሚጠናቀቅ ስራ አይደለም። ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው። ከIndustrialization ወደ ጋርዮሽ System እንግባ ካልን ዓይናችንን ጨፍነን መግባት እንችላለን።
ሰዎች በእጃቸው ወረቀትን እያጣበቁ በቀን ውስጥ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ግብይቶች መፍትሄ ያቀርባሉ ማለት አይቻልም። አሁን ባለው ሁኔታ ወረቀት እንኳን ለማሸጊያነት አይደለም ለኀትመት ውድ ከመሆኑ የተነሳ መፅሐፍትና ጋዜጦች መታተም እንዳቆሙ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ወረቀት እጅግ ውድ ነው። እንኳን ሙዝ፣ ብርቱካን በርበሬ እና ቃሪያ ሊያዝበት ደራሲያን መፅሐፍ ማሳተሚያ ያቃታቸው አንዱ ችግር የወረቀት ውድነት በዋጋው ያሳደረው ተፅዕኖ ነው።
ጋዜጦችንና መፅሔቶችን ከገበያ ያወጣቸው ነው እንግዲህ ለማሸጊያ መፍትሄ ይሆናል የተባለው። እሱም በኢንዱስትሪ ደረጃ ሳይሆን በጎጆ ኢንዱስትሪ ሰዎች እጅ በእጅ እያጣፉ በሚያዘጋጁት ነው። ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነው እንደ ፓሊሲ አማራጭ መቅረቡ።
በተጨማሪ ደግሞ ‘ቃጫ፣ ኮባ’ እየተባለ (ለእቃ መያዣነት) የሚጠቀሰውን እኔ ስላቅ ነው የምለው።
አንድ ተቋም አንድን ነገር በሌላ መልክ ይተካ ሲል በትክክል ጥናት ተደርጎ፣ በብቃት፣ በምቾት ሌላ ነገር እንዴት ይተካዋል ይባላል? እንጁ ኢንዱስትሪን በጋርዮሽ ሲስተም መተካት ዘመኑን ያልዋጀ መፍትሄ ስለሆነ ማህበራችን፣ አምራችን ያሳዘነ፣ ህብረተሰባችንን ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ መሆኑን ቀድመን አሳስበናል፤ ቀድሞ የተወሰደ መፍትሄ ባይኖርም። አሁንም አልረፈደም ነገሮችን ለማስተካከል።
ኢኮኖሚው ሳይጎዳ፣ ሠራተኞች ሳይበተኑ ህብረተሰቡ ምቹ የማሸጊያ አማራጮች ሊቀርቡለት ሲገባ ግለሰብ ቤት ለመቀየር አንድ አመት ይሰጠው በሚባልበት ዘመን ከአንድ ኢንዱስትሪ ወደ ሌላ ለመሸጋገር 6 ወር በቂ ነው፤ ለዚህም የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አይተናል ተብሎ።
Micro የሆኑ አገሮችን (በኢትዮጵያ Context ከአንድ ክፍለ ከተማ በላይ ህዝብና ኢኮኖሚ የሌላቸውን አገሮች ለኢትዮጵያ ምሳሌ አቅርቦ) እንደዚህ ነው የተደረገው ብሎ ማለት የሚያመጣውን የጉዳት መዘዝን አብረው የምናየው ይሆናል ” ብለዋል።
በአጠቃላይ ስንት ሠራኞች አሉ ? ለሚለው ጥያቄም፣ ” በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው ከ100 ሺሕ በላይ ሠራተኞች በቀጥታ ቅጥር፤ በምርት ግብዓት ሰንሰለት እና ምርትን ከተመረተ በኋላ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ አጠቃላይ ባሉ የፕላስቲክ ከረጢት ኢንዱስትሪው ከሚሊዮን ሰዎች ህይወት ጋር የተቆራኘ ኢንዱስትሪ መሆኑን አጥኚ ቡድኖች በጥናታቸው ያረጋገጡት ነው ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
” ስለዚህ የዚህ ሁሉ ህብረተሰብ የእንጀራ ገመድ ነው የሚበጠሰው” ብለው፣ “አሁን ባለው ኑሮ ውድነት ላይ ሌላ ኑሮ ውድነትን የሚያባብስ፤ ዜጎች ሥራ ሳይፈጠርላቸው በራሳቸው ጥረት አካባቢ ላይ ውድቆዳቂ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብ፣ ለፋብሪካዎች ግብዓት በማቅረብ፣ አካባቢን ከብክለት እየታደጉ ለራሳቸው ለልጆቻቸውም እንጀራ የፈጠሩበትን ይሄንን ኢንዱስትሪ ከስራ እንዲወጣ የማድረግን ፍርድ ለታሪክ ትተነዋል ” ነው ያሉት።
በስስ ፕላስቲክ (ስስ ፌስታል) እቃ ይዞ የተገኘን ሰው ለመቅጣት የወጣው ህግ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግና እስካሁን ባለው መረጃ የተራዘመም ሆነ የተሻሻለ ነገር እንደሌለ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸ።
ጉዳዩን ከሚያስፈጽሙት ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ” ከጥር 23 ጀምሮ ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶችን (ስስ ፌስታል) መጠቀም፣ ማምረትና ወደሀገር ውስጥ ማስገባት አይቻልም ” ማለቱ ይታወሳል።
– ማንኛውም ግለሰብ ፌስታል በእጅ ይዞ ከተገኘ ከተጠቀመ፣ ለመጠቀም ከሞከረ ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር ይቀጣል።
– አምራቾችና አከፋፋዮች፣ አስመጪዎችና አከማቾች ከ50 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር እንዲሁም የ5 አመት ጽኑ እስራት ይቀጣሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ጉዳዩ ተፈጻሚ ሊሆን ነው ወይስ የተለየ ነገር አለ ? ሲል በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባን ዛሬ ምሽት ጠይቋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ምን መለሱ ?
