የአብይ አሕመድ የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል

🔴 “ የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ ዘጠኝ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” – የሆስፒታሉ ሠራተኞች

➡️ “ እነርሱ ጋ ብቻ አይደለም ያልተከፈለው፤ ከ2000 በላይ ሠራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ ”  – የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ

በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ፣ የይርጋጨፌ ሆስፒታል ጤና ባለሙያዎችና የአስተዳደር ባለሙያዎች “ በጸጥታ አካላት ድብደባና እስራት ተፈጽሞባቸዋል ” ሲሉ ሠራተኞቱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

ተፈጽሟል ስላሉት እስራትና ድብደባ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ፣ እንደ ሀገር የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ባለመፈጸሙ የሥራ ማቆም አድማ መደረጉን ተከትሎ መሆኑን ሠራተኞቹ አስረድተዋል።

የአራት ወራት የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ከ150 በላይ ለሚሆኑ የሆስፒታሉ ሠራተኞች አለመፈጸሙን፣ እስከ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ/ም እንዲፈጸምላቸውና እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ካልተፈጸመላቸው ሥራ የማቆም አድማ ለማድረግ እንደሚገደዱ በደብዳቤ ጭምር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ክፍያው ባለመፈጸሙ የሥራ ማቆም አድማ እንዳደረጉ፣ የተወሰኑት ሥራ ማቆም አድማ ያላደረጉ ሰራተኞች ቢሮ ባሉበት “ አድማ አስመትታችኋል ” በሚል እስራትና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ አማረዋል።

በዚህም፣ “የካቲት 10 እና 11 ቀን 2017 ዓ/ም ሥራ አልገባንም። በቀን 12/2017 ዓ/ም ደግሞ ሙሉ ፓትሮል ፓሊስ መጥቶ በሥራ ላይ የነበሩ የማኔጅመንት አባላትን ይዘው ወጡ ” በማለት ተናግረዋል።

አክለው፣ “ ከየቤቱ ያሉት ሠራተኞችም መረጃው ደርሷቸው ‘ካሰራችሁ ሁላችንንም እሰሩን የሁላችንም ጉዳይ ነው’ ብለው እስሩ ከተፈጸመበት ፓሊስ ጣቢያ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል ” ሲሉ ሁነቱን አስረድተዋል።

የታሰሩት ምን ያክል ግለሰቦች ናቸው? ስንል የጠየቅናቸው ሠራተኞቹ በሰጡት ምላሽ፣ “የታሰሩት የሆስፓታሉ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ናቸው፡፡ የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ 9 ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የሠራተኞቹን ቅሬታ በመያዝ፣ ድርጊቱ ለምን እንደተፈጸመ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ቢሮን ምላሽ የጠየቀ ሲሆን፣ እስራቱ መፈጸሙን እና ደመወዙ አለመከፈሉን አምኖ ምላሽ ያለውን ሰጥቷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ማሞ በዝርዝር ምን መለሱ ?

“ ባለሙያዎቹ የካቲት 7 መጥተው ነበር። ከኛ ጋ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይት ካደረግን በኋላ ፕሮሰስ እያደረግን ለማክሰኞ ጠዋት ክልል ቀጠሮ እንደነበረ ገልጸንላቸው ነበር፡፡ ማክሰኞ ሂደን ዘጠኝ ሰዓት ላይ ምላሽ ታገኛላችሁ ብለናቸው ነበር፡፡

እነሱ ጋ ብቻ አይደለም ክፍያው ያልተከፈለው ከ2000 በላይ ሰራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ፡፡ እንደ ዞንም ሶስት ሆስፒታል ላይ ነው ክፍያው ያልተከፈለው፡፡ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችም በወረዳ ደረጃ ያልተከፈላቸው አሉ፡፡

በሦስቱ ሆስፒታሎች ነው ያልተፈጸመው። ግን ሁለቱ ሆስፒታሎች የስራ ማቆም አድማ አላደረጉም፡፡ እነርሱ ግን ለማክሰኞ ቀጥረናቸው እያለ ቀጠሮውን አንቀበልም ብለው ሙያዊ ሥነ ምግባር በማይፈቅድ መንገድ ስራ የማመጽ ነገር አድርገው ነበር።