” አዎ ምንም የተራዘመ ነገር የለም። በዚያው ጸንቷል። በፌደራል ፓርላማ ነው ይሄ ህግ የወጣው እኛ ማስፈጸም ነው ያለብን።
ቀነ ገደቡንም የሰጠው፣ ህጉንም ያወጣው የአገሪቱ ፓርላማ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት አባላት የጸደቀ ደንብ ነው። ከዚህ ያሉ ሰዎች ማሻሻል አይችሉም።
የደንብ አስከባሪዎች፣ የፓሊስ አባላት ፣ የባለስጣኑ ሠራተኞች ሆነው ህጉን ያስፈጽማሉ። ” ብለዋል።
ዜጎች ደግሞ ከወዲሁ፣ ” በምን ልጠቀም ነው ? የተተካ ነገር አለ ?” የሚሉ አስተያየት አዘል ጥያቄዎችን እየሰጡ ሲሆን፣ እኝህ የባለስልጣኑ አካል ግን፣ ” ይህ ህግ የወጣው ህዝቡን ለመጥቀም ነው። አሁን ያለውንም ቀጥሎ የሚመጣውንም ትልውልድ የሚጠቅም ነው ” ብለዋል።
አክለው ፥
” የተበላሸ መሬት ለትውልድ ከማስተላለፍ የወጣውን ህግ አክብረን ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆበትን መንገድ ነው መከተል ያለብን። ህጉ ወጥቷል፤ ማህበረሰቡ ማክበር አለበት። ካላከበረ ህግ አስከባሪ ሁሉ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት። ብዙ ይሄን (ፕላስቲክን) ሊተኩ የሚችሉ ከወረቀት፣ ከጨርቃጨርቅ የሚሰሩ ነገሮች እየተሰሩ ነው ያለው።
የ6 ወራት የጊዜ ገደብ ቢሰጥም ‘ብክለት ይምጣ ወይስ ውበት ይምጣ?’ በሚል የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ ከወጣው ንቅናቄ ጀምሮ ፕላስቲክ ላይ፣ ብክለት ላይ እየሰራን ነው የነበረው። ከዚያ በፊትም ስስ ፌስታል ለአገልግሎት እንዳይውሉ ህግ ወጥቶ ነበር። አሁንም ስስ ፌስታሎች ናቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የታገደው።
ስለዚህ ለአብዛኛው ህዝብ ጥቅም ሲባል የወጣ ህግ ስለሆነ በስራ ላይ ይውላል። ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል መባሉ ትክክል ነው። ደንብ ተጥሶ ሲገኝ ደንብ አስከባሪው እርምጃ ይወስዳል።
ስለዚህ ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ፣ ከአንድ አገልግሎት በኋላ የሚጣሉ፣ ከተጣሉ በኋላ ለመሰብሰብም የማይመቹ፣ በቱቦ፣ በእርሻ ማሳ ንፋስ የሚወትፋቸውና የጎርፍ አደጋ የሚያስከትሉ ስስ ፌስታሎችን (ስኳር፣ ጫት፣ ስጋ የሚያዝባቸው) መያዝ ታግዷል ” ብለዋል።
የቅጣቱም መጠኑም ቢሆን ከዚህ ቀደም የተነገረው ተግባራዊ እንደሚደረግና የተሻሻለ ነገር እንደሌለ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር ምን አለ ?
ማህበሩ ” አዋጁ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ነገ ከመሆኑ፣ እሱም ጊዜ ከመድረሱ ውጭ ከየትኛውም አካል በኩል የተለየ የተሰጠን ማብራሪያ የለም ” ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።
በውሳኔው ላይ ያለውን አስተያየት በመግለጽም፣ አሁንም ” ጉዳዩ በድጋሚ እንዲጤን ” የጠየቀ ሲሆን፣ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጠው ሙሉ ገለጻ በቀጣይ ይቀርባል።