ግን የተወሰኑ ልጆች ደግሞ ስራ ገበታ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ስለዚህ ኦሬዲ ድስከስ አድርገን ጉዳዩን ፈተን ልጆቹ ስራ ጀምረዋል አሁን፡፡ ስራ ላይ ናቸው ሁሉም ” ብለዋል።

ታሰሩ የተባሉት የሆስፒታሉ ባልደረቦች ሳይፈቱ እንዴት ሁሉም ስራ ላይ ሊገኙ እንደቻሉ ምላሽ የጠይቅናቸው ኃላፊው፣ “እነርሱ ያልተገባ አካሄድ የሄዱ አሉ፡፡ ከስነ ስርዓት ውጭ ያልተፈቀደ ሰልፍ የወጡበት ሂደትም አለ፡፡ እንግዲህ ከእስር እንዲወጡ እየተሰራ ያለበት ሂደት አለ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሠራተኞቹ ቅሬታ ያቀረቡት የአራት ወራት ገደማ ደመወዝ አለመጨመሩን ተከትሎ ነውና የመብት ጥያቄ በመቅረቡ እስርና ድብደባ መፈጸም አግባብ ነው? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ አንዷለም በሰጡት ማብራሪያ፣ “ሠራተኞቹና ባለሙያዎቹ፣ ‘የፈጸምናቸው ድርጊቶች ትክክል አይደሉም ህዝቡን በድለናል ብለው’ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ከአጠቃላይ ሰራተኞች ውይይት ተደርጎ ጤናማ ስራ ጀምረዋል አሁን” ሲሉ አስተባብለዋል።

ይቅርታ የጠየቁት ማን ናቸው? ሰራተኞቹ ወይስ አሳሪዎቹ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም  ኃላፊው፣ “ሰራተኞቹ ” ሲል የመለሰ ሲሆን፣ ታስረው እያለ እንዴት ይቅርታ ይጠይቃሉ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ በድጋሚ ጥያቄ አቅርቧል።

እሳቸውም፣ “ሙያዊ ክብር በጣሰ መልኩ ሰልፍ የወጡትም ይቅርታ እየጠየቁ ነው ያሉት አሁን፡፡ ‘እነርሱ ናቸው ጥፋተኛ’ በሚል ልከውልናል ቤተሰቦቻቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተወሰኑት ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ የተወሰኑት ደግሞ ስራ ላይ ተገኝተው ነበር፤ ነገርግን ‘ሌሎቹን አሳምጻችኋል’ በሚል ስራ የገቡትም ናቸው የታሰሩት። ሥራ ላይ እያሉ ታስረው ሳለ “ይቅርታ ጠይቀዋል” መባሉ ምን ማለት እንደሆም በድጋሚ ምላሽ ጠይቀናል።

አቶ አንዷለም በምላሻቸው፣ “ነገሩ እንግዲህ እንደዚሁ ነው። አሁን ውይይት ላይ ነን፡፡ እነርሱ የሰሩት ጥፋት ስለነበረ ነው የተጠየቁት። አሁን ይቅርታ ጠይቀው ውይይት ላይ ነን ችግሩን ለመፍታት” ነው ያሉት፡፡

እንዳጠቃላይ ችግሩን ለመፍታትስ ምን እየተሰራ ነው? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም፣ “አሁን በጀቱ እውቅና አግኝቷል፡፡ ለሰራተኞች የጸደቀላቸው በጀት እጃችን ላይ ገብቷል፡፡ የክፍያ ሂደት ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።

“ከክልል ፋይናንስ ገንዘብ እንድለቀቅ ሂደት ላይ እንደሆነና ያው ከዚያ እንደተለቀቀ ክፍያ እንደሚከፈል ተግባቦት ላይ ተደርሷል” ሲሉም አክለዋል፡፡